ለሕዳሴ ግድቡ ድጋፍ ሰልፍ ሲዘጋጁ የመድረክ መደርመስ አደጋ ካጋጠማቸው ታዳጊዎች መሀል ህይወታቸው ያለፈ መኖሩ ተሰማ

(መሠረት ሚድያ)- በመስቀል አደባባይ የተከናወነው ፕሮግራም ላይ ለመሳተፍ እና ትርዒት ለማቅረብ ሲለማመዱ የነበሩ ታዳጊዎች የመድረክ መደርመስ አደጋ እንዳጋጠማቸው ይታወሳል።

የህዳሴ ግድብ ተጠናቆ መመረቁን በማስመልከት የተካሄደው ሰልፍ ላይ ለመሳተፍ ልምምድ ሲያደርጉ የነበሩት ታዳጊዎች አደጋው ያጋጠማቸው ቅዳሜ ምሽት 3 ሰዓት ገደማ በመስቀል አደባባይ መሆኑ ታውቋል። በዚህ ዙርያ ዛሬ የደረሰን ተጨማሪ መረጃ እንደሚጠቁመው በአደጋው ተጎድተው ወደ ጥቁር አንበሳ ሆስፒታል ከተወሰዱ ታዳጊዎች መሀል ቁጥራቸው በውል ያልታወቁት ህይወታቸው ያለፈ መሆኑን መሠረት ሚድያ ሰምቷል።

“ገና በለጋ እድሜያቸው ጎበዝ ጎበዝ ተማሪዎችን ከየትምህርት ቤታቸው በመምረጥ መንግስት ለጎበዝ ተማሪዎች ያዘጋጀው የጉብኝት ፕሮግራም አለ፣ ለሶስት ቀን ስለምትቆዩ ብርድ ልብስ እና አንሶላ ይዛችሁ ኑ ተብለው ስድስት ኪሎ ካምፓስ አስገብተዋቸው ነበር” ብለው ለሚድያችን ቃላቸውን የሰጡ አንድ ስሜ አይጠቀስ ያሉ የመረጃ ምንጫችን ናቸው።

ምንጩ አክለውም “ከዛ አምስት ቀን ትቆያላችሁ፣ ቀጥሎ አስር ቀን ትቆያላችሁ፣ ብሎም በቃ ጳጉሜ ትሄዳላችሁ ካሏቸው በኋላ መውጣት አትችሉም በማለት ለአባይ ግድብ ምርቃት ትርዒት ታቀርባላችሁ ብለው ስልጠና አስጀምረዋቸው ነበር” ይላሉ።

ለአዲስ ዓመት በዓል ጭምር ታዳጊዎቹ ወደ ቤተሰቦቻቸው ሳይሄዱ ተነጥለው ማሳለፋቸው የታወቀ ሲሆን ላለፉት 15 ቀናት መስቀል አደባባይ ላይ በእንጨት እስከ 18 ደረጃ በተሰራ መድረክ ልምምድ ሲያደርጉ መቆየታቸው ታውቋል።

“ብዙዎቹን በአዲስ አበባ ባሉ ሆስፒታሎች ከፋፍለው ነው የላኳቸው። እኔ በምሰራበት ሆስፒታል 45 ልጆች ተጎድተው የመጡ ሲሆን ከመጡት ውስጥ 11 የሚሆኑት የጀርባ አጥንት ስብራት፣ የእጅ አጥንት ስብራት እና የእግር አጥንት ስብራት ያጋጠማቸው ሲሆን ሌሎች መለስተኛ የሆነ ጉዳት ደርሶባቸዋል” ብለው ለሚድያችን የተናገሩት አንድ የጤና ባለሙያ ናቸው። ወደ ጥቁር አንበሳ ሆስፒታ በብዙ መቶዎች የሚቆጠሩ ወጣቶች የተወሰዱ ሲሆን የሞት አደጋ ያጋጠማቸው እንዳሉ ተሰምቷል።

ወጣቶቹ ሰልፍ ለማድመቅ በየወረዳው ካሉ ትምህርት ቤቶች የተሰባሰቡ መሆናቸው የታወቀ ሲሆን ትናንት ምሽት የመጨረሻ ልምምድ እያደረጉ በነበረበት ሰዓት የመድረክ መደርመስ አደጋው መድረሱ ታውቋል።

“ብዙ ሆስፒታሎች በአምቡላንስ ተጨናንቀው ነበር፣ በየሆስፒታሉ በርካታ የፀጥታ አካላት ፈሰዋል። ከንቲባ አዳነች አቤቤ እና የጤና ሚኒስትሯ ዶ/ር መቅደስ ዳባን ጨምሮ በርካታ ባለስልጣናት እየዞሩ ተጎጂዎችን ሲጎበኙ ነበር” ያሉት ሌላኛው የመረጃ ምንጫችን ናቸው።

በዘውዲቱ ሆስፒታል የሚሰሩ አንድ የጤና ባለሙያ በአደጋው የተጎዱ በቁጥር ለመግለፅ የሚቸግራቸው ታዳጊዎች ወደ ከትናንት ምሽት 3:20 ጀምሮ መምጣታቸውን ገልፀዋል።

“የተለያየ የጉዳት መጠን ያላቸውን ወጣቶች ተቀብለናል” በማለት ተጨማሪ መረጃ አሁን ላይ መስጠት እንደማይችሉ ገልፀው ነበር።

“የልጆቹ ወላጆች በር ላይ እየተላቀሱ ነው” ያሉት አንድ የታዳጊ ዘመድ ብዙ ሰው ግራ ተጋብቶ ልጁን በመፈለግ ላይ ነበር ብለዋል።

በአደጋው ዙርያ እስካሁን በመንግስት አካላት የተባለ ነገር የለም።