“ለሁለተኛ ጊዜ ቀዶ ህክምና ተሰርቷል፤ የሚቀሩ እባጮች ነበሩ አሁን እነርሱን ነው ቆርጠው ያወጡለት” – የአቶ ክርስቲያን ታደለ የቅርብ ሰው

  • “ለሁለተኛ ጊዜ ቀዶ ህክምና ተሰርቷል፤ የሚቀሩ እባጮች ነበሩ አሁን እነርሱን ነው ቆርጠው ያወጡለት” – የአቶ ክርስቲያን ታደለ የቅርብ ሰው
  • ለሁለት ዓመት ከአንድ ወር በእስር የሚገኙት የህዝብ እንደራሴዎች ምክር ቤት አባሉ አቶ ክርስቲያን ታደለ ሰሞኑን ለሁለተኛ ጊዜ ቀዶ ህክምና ማድረጋቸውን ቤተሰባቸው ለቲክቫህ ኢትዮጵያ ገለጹ።

የአቶ ክርስቲያን የቅርብ ሰው በሰጡን ቃል፣ “ ለሁለተኛ ጊዜ ቀዶ ህክምና ተሰርቷል፤ የሚቀሩ እባጮች ነበሩ አሁን እነርሱን ነው ቆርጠው ያወጡለት ” ብለዋል፡፡
ከዚህ ቀደም የቀዶ ህክምና አድርጎ እንደነበር ያስታወሱት እኝሁ የአቶ ክርስቲያን ቤተሰብ፣ “እባጭ ነበረው፤ ያኔም ያን ነበር ቆርጠው ያወጡለት፤ ግን የሚቀር እባጭ ነበር ” ሲሉ የአሁኑን ቀዶ ህክምና ምክንያት አስረድተዋል፡፡
በእስር ቤት ቆይታቸው ” ለአንጀት ድርቀት ህመም በመዳረጋቸው ” ከዚህ ቀደም ቀዶ ጥገና ማድረጋቸውን ያስታወሱት እኝሁ አካል፣ ያኔ ሙሉ ለሙሉ ቀዶ ህክምናው ተደጎላቸው ቢሆን ኖሮ “ እዛው ተኝቶ ሊከታተል ስለማይችል ከፍተኛ ጉዳት ይደርስበት ስለነበር ጊዜያዊ ሰርጀሪ ነበር የተሰራለት ” ብለዋል።
“ የሰው ልጅ አይደለም ቀዶ ህክምና የማያክል ነገር ተሰርቶና ታሞ እስር ቤት ሆኖ እቤት ተኩኖም ያስቸግራል” ብለው፣ “ሰዎች፣ የሰባዓዊ መብት ተሟጋች ድርጅቶች ሂደው ቢያዩአቸው፤ ጠያቂ ቤተሰብ የሚደርስበትን ግፍም ቢመለከቱ” ሲሉ አሳስበዋል፡፡
ሰሞኑን በመቅረዝ ሆስፒታል ለሁለተኛ ጊዜ ቀዶ ህክምና ከተደረገላቸው በኋላ ተቆርጦ የወጣው እባጭ ለካንስር ቅድመ ምርመራ እንደተላከና ውጤቱ ለቀጣይ ሳምንት እየተጠበቀ እንደሆነ ተመልክቷል፡፡
የፍርድ ቤት ሂደቱ በምን ሁኔታ ላይ እንዳለ ቲክቫህ ኢትዮጵያ ሲጠይቃቸውም፣ “ ከፍተኛ ፍርድ ቤት ከመጋረጃ ጀርባ አቶ ክርስቲያን ላይ ምስክር አሰማለሁ ብሎ ነበር አቃቢ ህግ በዚህ መሰረት ከመጋረጃ ጀርባ ያሰሙ በሚል ተፈቅዶላቸዋል ” ሲሉ መልሰዋል።
የምስክር ቃል ከመጋረጃ በስተጀርባ እንዲሰማም ለጥቅምት 10 ቀን 2017 ዓ/ም ቀጠሮ መሰጠቱን ለቲክቫህ ኢትዮጵያ ገልጸዋል፡፡