በኢትዮጵያና ኬንያ ድንበር አካባቢ በሕጋዊ የድንበር ዘለል ንግድ የተሠማሩ ኬንያዊያን ነጋዴዎች በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ደቡብ ኦሞ ዞን ኛንጋቶም ወረዳ የኢትዮጵያ መንግሥት የጸጥታ ኃይሎች ካለፉት ሁለት ወራት ወዲህ፣ “ማስፈራሪያ”፣ “የዘፈቀደ እስር” እና “የንብረት መውረስ” ድርጊቶችን እየፈጸሙብን ነው በማለት መክሰሳቸውን የኬንያው ስታንዳርድ ጋዜጣ ዘግቧል። የጸጥታ ኃይሎቹ ድርጊት ድንበር ዘለል ንግድን እያስተጓጎለና የኛንጋቶምና ቱርካና ጎሳዎችን መተማመን እየሸረሸረ ነው መባሉንም ዘገባው ጠቅሷል። አንድ ኬንያዊ በኢትዮጵያ ጸጥታ ኃይሎች ታስሮ እንደሚገኝ የጠቀሠው ዘገባው፣ ኬንያዊውን ለማስለቀቅ የኬንያ ውጭ ጉዳይ ሚንስቴር ጣልቃ እንዲገባ የቱርካና ግዛት የጸጥታ ኃላፊዎች ጠይቀዋል ተብሏል። ሃላፊዎቹ፣ የኢትዮጵያው ደቡብ ኦሞ ዞን የአስተዳደርና ጸጥታ አካላት እንዲኹም የኹለቱ ጎሳዎች የአገር ሽማግሌዎችም ተሰብስበው ለችግሩ መፍትሄ እንዲፈልጉ ጥሪ ማድረጋቸው ተነግሯል።