የትግራይ ጊዜያዊ አስተዳደር ፕሬዝዳንት ጀኔራል ታደሠ ወረደ፣ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያን ሲኖዶስ በቅርቡ በደቡባዊ ትግራይ ዞን የፈጠረው አዲስ መዋቅር የትግራይ ወረዳዎችን በአማራ ክልል ሰሜን ወሎ ዞን ሥር ያደረገ “ፖለቲካዊ ውሳኔ” ነው በማለት ከሰዋል። ጀኔራል ታደሠ ዛሬ አክሱም ውስጥ በተከበረ አንድ የኦርቶዶክስ ኃይማኖታዊ በዓል ላይ ባደረጉት ንግግር፣ የትግራይ የኃይማኖት መሪዎችና ምዕመናን የሲኖዶሱን ውሳኔ እንዲቃወሙት ጠይቀዋል። የክልሉ የኦርቶዶክስ ኃይማኖት አባቶች፣ ሲኖዶሱ በማይጨው አገረ ስብከት ሥር የነበሩት አላማጣ፣ ኦፍላ፣ ዛታ እና ጨርጨር ወረዳዎች እንዲኹም አላማጣና ኮረም ከተሞች ራሱን በቻለ አገረ ስብከት እንዲተዳደሩ ወስኗል በማለት በቅርቡ ተቃውሟቸውን ገልጠው እንደነበር አይዘነጋም። ጀኔራል ታደሠ፣ የትግራይ ሕዝብ ችግሮች በዋናነት የሚመነጩት ከትግራይ አመራሮች መኾኑንና የሕዝቡ ችግሮች ከውስጥም ከውጭም ሥር እየሰደዱ መሄዳቸውንም በዚሁ ንግግራቸው ጠቁመዋል።