ከአማራ ፋኖ በጎጃም ወታደራዊ መምሪያ የተሰጠ አስቸኳይ መግለጫ፤
በትግል ውስጥ የአስተሳሰብ ልዩነት ይኖራል። የሀሳብ ልዩነት የነበረና የሚቀጥል ነው። የሀሳብ ልዩነቶችና ፍጭቶችን መስመር ማስያዝም ልክነት ነው። ሀሳብ ቢቻል በቅቡልነቱ ባይቻል ደግሞ በእጅ ብልጫ ድምር ውጤት እንዲያሸንፍ መስራትም ለህዝባችንና የትግላችን አላማ ያለንን ጤናማነት ያሳያል።
እውነት ለመናገር በአንፃራዊነት ካየነው ድርጅታችንም የአማራ ፋኖ በጎጃም ሆነ የቀጠናችን ትግል ‘ለጤነኛ ውይይት፣ የለውጥ ፍክክርና የአመራር ልምምድ’ ሰፊ የሆነ የተከፈተ በር አለው። ቅድመ አማራ ፋኖ በጎጃም የጎጃም ዕዝና ህዝባዊ ሀይል ልዩነትን የፈታንበት የጥበብ መንገድ ለዚህ ትልቅ ማሳያ ነው። ይህ መሆኑ እየታወቀ በጎንዮሽና ስውር አካሄድ በሚደረግ የጠላት ጋብቻ፣ በማወቅም ይሁን ባለማወቅ በመጠለፍ ድርጅታችን አፋጎና ከፍተኛ አመራሩ የተነጠሉ {ዓይነት ስሜት} ሲሰማ አብሮ ለወቀሳ መሰለፍ “አንድም የትግልን ባህሪይ ካለመረዳት የሚመጣ ሞኝነት ሲሆን ሌላም የሚዲያ ዋይታ ለማትረፍ የሚደረግ ጠባብ {ቅርብ የማደር} ፍላጎት ነው።
በእርግጥ የቀጠናዊ አንድነትን ያሰፈነ፣ የትግሉን የቢሆናል አቅጣጫ በወቅቱ የሚገመግም፣ ‘እምቅ ሀይልና ትግሉን መሪ’ ደጀን ህዝብ የያዘ፣ የተማከለ ዕዝና ሰንሰለት ያለው ድርጅት፣ በግለሰቦች ሚዲያ የዋይታ ገለፃና ጫጫታ እንደማይናወጥ ቢታወቅም፤ ለሚያጠፉት ጥፋትና ለሚሰሩት ስህተት ‘የተጠየቅነት ፍርሀትን’ ቀድሞ እወቁልኝ ለቅሶ፣ ተቀባይነት እንደማይኖረው ሲያውቁ ‘እጅ መስጠትን’ አማራጭ አድርገው ይዘው የመጡ አካላትም መገለጥ ጀምረዋል። ከዚህ ጋር አንድ ትልቅ መልዕክት አለ፦ ቀድሞውንም ነገር ጠላት ጋር ከተሳሰረ ውሎ ያደረ ጋብቻ እንዳለ ግልፅ ነው። ይህ ሂደት ከፊት የቀደሙንን ወንድሞቻችንን ለማስታወስና በእነሱ መንፈስ ጠላትን ልናሽመደምድበት እጅጉን ከተዘጋጀንበት “ዘመቻ ሰማዕታት” ጋር መገጣጠሙ ደግሞ ነገሮችን በአንክሮ ለመከታተል ተገደናል።
እውነተኛ የአማራ ፋኖ አንድነት የሚመጣው ከፋኖ ሰራዊታችን እስከ ከፍተኛ አመራሩ አምኖባቸውና ተከትሏቸው፣ ከፊት የተሰየሙትን የአማራ ፋኖ በጎጃም ፊታውራሪዎችን “መሪዎቻችን ናቸው” ብሎ ከመቀበል ይጀምራል። መሪዎቻችን ላይ የሚደረግ የገፅታ ገደላን በዝምታ እያለፉ፤ በመሪዎች ላይ የተደረገውን “የትግሉን አትመሩም” ሂደትን ይሁንታ እየሰጡ ‘አንድነትን መስበክ’ አይናችሁን ጨፍኑና ላሞኛችሁ አካሄድ መሆኑንም እንረዳለን።
መርህን መሰረት በማድረግ የድርጅታችንን መመሪያና ደንብ በማስከበር ድርጅታዊ አቋምንና መመሪያን ብቻ በመፈፀም “የሚዲያ አጠቃቀም ስነስርዓት” እንዲከበርም እናሳስባለን። የውስጥ አንድነትና ድርጅታዊ የትግል መስመራችንን በመናጥ፤ ለጠላት በር ከፋች የሆኑ ንግግሮችንና አስተያየቶችን በሚሰጡ ‘አመራርና አባላት ላይ’ ወታደራዊ መምሪያው የራሱን የእርምት እርምጃ የሚወስድ መሆኑን እያሳወቅን፤ በግለሰባዊ የራስ ማኅበራዊ ገፅ ላይ ድርጅትና አመራሩን የምታንቋሽሹ በተዋረድ ውስጥ ያላችሁ አመራሮች ከመሰል ድርጊታችሁ እንድትታቀቡ እንመክራለን። የጎጃም አማራን ቀጠናዊ አንድነት ያላስጠበቀ ህብረት የአማራን አንድነት ሊያመጣ እንደማይችልም መምሪያችን በፅኑ ያምናል። በአቅም ግንባታና በተሀድሶ ወቅት ለተደጋጋሚ ጊዜ ለፋኖ ሰራዊታችን እንደምንናገረው ጠላቶቻችንን ፊት ለፊት ብቻ አንጠብቅም። ከኋላም፣ ከጎንም፣ ከመካከላችንም፣ ከውጭና ከውስጥም አብረውን ሊኖሩ እንደሚችሉ እናምናለን። ከጠላት ጋር እየተዋደቁ በተሰውብን ጀግኖቻችን ሁሌም እንኮራባቸዋለን እንጅ አናፍርባቸውም። አብረውት በልተው ከጀርባው በሴራ እና በደባ ለሚያስመቱት ባንዳዎችና የክህደት መምህሮች የሚነካ የሰራዊታችን ሞራል የለም። ስለሆነም፦
ለፋኖ ሰራዊታችንና በተዋረድ ላለው አመራሩ፦ለአማራ ፋኖ ድርጅቶች ወደ አንድነት መምጣት ወታደራዊ መምሪያው የሚጠበቅበትን ተልዕኮ ሌት ከቀን ያለዕረፍት እየተወጣ መሆኑን እንድታውቁ እየገለፅን፤ ከድርጅታዊ ደንብና አሰራር ውጭ ለቀጠናችን አንድነት መታፈርና መከበር መጠራጠርን የዘሩ አካላትን ከድርጅታችን ሊቀ መንበር አርበኛ ዘመነ ካሴ “ለመዋቅርና አባላቱ በተሰጠው የውስጥ መመሪያ መሰረት” ተጠያቂ አመራርና አባላት በቁጥጥር ስር እንዲውሉ ስንል እናሳስባለን።
ለትግላችን ደጋፊዎች፦ የትግላችን አላማ ሊሳካ የሚችለው ነፍጥን አንግበው የጨበጣ ውጊያን በሚያካሂዱ የፋኖ ሰራዊታችን ነው ብለን እናምናለን። ትክክለኛና የመጨረሻ አማራጭ የሆነው የአማራ ህዝብ የመዳኛ መንገድ የሆነው የትጥቅ ትግል በድል የሚቋጨውም ዕዝና ንሰለት፣ መሪና ተመሪ ያለው ድርጅት ሲኖር ነው። ስለሆነም በማኅበራዊ ገፅ የሚለጠፉ ግላዊ አስተያየቶችን ትኩረት ባለመስጠት የተቋም አሰራርና መርህን ተገዥነት እንድትተገብሩ እንጠይቃለን። ባለፉት ፪ዓመት የአፋጎ ወታደራዊ መምሪያ ለአማራ ፋኖ ድርጅቶች አንድነት መሳካት የከፈለው ዋጋና የተወጣው ሚና በገሀድ እየታወቀ በትግሉም ሆነ ሰንሰለቱ ውስጥ ከዚህ ግባ የሚባል ሚና የሌላቸው አካላት “የድህረ ስልጣን ማደላደያ መንገድ ለማመቻቸትና ርካሽ ተወዳጅነት ለማግኘት” ሲባል ማኅበራዊ ገፃቸው ላይ ወጥተው የሚሞነጭሩት ፅሁፍ ፍፁም ተቀባይነት የሌለው መሆኑን እንድትገነዘቡ እንገልፃለን። በድርጅታችን ደንብና መመሪያ መሰረትም ለውስጥ አንድነታችን መሻከር በር የሚከፍቱትን ሁሉ ተጠያቂ እንደሚሆኑ እየገለፅን ትኩረታችን ሁሉ ደመኛ ጠላታችን ከሆነው የአብይ አህመድ ሰራዊት ላይ እንዲሆን ስንል እናሳስባለን።
አዲስ ትውልድ፤ አዲስ አስተሳሰብ፤ አዲስ ተስፋ፤