የውጭ ምንዛሪ እጥረት ጉዳይ በኢትዮጵያ ለረዥም ጊዜ የኢኮኖሚ ችግር ሆኖ መቆየቱ ይነገራል፡፡ ‹‹ዶላር ናረ፣ ብላክ አሻቀበ፣ ባንክ ስንት ገባ?›› የሚሉ ሐረጎች ከብዙዎች አፍ የማይጠፉ የወሬ መጀመሪያ ርዕሶች ከሆኑ ከራርመዋል፡፡ ይህ ሁሉ የኢትዮጵያ የውጭ ምንዛሪ እጥረት እጅግ ሥር የሰደደ ችግር ሆኖ መዝለቁን የሚጠቁም ነው፡፡ የዶላር የመደበኛ/የባንኮች ዋጋና የጥቁር ገበያ ዋጋ ልዩነት በኢትዮጵያ ኢኮኖሚ እንቅስቃሴና በገበያ ሁኔታ ላይ ከፍተኛ ተፅዕኖ አሳዳሪ መሆኑም በሰፊው ሲነገር ቆይቷል፡፡
የውጭ ምንዛሪ አቅርቦትን ለማሳደግ በመንግሥት ብዙ የፖሊሲ ዕርምጃዎች ቢወሰዱም፣ ነገር ግን በዚህ ረገድ ችግሩ እስካሁንም የተቀረፈ አይመስልም፡፡ የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ በውጭ ምንዛሪ ድርቅ የሚጠቃው በብዙ መነሻ ምክንያቶች እንደሆነ ይነገራል፡፡ አንዳንድ ወገኖች የመንግሥትን የኢኮኖሚ ጣልቃ ገብነት በምክንያትነት ሲያነሱ፣ ሌሎች የፋይናንስ ገበያ ሥርዓቱን ለዚህ ተጠያቂ ያደርጋሉ፡፡ ሌሎች ደግሞ የውጭ ምንዛሪ እጥረት ዋና ምንጩ የወጪና ገቢ ንግድ ገቢ አለመመጣጠን መሆኑን ነው የሚናገሩት፡፡ ከዚህ የተለየ ሐሳብ የሚያቀርቡ ወገኖች ደግሞ የፋይናንስ ሥርዓቱ የተጋፈጣቸው የገበያ አሻጥሮችን፣ ኢመደበኛ፣ እንዲሁም ሕገወጥ ንግዶችን በመዘርዘር ችግሩ የዚህ ውጤት እንደሆነ ይጠቁማሉ፡፡ የሐዋላ ወይም ሬሚታንስ ገቢ፣ ዕርዳታና ብድር ግኝት መጨመር ጉዳዮች ጭምር ከዚሁ የምንዛሪ ድርቅ ጋር ተያይዘው የሚነሱ ነጥቦች ሲሆኑም ይታያል፡፡
የውጭ ምንዛሪ እጥረት የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ችግር ብቻ ነው ተብሎ አይታመንም፡፡ ይሁን እንጂ በኢትዮጵያ ያለው የውጭ ምንዛሪ እጥረት ለረዥም ዓመታት በመቆየቱና ሊፈታ ያልቻለ ችግር በመሆኑ ከሌሎች አገሮች እንደሚለይ ብዙዎች ይናገራሉ፡፡ ሌላው ቀርቶ ችግሩ ከቅርብ የጎረቤት አገሮች ጋርም ተነፃፃሪ አለመሆኑን ነው የምጣኔ ሀብት ምሁራን ብቻ ሳይሆኑ፣ የውጭ አገር ጉዞ ልምድ ያላቸው ዜጎችም ሲናገሩ የሚደመጠው፡፡ በሌሎች አገሮች የውጭ ምንዛሪ እንደ ሽንኩርትና ቲማቲም በየገበያው ተደርድሮ እየተሸጠ፣ በኢትዮጵያ ግን በመደበኛ ባንኮች ጭምር ለማግኘት አስቸጋሪ የሆነበት እንቆቅልሽ ብዙዎችን ግራ ሲያጋባ መኖሩ ተደጋግሞ ይወሳል፡፡
በአፄ ኃይለ ሥላሴና በደርግ ዘመን የአንድ ዶላር ዋጋ ከሁለት ብር አይዘልም ነበር፡፡ በኢሕአዴግ ዘመን ግን በስድስትና በሰባት ብር የሚገዛ ሆነ፡፡ ወደ 12 ብር አድጎ ጥቂት ጭማሪ እያሳየ ለብዙ ጊዜ ከረመ፡፡ የዶላር የብር ምንዛሪ ዋጋ ወደ 17 ቀጥሎም ወደ 23 ብር ሲገባ ጉዳዩ ከፍተኛ መነጋገሪያ ሆኖ ነበር፡፡ ኢሕአዴግ ከሥልጣን ሲወርድ የዶላር ዋጋ ከ27 ብር በላይ በመደበኛው ገበያ መድረሱ የሚታወስ ነው፡፡ እስከ ኢትዮጵያ ሚሊኒየም መግቢያ የአንድ ዶላር ምንዛሪ ከስምንት ብር አልፎ እንደማያውቅ መረጃዎች ይጠቁማሉ፡፡ ባለፉት 17 ዓመታት ግን ይህ ፍፁም ተለውጦ በሁለት አኃዞች ማደጉን ተያያዘው፡፡ የሰሜን ኢትዮጵያ ጦርነት ሲጀምር አካባቢ ከ39 ብር በላይ መሻገር የጀመረው የአንድ ዶላር ዋጋ፣ ከጦርነቱ በኋላም ከ50 እስከ 60 ብር ባለው አኃዝ ላይ ሲዋልል ቆይቷል፡፡
ይህ ሁሉ በመደበኛ የባንኮች ግብይት የሚቀርብና ዘለግ ላሉ ጊዜያት የሚጠቀስ ተመን እንጂ የጥቁር ገበያውን ዕድገት አያሳይም፡፡ ከሚሊኒየሙ በኋላ የነበረው የዶላር ዋጋ በባንኮች ባደገበት ዓመታት በጥቁር ገበያውም ቢሆን ዋጋው ሽምጥ ሲጋልብ ነበር፡፡ የመደበኛውና የጥቁር ገበያው ልዩነት እየሰፋም ሄዶም ነበር፡፡ የዛሬ አንድ ዓመት የኢኮኖሚ ሪፎርም ዕርምጃው በመንግሥት ከመወሰዱ ቀደም ብሎ በመደበኛው ገበያ በ60 ብር የሚሸጠው ዶላር በጥቁር ገበያ ግን እጥፍ በሆነ ዋጋ በ120 ብር እስከ መሸጥ ደርሶ እንደነበር ይታወሳል፡፡ ይህ ሁሉ ደግሞ የአገሪቱን ሥር የሰደደ የምንዛሪ ዕጦት ችግር ማሳያ ተደርጎ ሲቀርብ ቆይቷል፡፡
‹‹ኢትዮጵያ ውስጥ ከነዳጅና ከማዳበሪያ ውጪ በጥቁር ገበያ የማይሠራ የለም፡፡ ባንኮች ራሳቸው የጥቁር ገበያ ነጋዴዎች ናቸው፡፡ ኮሚሽንና ጉቦ እየተቀበሉ ነው የሚሠሩት፤›› በማለት ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) በቅርብ ጊዜ እንደተናገሩት ሁሉ፣ ዶላር ከባንክ ማግኘት በኢትዮጵያ ከባዱ ጭንቀትና ፈተና ሆኖ ነው የኖረው፡፡
የዶላር ማግኘት ችግርን ለመቅረፍ ከኢሕአዴግ ጊዜ ጀምሮ ብዙ ዕርምጃዎች ተወስደዋል፡፡ በወረፋ የሚታደልበት ወቅት ነበር፣ አንድ ሰሞን በኮታና ቅድሚያ የሚሰጣቸው ጉዳዮች እየተለዩ ነበር የሚሰጠው፡፡ የጥቁር ገበያው ነው ችግር የፈጠረው እየተባለ አምባሳደርና ስታዲየም አካባቢ በፀጥታ ኃይሎች ሱቆች ሲወረሩ የነበረበት ጊዜም ተደጋግሞ ታይቷል፡፡ በስተኋላ ላይ የፍራንኮ ቫሉታ አሠራር ተፈቀደ ተብሎ ዶላር ያላቸው ነጋዴዎች በራሳቸው ገንዘብ ከውጭ ሸቀጥ እያስገቡ እንዲሸጡ የሚያደርግ አሠራር ተዘረጋ፡፡ ይህም ቢሆን አላዛልቅ በማለቱ የዶላሩን ምንጭ ሳይጠየቁ ነጋዴዎች የሚፈልጉትን እስከ ማስመጣት የሚፈቅድ አሠራር ተበጀ፡፡
የመጨረሻው ዕርምጃ ‹‹ቢመርም መድኃኒቱን መዋጥ ብቻ ነው›› ብለው ጠቅላይ ሚኒስትሩ እንደተናገሩት ሁሉ፣ የሁለቱን ገበያዎች ማለትም መደበኛውን የባንኮችና የጥቁር ገበያ ልዩነት ያጠባል የተባለ ዕርምጃ ተወሰደ፡፡ የውጭ ምንዛሪ ግብይትን በገበያ ዋጋ እንዲመራ የሚያደርግ አሠራር የዛሬ ዓመት በሥራ ላይ ዋለ፡፡ ‹‹ዕርምጃውን ተከትሎ የባንኮችና የጥቁር ገበያው ልዩነት በእጅጉ ሲጠብ ታየ፡፡ ባንኮች በጨረታ እየተወዳደሩ በዚህን ያህል አንዱን ዶላር ገዝተው በዚህን ያህል ሸጡ መባል በጀመረበት በዕርምጃው የመጀመሪያ ወራት የሁለቱ ገበያዎች ልዩነት የጎላ አልነበረም፡፡ ይህ ሁኔታ ግን ቀስ በቀስ እየተለወጠ እነሆ ከሰሞኑ ከ30 ብር በላይ በአንድ ዶላር ላይ መከሰት ሲጀምር፣ የውጭ ምንዛሪ አጀንዳ ተመልሶ በአሳሳቢነት የሚነሳ የኢኮኖሚ ችግር ሲሆን ታየ፡፡
ይህ ለምን ሆነ? እንዲሁም ከዶላር ችግር መላቀቅ የሚቻለው በምን ተዓምር ነው? ለሚሉ ጥያቄዎች የኢኮኖሚ ባለሙያና ፖለቲከኛ የሆኑት አቶ መሐመድ አብራር ሰፊ ማብራሪያ ነው የሚሰጡት፡፡
‹‹ከአቅርቦት ወገን ካልተሠራ በቀር በዚህ ረገድ የሚመጣ ለውጥ አይታየኝም፡፡ የውጭ ምንዛሪ ማግኛ መንገዶቻችንን በማስፋት በኩል የተሠራ የረባ ነገር አለ ብዬ አላምንም፡፡ እስከ የብር ዶላር የመግዛት አቅምን ማዳከም ድረስ ብዙ ዕርምጃዎች ወስደናል፡፡ በተደጋጋሚ የብርን ዋጋ ያወረድነው በመሠረታዊነት ይህን ችግር ለመቅረፍ ሊሰጠን የሚችለውን ጠቀሜታ ታሳቢ አድርገን ነው፡፡ ሆኖም ዝም ብለን ወደ ብር ማዳከም (ዲቫሉዌሽን) ገባን እንጂ ይህን ዕርምጃ በመውሰድ ይገኛል ተብሎ የሚታሰበውን የኢኮኖሚ ምቹ ሁኔታ ለመጠቀም በቂ ሥራ አልሠራንም፡፡ ለምሳሌ ዲቫሉዌሽን የወጪ ንግድን በማሳደግ የወጪ ንግድ ገቢን ይጨምራል ተብሎ ይታሰባል፡፡ ነገር ግን ኤክስፖርት በቀላሉ አያድግም፡፡ መጀመሪያ ምርትና ምርታማነትን ማሳደግ አለብህ፡፡ አብሮ ደግሞ ወደ ወደብ መድረሻ መሠረተ ልማቶችን ወይም የሎጂስቲክስ አቅምን ማሳደግ ያስፈልጋል፡፡ አሁን ባለው የአገራችን ሁኔታ ግን ወደ ውጭ ከመላክ ይልቅ ከውጭ የማስገባት ንግድ ላይ መሰማራት የሚቀልና ሲበረታታም የሚታይ ነው፡፡ አዳዲስ ካፒታል ወደ ገበያችን ለመሳብ የሚያስችሉ መንገዶች በአብዛኛው ዝግ ናቸው፡፡ ቢከፈቱም ለመጠቀም ምቹ ሁኔታ የለም፡፡ ሌላው ቀርቶ ታላቁ ህዳሴ ግድብን ለመገንባት እንኳን ለፀጥታ ሥጋቶች ጥበቃና ለአጀብ የሚደረገውን ፈተና መንግሥት ራሱ ሪፖርት ሲያደርግ እንሰማለን፡፡ ከሰሞኑ ጣና ነሽ የምትባል ጀልባን ለማስገባት የወሰደውን የሎጂስቲክስ ፈተናም አይተነዋል፡፡ የፀጥታ ሁኔታን ጨምሮ ከፖሊሲ ዕርምጃዎቹ ለመጠቀም የሚያስችል ተጨባጭ ሁኔታ በኢትዮጵያ የለም፡፡ የኢኮኖሚ ሪፎርም ዕርምጃው በመወሰዱ የተፈጠረውን ምቹ አጋጣሚም ለመጠቀም የተቻለበት ዕድል የለም፤›› በማለት አቶ መሐመድ ይናገራሉ፡፡
ጥቁርና መደበኛ ገበያውን በማቀራረብ የዋጋ መረጋጋት ለመፍጠር የተደረገው ሙከራ ምቹ የኢኮኖሚ ሁኔታ በአገሪቱ ባለመኖሩና ጊዜውን ሳይጠብቅ የተደረገ ዕርምጃ በመሆኑ፣ በየቀኑ ጥቁር ገበያው ጨምሮ የምንዛሪ አቅርቦቱ ተመልሶ ወደ ቀደመ አለመረጋጋቱ እንደገባ ባለሙያው አክለው ያስረዳሉ፡፡
መንግሥት እስከ መጪው 2020 ዓ.ም. የዶላር ወይም የውጭ ምንዛሪ ግብይትን በመደበኛውና በጥቁር ገበያው መካከል ያለውን ልዩነት ከሦስት በመቶ በታች በማውረድ ጤናማ ለማድረግ ማቀዱን አስታውቆ ነበር፡፡ የዓለም የገንዘብ ድርጅት (አይኤምኤፍ) በሰጠው ምክረ ሐሳብ መንግሥት በሁለቱ ገበያዎች መካከል ያለውን ልዩነት ከአሥር በመቶ በላይ እንዳይሆን ማድረግ እንዳለበት በቅርብ ሪፖርቱ አሳስቦ ነበር፡፡ የውጭ ምንዛሪ ግብይትን በገበያ ሥርዓት እንዲመራ የሚያደርግ ለገበያ ተወዳዳሪነት የመክፈት ዕርምጃ ከወሰደ አንድ ዓመት የተቆጠረው መንግሥት የመደበኛና የጥቁር ገበያን ልዩነትን ማጥበብ አንዱ ዋና ግቡ የነበረ ቢሆንም፣ በጥቂት ወራት ልዩነት ግን ይህን ለማሳካት ፈተና እንደገጠመው ነው አይኤምኤፍ በቅርብ ባወጣው ሪፖርቱ ያመለከተው፡፡
መንግሥት ጥብቅ ቁጥጥር ሲደረግበት የቆየውን የባንኮች የውጭ ምንዛሪ ግብይት ነፃ የማድረግ ዕርምጃ የወሰደው ከጥቁር ገበያው ጋር ተቀራራቢ በማድረግ ኢኮኖሚውን ተወዳዳሪና የተረጋጋ ማድረግ ይቻላል በሚል ዕሳቤ እንደነበር ሲገልጽ የቆየ ሲሆን፣ ይህንም አይኤምኤፍ ሲደግፈው ቆይቷል፡፡ የምንዛሪ ግብይቱን በሁለቱ መካከል ያለውን ልዩነት በማጥበብ በአንድ ዓመት ወደ አሥር በመቶ በማውረድ ቀስ በቀስ ደግሞ ጤናማ ወደሚባለው የሦስት በመቶ ደረጃ ላይ ማድረስ የሚል ዕቅድም በዚህ ሪፎርም ውስጥ ይገኝበታል፡፡ ይሁን እንጂ ይህ አለመሳካቱን የገለጸው አይኤምኤፍ የኢትዮጵያ የምንዛሪ ገበያ ለመረጋጋት ብዙ ዕርምጃ እንደሚቀረው ነው በአዲስ ሪፖርቱ ያመለከተው፡፡ አሁንም ቢሆን ኢትዮጵያ የፋይናንስ ሥርዓቷንና የምንዛሪ ገበያዋን የበለጠ እንድትከፍት አይኤምኤፍ እየወተወተ ነው፡፡
አይኤምኤፍ እንደሚጠቅሰው እ.ኤ.አ. ከ2013 እስከ 2022 ባሉት ዓመታት የጥቁር ገበያው የውጭ ምንዛሪ ዋጋ የመደበኛው የምንዛሪ ገበያን ርቆ መቅደም ጀመረ፡፡ እ.ኤ.አ. ከኖቬምበር 2023 ጀምሮ የጥቁር ገበያው የውጭ ምንዛሪ ዋጋ ከእጥፍ በላይ የመደበኛ ገበያውን ጥሎት የተሻገረ ሲሆን፣ ኢትዮጵያ በአስከፊ ደረጃ የውጭ ምንዛሪ ድርቅ አጋጠማት፡፡ ከማዳበሪያ፣ ከመድኃኒትና ከነዳጅ ውጪ መሠረታዊ ሸቀጦችን ከውጭ የምታስገባበት እጅ አጠራት፡፡ የብሔራዊ ባንኩ መጠባበቂያ የውጭ ምንዛሪ ክምችትም ከአንድ ወር በታች ወረደ በማለት ሪፖርቱ ይጠቁማል፡፡ ይህን አሳሳቢ ችግር ለመፍታት ዓምና የውጭ ምንዛሪ ግብይትን በነፃ ገበያ ሥርዓት እንዲመራ ተደረገ፡፡ ኢትዮጵያ የኢኮኖሚ ሪፎርም ማካሄድ ጀመረች ተብሎም ዜናው ተበሰረ፡፡ ለዘመናት የቆዩ የኢኮኖሚ ሸክሞችን ለመገላገል ሪፎርሙ መድኃኒት እንደሆነም ተነገረ፡፡ እ.ኤ.አ. በመስከረም 2024 የጥቁርና የመደበኛ ገበያው ተቀራርቦ ወደ ዜሮ ወረደ፡፡ ሆኖም በቀጣዩ ወር ጥቅምት ግን ተመልሶ ልዩነቱ ወደ 16 በመቶ ሰፋ፡፡ ጥቁር ገበያው ከዚያ ወዲህም ቢሆን ከመደበኛው ጋር ተስተካክሎ መዝለቅ አልቻለም፡፡ በግንቦት 2025 ደግሞ ወደ 17 በመቶ ልዩነቱ ጨመረ፡፡ በሚያዝያ ወር የኢትዮጵያ የመጠባበቂያ የውጭ ምንዛሪ ክምችት ወደ አራት ቢሊዮን ዶላር ደርሶ ነበር፡፡ ይህ ቀደም ካለው ዓመት ከነበረው አንፃር ትልቅ ዕድገት የታየበት ሲሆን፣ አገሪቱ የሁለት ወር የገቢ ሸቀጦችን (ኢምፖርት) ወጪዋን የምትሸፍንበት ክምችት አላት እንደማለት ነው በማለትም ሪፖርቱ ይጠቅሳል፡፡
አይኤምኤፍ በሀተታው አሁንም ቢሆን ከባንክ (ከመደበኛ ገበያው) መግዛት በሚቻለው የምንዛሪ መጠን ላይ ገደብ መደረጉ፣ ሰዎች ወደ ጥቁር ገበያው እንዲያማትሩ የሚያስገድድ መሆኑን ይጠቁማል፡፡ ወደ ውጭ በሚወጣው ምንዛሪ ፍሰት ላይ ብቻ ሳይሆን ደካማ የፋይናንስ ገበያና መገበያያ መሠረተ ልማትን የማሻሻል ዕርምጃ ጉዳዩ እንደሚፈልግም በመጥቀስ፣ አገሪቱ ተጨማሪ ዕርምጃ ለችግሩ እንድትወስድ ሲመክር ነው የታየው፡፡
መንግሥት ግን ይህን ዓይነቱን ሐሳብ ሲቀበለው አይታይም፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትሩን ጨምሮ ከፍተኛ የመንግሥት አመራሮች የኢኮኖሚ ሪፎርሙ ከታሰበው በላቀ ሁኔታ ውጤት ማምጣቱን ይናገራሉ፡፡ ማሻሻያውን ተከትሎ ብዙ ዘርፎች ማለትም የመጠባበቂያ ክምችት፣ የኤክስፖርት ገቢ፣ የውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንትና ሌሎችም ምላሽ መስጠት እንደጀመሩ ይከራከራሉ፡፡ የጥቁርና የመደበኛ ገበያው ከመጥበቡና የምንዛሪ ግብይቱ ከመስተካከሉ ባለፈ የኢኮኖሚ ሪፎርሙ የሚታይ ውጤት በማክሮ ኢኮኖሚው ላይ ማምጣቱን ነው መንግሥት አበክሮ የሚናገረው፡፡
ይሁን እንጂ በምንዛሪ ገበያው ላይ ይህን የሚደግፍ አኃዝ በቅርብ ጊዜ ማግኘት አለመቻሉ ይነገራል፡፡ ጥቁር ገበያው ከባንኮች ያለው ዋጋ እየሰፋ መሄዱ በተለያዩ መንገዶች የሚወጡ መረጃዎች ያመለክታሉ፡፡ በባንኮችም ቢሆን ግብይቱ የተረጋጋና የዶላር እጥረት ችግርም የተፈታ ነው ቢባልም፣ ነገር ግን ባንክ ሄደው ዶላር ማግኘት መቸገራቸውን የሚገልጹ ሰዎች መደመጥ ጀምረው ነበር፡፡
ማክሰኞ ሐምሌ 29 ቀን 2017 ዓ.ም. የ150 ሚሊዮን ዶላር የውጭ ምንዛሪ ጨረታ በ28 ባንኮች መካከል መካሄዱን ይፋ ያደረጉት የብሔራዊ ባንክ ገዥው አቶ ማሞ ምሕረቱ ግን፣ በዚህ ረገድ አቅርቦቱም ሆነ ግብይቱ የተስተካከለ ስለመሆኑ ነው የተናገሩት፡፡ ‹‹የውጭ ምንዛሪ ክምችታችን ባለፈው በጀት ዓመት በሦስት እጥፍ በመጨመሩና ዘንድሮም በመቀጠሉ፣ የውጭ ምንዛሪ ፍሰትና ግኝት ከተጠበቀው በላይ ሆኖ በመቀጠሉ ነው የምንዛሪ ግብይት ጨረታውን ያወጣነው፤›› ሲሉ ተደምጠዋል፡፡ መንግሥት እየጨመረ ከሄደው ከዚህ የውጭ ምንዛሪ ግኝቱ ደግሞ ከፊሉን ለባንኮች በጨረታ በመሸጥ የባንኮችን የውጭ ምንዛሪ አቅም ማሳደግ፣ ዋጋ ማረጋጋትና የውጭ ምንዛሪ ግብይትን የማስተካከል ዓላማ እንዳለው ነው የጠቆሙት፡፡ ሁሉም ባንኮች የሚፈልጉትን መጠን አግኝተዋል ሲሉ የተደመጡት አቶ ማሞ፣ አንድ ዶላር በባንኮች በ138 ብር እየተሸጠ መሆኑንም ገልጸው ነበር፡፡
አያይዘውም ስለማክሮ ኢኮኖሚ ሪፎርሙም ሆነ፣ የውጭ ምንዛሪ ግብይት፣ በውጭ ምንዛሪ መጠቀምን በተመለከተ አሉታዊና የሐሰት ወሬ በአንዳንድ ወገኖች ሲነዛ መሰንበቱን ተናግረዋል፡፡ ‹‹በእነዚህ ላይ የማያዳግም ዕርምጃ እንወስዳለን፤›› ያሉት አቶ ማሞ፣ የሕገወጥ የምንዛሪ ግብይት የሚያካሂዱ ሰዎችን ማሳሰቢያ ሲሰጡ ተደምጠዋል፡፡ እሳቸውም ሆነ መንግሥታቸው እንደሚናገሩት የባንኮች የምንዛሪ ግብይት ጤናማ ከሆነና አቅርቦቱ ከተሻሻለ ሰዎች በሕገወጥ መንገድ ወደ ዶላር ሸመታ ለምን ይገባሉ የሚለው ብዙ መከራከሪያ እየተነሳበት ነው፡፡
የኢኮኖሚ ባለሙያው አቶ መሐመድ ግን ይህን አይስማሙበትም፡፡ መንግሥት በወሰደው የኢኮኖሚ ሪፎርም ሰዎች ተጠቅመው በኢኮኖሚው በሰፊው እንዲንቀሳቀሱ የሚያደርግ ዕርምጃ ተያይዞ መወሰድ እንዳለበት ባለሙያው ቢጠቁሙም፣ ነገር ግን መንግሥት ያን የሚቃረኑ ዕርምጃዎች ማስከተሉን ነው የጠቀሱት፡፡
‹‹ለሪፎርሙ ኢኮኖሚው ምላሽ እየሰጠ ነው ቢሉም አያሳምንም፡፡ በቅርቡ የተወሰደውን የታክስ ሕግ ማሻሻያ ለምሳሌ እንመልከተው፡፡ ሰዎች በቀላሉ ወደ ቢዝነስ ገብተው፣ ነግደውና ወደ ውጭ ልከው ለአገሪቱ ተጨማሪ ገቢ መፍጠር እንዳይችሉ የሚያደናቅፍ አንገት የሚያስር የታክስ ማሻሻያ ነው የተደረገው፡፡ የንግዱ ከባቢ አየር ብዙ ማነቆ እንደተጫነው ነው፡፡ በእኔ ግምት ሪፎርሙ በመካሄዱ ሊገኝ የሚችለውን የኢኮኖሚ ዕድል ለመጠቀም ምቹ ሜዳ ገና አልተፈጠረም፡፡ መንግሥት እኔ እንደምረዳው በሌሎች አስገዳጅ ሁኔታዎች ነው የዶላር ግብይትን በገበያ ዋጋ እንዲመራ የወሰነውና የኢኮኖሚ ሪፎርም ያካሄደው፤›› በማለት ተወሰደው ዕርምጃ የተሻለ ውጤት አለመገኘቱን አስረድተዋል፡፡
አቶ መሐመድ አገሪቱ መሬት ላይ እንደሚታየው የዕዳ ጫና፣ የኢንቨስትመንትና የዕርዳታ መቀዛቀዝ፣ የሰላም ዕጦትና የኢኮኖሚ እንቅስቃሴም መስተጓጎል እንደገጠሟት ይጠቅሳሉ፡፡ ‹‹ከአይኤምኤፍ በሚገኝ የአራትም ሆነ የአሥር ቢሊዮን ዶላር ድጎማ የኢትዮጵያ የምንዛሪ ገበያ ይስተካከላል ብዬ አላስብም፡፡ ይህ ችግር በዘላቂነት የሚፈታው የውጭ ምንዛሪን በከፍተኛ ደረጃ ማመንጨት የሚያስችል የኢኮኖሚ ሁኔታ ስንፈጥር ነው፡፡ ከዚህ ውጪ ደግሞ የውጭ ምንዛሪ በከፍተኛ ደረጃ የሚጠይቁ ከውጪ የምናስመጣቸውን ሸቀጦች በመቀነስ ወይም በአገር ውስጥ በመተካት ነው የሚለወጠው፡፡ ሁለቱም መንገድ ቢሆን ግን ፈጠራ፣ ንግድን፣ ኤክስፖርትንና አጠቃላይ የኢኮኖሚ ከባቢ ሁኔታን የሚለውጥ ዕርምጃ ይፈልጋል፡፡ በእኔ ዕይታ አሁንም ቢሆን ለሪፎርሙ ኢኮኖሚው ምላሽ እየሰጠ አይደለም፡፡ ሌላው ቀርቶ የተደረገው የነፃ ገበያ የምንዛሪ ግብይት ዕርምጃም ነፃ ገበያ ነው ሊባል አይችልም፡፡ የትኛውም ባንክ ሄደህ በቀላሉ ዶላር አታገኝም፡፡ ለውጭ ጉዞ ግለሰቦች ጥቂት ሺሕ ዶላር ማግኘት አይችሉም፡፡ ባንክ ሄጄ አረጋግጬያለሁ ሰዎች ዶላር ለማግኘት የማይጠየቁት ጥያቄ የለም፡፡ ባለፉት ሦስት ወራት ምን ያህል ገንዘብ ቆጥበህ ነበር ይሉሃል፡፡ 200 እና 300 ዶላር ለመስጠት፡፡ አሁን አሁን እኮ ለመርከብ ጭነት ማጓጓዣ ነጋዴዎች የሚከፍሉትን ሳይቀር ብትፈልጉ ከጥቁር ገበያ አምጡና ክፈሉት እየተባሉ እኮ ነው፡፡ ሰዎች ወደ ጥቁር ገበያ እየተገፉ ነው፡፡ በተለይ ለመርከብ ማንም የሚሰጥህ አታገኝም፣ በራስህ መንገድ አምጣና ክፈል ነው የምትባለው፡፡ አምስትና አሥር ሺሕ ዶላር ፍለጋ ወደ ጥቁር ገበያ ሳትወድ ትሄዳለህ፡፡ በባንኮች እንደሚባለው ሳይሆን በቂ አቅርቦት አይገኝም፡፡ የባንኮች የአገልግሎት ክፍያ አስመራሪ ነው፣ ሌላም አካውንት አላቸው፡፡ ጥቁር ገበያ ከምትሄድና 160 ብር ከምትከፍል ለእኛ ይህን ያህል አምጣ ብለው በግልጽ ይጠይቁሃል፡፡ ነጋዴ አሥርም ሆነች አምስት ብር ልዩነት ለማትረፍ፣ ጊዜና ጉልበቱንም ለመቆጠብ ሲል የጠየቁትን በጎን በሚሰጡት አካውንት ለመክፈት ይገደዳል፡፡ በተለይ በመካከለኛ በአነስተኛ ደረጃ ላይ ያሉ ነጋዴዎች በጣም እየተፈተኑ ነው፡፡ ነጋዴውም ቢሆን ከጥቁር ገበያ ይልቅ ከባንኮቹ በሕገወጥ ያገኘውን ዶላር ሕጋዊ ለማድረግ ስለሚቀለው የተጠየቀውን ይከፍላል፡፡ ባንኮች ገዙ በጨረታ በሚባለው መጠን ፍትሐዊ ትርፍ አግኝተው አይሸጡም፤›› በማለት ነው በተግባር አረጋገጥኩት ከሚሉት ተነስተው ሐሳባቸው የሰጡት፡፡
ኢትዮጵያ ውስጥ የምንዛሪ አቅርቦትን ለማሳደግ የሚረዳ ምቹ ሁኔታም ሆነ የሰላምና ፀጥታ አመቺነት አለመኖሩን ባለሙያው ያሰምሩበታል፡፡ እሳቸው መንግሥት ሰላም ለመፍጠር አቅም ባያጣ ፍላጎት ያጣል የሚል ግምት እንደሌላቸው ይጠቅሳሉ፡፡ ያም ቢሆን የሰላም ጉዳይ መንግሥት ብቻውን የሚያመጣው አለመሆኑን ነው የተናገሩት፡፡ ‹‹የትኛውም መንግሥት አገር አረጋግቶ መምራትን ይመርጣል፣ ይህን ማድረግ ግን ቀላል አይደለም፤›› ሲሉ ነው የገለጹት፡፡ ምንዛሪ ገበያውን ብቻ ሳይሆን ለብዙ የኢኮኖሚ ሕመሞች ገበያን ክፍት ማድረግ መፍትሔ እንደሆነ ነው የሚናገሩት፡፡
‹‹ነፃ ገበያ ብለው የተወሰኑ ዕርምጃዎችን ቢወስዱም የዶላሩን ግብይት ፍፁም ክፍት ማድረግ የሚፈሩት፣ በፖለቲካና በብዙ ሌሎች ምክንያቶች እንደሆነ ይገባኛል፡፡ ለዚህ ምሳሌ በምናደርጋት ኬንያ ጠዋት የሄድክበት ታክሲ ስትመለስ ሊወደድብህ ይችላል እኮ፡፡ ኬንያ ውስጥ የታክሲ ዋጋ እንኳን በየሰዓቱ የሚለዋወጠው የትራፊክ መጨናነቅና የተሳፋሪ ፍላጎት መሠረት አድርጎ ነው፡፡ በአሥር ሽልንግ የሄድክበት መንገድ ላይ ስትመለስ የትራፊክ ፍሰት የሚጨምርበት ሰዓት ከሆነ ወደ 20 ወይም 30 ሽልንግ ልትጠየቅበት ትችላለህ፡፡ ሾፌሩ ብቻ ሳይሆን ሰውም ከእነዚህ የገበያ ለውጦች ጋር ራሱን አስተካክሎ ነው ተቀብሎት የሚኖረው፡፡ እኛ አገር ነዳጅ በከፍተኛ ሁኔታ ጨምሮ የታክሲ ዋጋ ግን አትጨምርም ትባላለህ፡፡ አሁንም የነፃ ገበያ አለ ማለት አንችልም፡፡ በኢትዮጵያ የዕዝ ኢኮኖሚ ተፅዕኖ በብዙ መንገዶች ይታያል፡፡ ዋናዎቹ የገበያ ኃይሎች ፍላጎትና አቅርቦት ተመጋጋቢ ሆነው እንዲሄዱ የሚያስችል ዕድል የለም፡፡ ይህ ሁሉ በምንዛሪ ግብይት የሚታይ ሲሆን፣ ይህን ዓይነቱ ችግር ደግሞ በመንግሥት አይታወቅም ማለት አንችልም፡፡ በባንኮች፣ በፖለቲካ ሥልጣን ውስጥ፣ እንዲሁም በሌሎች መዋቅር ውስጥ ያሉ አካላት የችግሩ አካል ናቸው፡፡ የመንግሥት እጅ ከሒደቱ በሥነ ሥርዓቱ አለመውጣቱ ችግሩን አክፍቶታል፡፡ ወይም በሥነ ሥርዓት መምራትና በቅጡ ማስተዳደር አልቻለም፣ ካልሆነም ለነፃ ገበያ ሥርዓት ሁሉንም አልተወም፡፡ መንግሥት በንግድ ውስጥ መዘፈቁ፣ የፖለቲካ ድርጅቶች የንግድ ድርጅትም ባለቤት መሆናቸው፣ የፖለቲካ ብልሽቱና ኢኮኖሚውን በወጉ መምራት አለመቻሉ ብዙ ችግሮችን አወሳስቧል፡፡ ፍራንኮ ቫሉታ ተብሎ፣ ቁጠባ ተብሎ፣ ሸቀጦችን በመገደብ ብዙ ነገሮች ተሞክሯል፡፡ መንግሥት ባለፉት ዓመታት የአገሪቱን ሀብት በዋናነት ምን ዓይነት ኢንቨስትመንቶች ላይ ነው እያዋለ ያለው የሚለው ጉዳይ ግን በቅጡ ሲፈተሽም ሆነ ማስተካከያ ሲደረግበት አታይም፡፡ ፈጣን የኢኮኖሚ ገቢ የማይፈጥሩ ሥራዎች ላይ ብዙ ሀብት ኢንቨስት ሲደረግባቸው አይተናል፡፡ ከውጭ የሚገቡትን የሚተኩ፣ ግብርናን ወይም መሠረታዊ አቅርቦትን የሚፈቱ ችግሮች ላይ አልተሠራም፤›› በማለትም ሰፊ ትንተና አቶ መሐመድ አቅርበዋል፡፡
የብሔራዊ ባንክ ገዥው አቶ ማሞ ባለፈው አንድ ዓመት ባንኮች የሚያቀርቡት የውጭ ምንዛሪ በእጥፍ እንደጨመረ በመግለጽ፣ ወደ 500 ሚሊዮን ዶላር በየወሩ ያቀርባሉ ሲሉ ተናግረው ነበር፡፡ የዶላር ግብይቱ ጤናማ በመሆኑም የፋይናንስ ሥርዓቱን የኢኮኖሚ ሪፎርሙን ስም ማንም ማጥፋት እንደሌለበት ነው ያሳሰቡት፡፡
የአይኤምኤፍ ሪፖርት ግን ከዚህ ሲቃረን ነው የሚታየው፡፡ በአንጎላ የምንዛሪ ተመን ማስተካከያ ከተደረገ በኋላ በነበሩት ስድስት ወራት ጥቁር ገበያው ወደ 48 በመቶ ደርሶ ነበር፣ ግብፅ 0.2 በመቶ ነበር ልዩነቱ፣ ናይጄሪያ ደግሞ 0.3 በመቶ ሲሆን፣ ኢትዮጵያ 12.4 በመቶ ነበር ልዩነቱ ይላል ሪፖርቱ፡፡ የአንጎላንና የኢትዮጵያን ከእነዚህ አገሮች ለይቶም ጤናማ ያልሆነ ልዩነት በጥቁርና በመደበኛ ገበያው የሚታይባቸው ናቸው ይላል፡፡ ስለዚህ ሁለቱ አገሮች ተጨማሪ ዕርምጃ ሊወስዱ ያስፈልጋል በማለት፣ ኢኮኖሚውን መክፈትና የምንዛሪ ግብይቱን የበለጠ ነፃ ማድረግ አስፈላጊ እደሆነም ያሰምርበታል፡፡
አንጋፋው ፖለቲከኛና ኢኮኖሚስት አቶ ሙሼ ሰሙ ከሰሞኑ ኔትወርክ ፖድካስት ከተባለ ሚዲያ ጋር ባደረጉት ቆይታ፣ ስለኢኮኖሚ ነፃነትና ስለገበያ መር የምንዛሪ ግብይት ጠቃሚ ሐሳቦችን አንስተው ነበር፡፡ መንግሥት ጣልቃ መግባቱ በጨመረ ቁጥር እጥረት ሁሉም ቦታ እንደሚፈጠር የጠቀሱት አቶ ሙሼ ምንዛሪም በዚሁ መንገድ እንደሚታይ አመልክተዋል፡፡
‹‹ለነፃ ገበያ ሥርዓት ክፍት ማድረግ ብዙ ነገር ይሰጣል፣ ዛሬ መርካቶ ገብተህ የማታገኘው ነገር የለም፡፡ በኢትዮጵያ ያለው ነጋዴ የውጭ ምንዛሪ መንግሥት ብቻ እያቀረበለት አይደለም የሚሠራው፡፡ መንግሥት መንገድ እየመራው አይደለም የሚያመጣው፡፡ መንግሥት በገበያው ውስጥ ጣልቃ መግባቱ በገበያው ውስጥ ሁሌም እጥረት ያመጣል፡፡ አንዳንዴ ችግሮች ሲፈጠሩ ካልሆነ በስተቀር መግባት የለበትም፡፡ ልግባ ሲልና ዋጋ ሲተምን ዕቃ ማሸሽ ይፈጠራል፣ ጥራት ይጓደላል፡፡ በመንግሥት ጣልቃ ገብነት በሚመራ ኢኮኖሚ ውስጥ ሁሌም እጥረትና የጥራት መጓደል አለ፡፡ በደርግ ጊዜ ዳቦ ሲሸጥልህ መሀል ላይ ይሰብሩታል፡፡ ለቤተሰብ ከመጠቀም ውጪ ወስደህ ለሱቆች እንዳትሸጠው ሲሉ ነው ይህን የሚያደርጉት፡፡ ፓስታውንም ሰብረው ነው የሚሸጡልህ፡፡ ይህ የሆነው የግሉ ዘርፍ ስንዴና ዱቄት ከውጭ አስመጥቶ ምርት ማቅረብ ስለሚከለከል ነበር፡፡ ደርግ እንደወደቀ ግን ኢሕአዴግ ገበያውን ከፈተው፡፡ ዓመት አልሞላውም ለዳቦ በየኅብረት ሱቁና በቀበሌ መሠለፍ ቆመ፡፡ የዳቦ ሠልፍ በአጭር ጊዜ ተረሳ፡፡ በማንኛውም ዘርፍ ቢሆን ገበያው መከፈት አለበት ብዬ ነው የማስበው፡፡ በደርግ ጊዜ የነበረው የዕዝ ኢኮኖሚና የጦርነት ኢኮኖሚ ብዙ የገበያ ችግር ፈጥሯል፡፡ ሰዎች የሚፈልጉትን ነገር በአግባቡ አያገኙም፣ ወይም የማይፈልጉትን ነገርም ለመግዛት ሊገደዱ ይችላሉ፡፡ ጦርነቱ የአገሪቱን ኢኮኖሚ ጥርግርግ አድርጎ በላው፡፡ ቀላል የማይባል የሚያመርት የሰው ኃይልም ነው የበላብን፡፡ ሥራ ላይ መሰማራት የሚገባው ቀላል የማይባል ወጣት ጦር ሜዳ ይሠለፋል፡፡ ለጦርነቱም ብዙ ወጪ ይፈሳል፡፡ አንዳንዴ ለወደፊቱና ለልጆቻችን ነው የምንሠራው የሚል ነገር ስሰማ ፈገግ እላለሁ፡፡ ዛሬ ልጆቻችን በሰቆቃ እንዲኖሩ እየፈረድን ስለየትኛው ትውልድ ነው የምናወራው? እኛ ዛሬ ልጆቻችንን ማብላትና ማጠጣት ካልቻልን በልብስም በሥነ ልቦናም ብቁ ካላደረግናቸው ስለየትኛው ትውልድ ነው የምናወራው፡፡ ዛሬ ያለው ትውልድ ይሰቃይ ዋጋ ይክፈል ሲባል ምኑን ነው አገር የሚረከበው? ደርግ ዓለም አቀፍ ማዕቀብ ነበረበት፡፡ የተወዳጃቸው አገሮች ለራሳቸውም አይተርፉም ነበር፡፡ ቅይጥ ኢኮኖሚ ተብሎ መጨረሻ አካባቢ መፍጨርጨር ነበር፣ ነገር ግን በቂ አልነበረም፡፡ ‹ሚክስድ ኢኮኖሚ› ብሎ ደርግ የሞከረው መንደርደሪያ ሆኗል ለኢሕአዴግ ነፃ ገበያ፡፡ ያኔ ዓለም የደረሰበትን አናውቅም ነበር፡፡ ነገር ግን በዚያች መስኮት ብዙ ሰዎች ሀብት መፍጠር ጀመሩ፡፡ ይህ ደግሞ ኢትዮጵያውያን በራሳቸው የራሳቸውን ኢኮኖሚ ለማቀላጠፍ እንደሚችሉ ያሳይ ነበር፡፡ ኢትዮጵያውያን ብዙ ጥንካሬ አላቸው፡፡ ወደኋላ ተመልሰን 100 ዓመት ብናይ የጦርነት ዘመን ነው ያሳለፍነው፡፡ አሁንም ነፃነት ቢያገኙ ተዓምር መሥራት እንደሚችሉ ነው የማስበው፡፡ ኢትዮጵያዊያን በታሪካችን ብዙ ዕፎይታና እረፍት አላገኘንም፡፡ አደግን የሆነ ቦታ ደረስን ስንል መውደቅ ይመጣል፡፡ እሱን ለማስተካከል ደግሞ ከዚያ እጥፍና ሁለት እጥፍ ይጠይቃል፡፡ በአግባቡ ከተያዘና በአግባቡ ከተመራ ራሱን የሚቀይር ማኅበረሰብ ነው፤›› በማለት ሰፊ ገለጻ ያደረጉት አቶ ሙሼ፣ ለዚህ ደግሞ መፍትሔው ከምንዛሪ ግብይት ጀምሮ የኢኮኖሚ ነፃነት መሆኑን አብራርተዋል፡፡
ለሪፖርተር ሐሳባቸውን የሰጡት አቶ መሐመድም ቢሆኑ ይህን ይጋሩታል፡፡ ከዚህ በተጨማሪም አገሪቱ ያላትን ሀብት በአግባቡ መጠቀም አስፈላጊ መሆኑን ይናገራሉ፡፡
‹‹አሁን ባለንበት ሁኔታ ውስን ሀብት እንዳለው አገር መንግሥት ቅድሚያ የሚሰጣቸውን ነገሮች ለመምረጥ መገደዱ የማይቀር ነው፡፡ ከግብርና መር ኢኮኖሚ ዘርፈ ብዙ ዘርፎችን ያቀፈ ፖሊሲ እከተላለሁ ማለት አያዋጣም፡፡ ወይም ብዙ አቅም ይጠይቃል፡፡ ስለዚህ ዘርፈ ብዙ ውጤት የሚኖራቸው ጉዳዮችን ቅድሚያ ሰጥቶ መሥራት ግዴታው ይሆናል፡፡ በብዙ አገሮች መሠረታዊ የሆኑ ለሰፊው ማኅበረሰብ የሚቀርቡ ምግብ ሸቀጦች ይኖራሉ፡፡ ዳቦ ወይ በቆሎ ወይ ሩዝ በተለያየ አገሮች ለሰፊው ሕዝብ መሠረታዊ ምግብ የሆነ ሸቀጥ ይኖራል፡፡ እነዚህ ሸቀጦች ላይ የፈለገ ነገር ቢፈጠር የዋጋ ጭማሪ እንዳይፈጠር አገሮቹ ይጠነቀቃሉ፡፡ ለሰፊው ማኅበረሰብ እንዲደርሱና ሰፊው ማኅበረሰብ እንዳይጎዳ ተብሎ ዋጋቸው ተረጋግቶ እንዲቀጥል የሚደረጉ አንድና ከዚያ በላይ የሆኑ ምርት ዓይነቶችን በተለያዩ አገሮች ማግኘት ብርቅ አይደለም፡፡ እነዚያ ላይ የአምስት ሳንቲም ለውጥ እንዳይመጣ መንግሥታቱ አስፈላጊውን መስዋዕትነት ይከፍላሉ፡፡ ስለዚህ በብዙ አገሮች ሆድ ሞልቶ መኖር ወይ ልጅ አጥግቦ ማደር ችግር ሲሆን ብዙም አይታይም፡፡ በእኛ አገር ግን ከዶላር ጋር አይነካኩም የሚባሉትም ሳይቀሩ ሽንኩርቱ ብርቅ ነው፣ ድንቹ ብርቅ ነው፣ ጤፉም ብርቅ ነው፣ ቡናም ሆነ ሁሉም ነገር ቅንጦት ነው፡፡ በግብርና፣ በጨርቃ ጨርቅ ወይም በሆነ ነገር አተኩረን የላቀ ውጤት ማስመዝገብ አለብን፡፡ ስንዴ እያለን ለምንነው ከውጭ ምናስገባው፡፡ ይህ አገር ወደ 20 ቢሊዮን ዶላር ሸቀጥ ከውጭ ያስገባል፡፡ የሚሸጠው ግን በሁለት እጥፍ ያነሰ ነው፡፡ ቡናና ወርቅ በቅርቡ በዓለም አቀፍ ገበያ ዋጋቸው ጨምሯል፡፡ የብራዚል በተፈጥሮ አደጋ መቀነሱ ለቡናው መጨመር ምክንያት ነው፡፡ ስለዚህ ቡናና ወርቅ ዋጋቸው የጨመረው በኢኮኖሚ ሪፎርሙ ነው ብሎ መደምደም ከባድ ነው፡፡ ወደ አይኤምኤፍ ስምምነት እንዲሁም ወደ ዓለም ንግድ አባልነት ስትገባ ታሪፍ ቀንሰህ ግብር ለመጨመር ትገደዳለህ፡፡ ያለህን ሽጥ፣ ለውጭውም ገበያህን ክፈት ነው የምትባለው፡፡ የሆኖ ሆኖ ግን ምርትን አሳድጎ ሳይሆን ብርን አዳክሞ የምንዛሪ ችግርን ለመፍታት መሞከሩ የባሰ አደጋ ነው የፈጠረው፤›› በማለት ነው ሐሳባቸውን ያጠቃለሉት፡፡