ዩኒቨርሲቲዎች ብቁ ተማሪ ከማውጣት፣ ጥናት ከማካሄድ፣ የምርምር ሥራዎችን ከማድረግ ይልቅ የመንግሥት የፖለቲካ መሣሪያ ሆነው በማገልገል ላይ ናቸው ሲሉ፣ የትምህርት ሚኒስቴር ሚኒስትሩ ገለጹ፡፡
ሚኒስትሩ ብርሃኑ ነጋ (ፕሮፌሰር) ይህንን የተናገሩት ሐምሌ 28 እና 29 ቀን 2017 ዓ.ም. ‹‹ከፍተኛ ትምህርት ለላቀ ተፅዕኖ›› በሚል መሪ ሐሳብ በጎንደር ዩኒቨርሲቲ በተካሄደው፣ የኢትዮጵያ ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት የለውጥ ምክር ቤት ጉባዔ ማጠቃለያ ፕሮግራም ላይ ነው፡፡
የትምህርት ሚኒስትሩ ብርሃኑ ነጋ (ፕሮፌሰር) እንደገለጹት፣ ‹‹ዩኒቨርሲቲዎች ብቃት ያላቸው መምህራንና ተማሪዎችን ከመፍጠርና ኅብረተሰቡን ተጠቃሚ የሚያደርጉ የምርምር ሥራዎችን ከማከናወን ይልቅ የፖለቲካ መድረኮች ሆነዋል፤›› ብለዋል፡፡
‹‹ኅብረተሰቡ ጥሩ ፖለቲከኛ እንዲኖሩት እንደሚፈልግ ሁሉ፣ ለአገራቸው የሚቆረቆሩና አርቀው የሚያስቡ ምሁራንንም ይሻል፡፡ ከዩኒቨርሲቲዎች የምንጠብቀውም ይህንኑ ነው፤›› ያሉት ብርሃኑ (ፕሮፌሰር)፣ ዩኒቨርሲቲዎች መጪውን ትውልድ ከመቅረፅና ከመፍጠር ባሻገር የሐሳብ መሪዎች መሆን ይኖርባቸዋል፡፡ ፖለቲከኞች ምሁራን የሚያነሷቸውን ሐሳቦች ተከትለው አገር መምራት ሲኖርባቸው፣ አሁን ግን ቦታው በመለዋወጥ በተቃራኒው በሐሳብ እየመሩ የሚገኙት ፖለቲከኞች ናቸው ሲሉ ተናግረዋል፡፡
ዩኒቨርሲቲዎች የሰላም ቦታ መሆን አለባቸው፡፡ ምሁራኑም ያለ ምንም ፍርኃትና ጭንቀት እውነትን መያዝና ዕውቀትን በመደገፍ መሥራት ይጠበቅባቸዋል፡፡ አገርም የምትሻው፣ እኛም የምንፈልገው ተቋማቱ የመንግሥት መሣሪያ ሆኖ ከማገልገል ነፃ እንዲሆኑ ነው ብለዋል፡፡
‹‹እዚህ አገር ዩኒቨርሲቲዎች ሙስና የሚሠራባቸውና ሙስና የሚነገርባቸው ሆነዋል፡፡ በሚዲያ አካባቢዎችና በኅብረተሰቡ ዘንድ ከኦዲት ሪፖርት ጋር በተያያዘ የዩኒቨርሲቲዎች ስም በስርቆት የሚነሳ ነው፤›› ያሉት ሚኒስትሩ፣ አሁን ላይ ዩኒቨርሲቲዎች እየታወቁና እየተለኩ የሚገኙት ከተልዕኳቸውና ከተቋቋሙለት ዓላማ ውጪ በሚሠሩት ሥራ ነው፡፡ ይህ ደግሞ የዩኒቨርሲቲ አመራሮችንና ምሁራንን የሚጎዳ፣ አገርንና ሕዝብንም ለሌላ ችግር የሚዳርግ ነው ሲሉ ገልጸዋል፡፡
ዩኒቨርሲቲዎች የሠለጠነና ውጤታማ ትውልድ የሚፈጠሩባቸው፣ ሐሳብ ያላቸው ሰዎች የሚበቅሉባቸውና ነፃ ሐሳብ የሚንሸራሸርባቸው ቦታዎች እንዲሆኑ እንፈልጋለን፡፡ በመሆኑም በዚህ ሥነ ምግባር ውስጥ ሆነው የተጣለባቸውን ኃላፊነት መውጣት ከፈለጉ ብዙ ርቀት ተጉዘው መሥራት ይገባቸዋል ብለዋል፡፡
From The Reporter Magazine
‹‹አንድ የኢትዮጵያዊ ልጅ 12ኛ ክፍል ሲጨርስ ለከፍተኛ ትምህርት የሚያማትረው የውጭ አገር ዩኒቨርሲቲዎችን ነው፡፡ በመሆኑም ተማሪዎች ውጭ አገር ሄደው የሚያገኙትን ጥራት ያለው ትምህርት አገር ውስጥ እንዲያገኙ ለማስቻል፣ ዩኒቨርሲቲዎች በሁሉም መመዘኛዎች ብቁ መሆን ይኖርባቸዋል፤›› ያሉት ብርሃኑ (ፕሮፌሰር)፣ በተቋማቱ የሚታዩትን ችግሮች ደረጃ በደረጃ በመቅረፍ ዩኒቨርሲቲዎችን ወደ እዚህ ከፍታ ለማምጣት ሥራዎች እየተሠሩ ናቸው፡፡ ይህንንም ሥራ ውጤታማ ለማድረግ የምሁራን ድጋፍና ዕገዛ ይጠይቃል፡፡ ስለሆነም የዩኒቨርሲቲ አመራሮች የዚህ ለውጥ አንድ አካል ለመሆን ካልቻሉ፣ ሥልጣን፣ ገንዘብና መሰል ጥቅሞችን የሚሹ ከሆነ ተቋማቱ አሁን ከሚገኙበት አዘቅት የመውጣት ዕድላቸው አነስተኛ ነው ሲሉ አስታውቀዋል፡፡
ዩኒቨርሲቲዎች ስለተማሪዎቻቸውና ስለሚሠሩት ሥራ ትክክለኛ መረጃ ስጡን ብለን ከጠየቅን ሦስት ዓመት አልፎናል፡፡ ሆኖም እስካሁን የተሟላ መረጃ ለማግኘት ችግር ሆኖብናል፡፡ በዩኒቨርሲቲዎች ዘንድ እውነተኛ መረጃ መስጠት አልተለመደም፡፡ ዕለት ዕለት ኑሯችን በውሸት ላይ የተመሠረተ በመሆኑ፣ ትክክለኛ መረጃ ለመስጠት አንደፍርም እንፈራለን ብለዋል፡፡
‹‹ባለፈው ዓመት ከተማሪዎች ምገባ ጋር ተያይዞ የውሸት ሪፖርት ሲቀርብ ነበር፡፡ ዩኒቨርሲቲዎች የተማሪ ቁጥር በውሸት በመጨመር በጀት እንዲጨመርላቸው ያደርጉ ነበር›› ያሉት ሚኒስትሩ፣ ዩኒቨርሲቲዎች አሉን የሚሏቸውን የተማሪዎች መረጃ ከእነ ፎቷቸው አምጡ ስንል ግን አሉን ብለው ካስመዘገቧቸው ተማሪዎች 251 ሺሕ ያህሉ የት እንደገቡ ያልታወቀና ለማምጣትም አልቻሉም፡፡ አንድ ዕውቀት ላይ እሠራለሁ የሚል ተቋም በዚህ ደረጃ ላይ የሚገኝ ከሆነና እውነተኛ መረጃ መስጠት የማይፈልግ ከሆነ፣ በከፍተኛ ትምህርት ተቋማት እንዲመጣ የምንፈልገውን ለውጥ አዝጋሚ ያደርገዋል ሲሉም ተናግረዋል፡፡