ጾመ ፍልሰታ !
” እግዚአብሔር በቅድስት ድንግል ማርያም ማሕፀን ሊያድር የቻለው ‘እንዳልኸኝ ይሁንልኝ’ ብላ ታዛዥነትዋን በገለጸች ጊዜ ነው፤ እኛም እንዳልከን ይሁንልን እያልን እንደእስዋ ታዛዥ መሆን አለብን ! ” – ቅዱስነታቸው
” በጾመ ማርያም ሱባዔ ስለሀገር ሰላምና ስለሕዝብ ደኅንነት በመጸለይ፣ በልዩ ልዩ ምክንያት በመከራ ላይ ወድቀው የሚገኙ ወገኖቻችንን በሚያስፈልጋቸው ሁሉ በመርዳት ሱባዔውን እንድናሳልፍ ኣባታዊ መልእክታችንን በእግዚአብሔር ስም ለመላው ሕዝበ ክርስቲያን እናስተላልፋለን ! ” – ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ቀዳማዊ ፓትርያርክ ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ ሊቀ ጳጳስ ዘአክሱም ወእጨጌ ዘመንበረ ተክለሀይማኖት
ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ቀዳማዊ ፓትርያርክ ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ ሊቀ ጳጳስ ዘአክሱም ወእጨጌ ዘመንበረ ተክለሀይማኖት ለ2017 ዓ/ም የቅድስት ድንግል ማርያም ጾመ ፍልሰታ የእንኳን በሰላም አደረሳችሁ መልዕክት አስተላልፈዋል።
ከቅዱስነታቸው መልዕክት ፦
” እኛ በየጊዜው ጾምን እንድንጾም ያስፈለገበት ዋናው ምክንያት ፈቃደ ሥጋችንን በመግራት ለእግዚአብሔር ታዛዦች እንድንሆን ነው።
ጾም የኃጢኣት መግቻ መሳሪያ በመሆኑ ‘ልጓመ ኃጢኣት’ ተብሎ ይታወቃል፤ በዚህም ሰውነታችንን ለግብረ ኃጢኣት ከሚያጋግሉ ምግቦች ኣርቀን በሰከነ መንፈስ እግዚአብሔርን እያሰብን ኃጢኣታችንንም እያስታወስን በንስሓ ወደ እርሱ ለመቅረብና ለሱ ለመታዘዝ እንጾማለን።
የጾም ጥቅም ከጥንት ጀምሮ የታወቀ በእግዚአብሔርና በሰውም ተቀባይነት ያለው ነው፤ እግዚአብሔር ከመሥዋዕት ይልቅ መታዘዝን ይወዳልና በጾምና በጸሎት ለሱ ልንታዘዝ ይገባል።
እግዚአብሔር በቅድስት ድንግል ማርያም ማሕፀን ሊያድር የቻለው ‘ እንዳልኸኝ ይሁንልኝ ‘ ብላ ታዛዥነትዋን በገለጸች ጊዜ ነው፤ እኛም እንዳልከን ይሁንልን እያልን እንደእስዋ ታዛዥ መሆን አለብን።
ዛሬ በዓለማችን ያለው መተረማመስ ለእግዚአብሔር ያለመታዘዝ ያመጣው ጣጣ እንደሆነ ማንም ኣይስተውም ፤ መታዘዙ ቢኖር ኖሮ የሰው ልጅ ሰውን የሚያድን ብቻ እንጂ ሰውን የሚገድል መሳሪያ ኣያመርትም ነበር፤ ምክንያቱም እግዚአብሔር ወንድምህን እንደራስህ ኣድርገህ ውደድ ኣለ እንጂ ግደል ብሎ ኣላዘዘምና ነው፤ ኣሁንም በዚህ ባለንበት ዓለም በጣም ተባብሶ የሚገኘው የመጠፋፋት ዝንባሌ ለእግዚአብሔር በመታዘዝ በሰላምና በሰጥቶ መቀበል ካልተቋጨ ዳፋው ኣስከፊ መሆኑ ኣይቀርም።
ከዚህ አንጻር ዛሬም ለሰው ልጆች ሁሉ የምናስተላልፈው መልእክት ‘ በፍቅር ከሆነ ትንሹም ለሁሉ ይበቃልና ያለውን በጋራ በመጠቀም በፍቅርና በሰላም እንኑር ‘ የሚል ነው፤ ፍትሕና ርትዕም ለሰው ልጅ መነፈግ የበለትም፤ ሰው በምድር ላይ ሰርቶ የመኖር መብቱ ሊከበርለት ይገባል፤ ይህንን ማድረግ ማለት ለእግዚአብሔር መታዘዝ ማለት ነው፤ ስለሆነም ለእግዚአብሔር ክብርና ለራሳችን መዳን ስንል ለእርሱ በመታዘዝ በሕይወትና በሰላም እንኑር፡፡ “