” የቢዝነስ እና የቱሪስት ቪዛ አመልካቾች እስከ 15 ሺህ ዶላር የሚደርስ ገንዘብ በማስያዣነት ይጠየቃሉ ” – አሜሪካ
የአሜሪካ ውጭ ጉዳይ መሥሪያ ቤት ወደ አገሪቱ ለመግባት የቢዝነስ እና የቱሪስት ቪዛ አመልካቾች እስከ 15 ሺህ ዶላር የሚደርስ ገንዘብ በማስያዣነት ሊጠየቁ እንደሚችሉ አስታውቋል።
ይህ በሁለት ሳምንት ውስጥ ተግባራዊ መሆን ይጀምራል የተባለው የሙከራ ፕሮግራም ከቪዛ ጊዜያቸው በላይ የሚቆዩ ጎብኚዎችን ለመከላከል ያለመ መሆኑ ተገልጿል።
የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ቢሮ ያወጣው ይህ ማስታወቂያ በርካታ ሰዎች ወደ አገሪቱ ለመግባት የሚያደርጉትን ሂደት አስቸጋሪ ያደርግባቸዋል ተብሏል።
እንደ የፌደራል መንግሥቱ የምዝገባ ማስታወቂያ ከሆነ ይህ አሠራር በቀጣዮቹ 12 ወራት ውስጥ በሙከራነት በተወሰኑ አገራት ላይ ተግባራዊ ይሆናል።
የሙከራ መርሃ ግብሩ አሜሪካ ውስጥ ከቪዛ ጊዜያቸው በላይ ለረጅም ጊዜ የሚቆዩ ዜጎች ባሏቸው አገራት እና የአገር ውስጥ ሰነዶች ላይ የላላ ቁጥጥር በሚያደርጉ አገራት ላይ ተግባራዊ መደረግ ይጀምራል ተብሏል።
የእነዚህ አገራት ዜጎች ለቪዛ ሲያመለክቱ 5,000, 10,000 ወይም 15,000 ዶላሮችን በማስያዣነት እንዲያቀርቡ ሊጠየቁ እንደሚችሉ ተገልጿል።
ፕሬዝደንት ትራምፕ ወደ ሥልጣን ከመጡ በኋላ ሰነድ አልባ ስደተኞችን ከአገር ማስወጣት እንዲሁም የድንበር ቁጥጥሩን ለማጠናከር በጀት ከፍ የማድረግ እና ወደ አገሪቱ በሕገወጥ የገቡ ግለሰቦችን በቁጥጥር ስር የማዋል እርምጃዎችን ሲወስዱ ቆይተዋል።
በሰኔ ወር ከ19 አገራት ወደ አሜሪካ ለመግባት የሚያመለክቱ ግለሰቦች ላይ ከብሔራዊ ደኅንነት ጋር በተያያዙ ምክንያቶች የጉዞ እገዳ ጥለዋል።
በትራምፕ የስደተኞች ፖሊሲ ምክንያት የተወሰኑ ጎብኚዎች ወደ አሜሪካ የሚያደርጉትን ጉብኝት እየሰረዙ መሆኑ ይሰማል።
ከነሐሴ 20 ጀምሮ ተግባራዊ ይሆናል የተባለው ይህ አዲሱ የቪዛ ማስያዣ ገንዘብ ፕሮግራም ለአንድ ዓመት ያህል ይቆያል ተብሎ ተገምቷል።
የቪዛ ጥያቄዎችን የሚመለከቱ ባለሥልጣናት 5,000፣ 10,000 እና 15,000 ዶላር ለማስያዣነት የመጠይቅ ምርጫ የተቀመጠላቸው ቢሆንም፣ በአብዛኛው ግን 10,000 ዶላር በማስያዣነት እንዲጠይቁ መመሪያው ያዛል።
ተጓዦች በተሰጣቸው የቪዛ መቆያ ጊዜ መሠረት ወደ አገራቸው የሚመለሱ ከሆነ ያስያዙት ገንዘብ እንደሚመለስላቸው አስቀምጧል።
በትራምፕ የመጀመሪያው የሥልጣን ዘመን ማብቂያ ላይ፣ በኅዳር ወር 2020 ተመሳሳይ አሠራር ተግባራዊ ሆኖ ነበር።
ነገር ግን ከኮሮና ወረርሽኝ ጋር በተያያዘ የዓለም አቀፍ ተጓዦች ቁጥር በመቀነሱ የተነሳ ሙሉ በሙሉ ተግባራዊ ሳይሆን ቀርቶ ነበር።
የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ መሥሪያ ቤት በዚህ መመሪያ ውስጥ የሚካተቱ አገራቱን ዝርዝር እንደሚገለጽ አሳውቋል።
አገራት የሚለዩት ፦
– ከተፈቀደላቸው ውጪ በአሜሪካ በሚቆዩ ዜጎቻቸው ብዛት፣
– የማንነት መለያ ሰነዶች ጉድለቶችን በመለየት እና በማጣራት፣
– ያለነዋሪነት መስፈርት ዜግነትን በኢንቨስትመንት ሰበብ ማግኘትን እና የውጭ ፖሊሲን ግምት ውስጥ በማስገባት ነው ብሏል።