714 ሚልዮን ዛፍ በአንድ ቀን… ቁጥሮቹ ሲፈተሹ! ( ኤሊያስ መሰረት እንደፃፈው )
በመጀመርያ፣ በቅርቡ በሌላ አንድ ፅሁፌ ላይም እንዳነሳሁት ሰባም ይሁን ሰባት መቶ ሚልዮን ችግኝ መትከል በጎ ስራ ነው፣ መንግስት ከሚያከናውናቸው ተግባራት መሀል የማደንቀው አንዱ ነው።
ይሁንና እንደ አንድ ተራ ዜጋም ሆነ የሚድያ ባለሙያ ቁጥሮች ላይ ፍተሻ ማድረግ ይጠቅማል ብዬ አስባለሁ፣ ቁጥሮቹ ዞረው ዞረው የደን ፖሊሲ የሚዘጋጅባቸው ግብዐቶች ስለሆኑ።
1ኛ: በዛፍ ተከላው ላይ 30 ሚልዮን ገደማ ኢትዮጵያዊ (ከኢትዮጵያ ህዝብ 25 ፐርሰንት ገደማው) ተሳትፏል ተብሏል። በዚህ ዙርያ ያነጋገርኳቸው እና በፕሮግራሙ ዙርያ የሰሩ ሰዎች ይህ ፍፁም ሊሆን እንደማይችል፣ በተለይ ዘንድሮ የመንግስት ሰራተኞች እና በአንዳንድ ስፍራዎች አርሶ አደሮችን ማሳተፍ ተቻለ እንጂ ከቀድሞ አመታት ያነሰ የሰው ቁጥር እንደነበር ተናግረዋል። በእለቱ ህፃናትን፣ አዛውንቶችን፣ ታማሚዎችን ጨምሮ ከአራት ኢትዮጵያዊ አንዱ ችግኝ ተክሏል? የሚለውን እጅግ ገራሚ ቀጥር እንያዝ
2ኛ: በእለቱ 714 ሚልዮን ችግኝ ተተክሏል የተባለው አንድ ሰው 24 ችግኝ ሲተክል ነበር ተብሎ ነበር። በድጋሚ በዚህ ዙርያ ያሉኝ መረጃዎች እንደሚያሳዩት ብዙ ቦታ የችግኝ እጥረት እንደነበር፣ ምናልባት አንድ ሰው በአማካኝ በዛ ከተባለ አምስት እና ስድስት ሲተክል እንደነበር ይጠቁማሉ። ገፋ እናርገው እና 10 ችግኝ ተከለ ብንል 714 ሚልዮን ችግኝ ለመትከል 71.4 ሚልዮን ኢትዮጵያዊ (ማለትም ከኢትዮጵያ ህዝብ ከግማሽ በላይ) ችግኝ ሲተክል ነበር ማለት ነው። ይህንንም እንያዝ።
3ኛ: የግብርና ሚኒስቴር ዳታዎች እንደሚያሳዩት አንድ ችግኝ ለመትከል 4*4 የሆነ መሬት ጥቅም ላይ ይውላል፣ 16 ሜትር ስኩዌር ማለት ነው። በዚህ ስሌት 714 ሚልዮን ችግኝ ለመትከል 11.4 ቢልዮን ሜትር ስኩዌር (ወይም 1.142 ሚልዮን ሄክታር) መሬት ያስፈልጋል። ይህ ደግሞ ከኢትዮጵያ የቆዳ ስፋት 1 ፐርሰንት ነው። ይህን ያህል መሬት በአንድ ቀን በደን ተሸፍኗል? ይህን ያህል ግዙፍ ቦታ ማን ለችግኝ ተከላ አዘጋጀው? ይህንንም እንያዝ።
4ኛ: ኢትዮጵያ ተመሳሳይ የችግኝ ተከላ ፕሮግራም ከዛሬ ስድስት አመት ጀምሮ ስታካሂድ ቆይታለች፣ ለምሳሌ እ.አ.አ በ2019 ዓ.ም 350 ሚልዮን ችግኝ ተተክሏል ተብሎ ነበር። ይሁንና የዛፎቹ የማደግ/መፅደቅ ምጣኔ 20 ፐርሰንት ገደማ ነው ብንል እጅግ ከፍተኛ ቁጥር ያለው መሬት በደን ተሸፍኗል። ይሁንና እንደ FAO እና Global Forest Watch ያሉ ተቋማት የሚያወጡት መረጃ ይህን አያሳይም።
ይህ ምን ይነግረናል?
ብዙ ግዜ በሀገራችን ቁጥሮችን እንደፍራለን፣ ለማመን የሚያስቸግሩ ቁጥሮችን መጥራት እየተለመደ ነው። በተጨማሪም እንዲህ አይነት ‘performance-based policymaking’ መሬት ላይ ተሰርቶ ውጤት ከማየት ይልቅ የተሰራው ስራን በብዛት ማስተጋባት በራሱ ውጤት ይሆናል።
ነገር ግን ከላይ የተጠቀሱት 5 ነጥቦች ሳይመለሱ፣ አንድም ነፃ አካል ሳያረጋግጠው፣ እንደ ሳተላይት ያሉ ማስረጃዎች ሳይቀርቡ ወዘተ የተሰራውን ስራ በዚህ መልኩ ማቅረቡ ካሁኑ ሀይ ካልተባለ በችግኝ ተከላ ዙርያ ብቻ ሳይሆን በሁሉም ዘርፍ መቀጠሉ አይቀርም።
እርግጥ ነው የግብርና ሚኒስትሩ ችግኝ ተከላው ካለፈ ከአንድ ቀን በኋላ ከስራ ተሰናብተዋል፣ ስንብታቸው ከዚህ ካነሳሁዋቸው ነጥቦች ጋር እንደሚያያዝ ፍንጮች አሉ።
In the absence of transparency and independent verification, bold reforestation claims may serve more as public relations exercises than true climate action. Tree planting is vital — but not if it’s treated like a numbers game disconnected from ecological and logistical realities.
ስራው የሚደነቅ ነው፣ ነገር ግን የቁጥሮችን ነገር በልክ!
ለዚህ ምላሽ የሚሰጥ አካል ካለ ለአንባቢዎች በቀጥታ አቀርበዋለሁ።