አፍራሽ ይዞታ ያላቸው የባለሥልጣናት ንግግሮች ሊገሩ ይገባል

 አፍራሽ ይዞታ ያላቸው የባለሥልጣናት_ንግግሮች_ሊገሩ_ይገባል!
(በወቅታዊ ጉዳይ ላይ ከመኢአድ፣ ኢሕአፓ፣ እናት ፓርቲ እና ዐማራ ግዮናዊ ንቅናቄ የተሰጠ መግለጫ)
ከባለሥልጣናት አንደበት የሚወጡ የማይጠበቁ ቃላት አንድ ጊዜ ሲሆን የአፍ ወለምታ ተብሎ ሊወሰድ ይችላል። በተለያዩ ከፍተኛ የመንግሥት ባለሥልጣናት በተለያዩ ጊዜያት የሚነገሩ ተመሳሳይ ንግግሮች ሥርዓታዊ የአመለካከት አቅጣጫን የሚያመላክቱ መሆናቸው ግን ጥርጥር የለውም። በዚህ ረገድ የሰሜኑ ጦርነት በሚካሄድበት ወቅት የአዲስ አበባ ከተማ ከንቲባ ሕወሓትና የትግራይ ክልልን አስመልክቶ “በሕዝብ አገር መሆን እንፈልጋለን ከኢትዮጵያ ተገንጥለን ካሉ እኮ ራሳቸው የቀረጹት ሕገ መንግሥት ላይ የተቀመጠ እኮ አንቀጽ አለ። በዚያ መሠረት መሄድ ነው!” ብለው መናገራቸው የአንድ ወቅት መነጋገሪያ የነበረ ሲሆን በተመሳሳይ መልኩ የጦር ኃይሎች ጠቅላይ ኤታማዦር ሹም በቅርቡ ባደረጉት ንግግር “ለመገንጠል ደግሞ ጉልበት አያስፈልግም። አሠራር ሕገ መንግስት አለ። በዚያ ሂዱ።” ሲሉ ተደምጠዋል።
እነዚኽ በይፋ የተነገሩትን ለአብነት ጠቀስን እንጂ ከቅርብ ጊዜያት ወዲኽ ለብልጽግና ሹማምንት ቅርበት የነበራቸው ግለሰቦች እያወጧቸው ያሉና ማስተባበያም ማስተማመኛም ያልተሰጠባቸው ተመሳሳይ ይዘት ያላቸው የከፍተኛ የመንግሥት ባለስልጣናት ንግግሮች ጆሮን ጭው የሚያደርጉ ናቸው። የኾነው ኾኖ በይፋም ከመጋረጃ ጀርባም የተነገሩና የተባሉ አደገኛ ንግግሮች በስሕተት የተነገሩ እንዳልኾኑ ከድግግሞሹና ከተናገሩት ባልሥልጣናት ደረጃ ማየት የሚቻል ሲኾን ይኽም ሥርዓታዊ አቋም ነው ወይ?! ለማለት ያስገድዳል፡፡
በሌላ በኩል በእንቅርት ላይ ጆሮ ደግፍ እንዲሉ አገር የምትገኝበት መጠነ ሰፊ የርስ በርስ ጦርነት አልበቃ ብሎ ባለፈው ያደናቀፈንና ሚሊዮን ዜጎቻችንን ጭዳ ያደረገው የጦርነት እንቅፋት ዳግም ሊመታን ከቋፍ መድረሱን እያየን ነው፤ ከላይ የተጠቀሱ ንግግሮችም የዋዜማው ነጋሪት መኾናቸው አያጠያይቅም። ልዩነት ተፈጥሯዊ ሲኾን በተለይ ትናንት በአንድ አብዮታዊ ዴሞክራሲ ትሪ ሲቆርሱ የነበሩ ኃይሎች በፈጠሩት የስልጣን ሽኩቻ መላው ሕዝብ እንዲኽ እየተመላለሰ በጦርነት እሳት መለብለቡ ልብ ሰባሪ፤ ፍጹም ተቀባይነት የሌለውና በአፋጣኝም መቆም ያለበት ነው፡፡
በትብብር ፓርቲዎች እምነት ሕወሓት ማለት የትግራይ ሕዝብና ክልል አይደለም ብልጽግና ፓርቲም ኢትዮጵያና የኢትዮጵያ ሕዝብ አይደለም፡፡ ሥርዓት ይመጣል፤ ይሄዳል፡፡ ኢትዮጵያና ኢትዮጵያዊነት ከአባት እናቶቻችን በቅብብሎሽ ያገኘነው በደምና በአጥንት የተሠራ ሥውር ሸማ ነው፡፡ በመሳሳቡና በማጠልሸቱ ብዛት ለጊዜው ቢቀጥንና ቢጎሳቆል እንጂ በድንገቴና ሞቅታ ንግግሮች የሚፈርስ የድቡሽት ላይ ጎጆ እንዳልኾነ ከቅርብም ከሩቅም ታሪካችን መረዳት አያቅትም፡፡ ይኽን “ፀሐይ በምሥራቅ ትወጣለች” ዓይነት እውነት በመዘንጋት አጋጣሚውን በመጠቀምም አገርን የመበተን ተልዕኮን ለማሳካት መንቀሳቀስና ይህንን ተግባራዊ ለማድረግ ከባለሥልጣናቱ አንደበት የሚወጡ ገፊ የሆኑ፤ ያልታረሙና ሕዝብን የሚከፋፍሉ ንግግሮች በእጅጉ ሊታረሙ እንደሚገባ አጽንኦት ሰጥተን ለመግለፅ እንወዳለን።
ላለፉት ሃምሳ ዓመታት የመከራ ጽዋ ሲጎነጭ የኖረውን የትግራይ ሕዝብ ለየትኛውም የፖለቲካ ዓላማ ማስፈጸሚያ ለመጠቀም መሞከር በሕዝቡ ቁስል ላይ እንጨት እንደ መስደድ መኾኑ በሚገባ ለሠመርበት ይገባል፡፡ ስለኾነም፣
1. በፌዴራል መንግሥቱም ኾነ በሕወሓት በኩል ባሉ ባለሥልጣናት የሚነገሩ ያልታረሙ ንግግሮችን በጽኑ እናወግዛለን፤ እርምት እንዲደረግባቸውም አጥብቀን እንጠይቃለን፤
2. በፌዴራል መንግሥቱ እና በሕወሓት መካከል ያለው የጦርነት ነጋሪት ጉሰማ በአፋጣኝ እንዲቆም እየጠየቅን ለዚህ ኹሉም ሰላም ፈላጊና የኢትዮጵያ ጉዳይ የሚገደው የየድርሻውን እንዲወጣና የችግሩ ቀጥተኛ ገፈት ቀማሽ የኾነው የትግራይ ሕዝብ ተቃውሞውን በአመች መንገድ እንዲያሰማ ጥሪያችንን እናቀርባለን፤
3. በትግራይ ክልል ከሰሞኑ የተጀመረው መጠነ ሰፊ አፈሳና አስተዳደራዊ ውጥረት በአፋጣኝ እንዲቆም እንጠይቃለን።
እግዚአብሔር አገራችን ኢትዮጵያንና ሕዝቧን ይጠብቅ!
መኢአድ፣ ኢሕአፓ፣ እናት ፓርቲ እና ዐማራ ግዮናዊ ንቅናቄ
ሐምሌ ፳፪ ቀን ፳፻፲፯ ዓ.ም
አዲስ አበባ፣ ኢትዮጵያ