ተፈናቃዮቹ ቤተክርስቲያን እና ሆቴል በር ላይ እየለመኑ ነው

” ተፈናቃዮቹ ቤተክርስቲያን እና ሆቴል በር ላይ እየለመኑ ነው ” – የተፈናቃይ ተወካይ

➡️ ” እነሱ በሚሉት ልክ አይደለም የተቋረጠባቸው ” – የዞኑ አደጋ መከላከልና ምግብ ዋስትና ማስተባበሪያ ፅ/ቤት

በአማራ ክልል በሰሜን ጎንደር በደባርቅ ከተማ ከማህበረሰቡ ጋር ተቀላቅለው የሚገኙ የትግራይ ተፈናቃዮች የእርዳታ እህል ካገኙ ከ8 ወር በላይ እንደሆናቸው ተናግረዋል።

በማኅበር የተደራጅተው ችግራቸውን ለቲክቫህ ኢትዮጵያ የተናገሩት ተፈናቃዮቹ የሚበሉት ከማጣታቸው የተነሳ ለልመና መውጣታቸውን  የመሀበሩ ጸሐፊ መርጌታ ጠበቃው ወልደ ገብርኤል ተናግረዋል።

መርጌታ ጠበቃው እንደሚሉት ወትሮም አልፎ አልፎ ይሰጥ የነበረው እርዳታ ከቆመ 8 ወር ሆኖታል።

ከሰሜኑ የኢትዮጵያው ጦርነት ጋር በተያያዘ  ተፈናቅለው በደባርቅ ከተማ መጀመሪያ በመጠለያ ጣቢያ በኃላም ከማህበረሰቡ ጋር ተቀላቅለው መቆየታቸውን የሚናገሩት መርጌታ ጠበቃው ካለፈው ህዳር ወር ጀምሮ እርዳታ እንደተቋረጠባቸው ተናግረዋል።

ምክንያቱ ደግሞ የአካባቢው ባለስልጣናት የወረዳና የከተማ ብለው ተፈናቃዮችን መከፋፈላቸው ነው ይላሉ።

” በከተማ ነዋሪነት የተመዘገቡ ተፈናቃዮች በየጊዜው እርዳታ ያገኛሉ በወረዳ ተፈናቃይነት የተመዘገቡት ግን እያገኙ አይደለም ሁለቱም በአንድ ሰፈር የሚኖሩ ናቸው ” ብለዋል።

በጉዳዩ ዙሪያ የሰሜን ጎንደር ዞን አደጋ መከላከልና ምግብ ዋስትና ማስተባበሪያ ፅ/ቤት ኃላፊ አቶ ሰላም ይሁን ሙላትን ቲክቫህ ኢትዮጵያ ያነጋገረ ሲሆን ” ተፈናቃዮቹ ለ8 ወራት ያህል እርዳታ ተቋረጠብን የሚሉት ስህተት ነው ” ባይ ናቸው።

ከህዳር ወር በኃላ ወሩን በትክክል ባያስታውሱትም ለእያንዳንዱ ተፈናቃይ የሁለት ወር እርዳታ እንደተሰጣቸው አስረድተዋል።

ከዛም አመልድ ኢትዮጵያ 4 ሚልየን ብር በመመደብ ለ200 በጣም ችግር ውስጥ ላሉና ለአቅመ ደካማ ተፈናቃዮች ግንቦትና ሰኔ ወር ላይ ለእያንዳንዳቸው 10 ሺህ 10 ሺህ ሰጥቷል። ይህንን ቅሬታ እያነሳ ያለው ሰርቶ መብላት የሚችል ነው ተብሎ ያልተሰጠው ነው ሲሉ አቶ ሰላም ይሁን አክለው ገልፀዋል።

” ሌላው ባለፈው ሰኔ ወር ላይ ለነባር ተፈናቃዮች ለመስጠት የታቀደ እርዳታ ነበር ነገር ግን በአጋጣሚ በወረዳው ውስጥ ያሉ በተፈጥሮ አደጋ ምክንያት ተፈናቅለው የመጡ ሰዎች ስለነበሩ ቅድሚያ ለእነዚህ ተፈናቃዮች ሰጥተናል ይህም በተፈናቃዩ ዘንድ ብዙ ቅሬታ አስነስቶ ነበር ” ሲሉ አስታውሰዋል።

በወረዳና በከተማ ተለይቶ ሲሰጥ ስለነበረው እርዳታና ሰለተፈጠረው ክፍተት ምን አሉ ?

” በወረዳው ውስጥ በሰው ሰራሽና ተፈጥሮ አደጋዎች ምክንያት ለችግር የተጋለጡ ሰዎች ከመንግስታዊና መንግስታዊ ካልሆኑ ድርጅቶች የሚገኝ እርዳታ ለሁሉም ተረጂዎች ሲሰጥ የቆየ ሲሆን የፌደራል አደጋ ስጋትና ስራ አመራር ኮሚሽን ለአሰራር ይመች ዘንድ አንድ ጥናት አጥንቶ ወደ ስራ ገብቷል።

ይህም በወረዳ የሚገኙ ተረጂዎች ማምረት ስለሚችሉ እርዳታ ይቁም በከተማ ለሚገኝ ተረጂዎች ግን ይቀጥል ብሎ ሲወስን  እንዳጋጣሚ በወረዳ ደረጃ የተመደቡትን የትግራይ ተፈናቃዮችን ጨምሮታል።

ይህም ስህተት በመሆኑ ዞኑ ለተፈናቃዮቹ እርዳታ እንዲቀጥል እየጠየቀ ያለበት ሁኔታ ነው ያለው ” ብለዋል።