በኦሮሚያ ክልል ምስራቅ ቦረና እና ቦረና ዞኖች ሕዝባዊ ተቃዉሞ ተቀሰቀሰ

በኦሮሚያና ሶማሌ ክልል አዋሳኝ የሚገኙ 14 ወረዳዎች ወደ ሶማሌ ክልል እንዲካለሉ የተወሰነውን ውሳኔ ተከትሎ በኦሮሚያ ክልል ምስራቅ ቦረና እና ቦረና ዞኖች ሕዝባዊ ተቃዉሞ መቀስቀሱን ዋዜማ ሰምታለች።

ይህ ውሳኔ የተወሰነው የሶማሌ ክልል ምክር ቤት ሰሞኑን ባካሄደው ዓመታዊ ጉባኤው ላይ መሆኑን ያስረዱት ምንጮች፣ ይህንኑ ተከትሎ በቅርቡ እንደ አዲስ በተዋቀረው የምስራቅ ቦረና ዞን መቀመጫ ነጌሌ ቦረና ከተማ እና የቦረና ዞን መቀመጫ በሆነችው ያቤሎ ከተማ፣ እንዲሁም በሌሎች ወረዳዎች ከዛሬ ማለዳ አንስቶ የተቃውሞ ሰልፎች እየተካሄዱ መሆኑን ዋዜማ የደረሳት መረጃ ያመልክታል።

ወደ ሶማሌ ክልል እንዲካለሉ በምክር ቤቱ የተወሰኑት 14ቱ ወረዳዎች በሶማሌ እና በኦሮሚያ ክልል አዋሳኝ በሚገኙት ቦረና፣ ባሌ፣ ሐረርጌ እንዲሁም ከድሬደዋ አካባቢዎች ወደ ሶማሌ ክልል እንዲካለሉ ውሳኔ የተሰጠባቸው እንደሆኑ ምንጮች ነግረውናል።

ይህ ዜና እስከተጠናቀረበት ዛሬ ሰኞ ሐምሌ 21፣ 2017 ዓ፣ም እኩለ ቀን ድረስ በፌዴራልም ሆነ በኦሮሚያ ክልል መንግሥት በኩል በጉዳዩ ላይ የተባለ ነገር የለም። [ዋዜማ]