የኬንያው ፕረዚዳንት 14 ሚሊየን የኬንያ ሽልንግ የሚያወጣ ሰዓት አድርገው መታየታቸው ግርምትን ፈጥሯል።
ፕሬዚዳንት ሩቶ ሮሌክስ ደይቶና የተባለውን ቅንጡ ሰዓት አድርገው የታዩት በአፍሪካ ከሚገኙት ትላልቅ ፓርኮች መካከል አንዱ በሆነው በማሳይ ማራ ብሔራዊ ፓርክ ጉብኝት ባረጉበት ወቅት ነው።
ሮሌክስ ደይቶና ለገበያ የቀረበው በፈረንጆቹ 1963 ሲሆን የተሰራው በዋነኝነት ለመኪና ውድድር ሹፌሮች ነው።
ሰዓቱ እስከ 72 ሰዓት ኃይል ማቆየት እንደሚችል ሲነገር እስከ 400 ማይልስ በሰዓት ድረስ አማካይ ፍጥነትንም ያሰላል ተብሏል።
በ2024 ዊሊያም ሩቶ እንደዚሁ 425,000 የኬንያ ሽልንግ የሚያወጣ ቀበቶ አድርገው መታየታቸው የሚታወስ ነው።
በቅርቡ ዊሊያም ሩቶ 8000 ሰዎችን መያዝ የሚችል ቤተክርስቲያን በቤተመንግስታቸው ውስጥ ለመገንባት ማቀዳቸውን ተናግረው የነበረ ሲሆን አጠቃላይ የግንባታ ወጪውም 1.2 ቢሊየን የኬንያ ሽልንግ ተገምቷል።
ፕሬዚዳንቱ ቤተክርስቲያኑን ለመገንባት ከህዝብ የሚሰበሰብ ገንዘብ እንደሌለና በራሳቸው ወጪ እንደሚገነቡት ቢናገሩም ከትችት አልተረፉም።
የኬንያ ባለስልጣናት ቅንጦት በማዘውተር ሲወቀሱ በቅርቡ የውስጥ ጉዳይ ሚኒስትሩ በቅርቡ 900,000 የኬንያ ሽልንግ የሚያወጣ ሰዓት፣ 80,000 ሽልንግ የሚያወጣ ጫማ እና የ20,000 ሽልንግ ከረቫት አለኝ ብለው መናገራቸው ቁጣን ቀስቅሶ ነበር።
በአፍሪካ መሪዎች የሚኖሩት ኑሮ ከህዝቡ በተቃራኒ እንደሆነና የቅንጦት ኑሮን የሚያዘወትሩ እንደሆነ በተደጋጋሚ የሚነገር ቢሆንም ባለስልጣናት አሁንም ቢሆን የቅንጦት ኑሮን ከማዘውተር አልቦዘኑም።
Source: The Kenya Times, Tuko News, Standard Media