ሳይንቲስቶች ሰዎች ህፃን አያሉ ወደፊት ከመጠን በላይ ይወፍራሉ ወይ የሚለውን መለየት የሚያስችል ሞዴል መስራታቸው ተነገረ።

ሳይንቲስቶች ሰዎች ህፃን አያሉ ወደፊት ከመጠን በላይ ይወፍራሉ ወይ የሚለውን መለየት የሚያስችል ሞዴል መስራታቸው ተነገረ።

የኮፐንሃገን እና ብሪስቶል ዩኒቨርሲቲ ተመራማሪዎች ከ5 ሚሊየን ሰዎች በተሰበሰበ መረጃ በተሰራ ትንተና ሰዎች ከመጠን በላይ ሊወፍሩ ይችላሉ የሚለውን ገና በልጅነታቸው መገመት እንደሚቻል እና ይህም ውፍረቱን ለማስቀረት በጊዜ እርምጃ ለመውሰድ እንደሚረዳ ገልፀዋል።

በ2035 ከአለም ህዝብ ውስጥ ግማሽ ያህሉ ከመጠን በላይ ይወፍራል ተብሎ ሲጠበቅ ሳይንቲስቶቹ የሰሩት ሞዴል ህፃናት እና ወጣቶች ከመጠን በላይ ለመወፈር ዘራቸው ያለውን ተጋላጭነት በአግባቡ በመገመት መፍትሄ እንዲኖር ያደርጋል ተብሏል።

አዲሱ ሞዴልም በሰዎች ላይ የሚኖርን 17 በመቶ የሰውነት መጠን መለኪያ(BMI) ልዩነት ያስረዳል ተብሏል።

ከመጠን በላይ ውፍረት በአሁኑ ጊዜ አሳሳቢ የማህበረሰብ የጤና ችግር ሲሆን ከአካባቢ፣ አኗኗር እና ከዘር ጋር በተያያዘ ይመጣል።

በተጨማሪ ሳይንቲስቶቹ ከዘር ጋር በተያያዘ ከመጠን በላይ የወፈሩ ሰዎች ክትትል አድርገው እንዲቀንሱ ሲደረግ በቶሎ እንደሚቀንሱ እንደዚሁም ሲያቆሙ በቶሎ ክብደታቸው እንደሚጨምር ገልፀዋል።

በአለም አቀፍ ደረጃ ከመጠን በላይ ውፍረት አሳሳቢ ደረጃ ሲደርስ ከመጠን በላይ የሚወፍሩ ጎልማሶች ቁጥር በ2010 ከነበረበት 524 ሚሊየን በ2030 1.13 ቢሊየን ይደርሳል ተብሎ ይጠበቃል።

በተጨማሪ በ2050 ነገሮች ካልተቀየሩ 3.8 ቢሊየን ጎልማሶች እና 746 ሚሊየን ህፃናት ከመጠን በላይ ውፍረት ያጋጥማቸዋል ተብሎ ተገምቷል።

በ2021 በአሜሪካ 42 በመቶ ወንዶች እና 46 በመቶ ሴቶች ከመጠን በላይ ወፍረው እንደነበር ተዘግቧል።

ከሰሃራ በታች ባሉ ሃገራት ከመጠን በላይ የሚወፍሩ ሰዎች ቁጥር በ2050 በ250 በመቶ በመጨመር 522 ሚሊየን እንደሚደርስ ይጠበቃል።

ከመጠን በላይ ውፍረት እንደ ካንሰር፣ ስኳር እና የልብ ህመም ላሉ በሽታዎች በማጋለጥ የሰዎችን ህይወት የሚቀማ ሲሆን ይህንን የማህበረሰብ የጤና ችግር ለመቅረፍ የሚያስችል በቂ የጤና ፖሊሲ ሃገራት እንደሌላቸው ተዘግቧል።

Source: Science Daily, Powers Health