የአሜሪካ የውጪ ጉዳይ ቢሮ ለግብፅ የ4.7 ቢሊየን ዶላር የመሳሪያ ሽያጭን አፅድቋል።
በመሳሪያ ሽያጩ መሰረት ግብፅ ራዳር፣ ሚሳኤሎች እና የሎጅስቲክስ እንደዚሁም የኢንጂነሪንግ ድጋፎችን ከአሜሪካ ታገኛለች።
አሜሪካ ለግብፅ የምትሰጠው የአየር ስርዓት መሳሪያ ሂሊኮፕተሮችን፣ ድሮኖችን እንደዚሁም ክሩዝ ሚሳኤሎችን ለመመከት ያስችላል።
አሜሪካ ይህንን ሽያጭ የኔቶ አባል ሃገር ካልሆኑት ዋነኛ አጋሮቿ ውስጥ የሆነችው የግብፅን ደህንነት ለማሻሻል መሆኑን ገልፃ ይህም በመካከለኛው ምስራቅ ሰላም እና የኢኮኖሚ ዕድገት እንዲኖር ያስችላል ብሏል።
በተጨማሪ ለግብፅ ጦር ስልጠና እና የቴክኒክ ድጋፍ ለማድረግ 26 የአሜሪካ መንግስት ሰራተኞች እና 34 ኮንትራክተሮች ወደ ግብፅ ያመራሉ ተብሏል።
የመሳሪያ ሽያጩን የአሜሪካ የውጪ ጉዳይ ቢሮ ያፀደቀው ሲሆን በቀጣይ የኮንግረሱ ውሳኔ ይቀረዋል።
ከ1979 ጀምሮ ግብፅ ከእስራኤል ጋር የሰላም ስምምነት በመፈራረሟ ከአሜሪካ የመሳሪያ ሽያጭ እና ድጋፍ በገፍ እያገኘች እንደሆነች ይታወቃል።
ግብፅ በተመሳሳይ በ2024 የ5 ቢሊየን ዶላር የመሳሪያ ግዢን ከአሜሪካ ፈፅማለች።
ሃገረ ግብፅ ከእስራኤል በመቀጠል ከአሜሪካ ሁለተኛዋ ከፍተኛ የወታደራዊ ድጋፍ የሚደረግላት ሃገር ስትሆን ከ1979 ጀምሮ በየአመቱ የ1.3 ቢሊየን ዶላር ወታደራዊ ድጋፍ ከአሜሪካ ታገኛለች።
Source: Al Jazeera, Madamasr, Defensepost