ከህወሓት ታጣቂ ኃይል ያፈነገጠው እና ራሱን ‹ሀራ መሬት› ብሎ የሚጠራው ኃይል በህወሓት ላይ የተቀናጀ ጥቃት ለመክፈት መዘጋጀቱ ተሰማ፡፡

‹‹በሕወሓት ላይ የተቀናጀ ጥቃት ለመክፈት ተዘጋጅተዋል..››
ከህወሓት ታጣቂ ኃይል ያፈነገጠው እና ራሱን ‹ሀራ መሬት› ብሎ የሚጠራው ኃይል በህወሓት ላይ የተቀናጀ ጥቃት ለመክፈት መዘጋጀቱ ተሰማ፡፡ በዚህ ዓመት መጨረሻ ትግራይን ሙሉለሙሉ ለመቆጣጠር እቅድ መንደፋቸውም ታውቋል፡፡

ጀነራል ታደሰ ወረደ በፌዴራሉ መንግስት ይደገፋል ያሉት ይህ ታጣቂ ኃይል በህወሓት ላይ የተቀናጀ ጥቃት ለመክፈት መዘጋጀቱን የፈረንሳዩ አፍሪኬ XXI ዘግቧል፡፡ ከመቀሌ በስተምስራቅ 110 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ በምትገኘው ላኮራ አቅራቢያ ከሚገኙት ግንባሮች የአንዱ አዛዥ የሆኑት ሸዊት ቢተው “በአመቱ መጨረሻ ትግራይን እንቆጣጠራለን” ሲሉ ለዜና ምንጩ ተናግረዋል፡፡

ታጣቂ ኃይሉ በአፋር ሁለት “ግንባሮች” ያሉት ሲሆን ሶስተኛው ግንባር በምዕራብ ትግራይ ወይም በወልቃይት አዋሳኝ በሆነው ሽሬ አቅራቢያ የጦር ሰፈር መስርቷል ብሏል ዘገባው። ከነዚህ ቦታዎች ታጋዮቹ የህወሓትን አመራር ለማፍረስ “ጸጥ ያለ አብዮት” ብለው የገለጹትን እቅድ እያዘጋጁ እንደሆነ ጠቅሷል።

ከተሾሙ አንድ መቶ ቀን ያስቆጠሩት ጀነራል ታደሰ ወረደ በዚህ ሳምንት መጀመሪያ በሰጡት አስተያት፣ ‹ይህ ታጣቂ ኃይል ጥቃት ከከፈተብን ትንኮሳው ከፌዴራሉ መንግስት እንደተደረገ እንቆጥረዋለን› በማለት ተናግረው ነበር፡፡ የሀራ መሬት አመራሮች ከፌዴራሉ መንግስት ምንም አይነት ድጋፍ እና እገዛ እንደማያገኙ በተደጋጋሚ የሚናገሩ ቢሆንም፤ አፍሪካን ኢንተነለጀንስ ግን ከወራት በፊት ባወጣው ዘገባ ቡድኑ በፌዴራል መንግስት እንደሚደገፍ ዘግቧል፡፡ ሕወሓትም መንግስት በአፋር ታጣቂ ኃይል እያደራጀብኝ ነው ሲል እየከሰሰ ይገኛል፡፡
ፎቶ፡- ብርጋዴር ጄነራል ገብረ እግዚአብሄር በየነ (ወዲ አንጥሩ) የሀራ መሬት አዛዥ