የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት፣ አወዛጋቢውንና የተሻሻለውን የፌደራል ገቢ ግብር አዋጅ ለውጥ ሳይደረግበት በ5 ተቃውሞና በ12 ድምጸ ተዓቅቦ በአብላጫ ድምጽ አጽድቋል። ግብር የሚቆረጥበት ዝቅተኛ ደመወዝ ከ2 ሺሕ ብር ወደ 8 ሺሕ 324 ብር ከፍ እንዲደረግ የቀረበው ሃሳብም ተቀባይነት ሳያገኝ ቀርቷል። አንዳንድ የምክር ቤቱ አባላት፣ ማሻሻያው የመንግሥት ሠራተኞችን የኑሮ ሁኔታ ታሳቢ አላደረገም በማለት ተችተው ነበር። የገንዘብ ሚንስትር ደኤታ እዮብ ተካልኝ፣ የመንግስት ሠራተኞችን ኑሮ ለማሻሻል፣ የመኖሪያ ቤት ጥናት እየተደረገ መኾኑን ተናግረዋል፡፡
የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት፣ የተሻሻለውን የምርጫና የፖለቲካ ፓርቲዎች ምዝገባና የምርጫ ሥነ ምግባር አዋጅ ዛሬ በሁለት ተቃውሞና በአራት ድምጸ ተዓቅቦ አጽድቋል። በምርጫ ጣቢያ ደረጃ የነበረው የቅሬታ ሠሚ ኮሚቴ ለምን እንደቀረ አንድ የምክር ቤት አባል የጠየቁ ሲሆን፣ የዲሞክራሲና ፍትሕ ቋሚ ኮሚቴም በክልል ደረጃ ብቻ ቅሬታ ሠሚ ኮሚቴ ማዋቀሩ የተሻለ ኾኖ ስለተገኘ እንደኾነ አስረድቷል።
አዲስ አገር ዓቀፍ ፓርቲዎች በአራት ክልሎች የድርጅት መስራች አባል ማፍራት እንዳለባቸው የሚለው ድንጋጌም፣ ስድስት ክልሎች እንዲኾን ተደርጓል።