የኤርትራ መንግስት ዛሬ ባወጣው መግለጫ ኢትዮጵያ ግጭት ለመፍጠር ሰበቦችን እየፈለገች መሆኑን ጠቅሶ ባለፉት ጥቂት ቀናት ለተባበሩት መንግስታትና ለበርካታ አገራት ‹‹ኤርትራ ሉአላዊ ግዛቴን ጥሳለች›› የሚል ስሞታ ማስገባቷን አስታውቋል፡፡
ሲቀጥልም ‹‹ይህ ጅራፍ እራሱ ገርፎ እራሱ ይጮሀል›› የሚል ዲፕሎማሲያዊ ዘመቻ እንደሆነ አስረድቷል፡፡ የኢትዮጵያ ገዥው ፓርቲ ባለፉት ሁለት አመታት የኤርትራ ወደቦችን ‹‹በውዴታም ሆነ በግዴታ›› ለመውሰድ ቅስቀሳ ሲያደርግ መቆየቱን ያወሳው መግለጫው ጨምሮም ‹‹ከቃላትም ባለፈ የኢትዮጵያ መንግስት የጦር መሳሪያ ሲገዛ ቆይቷል›› በሚል ክስ አቅርቧል፡፡
እነዚህን ቀስቃሽ ድርጊቶች በትእግስት ማሳለፉን ገልፆም ኤርትራ በአልጀርስ በተላለፈው የድንበር ኮሚሽን ውሳኔ መሰረት በግዛቷ ውስጥ እንዳለችና ምንም የወረረችው የኢትዮጵያ መሬት እንደሌለ አስረድቷል፡፡ በመግለጫው መጨረሻም ‹‹ኢትዮጵያ የጎረቤቷን ሉአላዊ መሬትና ባህር በር ለመውሰድ የምታደርገው ህገ ወጥ ጥረት ምኞት ነው›› ብሏል፡፡