የብልጽግና ፓርቲ ባለሥልጣናት እና ተሳዳቢዎቻቸው ከዲፕሎማሲያዊ መርኾዎች ያፈነገጡ ናቸው ( የኤርትራ መንግሥት ቃል አቀባይ)

የኤርትራ መንግሥት ቃል አቀባይ የማነ ገብረመስቀል፣ የኢትዮጵያው ገዥ “የብልጽግና ፓርቲ ባለሥልጣናት እና ተሳዳቢዎቻቸው ባኹኑ ወቅት እያንጸባረቋቸው ያሉት መከራከሪያዎች ከመሠረታዊ አመክንዮ እና ቀላል ከኾኑ የዓለማቀፍ ሕግ ድንጋጌዎች እና ከዲፕሎማሲያዊ መርኾዎች ያፈነገጡ ናቸው” በማለት ዛሬ በማኅበራዊ ትስስር ገጻቸው ባሠፈሩት አስተያየት ተችተዋል። የማነ በዚህ አስተያየታቸው፣ የብልጽግና ፓርቲ ባለሥልጣናትና ተሳዳቢዎቻቸው “ኤርትራና ኢትዮጵያ እንደገና በጀመሩት ቅርርብ ግራ መጋባት ይታይባቸዋል” ብለዋል። የማነ አያይዘውም፣ ይህ ግራ መጋባት የተፈጠረው፣ የብልጽግና ባለስልጣናትና ተሳዳቢዎቻቸው “ኤርትራ በባሕር ግዛቷ ላይ ያላትን የማይገሰስ ሉዓላዊ መብት በከፊል ለጨረታ ለማቅረብ ዝግጁ እንዳልኾነች ከተረዱ በኋላ ነው” በማለት አስተያየታቸውን ቋጭተዋል።