የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት፣ በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል በዲላ ዩኒቨርስቲ ሴት ሙስሊም ተማሪዎች ሒጃብ በመልበሳቸው ከትምህርት እንደታገዱ ትናንት ምሽት ባወጣው መግለጫ አስታውቋል።
ትምህርት የማግኘት ሕገመንግሥታዊ መብታቸው ተገፎ ወደ ዩኒቨርስቲው ቅጥር ግቢ እንዳይገቡ የተከለከሉት ሴት ተማሪዎች ባፋጣኝ ወደ ትምህርት ገበታ እንዲመለሱ የጠየቀው ምክር ቤቱ፣ ትምህርት ሚንስቴር ለችግሩ ዘላቂ አስተዳደራዊ መፍትሄ እንዲሰጥ በደብዳቤ መጠየቁን ገልጧል፡፡
በአክሱም ከተማ በኹለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ሴት ሙስሊም ተማሪዎች ላይ ተመሳሳይ እገዳ ከተጣለ ወዲህ፣ ለችግሩ ዘላቂ መፍትሄ እንዲበጅለት ለትምህርት ሚንስቴር ሦስት ጊዜ ደብዳቤ መጻፉን የጠቀሰው ምክር ቤቱ፣ ኾኖም እስካኹን ምላሽ አለማግኘቱንና ይህ ደብዳቤም የመጨረሻው መኾኑን አውስቷል።