- በዘጠኝ ወራት ከ37 ሺሕ በላይ ሠራተኞች መልቀቃቸው ተነግሯል
በትግራይ ክልል መቀሌ ከተማ በሚገኘው ኢንዱስትሪ ፓርክ የተሰማሩ ጦርነት ሸሽተው የወጡ ባለሀብቶች፣ ማሽኖቻቸውን ከአገር ለማስወጣት ጥያቄ እያቀረቡ መሆናቸውን፣ የኢንዱስትሪ ፖርኮች ልማት ኮርፖሬሽን ገለጸ።
ኮርፖሬሽኑ ይህንን የገለጸው የዘጠኝ ወራት ዕቅድ አፈጻጸሙን ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የመንግሥት የልማት ድርጅቶች ጉዳዮች ቋሚ ኮሜቴ ሲያቀርብ ነው፡፡
በሰሜን ኢትዮጵያ ጦርነት ወቅት ከአገር ሸሽተው የሄዱ ባለሀብቶችን ለረዥም ጊዜያት በኢንተርኔትና በአካል በመገናኘት ኩባንያዎቻቸው ተመልሰው ወደ ልማት እንዲገቡ ጥረቶች ቢደረጉም ፍላጎት አለማሳየታቸውን፣ በኢንዱስትሪ ፖርኮች ልማት ኮርፖሬሽን የኦፕሬሽንና ማኔጅመንት ምክትል ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ ካሚል ኢብራሂም ተናግረዋል፡፡
‹‹ኩባንያዎቹ ወደ ሌላ አገር ሄደው ለማልማት ማሽናቸውን ከአገር ይዘው ለመውጣት ጥያቄ በማቅረባቸው፣ እኛ እንደ መፍትሔ እያቀረብንላቸው ያለው አገር ውስጥ የገባና በአጠቃላይ አገራዊ ምርት የተመዘገቡ ማሽኖችን ወደ ሌላ አገር ከሚወስዱ፣ በአገር ውስጥ ወደ ሌላ አካባቢ በማዘዋወር ለማሠራት ጥያቄ አቅርበን እየጠበቅን፤›› ነው ብለዋል።
ነገር ግን ወ/ሮ ሶስና ጌታሁን የተባሉ የቋሚ ኮሚቴው አባል፣ መቀሌ የነበሩ ኢንቨስተሮች እዚያው መቆየት ካልፈለጉ ቦሌ ለሚ ወይም አዳማ እንዲያለሙ ለማድረግ እየተሠራ ነው የሚለው ምላሽ ትክክል አለመሆኑን፣ ኢንቨስተሮች በመቀሌ ኢንዱስትሪ ፓርክ ምን እንደጎደላቸው መጠየቅና ችግሩን መፍታት እንጂ ከአንድ አካባቢ አስነስቶ ወደ ሌላ ቦታ ለመውሰድ መሞከር ትክክል አይደለም ብለዋል። አክለውም ያልተመቹ ጉዳዮች ካሉ ኢንቨስተሮቹ ተጠይቀው መፍትሔ በማፈላለግ ሁኔታዎችን በማመቻቸት እዚያው ማቆየት እንጂ፣ ከአንድ አካባቢ ወደ ሌላ አካባቢ ማዘዋወር አግባብ አይደለም በማለት አሳስበዋል፡፡
ይህ በዚህ እንዳለ በዘጠኝ ወራት 128 ሚሊዮን ዶላር የሚያወጣ ምርት ወደ ውጭ ለመላክ ታቅዶ አፈጻጸሙ 83 ሚሊዮን ዶላር ብቻ ወይም የዕቅዱን 65 በመቶ ብቻ መሆኑን ኮርፖሬሽኑ ያቀረበው ሪፖርት ያስረዳል፡፡
የኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት ኮርፖሬሽን ዋና ሥራ አስፈጻሚ ፍሰሀ ይታገሱ (ዶ/ር) በዘጠኝ ወራት ለታየው የውጭ ምንዛሪ ማነስ ምክንቱን ሲያብራሩ፣ በግጭትና በአጎዋ ዕገዳ ሳቢያ ገቢ የመጨመር ሳይሆን እ.ኤ.አ. ከ2021 ጀምሮ የመቀነስ ሁኔታ እየታየ እንደነበር ተናግረዋል፡፡
ኢንቨስትመንት ሰላምና መረጋጋት የሚፈልግ በመሆኑ በሰሜኑ ጦርነት ምክንያት አዳዲስ ኢንቨስትመንቶች የመምጣት፣ እዚያ የነበሩት የመቀጠልና መልሶ ሥራ የመጀመር ጉዳይ በመቀሌ ብቻ ሳይሆን በሰሜን ኢትዮጵያ ባሉ ፓርኮች ተግዳሮት አጋጥሟል ያሉት ይታገሱ (ዶ/ር)፣ ‹‹ጦርነት እያለ ኢንቨስትመንት የሚታሰብ አለመሆኑን ልናስብበት፤›› ይገባል ብለዋል፡፡ አገር ጥለው የወጡት ከመቀሌ ብቻ ሳይሆን ከኮምቦልቻ፣ ከባህር ዳርና ከደብረ ብርሃን ብዙ ባለሀብቶች መሆናቸውን ገልጸዋል፡፡
ከመቀሌ ወጥተው ወደ ሌላ አገር እንሄዳለን ከሚሉ ባለሀብቶች በተጨማሪ፣ ከሐዋሳ፣ ከኮምቦልቻ፣ ከሰመራ፣ ከባህር ዳር፣ ከደብረ ብርሃን፣ ከቦሌ ለሚ ፓርኮች ጭምር ከአገር ለቀው መውጣታቸውን የገለጹት ዋና ሥራ አስፈጻሚው ችግሩ በአገር ላይ የመጣ ነው ብለዋል።
የመቀሌ ኢንዱስትሪ ፓርክ በ75 ሔክታር ላይ የተገነቡ 15 ሼዶችን የያዘ ሲሆን፣ በጦርነቱ ወቅት ከ50 በላይ ባለሀብቶች አገር ለቀው እንደወጡ ተገልጾ ነበር። ኮርፖሬሽኑ ባለፉት ዘጠኝ ወራት የፋብሪካ ሠራተኞች ፍልሰት ምጣኔ ከፍተኛ መሆን፣ የጥሬ ዕቃ አቅርቦት እጥረትና የይዞታ ይገባኛል ጥያቄዎች ዋና መሰናክል ሆነውብኛል ብሏል። የክፍያ ዝቅተኛ መሆንና የመኖሪያ ቤት እጥረት ለሠራተኞች መልቀቅ ዋነኛው መንስዔ መሆናቸው ተገልጿል፡፡ በኢንዱስትሪ ፓርኮች ከ72 ሺሕ በላይ ሠራተኞች ተቀጥረው እየሠሩ መሆናቸው ተገልጿል።
የመንግሥት የልማት ድርጅቶች ቋሚ ኮሚቴ ለኢንዱስትሪ ፓርኮች ኮርፖሬሽን ባቀረበው ጥያቄ፣ በልዩ ኢኮኖሚ ዞኖች በዘጠኝ ወራት 37,035 ሠራተኞች መልቀቃቸውን ከቀረበው ሪፖርት መረዳቱን ጠቅሶ ምክንያቱን ጠይቋል፡፡ ምክትል ዋና ሥራ አስፈጻሚው አቶ ካሚል በሰጡት ምላሽ በፓርኮቹ ውስጥ በሚቀጠሩ ሠራተኞች ልክ የሚለቁ መኖራቸውን፣ አልፎ አልፎም ከተቀጠሩት በላይ እንደሚለቁ ተናግረዋል። ለሠራተኞች መልቅቀ የቀረበው ምክንያት ከገጠር ጭምር የሚመጡና የኢንዱስትሪ ዕውቀት የሌላቸው በመሆናቸው ነው ተብሏል፡፡ አዳዲስ ፋብሪካዎች ሲቋቋሙ ሠራተኞች ከማሠልጠን ይልቅ በነባር ፋብሪካዎች ውስጥ ያሉ ሠራተኞችን እንደሚያስኮበልሉ ተናግረዋል፡፡
ምክትል ዋና ሥራ አስፈጻሚው ከፓርኮች የሚለቁት ሠራተኞች በክፍያና ጥቆማ ጥቅም ማነስ መሆኑን ጠቅሰው፣ ችግሩን በዘላቂነት ለመፍታት ቢታሰብበትና ሕግ ወጥቶ አነስተኛ የደመወዝ ወለል እንዲወሰን ቢደረግ ሲሉ ጠይቀዋል፡፡
ኢትዮጵያ የብሪክስ አባልነቷ ተጨማሪ የኢንቨስትመንት መዳረሻ እንድትሆን አድርጓታል ያሉት በኮርፖሬሽኑ የኢንቨስትመንት ፕሮሞሽንና ማርኬቲንግ ዘርፍ ሥራ አስፈጻሚው አቶ ዘመን ጁነዲን፣ አሜሪካ በቅርቡ በአገሮች ላይ በጣለችው ታሪፍ ምክንያት ኢንቨስተሮች ኢትዮጵያን መዳረሻ ለማድረግ ፍላጎት እያሳዩ ነው ብለዋል።
የኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት ኮርፖሬሽን የዋና መሥሪያ ቤት ሕንፃ ግንባታ ለማከናወን፣ እንግሊዝ ኤምባሲ አካባቢ አንድ ሔክታር መሬት ተቀብሎ የዲዛይን ሥራ ማጠናቀቁን አስታውቋል፡፡