ጌታቸው ረዳ የሚመሩት የሕወሓት ክንፍ ታደሰ ወረዳ ላይ ተቃውሞ ማሰማቱን ቀጥሏል

የቀድሞው የትግራይ ጊዜያዊ አስተዳደር ፕሬዝዳንት ጌታቸው ረዳ የሚመሩት የሕወሓት ክንፍ፣ ጀኔራል ታደሠ ወረደ እንደገና ያዋቀሩት ካቢኔ ሌሎችን ያገለለ፣ አቃፊ ያልኾነና ተቀባይነት የሌለው ነው በማለት ተቃውሟል።

ካቢኔው የተዋቀረው፣ የአንድን ቡድንና የወታደራዊ አዛዦችን ፍላጎት ብቻ በመስማት ነው ያለው ቡድኑ፣ የካቢኔው አወቃቀር ባስቸኳይ እንዲስተካከል ጠይቋል።

በጊዜያዊ አስተዳደሩ አወቃቀር ላይ ማስተካከያ ካልተደረገ ግን፣ የትግራይን ሕዝብ ከ”ኋላቀሩ ገዢ” ቡድን ለማላቀቅ ማናቸውንም የትግል ስልት ለመከተል እንገደዳለን በማለት አስጠንቅቋል።

ጀኔሬል ታደሠ የአዲሱን ካቢኔ ዝርዝር ይፋ ባያደርጉም፣ በደብረጺዮን የሚመራው የሕወሓት ክንፍ ምክትል ሊቀመንበር አማኑዔል አሠፋን ምክትል ፕሬዝዳንት ኾነው እንደተሾሙ ተሠምቷል።