ሆስፒታሉ ዝግ ስለሆነ አገልግልት ማግኘት አልቻልንም፤ ደምወዝ ስላልተከፈለን የስራ ማቆም አድማ እናደርጋለን

” ተመላላሽ የሕክምና ቀጠሮ ቢኖረንም ሆስፒታሉ ዝግ ስለሆነ አገልግልት ማግኘት አልቻልንም ” – ተገልጋዮች

➡️ ” ከ6 እስከ 9 ወራት ታግሰን የትርፍ ሰዓት ክፍያ ባለመከፈሉ ከአቅማችን በላይ ሆኖ ስራ አቁመናል” – የጤና ባለሙያዎች

🔴 ” የትርፍ ሰዓት ክፍያ አልተከፈለንም ብለዉ መደበኛ ስራቸዉን በሚያቆሙ ላይ ሕጋዊ እርምጃ እንወስዳለን ” – የዞን አስተዳዳሪ

በሲዳማ ክልል ማዕከላዊ ሲዳማ ዞን ሎካ አባያ ወረዳ በሀንጣጤ የመጀመሪያ ደረጃ ሆስፒታል የሚገኙ የጤና ባለሙያዎች ከ6 እስከ 8 ወራት የሰሩበት የትርፍ ሰዓት ክፍያ ባለመክፈሉ ስራ ለማቆም እንደሚገደዱ በመግለፅ ቅሬታቸዉን አሰምተዉ ነበር።

በወቅቱ የዞኑ አስተዳዳሪ ቅሬታዉ ተገቢ መሆኑን በመግለፅ ” ከክልል ብድር ጠይቀናል በጥቂት ቀናት ስለሚፈፀም የ5 ወራት ክፍያ በአንድ ላይ በመፈፀምና ቀሪዉን በየወሩ እንዲከፈላቸዉ ይደረጋል ” ሲሉ ምላሽ ሰጥተዉ ነበር።

ለቲክቫህ ኢትዮጵያ ቅሬታቸዉን ዳግም ያደረሱት የሆስፒታሉ ጤና ባለሙያዎች ” ከቅሬታዉ ምላሽ በኋላ ተጨማሪ አንድ ወር ታግሰን ለሙያ ቃል ኪዳናችንና ሕብረተሰቡን ማገልገል ስላለብን በችግሮች ዉስጥ አልፈን እየሰራን ብንቆይም አሁን ላይ ከአቅማችን በላይ በመሆኑ ስራ አቁመናል ” ሲሉ ገልፀዋል።

” ከ6 እስከ 9 ወራት የትርፍ ሰዓት ክፍያ ካለመፈፀሙም ባሻገር አመራሮች ነገሮች እንዲመቻቹላችሁ ‘ የብልፅግና ፓርቲ ሕንፃ ግንባታ መዋጮ የአንድ ወር ደመወዝ አዋጡ ‘ ብለዉን ሁሉም ባልተስማማበት ከመደበኛ ደመወዝ እየቆረጡ ነዉ ፤ በዚህም ለዘርፈ ብዙ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ቀዉሶች ተዳርገናል ” ሲሉ ተናግረዋል።

” ዶክተር ሆነህ ‘ ቸገረኝ አበድረኝ ‘ ማለት ያሳቅቃል ይህ በሞራልም እየጎዳን ነዉ ” ሲሉ ስሜታቸዉን ለቲክቫህ ኢትዮጵያ ያጋሩ ዶክተሮች ተናግረዋል።

እንዲሁ ሌላ የጤና ባለሙያ ” ለህክምና የመጣች አንዲት ታካሚ ዱቤ ልትጠይቀኝ መስሎኝ ተደብቅያለሁ ” ሲል እያሳለፉ ስላለው ህይወት ተናግረዋል።

ተገልጋዮች ምን አሉ ?

” በሀንጣጤ ሆስፒታል የሕክምና ክትትል ስለነበረን ግን ወደ ሆስፒታሉ  ቅዳሜ ጠዋት ስንሄድ ግቢዉ ዝግ ነበር፤ ጥበቃዉ የጤና ባለሙያዎች አለመግባታቸውን ነገረን ” ሲሉ አንድ የሆስፒታሉ ተገልጋይ ለቲክቫህ ኢትዮጵያ ተናግረዋል።

እኚሁ ተገልጋይ አማራጭ አጥተዉ በስልክ ከሕክምና ባለሙያዎች ባገኙት ምክር ከግል የጤና ተቋማት መድሐኒት ለመግዛት መገደዳቸውን ገልጸዋል።

ሳምንቱን በስራ ላይ አሳልፈዉ ለልጃቸዉ ሕክምና ቅዳሜ ወደ ሆስፒታሉ ቢመጡም ሐኪሞች ባለመኖራቸው ለሰዓታት ጠብቀዉ መዉጣታቸውን የገለፁት ሌላኛዉ የሀንጣጤ ከተማ ነዋሪ ከእሳቸዉም ዉጪ ሌሎችም አገልግሎት ለማግኘት መጥተዉ ሲያማርሩ ማየታቸዉንና ችግሩ ከጤና ባለሙያዎች የትርፍ ሰዓት ክፍያ ጋር የተያያዘ መሆኑን መስማታቸውን ተናግረዋል።

ሆስፒታሉ ለአከባቢዉ ሕብረተሰብ ከሚሰጠዉ አገልግሎት አንፃር የሚመለከታቸዉ አካላት ፈጣን መፍትሔ እንዲሰጡ ጠይቀዋል።

የዞን አስተዳዳሪ ምን አሉ ?

ቲክቫህ ኢትዮጵያም የማዕከላዊ ሲዳማ ዞን ዋና አስተዳዳሪ የሆስፒታሉ የቦርድ ሰብሳቢ አቶ መንግስቱ ማቴዎስን ለምን በተገባላቸዉ ቃል መሰረት ክፍያው አልተፈፀመላቸዉ ሲል ጠይቋል ? አቶ መንግስቱ በምላሻቸው ” አሁን ጥረት እያደረግን ነዉ፤ ከላይ በጀት ሲገኝ ነዉ ችግሩ የሚፈታዉ ” ያሉ ሲሆን ” ልጆቹም ስራ ለመስራትም ፈቃደኛ አይደሉም፣ መስራት የሚፈልግ ይቀጥላል ያልተመቸዉ ሊለቅ ይችላል ” ብለዋል።

” ኖሪማሊ ጉዳዩ እኔን የሚመለከተኝ አይደለም፤ ወረዳዉ ነዉ ባለቤቱ ” የሚሉት የዞኑ አስተዳዳሪ ” ሠራተኞቹ እየሄዱበት ያለው አካሄድ ተገቢ አይደለም፤ የትርፍ ሰዓት ክፍያ አልተከፈለንም ብለዉ መደበኛ ስራቸዉን በሚያቆሙ ላይ ሕጋዊ እርምጃ እንወስዳለን ” ሲሉ አስጠንቅቀዋል።

የሆስፒታሉ ሰራተኞች የትርፍ ሰዓት ስራ ብቻ ማቆማቸዉንና በተደጋጋሚ ቃል እየተገባ ስለማይፈፀምላቸዉ ስራ ማቆማቸዉን ገልፀዉልናል ይህን ማድረጋቸው ያስጠይቃቸዋል ወይ ? ሲል ቲክቫህ ኢትዮጵያ ላነሳላቸዉ ጥያቄ  ” መደበኛ ስራ ነዉ እያቆሙ ያሉት፣ ከደሞዝ መቁረጥ እስከ ማሰናበት እርምጃ ይወሰድባቸዋል ” ብለዋል።

” በአንፃሩ የትርፍ ሰዓት ስራ ማቆም መብታቸዉ ነዉ ሲሉም ” ተደምጠዋል።

ሰራተኞች ስራ ከማቆማቸዉ በፊት በጽሑፍ ለወረዳ ፣ ለዞኑና ለክልሉም ጤና ቢሮ ጭምር ቅሬታቸዉን ማቅረባቸውን ገልፀዉልናል ፤ በሆስፒታሉ የጤና ክትትል የበራቸዉና ለሕክምናም መጥተዉ በዕረፍት ቀናት አገልግሎት ባለማግኘታቸዉ የተቸገሩ ተገልጋዮችም ቅሬታቸዉን አሰምተዉናል ሲል ቲክቫህ ኢትዮጵያ ላነሳላቸዉ ጥያቄ አቶ መንግስቱ ” በአካል ካልመጣችሁ ከዚህ የበለጠ መረጃ ልሰጣችሁ አልችልም ! ” በማለት አቋርጠዋል።

ቲክቫህ ኢትዮጵያም ከሲዳማ ክልል ጤና ቢሮ በጉዳዩ ላይ ተጨማሪ ማብራሪያ ለማግኘት ያደረገዉ ሙከራ በድጋሚ አልተሳካም፤ ተጨማሪ መረጃዎችን ማግኘት ስንችል የምናካትት ይሆናል።