” ትግራይ ከተደገሰላት የባሰ አዘቅትና አዙሪት የምናድንበት ጊዜ አሁንና አሁን ብቻ ነው ” አለ በትግራይ ጊዜያዊ አስተዳደር ፕሬዜዳንት አቶ ጌታቸው ረዳ የሚመራው የህወሓት ቡድን።
አቶ ጌታቸው የሚመሩት የህወሓት ቡድን ባወጣው መግለጫ “ልዩነቶቻችን በይደር በማቆየት ቂምና ቁርሾ ቀርፈን እኔነትንና ጠቅላይነት አስተሳሰብ ከውስጣችን በማስወገድ ትግራይ እናድናት ” ብሏል።
ትግራይ ከገባችበት ቀውስና አጣብቂኝ ” ያድናታል ብዬ አምኜበታለሁ ” ያለውን የመፍትሄ ሃሳብ ለውይይት ማቅረቡ ያስታወቀው ቡድኑ ከቀረበው የተሻለ ክልሉን ማዳን የሚችል የመፍትሄ ሃሳብ ካለ ለማዳመጥ ዝግጁ መሆኑ ገልጿል።
ደብረፅዮን (ዶ/ር) የሚመሩትን ህወሓት በግልፅና ጠንካራ ቃላት የተቸም ሲሆን ጊዚያዊ አስተዳደሩ ለአንድ ዓመት መራዘሙ በመቀበል የሚከተሉት ሦስት የመፍትሄ ሃሳቦች አቅርበዋል :-
- ጊዚያዊ አስተዳደሩ ሁሉም አመለካከቶች በማቀፍ የፕሪቶሪያ የሰላም ስምምነት ማእከል በማድረግ መዋቅሩ ተጠናክሮ በአስቸኳይ መቋቋም አለበት።
- ዕድሜውን የተራዘመው ጊዚያዊ አስተዳደር ማቋቋም የሚያስችል ሁሉም አመለካከቶችና የፕሪቶሪያ የሰላም ስምምነት አፈራራሚዎች ያካተተ ፓለቲካዊ ውይይት ይቅደም።
- የትግራይ ሰራዊት ታጣቂዎች ወደ ማረፍያ ካምፓቸው ተመልሰው የሰላምና የፀጥታ ስራ ሙሉ በሙሉ በህዝባዊ ፓሊስ ይተካ ፤ የጊዚያዊ አስተዳደሩ መዋቅር እስከ ቀበሌ ድረስ ህዝብ ነፃ ሆኖ በመረጣቸው አስተዳዳሪዎች እንዲመራ ፣ ተግባሩ በአንድ ወር ውስጥ እንዲከናወን።
… ብሏል።
ፕሬዜዳንት አቶ ጌታቸው ረዳ የሚመሩት የህወሓት ቡድን ከደብረፅዮን (ዶ/ር) ህወሓት ቡድን ጋር ለመወያየት ዝግጁ መሆኑ ባወጣው ወቅታዊ መግለጫ ይፋ አድርጓል።