በከተሞች ባለቤትነት የሚነሱ ጥያቄዎች የፖለቲካ ውጥረት መንስዔ መሆናቸው ተነገረ

ሪፍት ቫሊ ኢንስቲትዩት በአዲስ አበባ ቤስት ዌስተርን ፕሪሚየም ሆቴል ባዘጋጀው ዓውደ ጥናት

በኢትዮጵያ በከተሞች ባለቤትነት ላይ የሚነሱ ጭቅጭቆችና ውዝግቦች፣ የፖለቲካ ውጥረት መነሻ እየሆኑ መምጣታቸውን በዘርፉ ጥናት ያቀረቡ ምሁራን ገለጹ፡፡

ሪፍት ቫሊ ኢንስቲትዩት “Urban Contestations in Ethiopia” በሚል ርዕስ በአዲስ አበባ ቤስት ዌስተርን ፕሪሚየም ሆቴል ባዘጋጀው ዓውደ ጥናት፣ የተለያዩ የኢትዮጵያ ከተሞችን ተሞክሮ ያቀረቡ ምሁራን እንደገለጹት፣ ከተሞችን በባለቤትነት የመቆጣጠር ሽሚያና መገፋፋት ከፍተኛ የፖለቲካ ውጥረት የፈጠረ ጉዳይ መሆኑን አመልክተዋል፡፡

የሆሳዕናን፣ የሐዋሳን፣ የአዲስ አበባን ጨምሮ የድሬዳዋን ከተሞች ሁኔታ ያቀረቡት ጥናት አቅራቢዎቹ በከተሞች ላይ የሚነሳው የባለቤትነት ፉክክርና ግጭት ኢኮኖሚያዊ፣ ባህላዊና ታሪካዊ መነሻ ያለው መሆኑን አስረድተዋል፡፡

በአዲስ አበባ የተለያዩ ሕዝባዊ በዓላትና ክንውኖች ፖለቲካዊ ገጽታን ተላብሰው መካሄዳቸው፣ ከተማው የእኛ ነው የሚለውን ፉክክር ለማጉላት እየዋለ መሆኑን ጥናት አቅራቢዎቹ ጠቅሰዋል፡፡ እንደ ሐዋሳ ያሉ ከተሞች ለሲዳማ ክልል መሰጠታቸው ‹‹በሌሎች የደቡብ ክልሎች ውስጥ በጋራ የገነባነውን ከተማ ተቀማን›› የሚል ስሜት መፍጠሩ ተገልጿል፡፡ በሆሳዕና ከተማ በሃይማኖት ተቋማት መካከል የሕዝብ መሰባሰቢያ ቦታ ለማግኘት የተፈጠረው ፉክክርና ከውጭ በሚላክ የሐዋላ ገንዘብ የሚፋጠነው የከተማው ዕድገት ውጥረት መፍጠሩ ተጠቁሟል፡፡ በድሬዳዋ ደግሞ ከዚህ አለፍ ብሎ የከተማ ባለቤትነት ፉክክሩ ሁለት ራሳቸውን የቻሉ ክልሎች የሚያነሱት ጥያቄ መነሻ እንደሆነ ተገልጿል፡፡ በእነዚህና በሌሎች ከተሞች ላይ የሚነሳው የይገባኛል ፉክክር በአግባቡ ካልተመራና ይህን ችግር የሚፈታ የከተማ ልማት ፖሊሲ ካልተተገበረ፣ ሁኔታዎች ወደ ግጭት ሊያመሩ የሚችሉበት ዕድል መኖሩን ነው ጥናት አቅራቢዎቹ አሳሳቢ ሲሉ የጠቆሙት፡፡

የሪፍት ቫሊ ኢንስቲትዩት ዋና ኃላፊ ሰሚር ዩሱፍ (ዶ/ር)፣ ኢትዮጵያ ‹‹ከአፍሪካ ከተሜነት ገና ያላደገባትና ያልተስፋፋባት›› በሚል የምትጠቀስ አገር መሆኗን ጠቅሰው፣ አሉ በሚባሉ ከተሞችም ባለቤት ነኝ በሚል ውዝግብ መስፋፋቱን አመልክተዋል፡፡ ‹‹ከተሜነት በኢትዮጵያ ገና 23 በመቶ ዕድገት ላይ ነው የሚገኘው፡፡ ከተሞች ለአገራዊ ጥቅል ምርት (ጂዲፒ) ያላቸው ድርሻም ገና 38 በመቶ ላይ ነው የሚገኘው፡፡ ይሁን እንጂ ገና ባላደገውም በዚህ መሰሉ የከተሜነት ሁኔታ ላይም ቢሆን የባለቤትነቱ ፉክክርና ሽሚያው እየተጠናከረ መጥቷል፤›› ሲሉ የተናገሩት ኃላፊው፣ ተቋማቸው ለዚህ ችግር መፍትሔ ለማፈላለግ አልሞ የተለያዩ ከተሞችን ያጠኑ ተመራማሪዎችን ያሰባሰበ መድረክ ማዘጋጀቱን አብራርተዋል፡፡

ከተሜነት በኢትዮጵያ ገና ያደገ ባይሆንም አሁን እያሳየ ያለው የማደግ ፍጥነቱ ግን ፈጣን በሚባል አምስት በመቶ ምጣኔ ላይ መገኘቱን በመጠቆም፣ ጉዳዩ ከወዲሁ ካልታሰበበት ወደፊትም በከተሞች ላይ የሚደረገው ፉክክር እንደሚጨምር ነው ያስረዱት፡፡

የሆሳዕና ከተማን ዕድገትና መስፋፋትና እየገጠማት ያለውን ፉክክር በተመለከተ ጥናት ያቀረቡት ደረጀ ፈይሳ (ዶ/ር)፣ ከተማይቱ ከጦር ካምፕነት ተነስታ ዛሬ ከውጭ የሚላክ የሐዋላ ገንዘብ (ሬሚታንስ) መዲና ለመሆን የበቃችበትን ታሪክ ፈትሸዋል፡፡ የሀዲያ ማኅበረሰብ ‹‹የሀዲያ ሡልጣኔት›› ተብሎ በታሪክ ከሚጠቀስበት ከመካከለኛው ክፍለ ዘመን ጀምሮ ሲሰፋና ሲጠብ የመጣ ጂኦግራፊያዊ ወሰኖችን ይዞ ቆይቶ፣ አሁን ሆሳዕናን ዋና ከተማው አድርጎ የተመሠረተ ዞን እንደሆነ ገልጸዋል፡፡ ‹‹ከዞኑ ሕዝብ ወደ 75 በመቶው ፕሮቴስታንት እምነትን የሚከተል ነው፡፡ ነገር ግን የፖለቲካ ልሂቃኑ በቀደመው የሀዲያ እስላማዊ ታሪክና በአሁኑ ፕሮቴስታንታዊ ማንነት መካከል ሲዋልሉ ይታያሉ፡፡ ዞኑ ከአጎራባች ከስልጤ፣ ከማረቆ፣ ከቀቤናና ከጉራጌ ማኅበረሰቦች ጋር ያለው ግንኙነትም በዚሁ የሚወሰን ይመስላል፡፡ አሁን ከውጭ በተለይም ከደቡብ አፍሪካ የሚላከው የሐዋላ ገንዘብ ለከተማዋ ዕድገትና መስፋፋት ዋና መሠረት ነው፡፡ ይሁን እንጂ ዕድገቱና መስፋፋቱ በከተማዋ ዳርቻ ያሉ አርሶ አደሮችን መሬት በከፍተኛ ደረጃ እንዲቸበቸብ እያደረገ ነው፡፡ የሆሳዕና ዕድገት በአንፃራዊነት ሰላማዊ የሚባል ቢሆንም፣ ነገር ግን ለሃይማኖት በዓላት ቦታ ለማግኘት በፕሮቴስታንትና በኦርቶዶክስ ሃይማኖቶች መካከል የተፈጠረው ውዝግብ በቀላሉ የሚታይ አይደለም፤›› ሲሉ የገለጹት ደረጀ (ዶ/ር)፣ የከተማው ባለቤት ሆኖ ለመታየት የሚደረገው ፉክክር ገና ያልለየለት መሆኑንና ከከተማው ዕድገት ጋር እንደሚጨምር ተናግረዋል፡፡ 

ሆሳዕና ከተማ የአዲሱ የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ዋና መቀመጫ ለማድረግ ከፍተኛ ጥረት ቢደረግም፣ ነገር ግን ሐዋሳ የሲዳማ ሆና በመቅረቷ በሌሎች ዞኖች ዘንድ ከፍተኛ ቅሬታ ስለተፈጠረ፣ ያ እንዳይደገም በርካታ ዞኖችን የኢኮኖሚ መቀመጫ የማድረግ አሠራር መተግበር መጀመሩን አመልክተዋል፡፡ ‹‹ሁሉንም እንቁላልህን በአንድ ቅርጫት ውስጥ አታስቀምጥ›› የሚል ስሜት በተለያዩ ዞኖች መስረፁን የጠቀሱት ደረጀ (ዶ/ር)፣ ሀዲያ የክልል ዋና ከተማ ለመሆን ከተለያዩ ዞኖች ከተሞች ጋር ፉክክር እንደገጠማት ነው የገለጹት፡፡

ይህንኑ በሚያጠናክር ሁኔታ የሐዋሳ ከተማን የባለቤትነት ፉክክር ያቀረቡት ሌላኛው ተመራማሪ ሮቤል ሙላቱ (ዶ/ር) በበኩላቸው፣ በሲዳማ ዋና መዲና ሐዋሳ የሚነሳው ሽኩቻ ብዙ ዓይነት መልክ ያለው መሆኑን አሳይተዋል፡፡ ‹‹ሐዋሳን ማዕከል አድርጎ በሲዳማና በወላይታ ማኅበረሰቦች መካከል የሚነሳው ፉክክር ለምሳሌ የሥራ ዕድል ተሻሙን የሚል፣ ወይም የኢኮኖሚ ጥያቄን ያነገበ ነው፡፡ በፕሮቴስታንቶችና በኦርቶዶክሶች መካከል ደግሞ በሕዝብ መሰብሰቢያ ቦታዎችና በሃይማኖታዊ በዓላት ፉክክር ይታያል፡፡ በሰፊው መነገር ያለበት ቋንቋ፣ በሰፊው መንፀባረቅ ያለበት ባህል የማን ማኅበረሰብ መሆን አለበት በሚለው ጥያቄ ላይም በከተማዋ ፉክክር ይታያል፡፡ ለመታየት፣ በሚዲያ ለመጉላት የሚደረገው ፉክክር ደግሞ የከተማው ዕድገትና መስፋፋት እየፈጠራቸው ካሉ የመሠረተ ልማት ዕድገቶችና የመሬት ቅርምቶች ጋር ተደማምሮ ውስብስብ ገጽታ ያለው ሽኩቻ ተፈጥሯል፤›› ሲሉ ተወልደው ያደጉበትን ከተማ ገጽታ አቅርበዋል፡፡

ሮቤል (ዶ/ር) የሐዋሳ ኢንዱስትሪ ፓርክ ከተለያዩ የኢትዮጵያ ክፍሎች ሠራተኞች እንዲመጡ ያደረገ መሆኑን በመጠቆም፣ የከተማዋ ዕድገት የፈጠረው ኅብረ ብሔራዊ ብዝኃነት ቀላል አለመሆኑን ጠቅሰዋል፡፡ ያም ቢሆን ግን የሲዳማ ማኅበረሰብ ታሪክን መሠረት ያደረገ የከተማ ባለቤትነት ጥያቄ ሲያነሳ መቆየቱን ጠቁመው፣ ሲዳማ ክልል መሆኑ በከተማዋ ላይ ሙሉ ባለቤትነት አለኝ የሚል ስሜት መፍጠሩን ገልጸዋል፡፡ ታሪካዊ የከተማ ባለቤትነት ጥያቄው ዕውቅና ሊሰጠው የሚገባ ቢሆንም፣ ነገር ግን የከተማዋን ሰፊ ብዝኃነት በዚያው ልክ ዕውቅና የሚሰጥና አካታች የከተማ አስተዳደር መመሥረት ካልተቻለ ሐዋሳ የግጭት ማዕከል ሆና እንደምትቀጥል ነው ያብራሩት፡፡

በአዲስ አበባ ከተማ የሚነሳውን ፉክክር በተመለከተ ጥናት ያቀረቡት ተመራማሪዋ ዳልያ አሸናፊ በበኩላቸው፣ ሕዝባዊ በዓላትንና ክንውኖችን ማዕከል ባደረገ ሁኔታ ከተማው የእኛ ነው የሚለውን ስሜት የተለያዩ ወገኖች ሊያንፀባርቁ ሲሞክሩ እንደሚታይ ገልጸዋል፡፡

‹‹የዓድዋ ድል በዓልን ለማክበር የሚደረገው ሽኩቻ፣ የኢሬቻ በዓል ሲከበር የሚንፀባረቀው ስሜት፣ ታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ ዝግጅት በየዓመቱ ሲመጣ የሚንፀባረቁ ስሜቶች፣ እንዲሁም በመስቀል አደባባይ ላይ የሚነሳው የባለቤትነት ጥያቄ በከተማው ዙሪያ የሚነሳውን የባለቤትነት ፉክክር ያጠናከሩ ጉዳዮች ናቸው፤›› ሲሉ ተመራማሪዋ ገልጸዋል፡፡ ይህ ደግሞ በአንድ በኩል በአገሪቱ መጣ የሚባለውን የፖለቲካ እንዲሁም የትርክት ለውጥን መሠረት በማድረግ የተፈጠረ የፉክክር ስሜት መሆኑን ገልጸዋል፡፡ በመንግሥት ወገንና በደጋፊዎቹ ከተማዋ የሁሉም ማኅበረሰቦች ማንነትና ባህል የሚንፀባረቅባት ኅብረ ብሔራዊ መዲና እየሆነች ነው የሚል አቋም የሚንፀባረቅ ቢሆንም፣ ነገር ግን በታሪክ ማደስና የጋራ ትርክት መፍጠር ስም ነባር የከተማዋ ማንነት የመደምሰስና የሌሎችን የኅብረተሰብ ክፍሎች ማንነትና መገለጫ የማሳጣት ዘመቻ ተከፍቷል የሚል ጠንካራ የተቃውሞ ስሜት የፈጠረ ጉዳይ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡

በአዲስ አበባ የሚካሄደው የባለቤትነት ሽኩቻ ከነባር ይዞታችንና መሬታችን ተገፋን ወይም ተነቀልን የሚል ኢኮኖሚያዊ መሰሠት ያለው ብቻ ሳይሆን ከተማዋ በፖለቲካ፣ በሃይማኖት፣ በባህል፣ በቋንቋና በአጠቃላይ በታሪክ ማንን የምትወክልና ምን መሳይ ትሁን የሚል ይዘት ያለው መሆኑን የጠቀሱት ተመራማሪዋ፣ መንግሥት ከእስካሁኑ የተሻለ አካታች ከተማ ፖሊሲ መተግበር አስፈላጊው እንደሆነ አሳስበዋል፡፡

በከተማዋ ሕዝባዊ በዓላትን ለማክበር ነፃነት የማጣት፣ ያለ መወከልና በልማት ሥራዎችም ተጠቃሚ ያለ መሆን ስሜት የሚሰማውና ቅሬታ የሚያቀርበው የኅብረተሰብ ክፍል ቀላል አለመሆኑን የጠቆሙት ተመራማሪዋ፣ አዲስ አበባ እያደገችና ዓለም አቀፍ የኢኮኖሚ ማዕከል እየሆነች ነው ቢባልም፣ ይህ ግን ከብዙኃኑ ነዋሪዋ ፍላጎት ጋር ታርቆ መሄድ አለበት ብለዋል፡፡ ከዚህ በተጨማሪም የመስቀል አደባባይ ባለቤትነት ጥያቄ፣ በተለይ በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህኦ ቤተ ክርስቲያን የሚነሳው የታሪክ ባለቤትነት ጥያቄ ቦታው ለሁሉም ወገኖች ሕዝባዊ በዓላት ሊውል ይገባል ከሚሉ የኅብረተሰብ ክፍሎች ጋር ሃይማኖታዊና ታሪካዊ መነሻ ያለው ፉክክር እንዲፈጠር ማድረጉንም አክለዋል፡፡

ድሬዳዋን በተመለከተ መነሻ ሐሳብ የሰጡትና ስለጥናቶቹ ማጠቃለያ ያቀረቡት እዮብ ባልቻ (ዶ/ር) በበኩላቸው፣ የኢኮኖሚ ዕድል ተጠቃሚ ለመሆን፣ በውጭና በአገር ውስጥ በሚፈጠሩ ለውጦች፣ የፖለቲካ ዕውቅና ለማግኘት ሲባል፣ እንዲሁም የጋራ መጠቀሚያ ቦታዎችን ለማግኘት ሲባል በከተሞች ላይ በተለያዩ ወገኖች የባለቤትነት ጥያቄዎች እንደሚነሱ ገልጸዋል፡፡ ጥያቄዎቹን ደግሞ ታሪካዊና ሃይማኖታዊ ቀለም አላብሶ ማቅረብ የተለመደ መሆኑንና በኦሮሚያ ቄሮ፣ በአማራ ሳተናው/ፋኖ፣ በሲዳማ ኤጀቶ፣ በሀዲያው ኬቤራ የተባሉ የወጣት አደረጃጀቶችን በመፍጠር በከተሞች ላይ ያለን የፖለቲካ ፍላጎት ለማስፈጸም ሲሞከር መቆየቱን አመልክተዋል፡፡

በድሬዳዋ ባለቤትነት ጉዳይ ደግሞ ጥያቄው በሁለት ክልሎች መነሳቱ ለየት ያለ መሆኑን በመጠቆም፣ በከተሞች ባለቤትነት ጉዳይ የሚነሳው ሽኩቻ ብዙ ዓይነት ገጽ ያለው መሆኑን የሚመልስና ችግሩን በዘላቂነት የሚፈታ የከተማ ፖሊሲ አገሪቱ ካልተከተለች ችግሩ እንደሚወሳሰብ ነው ያስረዱት፡፡