የግሪክ ኮሚኒቲ ትምህርት ቤት ቦታው ለኦሮሚያ ክልል ፕሬዝደንት ፅ/ቤት ማስፋፊያ ስለሚፈለግ እንዲነሳ ታዘዘ
(መሠረት ሚድያ)- እድሜ ጠገቡ የግሪክ ኮሚኒቲ ትምህርት ቤት እና የግሪክ ክበብ አሁን ላይ የሚገኙበት ቦታ ለኦሮሚያ ክልል ፕሬዝደንት ፅ/ቤት ማስፋፊያነት ስለሚፈለግ እንዲነሱ እንደተነገራቸው ማረጋገጥ ችለናል።
የቂርቆስ ክፍለ ከተማ ወረዳ 1 የመሬት ልማት እና አስተዳደር ፅ/ቤት በቅርቡ ለትምህርት ቤቱ እና ክበቡ በፃፈው ደብዳቤ ይዞታው ከኦሮሚያ ክልል ፕሬዝደንት ፅ/ቤት ማስፋፊያነት እንደሚፈለግ ገልጿል።
ትምህርት ቤቱ ደብዳቤው እንደደረሰው ለቦርዱ እንዲሁም ለውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር፣ ለትምህርት ሚኒስቴር እና ሌሎች ለሚመለከታቸው አካላት ማሳወቁን እና መልካም ምላሽ እየጠበቀ መሆኑን መሠረት ሚድያ የደረሰው መረጃ ይጠቁማል።
ከአንድ አመት ተኩል በፊት የግሪክ ኮሚኒቲ ት/ቤት ከፍርድ ቤት የእግድ ትዕዛዝ ውጪ ግቢው በፖሊስ እንደተያዘበት ለህዝብ አሳውቆ ነበር። በወቅቱ ጉዳዩን ሰምተው ለማብረድ ወደ ስፍራው ያቀኑት በኢትዮጵያ የግሪክ አምባሳደር እንደተገፈተሩ እና ከግቢው ለቀው እንዲወጡ እንደተደረጉ ይታወሳል።
“አምና ትምህርት ቤቱ ላይ ያ ሁሉ ወከባ እና የስም ማጥፋት ሲደርስ ለምን እንደነበር የገባን አሁን ነው፣ መሬቱን ለመንጠቅ የተጠነሰሰ ሴራ ነበር” በማለት አስተያየታቸውን የሰጡ አንድ ጉዳዩን የሚከታተሉ የኮሚኒቲው አባል ደብዳቤው ለብዙዎች አስደንጋጭ እንደሆነ ጨምረው ተናግረዋል።
የግሪክ ኮሚኒቲ ትምህርት ቤት ለበርካታ አስርት አመታት ተማሪዎችን ተቀብሎ ሲያስተምር የቆየ ሲሆን የግሪክ ኮሚኒቲ በኢትዮጵያ ያለውን ከ200 አመት በላይ ታሪክ ይዞ የቆየ መሆኑ ይነገርለታል።