በጅማ ዞን ጌራ ወረዳ በተፈጠረው ችግር የተፈናቀሉና ቤት ንብረታቸው ለተቃጠለባቸው ሰዎች ልዩ ትኩረት እንዲሰጥ፣ በጥቃቱ የተሳተፉት አካላትም ለሕግ እንዲቀርቡ እናት ፓርቲ አሳሰበ።
ወደ 10 ሺሕ ወገኖችን የከፋ ዞን በቀናነት ተቀብሎ እንዳስጠለለና የተወሰኑት ወደ ቄያቸው እየተመለሱ እንደሆነ መገንዘቡን፣ ተፈናቃዮችን ወደ ቄያቸው የመመለሱን ተግባር በመልካሙ እንደተረዳው፣ ይሁን እንጂ አሁንም ትኩረት የሚሹ ወገኖች እንዳሉ በላከንልን መግለጫ ገልጿል።
“ በአንጻሩ ቤት፣ ንብረት የተቃጠለባቸው በትምህርት ቤቶች ተጠልለው ስለሚገኙ፣ አሁንም አላስፈላጊ ወከባዎችና ‘ያላስረከባችሁት መሣሪያ አለ አምጡ’ በሚል ማንነት ተኮር ማሳደድ እየደረሰ እንደሚገኝ” አስረድቷል።
“እንዲያውም የተወሰኑ ሰዎች ተመልሰው ለመፈናቀል እየተዳረጉ መሆኑን፣ በግድያና ማቃጠል የተሳተፉ በውል ተጣርቶ ለፍርድ አለመቅረባቸውና ፍትህ አለመስፈኑ ችግር እንደፈጠረ፣ ሕዝቡ ሀብትና ንብረቱን ስላጣ ለረሃብ እንደተጋለጠ ለመረዳት ችለናል” ነው ያለው።
“ ስለሆነም አሁንም በአቅራቢያ የሚገኘው የመከላከያ ኃይል የማረጋጋቱን ሥራ ወስዶ እንዲሰራና ቤታቸው ተቃጥሎ በድንኳንና ትምህርት ቤት የተጠለሉ ወገኖቻችን በአፋጣኝ የሚቋቋሙበት ሁኔታ እንዲመቻች በአጽንዖት እንጠይቃለን ” ሲል አሳስቧል።
የተፈጠረውን “ሞትና ከፍተኛ የንብረት ውድመት” ያስከተለ፣ “እጅግ አስከፊ ማንነት ተኮር ጥቃት” በማውገዝ የመከላከያ ኃይል ቦታውን እንዲቆጣጠረው፣ ተፈናቃዮች ወደ የቄያቸው እንዲመለሱ፣ “ወደ እልቂት የሚመሩ የባለስልጣናት ያልተገሩ ንግግሮች እንዲታረሙ” ከዚህ ቀደም ማሳሰቡን ፓርቲው አስታውሷል።
