የዩክሬኑ ፕሬዝዳንት ቮለድሚር ዘለንስኪ ስልጣን ሊለቁ እንደሚችሉ ጠቆሙ።
ፕሬዝዳንቱ ከሩሲያ ጋር የገቡበትን ጦርነት 3ኛ ዓመት ምክንያት በማድረግ ከጋዜጠኞች ጋር ቆይታ አድርገው ነበር።
በዚህም ወቅት ” በዩክሬን ዘላቂ ሰላም የሚረጋገጥ ከሆነና ግጭትን ለማስቀረት የሚጠቅም ሆኖ ከተገኘ ከኃላፊነት እነሳለሁ ” ሲሉ ተናግረዋል።

” ለሰላም አስተዋጽኦ ለማድረግ ስልጣን እንዳስረክብ ከተጠየኩ ዝግጁ ነኝ ” ነው ያሉት።
የNATO አባል የሚያደርግ እድል ካለም ስልጣናቸውን እንደሚለቁ አሳውቀዋል።
ይህ የዘለንስኪ አስተያየት የተሰነዘረው የአሜሪካ ፕሬዜዳንት ዶናልድ ትራምፕ ዘለንስኪን ‘ አምባገነን ‘ ብለው ከወረፏቸው በኋላ ነው።
ትራምፕ ዘለንስኪን ” ያለ ምርጫ ሥልጣን የተቆናጠጡ አምባገነን ” ብለዋቸው ነበር።
በተጨማሪ ‘ ዘለንስኪ በሕዝብ ዘንድ ቅቡልነት የሌላቸው ‘ ሲሉ አጣጥለዋቸዋል።
ዘሌንስኪ በትራምፕ አስተያየት ” እምብዛምም አልተናደድኩም ” የሚል ምላሽ ሰጥተዋል።
አክለውም ” በዛሬ የዩክሬን ደኅንነት ላይ አተኩራለሁ፤ መቼስ ለዐሥርታት በሥልጣን ላይ አልቆይም ” ብለዋል።
በዩክሬን አገሪቱ ጦርነት ላይ ስላለች በማርሻል ሕግ ምርጫ ታግዷል።
አሜሪካ በዩክሬን ላይ ፊቷን ማዞሯን ተከትሎ ዘለንስኪ በተከታታይ የምዕራብ አገራትን እርዳታ እንዲለግሷቸው እየወተወቱ ነው።
ዛሬ ሰኞ ከበርካታ ምዕራባውያን መሪዎች ጋር በአካልና በስልክ እንደሚገናኙ ተነግሯል።
ዘለንስኪ፣ አሜሪካን በተመለከተ ከአስታራቂነት ሚናዋ ባሻገር አጋራቸው እንድትሆን ምኞታቸው እንደሆነ ተናግረዋል።
የአሜሪካ ሚና “በእርግጥ ከሽምግልና በላይ እንዲሆን እፈልጋለሁ…ሽምግልና ብቻውን በቂ አይደለም” ብለዋል፤ ዘለንስኪ።
በአንጻሩ አሜሪካ ዩክሬንን ገሸሽ ያደረገ የሰላም ንግግርና ድርድር በሳኡዲ አረቢያ ጀምራለች።
ዶናልድ ትራምፕ የዩክሬን ጦርነት በአጭር ጊዜ እንዲቆም አበክረው ይሻሉ።
ይህም ብቻ ሳይሆን አገራቸው አሜሪካ በባይደን አስተዳደር ለዩክሬን የሰጠችውን ‘ግማሽ ትሪሊዮን’ ዶላር እርዳታ ዩክሬን መልሳ እንድትከፍል እየጠየቁ ነው።
ዘለንስኪ በበኩላቸው እንዲህ ዓይነት ገንዘብ ከአሜሪካ እንዳልተሰጣቸውና በድምሩ100 ቢሊዮን ዶላር ብቻ እንደተሰጣቸው፣ ያም ቢሆን ብድር ሳይሆን እርዳታ እንደነበረ ነው የሚናገሩት።
የትራምፕ አስተዳደር አሜሪካ ለዩክሬን ለሰጠችው ወታደራዊ ዕርዳታ በምላሹ የዩክሬን የተፈጥሮ ውድ ማዕድን እንዲሰጠው ይሻል።
ዘለንስኪ በበኩላቸው፣ “ከትውልድ ወደ ትውልድ ተከፍሎ የማያልቅ ዕዳ” ላይ ስምምነት ፊርማቸውን እንደማያኖሩ ተናግረዋል።
ሆኖም በጉዳዩ ላይ ከአሜሪካ ጋር ንግግር እንዳልተቋረጠ መጠቆማቸውን ቢቢሲ ዘግቧል።