ለፕሪቶሪያው ስምምነት ገለልተኛ ዋስትና ሰጪ አካል አለመኖሩ ስጋት አሳድሯል ተባለ

አፍሪካ ኅብረት፣ ለፕሪቶሪያው የግጭት ማቆም ስምምነት ገለልተኛ ዋስትና ሰጪ አካል አለመኖሩ የስምምነቱ አተገባበር እንዲጓተት ምክንያት መኾኑን ከሳምንት በፊት ከስምምነቱ በተገኙ ልምዶች ዙሪያ በኅብረቱ ጽሕፈት ቤት የተካሄደው ውይይት ማጠቃለያ ሪፖርት አመልክቷል።

በዚህ ምክንያት፣ የስምምነቱ አተገባበር ሂደት ተዓማኒነት እንዲያጣና የርስበርስ መተማመን እንዲጠፋ ማድረጉን ሪፖርቱ ይጠቅሳል። በሕወሓትም ኾነ በፌደራል መንግሥቱ አንዳንድ ባለሥልጣናት ዘንድ በኦሊሴጎን ኦባሳንጆ ገለልተኛነት ላይ ጥርጣሬዎች የነበሩ መኾኑ ሌላው ችግር እንደነበርም ሪፖርቱ ያብራራል።

የአንዳንድ የፌደራል መንግሥቱ ባለሥልጣናት ጥርጣሬ፣ ኦባሳንጆ ለቀድሞው ጠቅላይ ሚንስትር መለስ ዜናዊ ቅርበት ነበራቸው ከሚል የሚመነጭ መኾኑንም ሪፖርቱ ያስረዳል። ኹለቱ ወገኖች ፕሪቶሪያ ላይ ላደረጉት ድርድር ወጪውን የሸፈነው የአፍሪካ ልማት ባንክ ነበር ተብሏል።