በአማራ ክልል በመንግሥት የጸጥታ ኃይሎችና በፋኖ ታጣቂዎች ግጭት ከተፈጠረ ወዲህ፣ በክልሉ እስከታችኛው የመንግሥት መዋቅር ያሉ አመራሮች ከሥራ መልቀቅ እንደማይፈቀድላቸው ዋዜማ ሰምታለች።
ዋዜማ፣ አመራሮቹ ከአመራርነት ተነስተው በባለሙያ የሥራ መደብ ለመቀጠል እንኳ ጥያቄያቸው ተቀባይነት እንደማያገኝ የተለያዩ አመራሮችን አነጋግራ ተረድታለች።
በባሕርዳር ከተማ አንድ የክፍለ ከተማ የብልጽግና ፓርቲ ቅርንጫፍ ኃላፊ በፋኖ ታጣቂዎች ታግተው 700 ሺሕ ብር ገደማ ከፍለው ከተለቀቁ በኋላ በኃላፊነት መቀጠል እንደማይፈልጉ ቢያሳውቁም፣ ጥያቄያቸው ውድቅ እንደተደረገም ምንጮች ተተናግረዋል።
ምንጮቹ፣ ሥራ ለመልቀቅ የሚጠይቅ አመራር፣ “የጽንፈኛው ቡድን” ደጋፊ ነህ ተብሎ ሊጠረጠርና ሊታሠር ይችላል ብለዋል።
የከተማዋ ኮማንድ ፖስት ከታጣቂዎች ጋር ግንኙነት አላቸው በሚል የሚጠረጥራቸው አመራሮች በዳንግላ ከተማ ወደሚገኝ የተሃድሶ ማሠልጠኛ እንደሚላኩም ተገልጧል። ከታጣቂዎች ጋር ግንኙነት አላችሁ በሚል ስለተጠረጠሩ ብቻ አለቆቻቸው ከሕግ ውጭ ከሥራ ያባረሯቸው ኹለት የከተማዋ አመራሮችን እንደሚያውቁም አንድ ምንጩ ለዋዜማ ተናግረዋል። https://youtu.be/Dj101hK0ETU?si=gyf6kU6Kc-mIAUQE