የአይደር ሪፈራል ሆስፒታል ሠራተኞች የተቃውሞ ሰልፍ አካሄዱ

በመቀሌ የሚገኘው የአይደር ሪፈራል ሆስፒታል ሠራተኞች፣ ያልተከፈለ ውዝፍ ደመወዛቸው ሳይከፈላቸው መቅረቱን በመቃወም ትናንት በከተማዋ የተቃውሞ ሰልፍ ማካሄዳቸውን የትግራይ ቴሌቪዥን ዘግቧል።

የሆስፒታሉ ሠራተኞች፣ በሰሜኑ ጦርነት ወቅት ያልተከፈላቸው የ17 ወራት ውዝፍ ደመወዝ እንዲከፈላቸው በሰልፉ ላይ መጠየቃቸውን ዘገባው ጠቅሷል።

ሠልፈኞቹ ያልተከፈላቸው የትርፍ ሰዓት ክፍያ ጭምር እንዲከፈላቸውና የትራንስፖርት አገልግሎት እንዲሻሻልላቸው መጠየቃቸውንም ዘገባው አመልክቷል። በተቃውሞ ሰልፉ ላይ ሐኪሞች፣ ነርሶችና ሌሎች ባለሙያዎችና ሠራተኞች ተሳትፈዋል ተብሏል።

የሆስፒታሉ ሠራተኞች ተቃውሟቸውን ያሰሙት፣ የክልሉ ጊዜያዊ አስተዳደር የመንግሥት ሠራተኞች በውዝፍ ደመወዛቸው ዙሪያ በፍርድ ቤት ክስ እንዳይመሠርቱ በማገድ ያወጣውን ደንብ ውድቅ በማድረግ፣ የክልሉ መምህራን ማኅበር ውዝፍ የመምህራን ደመወዝ እንዲከፍል የመሠረተው ክስ በፍርድ ቤት መታየቱን እንዲቀጥል በወሰነ ማግስት ነው።