የአሌክሳንደሪያ ከተማ፣ቨርጂኒያ ለመጀመሪያ ጊዜ 129ኛውን የአድዋ ድል በዓል አስመልክቶ አዋጅ አውጇል

የኢትዮጵያ ውርስና ቅርስ ማኅበር በሰሜን አሜሪካ ለመጀመሪያ ጊዜ የአሌክሳንደሪያ ቨርጂኒያ ከተማ ምክር ቤት የአድዋ ድል በዓልን አስመልክቶ አዋጅ እንዲያውጅ አስደርጓል። የአሌክሳንደሪያ ከተማ ምክር ቤት በከንቲባዋ ወ/ሮ አሊያ ጋስኪን ፊርማ ባወጣው አዋጅ 129ኛውን የአድዋ ድል አስመልክቶ ለኢትዮጵያዊያን “የእንኳን ደስ አላችሁ” መልዕክት አስተላልፏል። ከዚህም በተጨማሪ የአድዋ ድል የሚከበርበትን የካቲት 23 ቀን 2017 ዓ.ም. (ማርች 2 ቀን 2025) የአድዋ ድል በዓል ቀን ሆኖ እንዲታሰብ አዋጅ አውጇል። በአዋጁ ላይ የአድዋ ድል ለኢትዮጵያዊያን ብቻ ሳይሆን ለመላው ጥቁር ህዝብም ድል መሆኑንና በቅኝ ግዛት ተይዘው ለነበሩ በመላው ዓለም ለሚገኙ ህዝቦችም ለነጻነታቸው እንዲታገሉ መልካም ምሳሌና ማበረታቻ እንደሆናቸው ተመልክቷል። በአሌክሳንደሪያ ከተማ ውስጥ በርካታ ኢትዮጵያዊያን እንደሚኖሩ የሚታወቅ ሲሆን የወጣው አዋጅ ኢትዮጵያዊያን አሜሪካዊያን በማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊያው፣ ባህላዊ መስኮች ያበረከቱትን ገንቢ አስተዋጽኦ ዕውቅና ሰጥቷል።

የኢትዮጵያ ውርስና ቅርስ ማኅበር በሰሜን አሜሪካ የዘንድሮውን የአድዋ ድል በዓል ከአቡጊዳ የቋንቋና ባሕል ተቋም ጋር በትብብር ቅዳሜ፣ ማርች 1 ቀን 2025 እንደሚያከብር አስታውቋል። ዝርዝር መረጃዎችን ለማግኘት የኢትዮጵያ ውርስና ቅርስ ማኅበር በሰሜን አሜሪካ ድረ ገጽ ጎብኙ። www.ehsna.org