Related Posts

ባርሴሎና ከ ጁቬንቱስ – የቻምፕየንስሊግ የመልስ ጨዋታ ቅድመ ትንተና


ከፓሪሱ ጨዋታ በኋላ ወደ ቱሪን አቅንተው ሌላ አስደንጋጭ ሽንፈት የገጠማቸው ባርሴሎናዎች የመልሱን ጨዋታ በሜዳቸው የ3-0 ሽንፈታቸውን ቀልብሰው ወደ ግማሽ ፍጻሜ ለመቀላቀል አቅደዋል።


የሊዮ ሜሲ፣ኔይማር እና የስዋሬዝ ምትሀተኛ እግሮች በድጋሚ ባርሴሎናን ወደ ግማሽ ፍጻሜው ለመውሰድ በፓሪሱ ቡድን ላይ ያሳኩትን ድል በቱሪኑ ቡድን ላይ ለመድገም ምሽቱን እየጠበቁ ይገኛሉ።


የተጠናቀቀ በሚመስለው ጨዋታ የጣሊያኑ ተወካይ ጁቬንቱስ በፓሪስ ሴንት ጄርሜይን ላይ የደረሰው ሽንፈት በነሱ ላይ እንዳይደገም ጥንቃቄን ላይ ትኩረት በመጨመር ፈጣን የመልሶ ማጥቃት እንቅስቃሴ ምርጫቸው እንደሚያደርጉ ይጠበቃል።


ፓብሎ ዲባላ


የመጀመሪያ ጨዋታ


ጁቬንቱስ 3-0 ባርሴሎና


ፓብሎ ዲባላ ድንቅ ሆኖ ባመሸበት ጨዋታ አሮጊቷ ባርሴሎና ላይ የ 3-0 አስደናቂ ድል በማስመዝገብ በመልሱ ጨዋታ የተሻለ እድል ይዘዋል። ጁቬንቱሶች በሜዳቸው ያደረጉትን የመጀመሪያው ጨዋታ ያገኟቸው አጋጣሚዎች መጠቀም ቢችሉ ኖሮ የጎሉን መጠኑን ማስፋት ይችሉ ነበር። ባርሴሎናዎችም በበኩላቸው በኳስ ቁጥጥር የተሻሉ ቢሆኑም የመጽናኛ ጎል እንኳን ለማግኘት ሳይችሉ ቀርተዋል።


የቡድን ዜናዎች


ባርሴሎና


የባርሴሎና ትልቁ ስጋት የሀቪየር ማሼራኖ በጉዳት ለጨዋታው መድረሱ አጠራጣሪ መሆን ነው።


አልካንታራ እና አሌክሲስ ቪዳል የረጅም ጊዜ ጉዳት ላይ ያሉ ተጨዋቾች ናቸው።


የመጀመሪያው ጨዋታ በቅጣት ያልተሰለፈው ሰርጂዮ ቡስኬት ወደ ሜዳ በመመለስ የባርሴሎናዎችን የመሀል ክፍል ብርታት እንደሚሆን ይጠበቃል።


በላሊጋው ኤልክላሲኮን ጨምሮ በቅጣት እንደማይጫወት የታወቀው ኔይማር በቻምፕየንስሊጉ ላይ በማጥቃት ከሜሲ እና ሱዋሬዝ ጋር ይጣመራል።


አርዳ ቱራን ከጉዳቱ አገግሞ ለጨዋታው የመድረስ ጠባብ እድል እንደሚኖረው ተገምቷል።


ግምታዊ የጨዋታ አቀራረብ


ባርሴሎና(4-3-3)


ቴርስቴገን፣ሰ.ሮቤርቶ፣ፒኬ፣ኡምቲቲ፣አልባ፣ቡስኬት፣ራኪቲች፣ኢኒየስታ፣ኔይማር፣ሜሲ፣ስዋሬዝ


ቢጫ ከተመለከቱ በቀጣይ ጨዋታ የማይሰለፉ


ኔይማር፣ፒክዌ፣ራኪቲች እና ስዋሬዝ


ጁቬንቱስ


የፓብሎ ዲባላ ለጨዋታው ብቁ ሆኖ መገኘት የአሮጊቷ ስጋት ቢሆንም ሰኞ ለታ ልምምድ መስራቱ በመጠኑም ቢሆን እፎይታ ሰጥቷቸዋል።


ፒያካ በጉልበት ጉዳት ከጨዋታው ውጭ መሆኑ ቀደም ብሎ ታውቋል።


ግምታዊ የጨዋታ አቀራረብ


ጁቬንቱስ(4-2-3-1)


ቡፎን፣አልቬስ፣ቦኑቺ፣ቼሊኒ፣ሳንድሮ፣ፒያኒክ፣ከዲራ፣ኳድራዶ፣ዲያባላ፣ማንዙጊች፣ሂጉዌይን


ቢጫ ከተመለከቱ በቀጣዩ ጨዋታ የማይሰለፉ


ኩዋድራዶ፣ኬዲራ እና ማንዙጊች


የቅርብ ጊዜ አቋም


ጁቬንቱስ (ድል፣አቻ፣ሽን፣ድል፣ድል፣ድል)


አሮጊቷ ባርሴሎናን የምትገጥመው ከባለፉት ስድስት ጨዋታዎች አንድ ጊዜ ብቻ ሽንፈት ገጥሟት ነው።ሽንፈቱም ከሜዳ ውጭ በኮፓ ኢታሊያ በናፓሊ የተሸነፉበት ነው።ባርሴሎና (ሽን፣ድል፣ድል፣ድል፣ሽን፣ድል)


ባርሴሎና አቋሙ ወጥ መሆን አልቻለም።ቡድኑ ብዙውን ጊዜ ለአይን የሚማርክ ጨዋታን በመጫወት ተጋጣሚዎቹን ማፈራረስ ቢችልም አንዳንዴ ደግሞ ያልተገመተ አስደንጋጭ ውጤት በማስመዝገብ ሲሸነፍ ይታያል።ለሶሲሳድ ጋር ያደረጉት የቅዳሜ ጨዋታ 3-2 ማሸነፍ ችለዋል።


 


የእርስ በርስ ፍጥጫዎች


ዳኒ አልቬስ ከኔይማር


ሁለቱ ቀደም ብለው በባርሴሎና ማሊያ በአንድ ክለብ የተጫወቱ ሲሆን የብራዚል ብሄራዊ ቡድንን ወክለውም ቢጫውን ማሊያ ለብሰው እየተጫወቱ ይገኛሉ። ነገር ግን ረቡዕ ምሽት የተለያየ ማሊያ ለብሰው በተቃራኒ ሆነው በድጋሚ ይፋለማሉ።


እርስ በእርስ በደንብ የሚተዋወቁ በመሆኑ በመስመር ላይ የሚኖረው የበላይነት ምናልባትም ጨዋታን ውጤት የመለወጥ አቅም ሊኖረው እንደሚችል ይጠበቃል።


ይህን ጽሁፍ ያዘጋጀሁላችሁ የኢትዮአዲስ ስፓርት ድረገጽ አዘጋጅ እና የስፓርት ፀሀፊ ዕዮብ ዳዲ ነኝ።