Related Posts

በሥልጣን ላይ ሳሉ የሞቱ አስር አፍሪቃዉያን ፕሬዚዳንቶች


1) ሚሻኤል ሳታ፤ የዛምቢያ ፕሬዚዳንት (2014)


በ77 ዓመታቸዉ ከዚህ ዓለም የተለዩት ሚሻኤል ሳታ፤ በምን በሽታ እንደሞቱ በግልፅ አልተነገረም። ሳታ በጎርጎርዮሳዊዉ 2014 ዓ.ም እንጊሊዝ ዉስጥ ነዉ ያረፉት። በጎርጎርዮሳዊዉ 2011 ዓ.ም በዛምቢያ ዉስጥ ምርጫ ከተካሄደ በኋላ የሳታ ጤንነት አሳሳቢ ደረጃ ላይ መሆኑ ይወራ ነበር። ሳታ በሃገሪቱ መድረኮች ሁሉ ለሕዝብ ባለመታየታቸዉ ማኅበረሰቡ ስጋት ላይ ወድቆ ነበር። ቃል አቀባያቸዉ በበኩላቸዉ ለተደጋጋሚ ጊዜ ወደ መድረክ እየቀረቡ ሳታ ጥሩ ጤና ላይ እንደሚገኙ ይገልፁ ነበር።2) ላንሳና ኮንቴ፤ የጊኒ ፕሬዚዳንት (2008)


ከ 24 ዓመት የስልጣን ዘመን በኋላ በሞት የተለዩት የ74 ዓመቱ የጊኒ ፕሬዚዳንት ላንሳና ኮንቴ ለረጅም ጊዜ የልብና የስኳር በሽታ ታማሚ ነበሩ። ከጎርጎረሳዊዉ ሚያዝያ 1984 እስከ 2008 ዓ,ም ድረስ ጊኒን በፕሬዚዳንትነት የመሩት አላሳና ኮንቴ ጊኒ ከፈረንሳይ ቅኝ ግዛት ከተላቀቀች በኋላ ሁለተኛዉ ፕሬዚደንት ናቸዉ። ሦስት ጊዜ የፕሬዚዳንት ምርጫን ያሸነፉት ኮንቴ በብዙ አይነት በሽታዎች በመታወካቸዉ ለተደጋጋሚ ጊዜ ለህክምና ወደ ዉጭ ሃገር ይጓዙ ነበር።3) መለስ ዜናዊ፤ የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስቴር (2012)


ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ በጎርጎረሳዉያኑ 2012 ዓ.ም ነሐሴ ወር ቤልጂየም ዉስጥ ነዉ ያረፉት። መለስ ዜናዊ ኢትዮጵያን ለ 21 ዓመታት መርተዋል። መለስ ከጎርጎረሳዊዉ 1991 ዓ.ም እስከ 1995 ዓ.ም የኢትዮጵያ ፕሬዚዳንት ነበሩ። ከጎርጎረሳዊዉ 1995 ዓ.ም እስከ 2012 ዓ.ም ድረስ በጠቅላይ ሚኒስትርነት አገልግለዋል። መለስ ዜናዊ በኢትዮጵያ መድብለ ፓርቲ ሥርዓትን በማስተዋወቃቸዉ ይታወቃሉ። ይሁንና መንግሥታቸዉ ሠብዓዊ መብትን በመርገጥ ከፍተኛ ወቀሳና ትችት ይሰነዘርበታል።4) ጆን አታ ሚልስ፤ የጋና ፕሬዚዳንት (2012)


የጋናዉ ፕሬዚዳንት ጆን አታ ሚልስ ከዚህ ዓለም የተለዩትም በጎርጎርዮሳዊዉ 2012 ዓ.ም ነዉ። በ 2008 ዓ.ም በጋና የተካሄደዉን ፕሬዚዳንታዊ ምርጫ ያሸነፉት ጆን አታ ሚልስ በልብ መታወክና ደም ግፊት እንዲሁም የሳምባ ነቀርሳ በሽታ ነዉ በ 69 ዓመታቸዉ የሞቱት። አታ በጋና ሰፊ ኢኮኖሚያዊ እና ማህበራዊ ተሃድሶ በማካሄዳቸዉ በሃገራቸዉም ሆነ በዓለም አቀፍ ደረጃ ከፍተኛ ዉደሳን ተቸረዋል።5) ቢንጉ ዋ ሙታሪካ፤ የማላዊ ፕሬዚዳንት (2012)


የማላዊዉ ፕሬዚዳንት ቢንጉ ዋ ሙታሪካ የሞቱት በጎርጎረሳዊዉ 2012 ዓ.ም ሚያዝያ ወር ዉስጥ ነዉ። በ 78 ዓመታቸዉ በድንገተኛ የልብ ሕመም ከዚህ ዓለም የተለዩት ሙታሪካ ማላዊን ለስምንት ዓመታት በፕሬዚዳንት አገልግለዋል። ሙታሪካ በስልጣን ዘመናቸዉ በሃገሪቱ ስኬታማ የነበረ የምግብና እርሻ ፖሊስ ፖለቲካን አራምደዋል። ሙታሪካ የነበራቸዉን ጥሩ ስም ያጎደፉት 13 ሚሊዮን ይሮን አዉጥተዉ የግል ጀት አዉሮፕላንን በመግዛታቸዉ ነበር።


 


6) ማላም ባቺ ሳና፤ የጊኒ ቢሳዉ ፕሬዚዳንት (2012)


የጊኒ ቢሳዉ ፕሬዚዳንት ማላም ባቺ ሳና በጎርጎርዮሳዊዉ 2012 ዓ.ም በስልጣን ላይ ሳሉ ከዚህ ዓለም በሞት የተለዩት አራተኛዉ ፕሬዚዳንት ናቸዉ። ከአራት ዓመት የስልጣን ዘመን በኋላ በ64 ዓመታቸዉ ፓሪስ ዉስጥ የሞቱት ማላም ባቺ ሳና በስኳር በሽታ ይሰቃዩ ነበር። በስልጣን ዘመን ላይ ሳሉ በተለያዩ በሽታዎች ይሰቃዩ ስለነበር ለተደጋጋሚ ጊዜ ሆስፒታል ይገቡ ይወጡ ነበር። 7) ሙአመር ኧል-ጋዳፊ፤ የሊቢያ አብዮታዊ መሪ (2011)


ራሳቸዉን የሊቢያ አብዮታዊ መሪ ሲሉ ይጠሩ የነበሩት ሙአመር ኧል-ጋዳፊ ስልጣን ላይ ሳሉ በ 69 ዓመታቸዉ ወደ ሊቢያዋ ከተማ ሲርት ሽሽት ላይ ሳሉ ነዉ በአማፅያን የተገደሉት። ሙአመር ኧል-ጋዳፊ የሊቢያን በትረ ስልጣን ለ 42 ዓመታት ተቆናጠዉ ገዝተዋል። በጎርጎረሳዊዉ 1969 ዓ.ም ወደ ስልጣን የመጡት የሊቢያዉን የንጉሠ ነገስት መንግሥት ከስልጣን ገልብጠዉ ነዉ። በጎርጎረሳዉያኑ 2011 ዓ.ም ዴንሃግ ኔዘርላንድ የሚገኘዉ የዓለም አቀፉ የጦር ወንጀለኞች መዳኛ ፍርድ ቤት ጋዳፊ በሰው ልጆች ላይ ፈፀሙት ባለዉ ወንጀል እንዲያዙ የእስር ማዘዣ ቆርጦባቸዉ ነበር።8) ኡመር ሙሳ ያር አድዋ፤ የናይጀርያ ፕሬዚዳንት (2010)


የናይጀርያዉ ፕሬዚዳንት ኡመር ሙሳ ያር አድዋ በጎርጎረሳዊዉ 2011 ዓ.ም በ 58 ዓመታቸዉ በልብ ሕመም ከዚህ ዓለም ተለዩ። ኡመር ሙሳ በስልጣን ላይ ለሦስት ዓመት ብቻ ነዉ የቆዩት። በሃገሪቱ በተካሄደዉፕሬዚዳንታዊ የምረጡኝ ዘመቻ ወቅት ብዙም ያልታዩት ሟቹ ፕሬዚዳንት፤ ምርጫዉን ካሸነፉ በኋላ በጎርጎረሳዊዉ 2007 ዓ.ም ሚያዝያ ወር ላይ እጅግ ፈጣን በሚባል ሁኔታ የጤንነታቸዉ ይዞታ አሽቆልቁሎ ነበር። 9) ዥዋዉ ቤርናዶ ቪራ፤ የጊኒቢሳዉ ፕሬዚዳንት (2009)


የጊኒቢሳዉ ፕሬዚዳንት ዥዋዉ ቤርናዶ ቪራ የ69 ዓመታቸዉ በጎርጎረሳዊዉ 2009 ዓ,ም ሃገራቸዉ ዉስጥ በወታደሮች ተገድለዉ ነዉ የሞቱት። የጊኒቢሳዉን በትረ ስልጣን ለ 31 ዓመታት ተቆናጠዉ የቆዩት ፕሬዚዳንት ዥዋዉ ቤርናዶ ቪራ፤ በጎርጎረሳዊዉ 1978 ዓ.ም ጠቅላይ ሚኒስትር ሆነዉ ተመርጠዉ ለ 19 ዓመታት ስልጣን ላይ ቆይተዋል። ቆየት ብሎም የፕሬዚዳንትነቱን ስልጣን ጨበጡ። ቪራ በሃገሪቱ የእርስበርስ ጦርነት በመከሰቱ በጎርጎረሳዊዉ 1999 ዓ.ም ወደ ፖርቱጋል ተሰደዱ። ከስደት መልስ ዥዋዉ ቤርናዶ ቪራ በጎርጎረሳዊዉ 2005 ዓ.ም ዳግም ፕሬዚዳንት ሆነዉ ተመርጠዉ ነበር።10) ኦማር ቦንጎ፤ የጋቦን ፕሬዚዳንት (2009)


በአንጀት ነቀርሳ በሽታ ሲሰቃዩ የነበሩት የጋቦኑ ፕሬዚዳንት ኦማር ቦንጎ በ72 ዓመታቸዉ በጎርጎረሳዊዉ 2009 ዓ.ም ስፔን ዉስጥ ነዉ የሞቱት። ለ42 ዓመታት ጋቦንን በፕሬዚዳንትነት የመሩት ኦማር ቦንጎ፤ በዓለማችን ለረጅም ጊዜ መንበረ ስልጣን ተቆጣጥረዉ የቆዩ የዓለማችን የመጀመርያዉ ፕሬዚዳንት ናቸዉ። ኦማር ቦንጎ ከፍተኛ ሙስና የሚታወቁም ናቸዉ። በተፈጥሮ ነዳጅ ዘይት ሃብት የበለፀገችዋ ጋቦን ማኅበረሰብዋ በድህነት ሲማቅቅ ቦንጎ እጅግ ከፍተኛ ሃብትን ያካበቱም ነበሩ። 


DW Amharic


Save