Related Posts

የአፍሪካ እግር ኳስ አድባር በቅሌት የታጀበውንና ሰው ሸኝታ አብዮተኛውን ወደ መድረኩ አምጥታለች

የአፍሪካ እግር ኳስ አድባር በቅሌት የታጀበውንና አምባገነኑን ሰው ሸኝታ አብዮተኛውን ማዳጋስካራዊ ወደ መድረኩ አምጥታለች


ትናንት አመሻሽ በነበረው የካፍ ፕሬዝደንትነት ምርጫ የአፍሪካ ህብረት ኔልሰን ማንዴላ አዳራሽ በደስታ ሰክረው አሸናፊውን በእሽኮኮ አዝለው ከሚጨፍሩ ተሰብሳቢዎች ጀምሮ ባልጠበቁት ውጤት ተደናግጠው በሲቃ በሚያነቡ አፍሪካውያን ተሞልቶ ደምቆ አምሽቷል። በዚህ መሀከል ግን አንድ ሰው ብቻ በምርጫው ውጤት በእጅጉ ንዴት ውስጥ ገብተው ከፕሮግራሙ መጠናቀቅ በፊት አዳራሹን በጥድፊያ ለቀው ሲወጡ ታይተዋል።እንቅልፋሙ ኢሳ ሀያቱ ካፍን ለዘመናት እንቅልፋም አድርገውት የቆዩበት የተንዛዛ የስልጣን ዘመናቸው በትናንትናው እለት ላይመለስ ተሸኝቷል።


በሚኪያስ በቀለ


ምንም እንኳን እግር ኳስ ቢሆንም በአምባገነኖች የተሞላችው አፍሪካ ትናንት ከሰአት አንዱን በመሸኘት ሌላኛውን ተስፈኛ በመንበረ ስልጣኑ ላይ አቆናጣለች። የአፍሪካ ህብረት አዳራሽ ትናንት አመሻሽ በደስታ በተሞሉ ሰዎች ተጥለቅልቆ ዲሞክራሲያዊ የእግር ኳስ አስተዳዳሪ ምርጫ ማድረግ ችሏል።


ለ 29 አመታት የአፍሪካ እግር ኳስን በመዳፉቸው ስር አስገብተው እንደፈለጉ ሲያሽከረክሩ የነበሩት የ 70 አመት አዛውንት ላይመለሱ ተሸኝተዋል። የአሸናፊው ሰው ደጋፊዎች አህመድን ትከሻቸው ላይ በማውጣት እሽኮኮ ብለው በደስታ ሲቃ የህብረቱን አዳራሽ ቀውጢ ሲያደርጉ በአዳራሹ የነበሩ አንዳንዶች በስሜት ተሞልተው ስቅስቅ ብለው ሲያነቡ ታይተዋል።


ኢሳ ሀያቱ እወክላቸዋለሁ በሚሏቸው የአፍሪካ ሀገራት እግር ኳስ አፍቃሪዎች ላይ ከፈረንሳይ ቴሌቪዥን ጣቢያዎች ጋር ደባን በመስራት የማስተላለፊያ ገቢን ከፍ በማድረግ ከሚወዱት የአፍሪካ ዋንጫ ካለያዩዋቸው ቅሌታማ ተግባራቸው ጀምሮ በሙስናና በስልጣን መባለግ የጨቀየው የአፍሪካ እግር ኳስ ፌደሬሽን (CAF) ስልጣናቸው ትናንት አመሻሽ ፀሀይ ጠልቆበት ጨልሟል።


ከምርጫው በፊት “በሀያቱ ዘመን የአፍሪካ ዋንጫ ተሳታፊዎች ቁጥር ከ 12 ወደ 16 ማሳደጉን፣ የአፍሪካን ቻምፒዮንስ ሊግን እንደገና ማዋቀሩንና በአለም ዋንጫ የተሳታፊ አፍሪካዊ ሀገሮች ቁጥር ከሁለት ወደ አምስት ለማሳደግ መቻሉን ልንረሳ አይገባም።” የሚለውን የፊፋና የካፍ ስራ አፅፈፃሚ አባል ክዊሲ ንያንታኪ ጨምሮ ብዙ የአፍሪካ እግር ኳስ ፌደሬሽን ሀላፊዎች ልባቸው ከኢሳ ሀያቱ ጋር መሆኑ ተገምቶ ነበር።


በትናንቱ ምርጫም ከጥቂት ፌደሬሽኖች በስተቀር ብዙዎች ከዚህ ቀደም እንደነበረው ድምፃቸውን የሚሰጡት ለካሜሮናዊው እንደሚሆን እርግጠኝነት ላይ ተደርሶ ነበር። ነገርግን ህልም በሚመስል መልኩ እድል ወደ አህመድ አህመድ ፊቷን አዙራ የትንሿ ደሴት ሀገር ማዳጋስካር ተስፈኛ ሰው ትናንት አመሻሽ የአፍሪካ እግር ኳስን ወደፊት ለመዘወር መሪውን ከካሜሮናዊው እጅ ተቀብለዋል።


የዛሬ 70 አመት ጋሩ በተሰኘችው የካሜሮን ግዛት ወደዚች ምድር የተቀላቀሉትና አራት ልጆችን ያፈሩት ኢሳ ሀያቱ በካሜሮን ተፅዕኖ አሳዳሪ በሆኑ ሰዎች የተከበቡ ናቸው። የሀያቱ ወንድም ሳዱ የቀድሞ የሀገሪቱ ጠቅላይ ሚኒስትር ነበሩ። ሀያቱን በቅርበት የሚያውቋቸው በሰው የሚሳለቅ፣ ሰው የሚንቅና ጓደኝነትን የማያውቅ፣ ኩራተኛና ጊዜ ያለፈበት አመራርን የሚከተል ሲሉ ይወነጅሏቸዋል። ብዙዎች ሌሎች ደግሞ የፈፀሙትን ቅሌት በመግለፅና ደካማ አስተዳዳሪነታቸውን በማንሳት ለዘመናዊ እግር ኳስ የማይሆኑ ሰው መሆናቸውን በመጥቀስ ከስልጣን እንዲወርዱ ግፊት ሲያሳድሩ ቆይተዋል።


በቢሲ “ፓናሮማ” በሚለው ፕሮግራም ላይ የሚሰራው አንድሪው ጄኒንግስ የኢሳ ሀያቱን የአመራርነት ቆይታ ሲያጠለሸውና ፈተናቸውን ሲያበዛው ቆይቷል። በአንድ ዘገባው ላይ የአለም ዋንጫን የቴሌቪዥን መብትን ከመሸጥ ጋር በተያያዘ ሀያቱ ጉቦ መቀበላቸውን ማስረጃ በመጥቀስ መዘገቡ ይታወሳል። ፓናሮማም ከኢንተርናሽናል የስፓርትና የመዝናኛ ተቋም (ISL) ያገኘውንና የቴሌቪዥን መብትን ከማሰራጨት ጋር በተያያዘ 100,000 የፈረንሳይ ፍራንክ የተቀበሉበትን ሰነድ ይፋ አድርጓል።


የኢሳ ሀያቱ ሌላኛው ቅሌት ደግሞ ግንቦት 2011 በወጣው ሰንዴይ ታይምስ ጋዜጣ ይፋ የተደረገው ነው። በወቅቱ መቀመጫውን ለንደን ያደረገው ተነባቢው ጋዜጣ ሀያቱ ከሌላው የፊፋ ስራ አስፈፃሚ አባል ጃኪውስ አኑማ ጋር በመሆን ለ 2022 አለም ዋንጫ አዘጋጅነት ምርጫ ድጋፋቸውን ለኳታር ለመስጠት የ 1.5 ሚሊዮን ዶላር ጉቦ መቀበላቸውን ይፋ አድርጎ ነበር። ካሜሮናዊው ሰው ግን የጋዜጣውን ውንጀላ ሙሉ ለሙሉ በመካድ ከደሙ ንፁህ መሆናቸውን ለማስመስከር ከወዲህ ወዲያ ሲሉ ታይተዋል።


የቀድሞው የአጭር ርቀት ሯጭ ሀያቱ በ 400 እና 800 ሜትር ርቀት ከመወዳደራቸው በተጨማሪ በ 1965 የመላው አፍሪካ ውድድር ካሜሮንን ወክለው በቅርጫት ኳስ ውድድር መሳተፍ ችለዋል። ሀያቱ ያላቸው ዝምተኛ ባህሪ በተሳሳተ መልኩ መተርጎሙን ታሪካቸውን በመፅሀፍ መልክ የከተበው አዩትንዴ አዴላኩን “እሱ በጣም ዝምተኛ ሰው ነው። ሁሌም ነገሮችን የሚቆጣጠር ነው። ምንም ነገር የሚያሳፍረው ሰው አይደለም። እኔ የማውቀው ሁሌም ነገሮችን በቀጥታ ሲጋፈጥ ነው። ውሳኔዎች ሲወስንም ሙሉ ለሙሉ ሀላፊነት ይወስዳል። ቢሆንም ግን እሱ አወዛጋቢ ነው።” በማለት ገልጿቸዋል።


ይህ የአዴላኩን ገለፃ ሀያቱ ቶጎን ከ 2010 የአፍሪካ ዋንጫ ያገዱበትን ጠንካራ ውሳኔ በመመልከት ማረጋገጥ ይችላል። በወቅቱ የአንጎላን መንግስት የሚዋጉ ሽፍቶች ወደ አንጎላው ውድድር ሲያመሩ የነበሩ የቶጎ እግር ኳስ ብሔራዊ ቡድን አባላትን አውቶብስ አጥቅተው ሶስት የሚሆኑት ሲሞቱ ብዙ የስብስቡ አባላት ተጎዱ። ቶጎም በውድድሩ ላይ ለመካፈል ሁኔታዎች ጥሩ እንዳልሆኑ በመረዳቷ ራሷን አገለለች። ኢሳ ሀያቱ ግን ይህን ሁሉ ከግምት ባላስገባና ትዝብት ላይ በጣላቸው ውሳኔ ምዕራባዊቷን ሀገር ከአንጎላው ውድድርና ከተከታታይ ሁለት የአፍሪካ ዋንጫዎች አገዱ።


በወቅቱም የቶጎ ብሔራዊ ቡድን አምበል የነበረው ሼይ አዲባየር በካሜሮናዊው የእግር ኳስ አስተዳዳሪ ሰው ውሳኔ በእጅጉ በማዘን ካሜሮናዊው ሰው በችግር ውስጥ ያለ አካልን መርዳት የማይፈልጉ መሆናቸውን በመግለፅ ከስልጣን እንዲወርዱ ጥያቄ እስከማቅረብ ደረሰ። ለብዙ አመታትም ቃለ መጠይቅ የማድረግ ጥያቄን ውድቅ የሚያደርጉትን ሀያቱን ለማነጋገር ጋዜጠኞች ደስተኛ ሳይሆኑ አሳልፈዋል። አዴላኩን ግን ሀያቱ ለሚዲያ ክብር እንዳላቸው ይናገራል።


“ሚዲያን የሚያከብር ሰው ነው። ነገርግን መፈራትና ክብርንም ይወዳል። የካሜሮን እግር ኳስ ዋና ፀሀፊ ሆኖ ከተመረጠበትና የህይወቱ የመጀመሪያ ጊዜ ከሆነው የ 20ዎቹ አጋማሽ እድሜው ጀምሮ ከአስቀያሚ ሚዲያዎች ጋር አሳልፏል። በወቅቱ ሚዲያው የካሜሮን እግር ኳስን የሚተችበት አስቸጋሪ ወቅት ነበር። ከእዛ ጊዜ ጀምሮም ሚዲያዎችን የሚመለከተው ድክመቶችንና ቀዳዳዎችን ብቻ የሚፈልጉ አድርጎ ነበር።” ይላል አዴላኩን።


አንዳንዶች ‘ሀያቱ ለምን ከብላተር እገዳ በኋላ ፊፋን ለመምራት እጃቸውን ሳያረዝሙ ቀሩ?’ በማለት ሲናገሩ ተደምጠዋል። ነገርግን በ 2002 ምርጫ ከብላተር ጋር ለፊፋ ፕሬዝዳንትነት ተወዳድረው በ 106-56 የድምፅ ልዩነት መሸነፋቸው አይረሳም። “ለመጀመሪያ ጊዜ የሞከረው (ለፊፋ ፕሬዝዳንት ለመመረጥ) ከ 15 አመት በፊት ነው። ከእዛ በኋላ ግን ብዙ ነገሮች ተፈጥረዋል። ለፊፋ ፕሬዝዳንትነት የመወዳደር ጉጉቱም ተመሳሳይ አይደለም። ከብላተር ጋር የቅርብ ሰው በመሆኑም ‘ተገቢ ያልሆነ ጥቅም (undue advantage) በብላተር ላይ ላለመውሰድ ሲል ለፊፋ ፕሬዝዳንትነት ለመወዳደር አልፈለገም ነበር። በሌላ በኩል ወጣት እየሆነ ስለማይሄድ የአለም አቀፉን ተቋም የመምራት አስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ ነበር።” ሲል አዴላኩን ምስክርነቱን ሰጥቷል።


ሀያቱ የአፍሪካ ዋንጫን ከማስተላለፍ ጋር በተያያዘ ከአንድ የፈረንሳይ የቴሌቪዥን ተቋም ጋር በ 2015 የፈፀሙት የቴሌቪዥን መብት ስምምነት በድህነት በምትታወቀው አህጉር ላይ ትልቅ ወቀሳና የመሰናበቻ እጣ እንዲደርሳቸው ምክንያት ከሆኑ ዋነኛ ምክንያቶች መሀከል ይጠቀሳል። የቀድሞው መምህር ሊጋርዴር ከተሰኘው የቴሌቪዥን ተቋም ጋር ለ 12 አመታት የተፈራረሙት ስምምነት ከ 2008-16 ድረስ ከቆየውና 150 ሚሊዮን ዶላር ከነበረው ውል በአስር እጅ ብልጫ ያለውና ከአንድ ቢሊዮን ዶላር በላይ ዋጋ ያለው ነው።


ይህም ጨዋታዎችን ከፈረንሳዩ ቴሌቪዥን በመግዛት ለሚያሳዩት የአፍሪካ ቴሌቪዥን ተቋማት ትልቅ ገንዘብ የሚጠይቅ ነው። የሀጉሪቱ ቴሌቪዥን ጣቢያዎች ስፓንሰሮችን በመተማመን ጨዋታዎቹን በውድ ገንዘብ ገዝተው ለማስተላለፍ ቢፈልጉም እንኳን ከውድድሩ የተመልካች መቀዛቀዝና የገንዘብ ማጣት ጋር በተያያዘ የማይቻል ነገር ነው። እዚህ ላይ ሀያቱ ስምምነቱን ለፈረንሳዩ ድርጅት የሰጡበት ምክንያት በቴሌቭዥኑ የባለቤትነት ድርሻ ውስጥ የቅርብ ቤተሰቦቻቸው እጅ መኖሩ በመሆኑን መሆኑን በቅርቡ ይፋ የሆኑ መረጃዎች አስታውቀዋል። በካሜሮናዊው ያልተገባ ጥልፍልፍ ሴራ ምክንያትም የኢትዮጵያ እግር ኳስ አፍቃሪዎችን ጨምሮ ብዙ አፍሪካውያን የሚወዱትንና በጉጉት ይጠብቁት የነበረውን ውድድር የመከታተል እድል አጥተው የአህጉሪቱን ትልቅ ውድድር ወደ መዘንጋት እየተሸጋገሩ ይገኛል።


በዚህ ሁሉ መሀከል ግን በአፍሪካ ህብረት ኔልሰን ማንዴላ አዳራሽ ሀያቱ በትናንትናው እለት ባደረጉት የመጨረሻ ንግግር ከካፍ የ 1957 ምስረታ በኋላ ባለፉት 60 አመታት የአፍሪካ እግር ኳስ ማደጉን በመጠቆምና በአዲሱ የአለም ዋንጫ ደንብ መሰረት ከ 2026 ጀምሮ በአለም ዋንጫ ላይ የሚሳተፉ የአፍሪካ ሀገሮች ተሳትፎ ወደ አስር የሚያድግ መሆኑን በመግለፅ በጎ በጎውን ጎን ብቻ ለማሳየት ሲጥሩ ታይተዋል። የምርጫው ውጤት ሲገለፅ ግን ሀያቱ ከዚህ በኋላ ባማሩ ቃላት እየደለሉ በስልጣን ላይ መቀጠል እንደማይችሉ 34-20 በሆነ ሰፊ ውጤት የተጠናቀቀው ምርጫ በግልፅ ለማሳየት ቻለ። ካሜሮናዊው የቀድሞው የአጭር ርቀት ሯጭም ከዚህ ቀደም በሚታወቁበት ባህሪያቸው ለጋዜጠኞች ፊት በመንሳት ለቃለ መጠይቅ ፈቃደኛ ባለመሆን በፍጥነት አዳራሹን ለቀው ሲወጡ ታዩ።


የአፍሪካ እግር ኳስ መንበረ ስልጣን አሁን በአዲሱ የአፍሪካ እግር ኳስ ተስፋ አህመድ መሀመድ ተይዟል። ለዚህ ውድድር ከመቅረባቸው በፊት እውቅና ያልነበራቸውን ማዳጋስካራዊው ሰው የህይወት ታሪክ ገለጥ ገለጥ አድርጋችሁ ስታነቡ የማላጋሲ ደሴቶች ወይም የማዳጋስካር እግር ኳስ አስተዳዳሪ እንደነበሩ ትመለከታላችሁ። የቀድሞው እግር ኳስ ተጫዋችና አሰልጣኝ በሶስተኛ ዙር የስልጣን ቆይታቸው ላይ የሚገኙ ሲሆን በሀገራቸው ማዳጋስካር ትልቅ የፓለቲካ ተሳትፎ ያላቸው ሰው ናቸው።


በሰሜን ምዕራብ ማላጋዚ የተወለዱት አህመድ በዝምታ የተዋጡና ዝናን የማይወዱ ሰው ነበሩ። የአፍሪካ እግር ኳስን ለመምራት መወዳደርና ሀያቱን ለመቀናቀን እንደተዘጋጁ ካሳወቁበት ጊዜ ጀምሮ ግን ነገሮች በአንድ ጊዜ ተለወጡ። በካሜሮናዊው ደካማና ግልፀኝነት የጎደለው አመራር የተማረሩ የእግር ኳስ ቤተሰቦች በሙሉ ለማዳጋስካሩ ሰው ድጋፋቸውን መስጠትን ስራዬ ብለው ተያያዙ።


ከወር በፊት አህመድ የደቡብ አፍሪካ ክፍለ አህጉር እግር ኳስ ማህበር (Cosafa) አባላትን መተማመኛ ድምፅ ማግኘታቸውን አረጋገጡ። በዚህ ሁሉ መሀከል ግን የቀሪዎቹ ሶስቱ (ሰሜን፣ ምስራቅና ምዕራብ) እግር ኳስ ማህበር አባላት ድምፅ ለሀያቱ ያደላ መምሰሉ የምርጫው ውጤት እስኪታወቅ ድረስ በብዙዎች ዘንድ ለአሸናፊነት ትልቅ ግምት ያገኙት ለ 29 አመታት ስልጣን ላይ የቆዩት ካሜሮናዊው አዛውንት ነበሩ።


በሌላ በኩል አህመድ ትችት የበዛበትን የካፍ አመራር ጉዞ ለመቀየር አራት ነገሮች ላይ ትኩረት እንደሚሰጡ በመግለፅ ዘመቻቸውን ስኬታማ አድርገዋል። የአህመድ የመጀመሪያ አላማ እግር ኳስ ሁሉንም ባማከለ መልኩ አሳታፊ እንዲሆንና በፌደሬሽኑ አሰራር ላይ ትልቅ የአሰራር ግልፀኝነት እንዲሰፍን ማድረግ ነው። ሁለተኛ እቅዳቸው ደግሞ ከአፍሪካ እግር ኳስ ጋር መታረቅና ፓለቲካን ከእግር ኳስ አስተዳደር መለያየት ነው።


ሶስተኛው የአህመድ አላማ ደግሞ በአፍሪካ እግር ኳስ ላይ ትልቅ አስተዋፅኦ ለሚያደርጉ ሰዎች ክብር መስጠትና በአህጉሪቱ እግር ኳስ እድገት ላይ አስተዋፅኦ እንዲያደርጉ እድል መፍጠር ነው። አራተኛውና ለአፍሪካ እግር ኳስ እድገት ትልቅ መሰረት ሊሆን ይችላል ተብሎ የሚጠበቀው የአህመድ እቅድ ደግሞ ጥቅም የማይሰጡና ባክነው የሚቀሩ ትልልቅ የስታዲየም ግንባታዎችን በማስቀረት ለአፍሪካ እግር ኳስ የሚመጥኑ የስፓርት መሰረተ ልማት ግንባታዎችን ከዳር ማድረስ ነው።


“የእኔ አላማ በተቋሙ (ካፍ) ላይ ያለውን ፓለቲካ ማስወገድ ነው። ጥሩ ተመራጭ ነኝ ብዬ አላስብም። ነገርግን ለለውጥ የተዘጋጀሁ ነኝ። አብዛኛው ሰውም ለውጥ ይፈልጋል። የእኔን የለውጥ ፕሮግራም ለየት የሚያደርገው ያልተለመደ መሆኑ ነው። አስተዳደሩን መቀየር እፈልጋለሁ። አሁን ባለው አስተዳደር መቀጠል አልፈልግም። በምርጫው ለመሳተፍ ውሳኔ ላይ የደረስኩት አንዳንድ የእግር ፌደሬሽን ፕሬዝዳንቶች ለውጥ እንደሚፈልጉ ከነገሩኝ በኋላ ነው።” በማለት ምን ያህል ለለውጥ የተዘጋጁ ሰው እንደሆኑ አህመድ ከምርጫው በፊት ባደረጉ ቅስቀሳ ይፋ አድርገዋል።


የምርጫው ውጤት ከታወቀና መንበረ ስልጣኑን መቆጣጠራቸውን ካወቁ በኋላም ማዳጋስካራዊው ሰው አቋማቸው ተመሳሳይ ነበር። አህመድ በድሉ ዙሪያ በሰጡት መግለጫ “የሆነ ነገርን ለማድረግ ስትሞክር ታደርገዋለህ እንደማለት ነው። ማድረግ ካልቻልኩ አልወዳደርም ነበር። ይህ በጣም ጣፋጭ ድል ነው። ለአመታትና ወራት ጠንክረህ ሰርተህ ሲሳካልህ ያስደስታል።” በማለት ምን ያህል የአህጉሪቱ እግር ኳስ አፍቃሪዎች ሊተማመኑባቸው የሚችሉባቸው ሰው እንደሆኑ አስረድተዋል።


በትናንቱ ታሪካዊ እለትም አፍሪካ አምባገነኑን የእግር ኳስ አስተዳዳሪ ሰው የ 29 አመት የተንዘላዘለ አምባገነናዊ ስልጣን ነጥቃ የመሪነት ዱላውን ለቆፍጣናው ሰው አህመድ አህመድ አሻግራለች። ይህም በአፍሪካ እግር ኳስ ቀጣይ ጉዞ ላይም ተፈጥሮ የነበረው ተስፋ ይበልጥ እንዲያንሰራራ ምክንያት ሆኗል። በዚህ ሁሉ መሀከል ግን የትናንቱ ምርጫ ከተጠበቀው በተቃራኒ የአፍሪካ እግር ኳስ ከአንዱ አምባገነን ወደ ሌላ አምባገነን የሚሸጋገርበትን እድል የፈጠረ ሊሆን ይችላል። አረረም መረረም ግን ከበጣም መጥፎ አምባገነን መጥፎ አምባገነን ይሻላልና እንኳን ደህና መጡ አህመድ አህመድ ማለቱ ያዋጣል።