በግምት ከጸገዴ እስከ ዓዲጎሹ ከ500,000 እስከ 1,0000,000 ህዝብ ይኖር ነበር። ከተማ ንጉስ፣ ዳንሻ፣ ዲቪዥን፣ቃፍታ፣ ትርካን፣ ባዕኸር ፣ ማይካድራ ፣ ራውያን፣ በረኸት፣ ሑመራ፣ ኣደባይ፣ ኢድሪስ፣ ዓዲጎሹ ፣ ዓዲረመፅ፣ ቆራሪት ደስተኛና ብዙ ህዝብ ይኖርባቸው ከነበሩ ከተሞች ናቸው። በየመሃሉ ኣነስተኛ ከተሞች፣ የተለያዩ ገጠሮች ኣሉ። እነዚህ ነዋሪዎች ብዙ ቋሚና ተንቀሳቃሽ ሀብት ያፈሩ፣ በመሬታቸው አዝመራ የዘሩ ህዝቦች ነበሩ። አንድም ቀን ከቀዮአችን እንወጣለን ብለው አስበው አያቁም። አነዚህ ከ500,000 እስከ 1,000,000 ብዛት ያላቸው ህዝቦች ገሚሱ ተገድሎ ገሚሱ ደግሞ ከቀዮው ተፈናቅሎ ዛሬ የሀገሬ ህዝብ በሚሉት የጎረቤት ህዝብ አዝመራቸው ታጭዶ፣ እንስሳቸው ተነድቶ፣ ያፈሩት ንብረት በሙሉ ተግዞ፣ ቤታቸው ከነ ቁሱ ሌላ ቤተሰቦች ገብተውበት ብቻ በዓለም ላይ አለ የሚባል ክህደት ተፈጽሞበት ሙሉ በሙሉ ከቀዮው ተነቅሎ ይገኛል። ይህ ድርጊት ድሮ በመካከለኛው የሰው ልጅ በሕገ አራዊት ሲመራ በነበረበት ጊዜ የተፈጸመ እንጂ በዚህ ዘመን የሆነ አይመስልም።
የሆነው እንደዚህ ነው። ከታሕሳስ 05/2013 ዓ/ም በፊት የአማራ ክልል ሚሊሻ፣ ፋኖ ከኢትዮጵያ መከላከያ ጀርባ እየተከተሉ በየግላቸው ያገኙትን እየገደሉ ፣ እየዘረፉ ህዝቡን አበሳበሱት። በቀን 05/04/2013 ዓ/ም አንድ ኣቡነ ሉቃስ የሚባሉ በኦርቶዶክስ ቤተክርስትያን በማዕከል የሚሰሩ፣ የጎንደር ቤተክህነት ሐላፊ ( ከፍተኛ ሹም) ሊቀብርሃናት ኤልያስ የተባሉ የኦርቶዶክስ ተወካዮች ሑመራ ገቡ። በየቤተክርስትያኑ እየዞሩ ኣማራ ርስቱን ማስመለሱ መፅሓፍ ቅዱሳዊ እንደሆነ፣ ይሄን የማይቀበል መግደል ማሳደድ ሐጥያት እንደሌለው፣ አማራ በርስቱ ያገኘው ሁሉ መጠቀም እንደሚችል የመፅሐፍ ቅዱስ ቃሎች እየጠቀሱ ሰበኩ። ይሄን ሁሉ እንዲደረግ ፈቅደናል፣ ፈትተናል አሉ።
ከዛን ጊዜ ጀምሮ በየግል ውሳኔ ሲደረግ የነበረ ግድያ፣ ዘረፋ ፣ ማሳደድ መንግስታዊ ቅርፅ ይዞ በመከላከያ፣ ልዩ ኃይል፣ እንደነ ደመቀ ዘውዱ እና ነጋ ባንተ ያሉ እራሳቸው አስተዳዳሪነት የሾሙ ሰዎች ጥምረት በተቀናጀ መልኩ መተግበር ጀመረ። ዋጋው ሲጨምር ይሸጣል ተብሎ በነጋዴዎች የተከማቸ ሰሊጥና የዘንድሮ አዝመራ ሰብስበው በከባድ መኪኖች ማጓጓዝ ጀመሩ። እሱን ከጨረሱ በኃላ በየሆቴሉ፣ በየሱቁ፣ በየቤቱ የነበሩ ውድ እቃዎች እየሰበሰቡ አጓጓዙት። አነስ አነስ ያለ ደግሞ ከጎንደርና አርማጨሆ ለመጡት ሚሊሻዎችና ፋኖዎች መስጠት ጀመሩ። ለምሳሌ ዓሲምባ ሆቴል ውስጥ የነበሩት ውድ አልጋዎች፣ ፍሪጆች እና የተለያዩ እቃዎች ከፍ ያሉ ባለስልጣኖች ወሰዱት። ሆቴሉ ስሙን ተከዜ ሆቴል ብለው በመቀየር ከገመድ የተሰሩ አልጋዎች በማስገባት አነስ ላሉ ካድሬዎች እንዲሰሩበት ሰጡዋቸው። እያንዳንዱ መኖርያ ቤት ከነ ቁም ሳጥኑ ፣ ከነ ልብሶቹ ከሌላ ቦታ የመጡ ቤተሰቦች ቁልፉ እየተሰበረ ገቡበት።
አሁን የእርሻ መሬት መከፋፈልም ጀምረዋል። ድንገት እዛ የቀየረ ትግርኛ ተናጋሪ ሲያገኙ እስር ቤት ያስገቡታል። የፈለጉት ይገድሉታል። ሴቶችና ሽማግሌዎች ሲሆኑ ደግሞ በሌሊት ጭነው ተከዜ ያሻግሩዋቸዋል። ጥር 10/2013 ሌሊት የሆነው ደግሞ አሰቃቂ ነበር። 80 ሰዎች ጭነው ተከዜ ለማሻገር ሲሄዱ በአንዱ ቦታ የአማራ ልዩ ሀይል በትግራይ ልዩ ሀይሎች ይመታሉ። በዚህ ምክንያት የተበሳጩት ጫኞች 80 ሰዎች ሌሊት 6 ሰዓት ላይ በቦንብ ተከዜ ዳር ላይ ፈጅተዋችዋል። ከነዚህ 80 ሰዎች ገ/ሃንስ እና ገ/ኣብዝጊ የተባሉ ሁለት ለስራ የመጡ የተንቤን ተወላጅ ሰዎች ተርፈዋል። በምዕራብ ትግራይ የሆነው ሙሉ በሙሉ የዘር ማፅዳት ስራ ነው። የተፈፀመውን እያንዳንዱ ዘግናኝ ተግባር እዚህ አልፅፈውም። ለሰሚውም ይሰቀጥጣል። ሰው የዘራውን የሚያጭድ፣ የሰው አልጋ ላይ የሚተኛ ይሁዳ ጋር እንዴት ሳናውቀው ኖርን? የሚገርመው ከአርማጭሆ እስከ መተማ የሚመጡ ሰዎች በአብዛኛው አያታቸው ገ/መድህን፣ ሓጎስ ወዘተ ነው። assimilated የሆኑ ተጋሩ ናቸው። የማንነት ቀውስ ከባድ ነውና ግፋቸው ሞልቶ ይፈሳል። ለነገሩ እኛም አልታደግናቸውም። እንዲጨፈለቁ ነበር የፈረድንባቸው።
አንድ እውነታ ልንገራችሁ የሌላ ሃገር ወታደር የሆኑት የምድሪ ባሕሪ ወታደሮች( የውሸት ስሟ ኤርትራ) እንኳ የኔ ነው ብለው በያዙት መሬት ያገኙት ህዝብ ባለበት ብዙ ገደሉበት፣ ዘረፉት፣ ነጠቁት እንጂ መሬቱ የኔ ነው እና ልቀቅ ብለው ከመሬቱ፣ ከቤቱ በጅምላ አላስለቀቁትም ( አላቅም)። በዚህ በኩል ያለው ችግር በዋናነት ከስርዓት ለውጥ ጋር የሚፈታ ነው።
ከዚሁ ጋር ተያይዞ አንድ የሰማሁት ነገር አደባይ በተባለችው ከሁመራ ወደ 20 ኪሜ የምትገኝ ከተማ አንድ እዚህ መግለፅ የማልፈልገው ለየት ያለ የተሻለ ነገር አለ። መጠየቅ ይቻላል።
አንድ የትግል ጓደኛየ ስለ ምዕራብ ትግራይ አምርሬ ስነግረው እንደዚህ አለኝ። አንተ እንደዚህ ነገሩ ወደ ውስጥህ ከገባ ታብዳለህ፣ ትልቅ ነገር እንዳታስብ ያረገኃል። ስለዚህ ከቻልክ ተረጋግተህ ስለ ትልቁ መፍትሄ አስብ አለኝ። ልክ ነው። ይህ ሞልቶ የፈሰሰ ግፍ ለትግራይ አዲስ ነገር ይዞ እንዲመጣ መስራት አለብን።
Please wait, video is loading...