Ethiopian News, Current Affairs and Opinion Forum
Meleket
Member
Posts: 1109
Joined: 16 Feb 2018, 05:08

Re: ‘የብልህነት መንገድ’ - ምርጥ መጠሓፍ በምርጥ ተርጓሚ - ይዘቷን እንካችሁ አጣጥሙ!

Post by Meleket » 16 Apr 2019, 11:11

ዛሬም ሕዝብን ለማንቃት እዉነትን ለመግለጥ ሓሰተኛንም ለመዘርጠጥ ብዕራቸዉን አንስተዉ በተለያዩ መስኮች ጽሑፎችን በማበርከት ለህዝብ ዉለታን ለዋሉ ሆድአደር ላልሆኑ ደራስያን ሁሉ ክብር 10 የብልህነት መንገዶችን እንጋራለን። :lol: ይህን ስናደርግ የድንበር ኮሚሽኑን ትግባሬ ለማደናቀፍ የጦቢያን ማዕከላዊ መንግስት ገንቢ ሚናም ለማደፍረስና ለማጠልሸት ሌት ተቀን የሚለፋዉን የሕወሓት እርኩስ መንፈስ መፈራፈር እየታዘብንበት ያለዉን፡ የኤርትራና የኢትዮጵያ ህዝቦች 1ኛ ዓመት የጋራ የድል በአልን እያከበርን ነዉ!

111. ጓደኖች ይኑሩህ። ይህ ሁለተኛዉ ህይወትህ ነዉ። በጓደኛ አይን ሁሉም ሰዎች መልካም እና ጠቢብ ናቸዉ። ከነሱ ጋር እያለህ ሁሉም ነገር መልካም ይሆናል። የሰዉ ልጅ ዋጋ የሚወሰነዉ ሌሎች ሰዎች በሚሰጡር ዋጋ ልክ ነዉ። እናም በሰዎች ዘንድ ከበሬታን ብትሻ ልባቸዉን አሸንፍ። ሌሎችን እንደማገልገል የመሰለ ሰዉን የሚያሸንፍ ነገር የለም። ጓደኛ ብትሻ አንተ ራስህ ጓደኛ ሆነህ ቅረብ። እናም ድንቅ እና መልካም የምንለዉ ነገር ሁሉ ያለዉ በሰዎች ዘንድ ነዉ። ከጠላት ወይም ከጓደኛ ጋር መኖር ግዴታህ ነዉ። እናም በእያንዳንዷ ቀን ሚስጥረኛ ባይሆንህ እንኳ መልካም ባልንጀራ ይሆንህ ዘንድ አንድ ሰዉ አፍራ። በደንብ ከመረጥክ ደግሞ አንዳንድ ታማኝ ሰዎችን ታገኛለህ።

112. የሰዎችን መልካም ፈቃድ አግኝ። ፈጣሪ እንኳ በታላላቅ ስራዎች ዉስጥ ለመልካም ፈቃድ ቦታ አለዉ። መልካም ስም የሚገዛዉ በፍቅር ነዉ። አስተዋዮች የሰዎች እርዳታ ካልተጨመረበት በስተቀር ችሎታ ብቻዉን የትም እንደማያደርስ ያዉቃሉ። ቅን መሆን ነገሮችን ሁሉ ከማቅለሉ በላይ፤ የጎደሉህን እንደ ድፍረት እና ጉብዝና ያሉ ነገሮችን ብቻ ሳይሆን አስተዋይነትን እንኳ ይሞላልሃል። የሰዎችን በጎ ፈቃፍ ካገኘህ ሰዎች መመልከት ስለማይፈልጉ ጉድለትህን አያዩም። አብዛኛዉን ጊዜ የሰዎች መልካም ፈቃድ የምትወለደዉ በብሔር፤ በቤተሰብ፣ በሀገር፣ በፀባይ ወይም ከሙያ ጋር በተያያዘ መመሳሰል ነዉ። የሰዎች መልካም ፈቃድ ከመመሳሰል አልፎ ጠለቅ ያለ እንደሆን ግን አብዛኛዉን ጊዜ ከብቃት፣ ከችሎታ፣ እና ከዝና ጋር የተያያዘ ነዉ። የሰዎችን መልካም ፈቃድ ማግኘት ከባድ ቢሆንም አንዴ ካገኘኸዉ በኋላ ግን ጠብቆ ማቆየቱ ቀላል ነዉ። መልካም ፈቃድን ለማግኘት ጥረት ማድረግ ትችላለህ፤ ሆኖም ግን እንዴት መጠበቅ እንዳለብህ እወቅበት።

113. መልካም እድል ያንተ እያለች ለመጥፎ እድል አቅድ። በመኸር ወቅት ለክረምት መዘጋጀት ቀላል ነገር ነዉ። በዚህ ወቅት የሰዎች ችሎታ ብዙ ነዉ፤ ጓደኞችም እንደዛዉ ብዙ ናቸዉ። በችግር ጊዜ ሁሉም ነገር ውድ ስለሆነ፤ ለዝናባማዉ ቀን ቀድሞ መዘጋጀት በጎ ነገር ነዉ። የማይጠቅም የሚመስልህ ነገር ሁሉ አንድ ቀን ስለሚጠቅምህ መልካም ጓደኞች እና ዉለታ የዋልክላቸዉ ሰዎች ይኑርህ። ባለጌወች በመልካም ቀን ጊዜ ጓደኝነት ስለማይታያቸዉ በክፉ ቀን ጊዜ በባልንጀሮቻቸዉ ይገለላሉ

114. ፈፅሞ ክርክር ዉስጥ እንዳትገባ። ከባላንጣዎችህ ጋር ስትፎካከር መልካም ስምህን ታጣለህ። ተፎካካሪህ ያለብህን ጉድለት ሁሉ እያነሳ ያራክስሃል። ጦርነትን በሀቀኝነት የሚዋጓት ጥቂቶች ናቸዉ። ፉክክር ትህትና የናቃቸዉን እንከኖች ሁሉ እየመዠለጠ ያወጣቸዋል። የብዙ ሰወች መልካም ስም የሚሰነብተዉ ክፉ ተፎካካሪ እስከሚያጋጥማቸዉ ነዉ። የባላንጣነት ግለት የተረሱ ነዉሮችን እየቆፈረ ያወጣቸዋል። ፉክክር የሚጀመረዉ የሰዉን መጥፎ ጎን በማጋለጥ ስለሆነ ባላንጣወቻችን የሚገባዉን እና የማይገባዉን ነገር ሁሉ ለክፋታቸዉ ያዉሉታል። አብዛኛዉን ጊዜ ባላንጣዎች ርካሽ ከሆነ የበቀል እርካታ ዉጭ ሌሎችን በማስቀየም ምንም ጥቅም አያገኙም።

115. መልከ ጥፉን እንደምትታገሰዉ ሁሉ የባልንጀሮችህን ድክመትም ታገስ። በተለይ የእርስ-በርስ ጥገኝነት ያለ ጊዜ መስማማትን ተጠቀም። አንዳንዴ ከህይወታችን ልናስወግዳቸዉ የማንችል መጥፎ ሰዎች ያጋጥማሉ። እናም የእነዚህ ሰዎች መጥፎ ስራ በድንገት እንግዳ እንዳይሆንብን መልከ ጥፉን እንደምንላመደዉ ሁሉ እነሱንም ልንላመዳቸዉ ይገባል። እነዚህ ሰዎች በመጀመሪያ ቢያስደነግጡንም ቀስ በቀስ ግን መጥፎነታቸዉ እየቀነሰ እንደሚሄድ ይሰማን እና በአስተዋይነታችን ባህሪያቸዉን ቀድመን መተንበይ እንችላለን አሊያም መጥፎነታቸዉን እንለምደዋለን።

116. ሁሌም ነገርህ ግብረገብነት ካላቸዉ ሰዎች ጋር ይሁን። ለነዚህ ሰዎች ደግ ሁንላቸዉ፤ እነሱም ደግ እንዲሆኑልህ አድርግ። እንዲህ አይነት ሰዎች ሲቃወሙህ እንኳ መልካምነትን በተላበሰ ሁኔታ ሲሆን ይህ የመነጨዉ ደግሞ ከግብረገብ ባህሪያቸዉ ነዉ። እናም መጥፎ ሰዎችን ተጣልቶ ከማሸነፍ ይልቅ መልካም አስተሳሰብ ካላቸዉ ሰዎች ጋር መጣላት ይሻላል። ተንኮለኞች ለግብረገብነት መገዛት ስለማይፈልጉ ልንግባባቸዉ አንችልም። ለዚህም ነዉ ከመጥፎዎች ጋር እዉነተኛ ጓደኝነት መመስረት የማይቻለዉ። ከእንደዚህ አይነት ሰዎች የሚወጡ መልካም ቃላት ምንጫቸዉ ከጨዋነት ስላልሆነ እምነት ሊጣልባቸዉ አይገባም። ምንም ክብር የሌለዉን ሰዉ አትጠጋ፤ ምክንያቱም ይህ ሰዉ ክብርን ካላወቀ የጨዋነት ተግባርንም ሊያዉቅ ስለማይችል ነዉ። ክብር ማለት ጨዋነት የሚነግስበት ዘዉድ ነዉ

117. ስለራስህ አታዉራ። ስለራስህ ስታወራ ወይ ራስህን ማጣጣል አሊያም ማሞገስ ይኖርብሃል። ራስን ማሞገስ ከንቱነት ሲሆን፤ ራስን ማጣጣል ደግሞ የዋህነት ነዉ። እነዚህን ተግባራት ስትፈጽም ማመዛዘን እንደጎደለህ ከማሳየት በላይ ሌሎችን ትረብሻለህ። እናም ስለራስ ማዉራት በግል ህይወትህ መወገዝ ካለበት በህዝብ ፊት ደግሞ የበለጠ መወገዝ ይገባዋል። ለዚህ ምክንያቱ በህዝብ ፊት በትንሹም ቢሆን ስለራስህ ማዉራት እንደ ቂላቂል ስለሚያስቆጥርህ ነዉ። እንዲሁ በፊትህ ስላሉ ሰዎች ማዉራት አስተዋይነት አይደለም፤ ምክንያቱም ይህን ስታደርግ ሰዉን ከልክ በላይ እንዳሞገስክ ወይም እንዳንኳሰስክ ስለሚቆጠርብህ ነዉ።

118. በጨዋነትህ የታወቅክ ሁን። ይህ በራሱ በሰዎች ዘንድ ለመወደድ በቂ ነዉ። ብልግና በሰዎች ዘንድ ብስጭትን እንደሚቀሰቅስ እና ዉግዘትን እንደሚያመጣ ሁሉ፤ ግብረገብነት ደግሞ የጨዋነት መልካም ጎን እና በጣም አስደሳች በመሆኑ የሰዎችን መልካም ፈቃድ ያስገኝልናል። ብልግና የመጣዉ ከኩራት ከሆነ በጣም አስቀያሚ ነዉ፤ ከመጥፎ አስተዳደግ ከሆነ ደግሞ የሚናቅ ተግባር ነዉ። እናም ሁሌም ጨዋነት እንደየሰዉ የተለያየ ሊሆን ይገባል፤ አለዚያ ፍርድ ማጋደል ይሆንብናል። ጠላቶችህን እንኳ በጨዋነት አስተናግዳቸዉ እና ጨዋነት ምን ያህል ጠቃሚ እንደሆነ ትረዳለህ። የጨዋነት ተግባር ብዙም ልፋት ሳይጠይቀን ብዙ ጠቀሜታን ያስገኝልናል ምክንያቱም ክብርን ለባልንጀራ ማሳየት ከበሬታን ስለሚያስገኝ ነዉ

119. የሰዎችን ጥላቻ እንዳታተርፍ። ጥላቻ ብዙም መልፋት ሳያስፈልግህ በራሷ ትመጣልሃለች። ብዙ ሰወች ሳይታወቃቸዉ ወይም ያለምንም ምክንያት የጥላቻ መንፈስ ያድርባቸዋል። መጥፎ ነገር የማድረግ ፍላጎት መልካም የማድረግ ፍላጎትን ይበልጠዋል። ለዚህ ምክንያቱ ሌሎችን ለመጉዳት ያለን ፍላጎት ራሳችንን ለመጥቀም ካለን ፍላጎት ስለሚበልጥብን እና ፈጣን ስለሆነ ነዉ። አንዳንድ ሰዎች በሁሉም ሰው ዘንድ መጠላት ያስደስታቸዋል። ይህ የሚሆነዉ እነዚህ ሰዎች የተናደዱ እንደሆነ ወይም ሰዉን ማናደድ ሲያምራቸዉ ነዉ። እንዲህ አይነት ሰዎችን ጥላቻ የተሰቀላቸዉ ጊዜ ነገሩ ልክ እንደ መጥፎ ስም ለማጥፋት አስቸጋሪ ይሆናል። እነዚህ ሰዎች አስተዋዮችን ይፈራሉ፤ እብሪተኞችን ያንቋሽሻሉ፤ ቂላቂሎችን ደግሞ ይጠየፋሉ፤ ታላቅ ሰዎችን ግን አይነኩም። ትመስገን ዘንድ አመስግን ፍቅርን ታገኝ ዘንድ ደግሞ ፍቅር ይኑርህ

120. ተግባራዊ ሁን። እዉቀትህ እንኳ የሚታወቅ እና ጥቅም ላይ ሊዉል የሚችል መምሰል አለበት፤ ሆኖም ግን እዉቀት ባልተለመደበት ስፍራ የማታዉቅ ምሰል። አመለካከት እና ምርጫ ዘመንን ተከትለዉ ስለሚለዋወጡ አኗኗርህ ዘመናዊ ይሁን፤ አስተሳሰብህም ኋላ ቀር እንዳይሆን። በሁሉም መስመር የብዙ ሰዎች ድጋፍ ያለዉ ነገር ተቀባይነትን ስለሚያገኝ ወደ ስኬት ስታመራ ይህን ነገር ልብ ልትል ይገባል። ምንም እንኳ የጥንቱ ነገር መልካም መስሎ ቢታይም ብልህ በአስተሳሰቡ ሆነ በአመለካከቱ ጊዜዉን መስሎ ማደር አለበት። ይህ አባባል ለሁሉም ነገሮች ቢሰራም ለደግነት አይሰራም፤ ይህ የሆነዉ ሁሌም መልካምነትን መከተል ስላለብን ነዉ። እንደ እዉነት መናገር እና ቃልን ማክበር የመሰሉ ብዙ ነገሮች እንደ ኋላ ቀር እየታዩ መጥተዋል። መልካም ሰዎች የተወደዱ ቢሆኑም ጥንት የቀሩ ይመስላል። ባሁኑ ዘመን ምንም መልካም ሰዎች ቢኖሩ እንኳ በጣም ጥቂት ሲሆኑ የእነርሱን አርአያ መከተል የሚፈልጉ ሰዎችም አይገኙም። ጨዋነት ብርቅ የሆነበት፤ ተንኮል የበዛበት ምን አይነት አሳዛኝ ዘመን ነዉ? እናም አስተዋይ የሆነ ሰዉ የሚመኘዉን ያህል ባይሆን እንኳ የሚችለዉን ያህል ይኑር። እንዲሁ እነዚህ አስተዋዮች እድል ከነሳቻቸዉ ነገሮች ይልቅ የቸረቻቸዉን ነገሮች የሚወዱ ያድርግልን!

ጎበዝ፣ በብልህነት መንገድ እንጓዝ፣ ብልሆችም እንሁን! :mrgreen:

Meleket
Member
Posts: 1109
Joined: 16 Feb 2018, 05:08

Re: ‘የብልህነት መንገድ’ - ምርጥ መጠሓፍ በምርጥ ተርጓሚ - ይዘቷን እንካችሁ አጣጥሙ!

Post by Meleket » 17 Apr 2019, 11:43

ጎበዝ የዛሬዎቹን አስር የብልህነት መንገዶች ስናጣጥም፣ በተለያዩ ሰብአዊ ሆነ ባህርያዊ ምክንያቶች ከሃገራቸዉ ለተሰደዱ ምስኪን ያፍሪካ ቀንድ ወጣቶች ክብር ነው። ይህን ስናደርግ ሩቅ አልመዉ ሜድትራኒያን ባህርን ሆነ ቀይባህርን ለመሻገር ሞክረዉ ህይወታቸዉን ያጡትን ዜጎች ሁሉንም እዘክራለን፣ የቅርቡን የአጽቢ ወንበርታን ወጣቶች እልቀትንም እየዘከርንና ለወላጆቻቸው ልባዊ ጽናት እየተመኘን ነዉ ለዚህ ሁሉ ችግር ምክንያት የሆነችዉን የአፈንጋጯን የሕወሓትን ውድቀት እየዘከርን የኤርትራና ኢትዮጵያ ህዝቦችን 1ኛ ዓመት የድል በዓልም እያከበርን ነዉ።

121. በጥቃቅን ነገሮች ላይ ነገር አታክብድ። አንዳንዶች ሁሉንም ነገር እንደሚንቁት ሁሉ ሌሎች ደግሞ ያገኙትን ሁሉ የሙጥኝ ይላሉ። እነዚህ የኋለኞቹ ሰዎች ሁሉንም ነገር እንደ አስፈላጊ እና ብርቱ ጉዳይ ወስደዉ ወደ መከራከሪያ ርዕስ ወይም ረቂቅ ነገር ይቀይሩታል። ጥቃቅን ነገሮችን አግዝፎ ማየት በምን ስራ ልፍታ እንደ ማለት ነዉ። ስለዚህ ጀርባህን ልትሰጠዉ በሚገባ ጉዳይ ላይ ማምረር እንደ ቂልነት ይቆጠራል። አንዳንድ ትልቅ የሚመስሉ ጉዳዮች ናቅ ከተደረጉ ምንም ይሆናሉ፤ እንዲሁ ሌሎች ምንም ያልሆኑ ጉዳዮች ደግሞ ሙጭጭ ስንልባቸዉ ብቻ ይገዝፋሉ። መጀመሪያ ላይ ችግሮችን ባጭሩ መቅጨት ቢቻልም ዉለዉ ያደሩ እንደሆን ግን የማይሆን ነገር ነዉ። አንዳንዴ ደግሞ መድሀኒት በሽታን ያስከትላል። እናም ታናሽ የማይባለዉ የህይወት አስተምህሮ ነገሮችን አለመነካካት ነዉ።

122. በንግግር እና በምግባር ላቅ ማለት። ይህ በፍጥነት ከበሬታን ከማስገኘቱም በላይ፤ በሄድክበት ሁሉ መንገድህን ይጠርግልሀል። ላቅ ማለት ራሱን በሁሉም መንገድ ይገልጻል። በአያያዝ፤ በአነጋገር፤ እና በፍላጎት ብቻ ሳይሆን፤ አንዳንዴ በእርምጃ እና በመልክ እንኳ ይገለፃል። የሌሎችን ልብ ማሸነፍ ታላቅ ችሎታ ነዉ። እንዲህ አይነቱ ችሎታ ከቂላቂል ድፍረት ወይም ከደደብ ዳኝነት የሚመጣ ሳይሆን በችሎታ ምክንያት ከታላቅ ኣእምሮ የሚወለድ ነገር ነዉ።

123. ልምሰል ባይ አትሁን። በተለይ በችሎታህ ልምሰል ባይ መሆን የለብህም። አስመሳይነት ለአስመሳዩ ራሱ ሸክም እና ስቃይ ከመሆኑ በላይ በሰወች ዘንድ ደግሞ የተጠላ ነገር ነዉ። ከሰዉ ሰራሽ ነገር ይልቅ ሁሌም በተፈጥሮ ወይም ያለልፋት የተገኘ ነገር ተወዳጅ በመሆኑ፤ የተፈጥሮ ተሰጥኦዎች ልምሰል ባይነት ሲጨመርባቸዉ በሰዎች ዘንድ በመፍጨርጨር የመጡ ናቸዉ ተብለዉ ስለሚታሰቡ ዋጋቸዉ ዝቅተኛ ይሆናል። እናም አስመሳዮች ልምሰል ለሚሉላት ሙያ እንደ ባዳ ተደርገዉ ይቆጠራሉ። በአንድ ነገር ላይ ላቅ ያለ ችሎታ ካለህ ችሎታህ በተፈጥሮ የመጣ ይመስል ዘንድ ብዙ ስትለፋ እንዳትታይ። እንዲሁ አስመሳይ ላለመምሰል ስትል ደግሞ ልመሰል ባይ እንዳይሆን። አስተዋይ ሰዉ ይህን እችላለሁ እያለ መናገር የለበትም። ለችሎታዉ ብዙም ትኩረትን ያልሰጠ ሲመስል ግን የሌሎችን ትኩረት ይስባል። እንዲሁ ላለዉ ችሎታ ትኩረት የማይሰጥ ላቅ ያለ ሰዉ በእጥፉ ላቅ እንዳለ ይቆጠራል። ይህ ሰዉ ወደ ተደናቂነት የሚጓዘዉም የራሱን ለየት ያለ መንገድ ተከትሎ ነዉ።

124. ራስህን ተፈላጊ አድርግ። ጥቂት ብቻ ናቸዉ በሰዎች ዘንድ ድጋፍን ያገኙ፤ የጠቢቦችን ድጋፍ ካገኘህ ደግሞ ራስህን እንደ እድለኛ ቁጠር። ሰዎች አብዛኛዉን ጊዜ ብዙ ላከናወኑ ሰዎች ያላቸዉ አመለካከት ቀዝቀዝ ያለ ነው። የሰዎችን ድጋፍ ለማግኘት እና ካገኙም በኋላ ጠብቆ ማቆያ ዘዴ ቢኖር በችሎታ ላቅ ማለት እና ሙያን በደንብ ማከናወን ሲሆን፤ እንዲሁ ሰዎችን የሚያስደስት ምግባርም የሰዎችን ድጋፍ ያስገኝልሃል። በሙያህ ያለህን ልቀት ሰዎችን ጥገኛ ለማድረግ ተጠቀምበት፤ ይህ ሲሆን ሰዎች በያዝከዉ ሙያ የምትፈልግ እንጅ አንተ ሙያዉን የምትፈልገዉ አድርገዉ አይቆጥሩብህም። አንዳንድ ሰዎች በስልጣናቸዉ ብቻ ክብርን ሲያገኙ ሌሎች ደግሞ ለስልጣናቸዉ ክብርን ያላብሱታል። የመጥፎ ሰዉን እግር ተከትለህ ስልጣን ላይ ስለወጣህ ብቻ እንደ መልካም መታየት ከክብር አይቆጠርም። ምክንያቱም ይህ ነገር የሚያሳየዉ የአንተን መወደድ ሳይሆን የመጥፎዉን ሰዉ መጠላት በመሆኑ ነዉ

125. የሰዎችን ጉድፍ ነቃሽ እንዳትሆን። የሰዎች ነዉር ላይ ጣትን መቀሰር የራስህን ነዉረኛነት ያሳያል። አንዳንዶች የራሳቸዉን ነዉር በሌሎች ሰዎች ነዉር ለመደበቅ ወይም ለማጽዳት ወይም የሌሎችን ነዉር እንደ መፅናኛ ይጠቀማሉ፤ ይህ ደግሞ የቂሎች መፅናኛ እንጅ ሌላ አይደለም። እንዲህ አይነት ሰዎች አፋቸዉ የቀረና የቆሻሻ ማጠራቀሚያ ገንዳወች ናቸዉ። የሰዎችን ነዉር እየቆፈረ የሚያወጣ ራሱ የበለጠ ነዉርን ይከናነባል። በተፈጥሮ ሆነ ከሰዉ የወረሱት እንከን የሌለባቸዉ በጣም ጥቂት ሰዎች ብቻ ናቸዉ። አንተ በጣም ታናሽ የሆንክ እንደሆን ብቻ ነዉ ጥፋትህም ከሰዉ አይን የማይገባዉ። እናም በሰዎች ዘንድ ስለሚያስጠላህ እና እንደ እንስሳም ስለሚያስቆጥርህ የሰዎችን ጉድፍ ከመንቀስ ተቆጠብ።

126. ሞኝ ማለት የሞኝ ስራ የሚሰራ ሳይሆን የሞኝነት ስራዉን መደበቅ የማይችል ነዉ። አንድ ሰዉ መልካም ጎኑን እንኳ እወቁልኝ ማለት እንደሌለበት ከታወቀ መጥፎ ጎኑን ደግሞ የበለጠ መደበቅ አለበት። ማንኛዉም ሰዉ ስህተት ይሰራል ልዩነቱ ግን ጠቢቦች ስህተታቸዉን መደበቅ ይችላሉ፤ ሞኞች ደግሞ ሊሰሩ ስላቀዱት ስህተት ይናገራሉ። መልካም ስም የምትመሰረተዉ ለሰዎች ከምናሳያቸዉ ይልቅ በምንደብቃቸዉ ነገሮች ነዉ። ስለዚህ መልካምነትን የማይችል ሰዉ ጥንቁቅ መሆን አለበት። የታላላቅ ሰዎች ስህተት እንደ ፀሀይ እና ጨረቃ ግርዶሽ በጉጉት የሚጠበቅ ነገር ነዉ። እናም ስህተትህን ለጓደኛህ እንኳ መናገር የለብህም፤ የሚቻል ቢሆንም ለራስህም መንገር ባልነበረብህ፤ ሆኖም ግን ይህ ስለማይቻል መርሳት የሚባለዉን የህይወት ህግ ተጠቀም

127. በምትሰራዉ ነገር ሁሉ ግርማ ሞገስ ይኑርህ። ይህ ለችሎታችን ህይወትን ይዘራበታል፤ ለንግግራችን ትንፋሽን ያወርሳል፤ ለምግባራችን መንፈስን ይሰጣል እንዲህ ላቅ ያሉ ተሰጥኦወች መገለጫም ነዉ። ሌሎች ልቀቶች ከተፈጥሮ የሚቸሩ ጌጦች ቢሆኑም፤ ግርማ ሞገስ ግን ልቀቶችን ራሱ የሚያስጌጥ ነገር ነዉ። ግርማ ሞገስ ብዙዉን ጊዜ በተፈጥሮ የሚገኝ ነገር ሲሆን፤ እንዲሁ ብዙም በትምህርት የሚገኝ ነገር ብቻ ሳይሆን በትምህርት ወይም በጥረት ከሚገኝ ነገርም በላይ ነዉ። ግርማ ሞገስ ማለት ዘና ከማለት በላይ ነዉ፤ ከነጻነት እና ቀለል ከማለት ጋር ይቀራረባል፤ የማፈር ነገርን ልብ አይልም፤ እንዲሁ ለስራም ልቀትን የሚጨምር ነዉ። ያለግርማ ሞገስ ቁንጅና በድን ነዉ፤ ግርማም ግርማ የለሽ፤ ለዚህ ምክንያቱ ሞገስ ከብርታት፣ ከጠቢብነት፣ ከአስተዋይነት እና ሀያልነትን ጨምሮ ከሁሉ በላይ ስለሆነ ነዉ። ግርማ ሞገስ ባቋራጭ ጉዳይን ለማስፈጸም የሚረዳ ነገር ሲሆን፤ ከችግር ማምለጫ ዘዴም ነዉ

128. አስተሳሰብህ ታላቅ ይሁን። ሁሉንም አይነት የታላቅነት ስሜት ስለሚቀሰቅስ ታላቅ አስተሳሰብ የጀግንነት ዋነኛ መሰረት ነዉ። ለዚህ ምክንያቱ ታላቅ አስተሳሰብ የመምረጥ ችሎታን፣ ፈጣንነትን፣ የአእምሮ ንቃትን፣ የመንፈስ ጨዋነትን፣ እና ክብርን ስለሚያላብስ ነዉ። ታላቅ ሀሳብ በተገኘችበት ሁሉ ሀያል ነች። አንዳንዴ እድል ራሱ ይቀናባት እና ሊያኮላሻት ቢሞክርም ሁሌም ላቅ ለማለት ጥረት እንዳደረገች ነዉ። ሀያልነት፤ ቸርነት እና ማናቸዉም የጀግንነት ስራ መነሻዉ የአስተሳሰብ ታላቅነት ነዉ

129. በፍጹም አታማርር። ማማረር ሁሌም ዋጋህን ዝቅ ያደርገዋል። ሰዎች ስናማርር ሲያዩን ከማፅናናት እና ከመርዳት ይልቅ በብልግና እና በንቀት ስሜት ያዩናል። ከዚህም በላይ ራሳቸዉም የምናማርርባችዉን ነገሮች መልሰዉ በኛ ላይ እንዲፈጽሙብን ያደፋፍራቸዋል። እናም ስለተፈጸመብን ክፉ ነገር ለሰዎች ስንናገር ሰሚዎቻችን የተፈጸመብን በደል እንደሚገባን ሊያስቡ ይችላሉ። አንዳንዶች በፊት ስለተፈጸመባቸዉ በደል ሲናገሩ ወደፊት ለሚመጡ በደሎች በራቸዉን ይከፍታሉ። እንዲህ የሚናገሩ ሰዎች የሚፈልጉት እርዳታ እና መጽናናትን ቢሆንም ለሰሚ ጆሮ እርካታን ከማስገኘት አልፈዉ ንቀትን ስሜትን ሊቀሰቅሱ ይችላሉ። ስለዚህ ብዙ ደግ ስራ ይደረግልህ ዘንድ ሰዎች ስለሰሩልህ መልካም ነገር እያሞጋገሱ ማዉራት የተሻለ ዘዴ ነዉ። ለዚህ ምክንያቱ የቀደሙት ስላደረጉልህ መልካም ነገር ስታወራ ይሁን ያሉት ደግሞ ተመሳሳይ እንዲያደርጉ ስለምትጋብዛቸዉ ነዉ። አስተዋይ ሰዉ ሰዎች ስላሳዩት ከበሬታ እንጅ የደረሰበትን ዉርደት እና ንቀት በፍጹም መልፈፍ የለበትም። ይህን ያደረገ እንደሆን ወዳጅነትን ይጨምራል፤ ጠላቶችን ደግሞ ይቀንሳል

130. ስራ፤ ግን ደግሞ የምትሰራ ምሰል። ነገሮች ግምት የሚሰጣቸዉ በሚታዩት እንጅ በሆኑት አይደለም። ላቅ ማለትና እና ልቀት ማሳየት መቻል እጥፍ ጊዜ ላቅ እንደ ማለት ይቆጠራል። የማናየዉ ነገር እንደሌለ ይቆጠራል። ምክንያት ራሷ ምክንያት መስላ ካልቀረበች ከበሬታን አታገኝም። በቀላሉ የሚታለሉ ሰዎች ቁጥር ከአስተዋዮች ቁጥር የበለጠ ነዉ። የይምሰል ነገር በመንገሱ ምክንያት ምንም እንኳ ነገሮች አብዛኛዉን ጊዜ በዉጭ እንደሚታዩት ባይሆኑም ግምት የሚሰጣቸዉ ግን በዉጭ ገጽታቸዉ ነዉ። እናም መልካም ዉጫዊ ገጽታ ዉስጣዊ ልቀትን ለማመልከት በደንብ ይረዳል።

ጎበዝ፣ በብልህነት መንገድ እንጓዝ፣ ብልሆችም እንሁን! :mrgreen:

Meleket
Member
Posts: 1109
Joined: 16 Feb 2018, 05:08

Re: ‘የብልህነት መንገድ’ - ምርጥ መጠሓፍ በምርጥ ተርጓሚ - ይዘቷን እንካችሁ አጣጥሙ!

Post by Meleket » 18 Apr 2019, 11:49

የዛሬ 10 የብልህነት መንገዶችን የምንዘክር ለእዉነተኛ ጋዜጠኞች ሙያቸዉን በቅንነት ህዝብ ለማደናገር ሳይሆን ህዝብን ለማገልገል የሚጠቀሙበትን የሕዝብ ቀንዴል የሆኑትን ጋዜጠኞች እያከበርንና እየዘከርን ነዉ። አያይዘንም የገዱንና የለማን ወደ አዲስ መድረኽ መሸጋገር ምክንያት በማድረግ ባገሬ በኤርትራና በኢትዮጵያ መካከል ያለዉን ያልተቋጨ ጉዳይ እልባት እንደሚያደርሱ ተስፋ እያደረግን፤ ነቀርሳዋን ሕወሃት ከዓለም መድረክ የመነገልንበትን 1ኛ ዓመት የድል በዓል በድምቀት እያከበርን ነዉ። :lol:

131. የጀግና መንፈስ። እነሆ ለባህሪያችን በሙሉ ሞገስን የሚያላብስ እና በሀሳበ ሰፊነት የጀግንነት ስራን የሚሰራ ለየት ያለ የመንፈስ ልቀት አለ። ሀያልነትን የሚጠይቅ ስለሆነ ጀግንነት በሁሉም ሰዉ ዘንድ አይገኝም። የጀግና መንፈስ የመጀመሪያ አላማ ስለባላንጣዉ መልካም ነገርን እያወራ ግን ከባላንጣዉ በላይ ብዙ ማከናወን ነዉ። የጀግና መንፈስ በቀልን የመፈጸም አጋጣሚ ያገኘች ጊዜ አንጸባራቂ ትሆናለች። የጀግና መንፈስ እንዲህ አይነት አጋጣሚዎችን ከመሸሽ ይልቅ፤ መበቀል ስትችል ያልተጠበቀ የደግነት ስራን ትሰራ እና አጋጣሚዉን በብቃት ትጠቀምበታለች። ይህ ዘዴ ሌሎችን ለማስተዳደር የሚረዳ የዲፕሎማሲ አበባ ነዉ። ጀግና መንፈስ አሸናፊነቷን አታሳይም፤ ምንም እንኳ አሸናፊነቷ በችሎታ ቢሆንም ችሎታዋን መደበቅ ትችላለች።

132. ነገሮችን መለስ ብሎ የመመርመርን ጥቅም እወቅ። በተለይ በደንብ እርግጠኛ ያልሆነ ጊዜ ነገሮችን እንደገና መመርመር ከችግር ይጠብቃል። አንድን ነገር ለመፍቀድ ሆነ ለማድረግ በቂ ጊዜ ብትወስድ ዉሳኔህን የምታጠነክርበት እና የዉሳኔህን ተገቢነት የምታረጋግጥበት ዘዴ ታገኛለህ። የስጦታ ጉዳይ ከሆነ ደግሞ በፍጥነት ከሚሰጥ ይልቅ በጠቢብነት ቢሰጥ ዋጋዉ በሰዎች ዘንድ ከፍ ያለ ይሆናል። በጣም የተመኙት ነገር ሲገኝ በጣም ያስደስታል። አንድን ነገር ልትከለክል ከሆነ ደግሞ እንዴት መከልከል እንዳለብህ ትኩረት ስጥ፤ እናም ተቃዉሞህ ለሰዎች መራራ እንዳትሆን በሰል እንድትል ፍቀድላት። ይህ ሲሆን መጀመሪያ ያለዉ ከፍተኛ ፍላጎት ቀዝቀዝ ይል እና ተቃዉሞን ለመቀበል ቀላል ይሆናል። ሰዉ በፍጥነት ስጠኝ ቢልህ አቆይተህ ስጠዉ። ይህ የሰዉየዉን ፍላጎት የመያዣ ዘዴ ነዉ።

133. ለብቻ ጤነኛ ከመሆን ይልቅ ከሁሉም ጋር ማበድ ይሻላል። ይህ የፖለቲከኖች አባባል ነዉ። ሁሉም እብዶች ከሆኑ ከሁሉም ጋር እኩል ትሆናለህ። ብቻህን ጤነኛ ከሆንክ ግን እንደ እብድ ትቆጠራለህ። ዋናዉ ነገር ነፋሱን ተከትሎ መንፈስ መቻሉ ላይ ነዉ። አንዳንዴ የተሻለ የሚሆነዉ አለማወቅ ወይም ያላወቁ መምሰል ነዉ። ከሌሎች ጋር መኖር አለብን፤ አብዛኞች ደግሞ ደንቆሮዎች ናቸዉ። ብቻህን ለመኖር ወይም አዉሬ አሊያም ደግሞ የፈጣሪ አምሳያ መሆን አለብህ። እኔ ግን ይህን አባባል አሻሽለዉ እና ለብቻ ከማበድ ከሌሎች ጋር ጤነኛ መሆን ይሻላል እላለሁ። ሆኖም ግን አንዳንድ ሰወች በሞኝነት ለየት ያሉ ለመሆን ጥረት ያደርጋሉ

134. ለህይወት አስፈላጊ ከሆኑት ነገሮች እጥፍ እጥፉን ያዝ። ይህ ለህይወትህ እጥፍ የሆነ መድህንን ያስገኝልሃል። የፈለገ ብርቅየ እና የማይገኝ ነገር ቢሆን እንኳ ራስህን በአንድ ነገር ብቻ አትወስን። እንዲሁ የአንድ ነገር ብቻ ጥገኛ እንዳትሆን። ጥቅማጥቅምን፤ ድጋፍን፤ ኣንዲሁ ምርጫን ጨምሮ ሁሉንም ነገር በእጥፉ ያዝ። ዘላለማዊ ሆኖ እያለ ጨረቃ እንኳ ፊቷን ትለዋዉጣለች፤ ይህም የቋሚነትን ዘላለማዊ አለመሆን ያሳያል። ለህይወት የሚያስፈልጉን ነገሮች ደግሞ ስስ በሆነዉ የሰዎች ፈቃድ የተመሰረቱ ስለሆኑ የበለጠ ይቀያየራሉ። የክፉ ቀን ክምችት ይኑርህ። ይህ ደስታን እጥፍ የሚያደርግ የኑሮ ህግ በመሆኑ መርህ ይሁንህ። ተፈጥሮ በጣም አስፈላጊወቹን እና በጣም የተጋለጡትን እንደ እጅ እና እግር ያሉ የሰዉነት ክፍሎች በእጥፉ ስለሰጠችን፤ ጥበብ ደግሞ ለህይወት አስፈላጊ የሆኑትን ነገሮች በእጥፉ ልትሰጠን ይገባል።

135. የተቃዋሚነት መንፈስ እንዳይጠናወትህ። ይህ ሞኝነትን እና ንዴትን ከማሸከም ዉጭ ሌላ ነገር አያደርግልህም። እናም አስተዋይነት ከእንዲህ አይነቱ ቅሌት እንዲጠብቅህ ይሁን። ለሁሉም ነገር መቃወሚያ ማግኘት ጉብዝና ሊሆን ይችላል፤ ሆኖም ግን ደረቅ ሰዉ ሁሌም ቂል ከመባል አያመልጥም። አንዳንዶች ጣፋጭ የሆነ ጭዉዉትን ወደ ጭቅጭቅ ይቀይራሉ። እንዲህ አይነት ሰዎች ከማያዉቋቸዉ ይልቅ ለሚያዉቋቸዉ እና ለጓደኞቻቸዉ እንደ ጠላት ናቸዉ። ክርክር ጠንካራ የሚሆነዉ በጣፋጭ ጭዉዉቶች ላይ ስለሆነ ተቃዉሞ መልካም የሆነን አጋጣሚ ይበክላል። አዉሬነትን ከአስጠሊታነት ጋር የሚይዙ ሰዎች ሊለወጡ የማይችሉ ቂሎች ናቸዉ

136. ራስህን ከነገሮች መሀከል አድርግ። ይህ የነገሮችን ትርታ እንድትረዳ ያደርግሃል። አብዛኞች የነገሩን ጭብጥ ሳይዙ ያለ ምንም ጥቅም ዙሪያ ጥምጥም ንግግር እና ዳርዳርታን ያበዛሉ። እነዚህ ሰዎች ከነገሩ ጭብጥ ላይ ሳይደርሱ መቶ ጊዜ እየተመላለሱ እራሳቸዉን እና ሌሎችን ያደክማሉ። ይህ የሚያሳየዉ ራሱን መሰብሰብ አቅቶት የተበታተነን ጭንቅላት ነዉ። እንዲህ አይነት ሰዎች ጊዜን ያጠፋሉ፤ ትእግስትንም ያስጨርሳሉ። መንካት የሌለባቸዉን ጉዳይ እየነካኩ ጊዜን ያጠፋሉ፤ ትእግስትንም ያስጨርሳሉ። ይህ ከሆነ በኋላ ደግሞ ወደ አለፏቸዉ ጉዳዮች ሲመለሱ ጊዜ እና ትእግስት ያጥራቸዋል።

137. ብልህ ራሱን የቻለ ነዉ። ሁሉንም በዉስጡ የያዘ ሲሆን ሲሄድም ሁሉንም ይዞ ይሄዳል። ሁሉንአወቅ ጓደኛ አለሙን ሁሉ ሊወክል ይችላል። እንዲህ አይነት ሰዉ ብትሆን ራስህን ችለህ መኖር ትችላለህ። በምርጫዉ ሆነ በእዉቀቱ ካንተ በላይ የሆነ ሰዉ ከሌለ እንዴት ሰዉ ያስፈልግሃል? ይህ ሲሆን በራስህ ብቻ የምትተማመን ትሆናለህ፤ ይህ ደግሞ ከፈጣሪ ጋር ስለሚመሳሰል በጣም አስደሳች ነዉ። በራሱ መኖር የሚችል ሰዉ በምንም ምክንያት አዉሬ አይደለም፤ ይህ ሰዉ በብዙ መልኩ ብልህ ሰዉ ሲሆን፤ በብዙ መንገድም በጣኦት ይመሰላል።

138. ነገሮች ይረጉ ዘንድ አለመነካካትን እወቅበት። በተለይ ይህ ነገር አስፈላጊ የሚሆነዉ እንደ ዉቅያኖስ የምንቆጥራቸዉ ህዝብ እና ባልንጀሮቻችን በነዉጥ የተሞሉ ጊዜ ነዉ። አንዳንዴ ህይወት በነዉጥ እና ማዕበል ስለምትሞላ ዉሀዉ ወደ ሰከነበት የባህር ዳርቻ ተጠግቶ ነዉጡ እስኪበርድ ድረስ መጠበቅ ጥበበኝነት ነዉ። ብዙዉን ጊዜ መፍትሄው ችግሩን ያባብሰዋል። ይህ በሚሆንበት ጊዜ ነገሮች የተፈጥሮ ሂደታቸዉን ይከተሉ ዘንድ መፍቀድ እና ጊዜም እንዲያገኝ መተዉ ነዉ። ጠቢብ የሆነ ሀኪም መድሀኒት ማዘዝ እና አለማዘዝ ያለበትን ጊዜ ጠንቅቆ ያዉቃል። ስለዚህ አንዳንዴ ምንም አለማድረግ ታላቅ ጥበብ ነዉ። ስዶች የሚያስነሱትን ነዉጥ ለማረጋጋት ትክክለኛዉ መንገድ ራስን መግታት እና በራሳቸዉ ፀጥታን እንዲያወርዱ መተዉ ነዉ። ለጊዜዉ መሸነፍ ለወደፊቱ ማሸነፍን ሊያስከትል ይችላል። ጅረትን ማቆሸሽ ብዙም ከባድ አይደለም፤ የጎሸዉን ማጥራት የሚቻለዉ ደግሞ በመነካካት ሳይሆን ምንም ባለማድረግ ብቻ ነዉ። ነዉጥን ለማረጋጋት የተፈጥሮ ሂደቱን ይከተል ዘንድ ፈቅዶ በራሱ እንዲረጋጋ ከመተዉ ውጭ የተሻለ መድሀኒት የለም

139. እድለኛ ያልሆንክባቸዉ ቀናት ስላሉ ቀናቶቹን እወቃቸዉ። በነዚህ ቀናት ምንም ነገር ልክ አይሆንም። ጨዋታህን ብትቀይር እንኳ መጥፎ እድልህ አትቀየርም። ስለዚህ እድልህን ለጥቂት ጊዜ ፈትናት እና መጥፎ ከሆነች ገለል በል። ኣእምሯችን እንኳ የራሱ መልካም ጊዜያት አሉት፤ ማንም ሰዉ በማንኛዉም ሰኣት ጠቢብ ሊሆን አይችልም። እናም በደንብ ማሰብ እንደ መልካም ደብዳቤ ሁሉ መልካም እድልን ይጠይቃል። ልቀት ሁሌም መልካም ጊዜን ተገን ያደረገ ነዉ። ቁንጅና እንኳ የራሱ ጊዜ አለዉ። ስለዚህ መልካም ዉጤትን ለመስጠት ሁሉም ነገር የራሱ ጊዜ አለዉ። አንዳንድ ቀን ሁሉም ነገር ይበላሻል፤ ሌላ ቀን ደግሞ ሁሉም ነገር ያለድካም መልካም ይሆናል። በመልካም ቀናት ጊዜ ነገሮች በቀላሉ ይሳካሉ፤ የማስተዋል ችሎታ እና ፀባይም መልካም ናቸዉ፤ ኮከብም የስኬት ትሆናለች። እንዲህ አይነት ገር ቀናትን ምንም አፍታ ሳታባክን በብቃት ተጠቀምባቸዉ። ሆኖም ግን በአንዲት መጥፎ ሆነ መልካም እድል ብቻ ቀኑን በሙሉ ቀና ወይም መጥፎ ብሎ መፈረጅ የአስተዋይነት ተግባር አይደለም

140. ነገርህ ከማንኛዉም ነገር መልካም ጎን ጋር ይሁን። ይህ መልካም ነገርን የሚያዉቁ ሰዎች አስደሳች ሽልማት ነዉ። ንብ በቀጥታ ወደ ጣፋጩ ስትሄድ፤ እፉኝት ደግሞ ለመርዙ መስሪያ ወደሚጠቅመዉ መራራ ያመራል። ምርጫ ላይ አንዳንዶች ወደ መልካሙ ሲሄዱ ሌሎች ደግሞ ወደ መጥፎዉ ያመራሉ። መልካም ነገር የሌለዉ ነገር የለም፤ በተለይ ደግሞ መልካም ሀሳብን ሊይዙ ከሚችሉት መፀሀፍት። አለመታደል ሆኖባቸዉ አንዳንድ ሰዎች ከሽህ መልካም ነገሮች አንዲት ዘለላ ህፀፅ ያገኙና እሷንም ከመጠን በላይ ያጋንኗታል። እነዚህ ሰዎች በቆሻሻ የተሞላ የማድረግ ፍላጎት እና የማስተዋል ቆሻሻ ማጠራቀሚያወች ናቸዉ። ይህ ደግሞ ለብልጠታቸዉ ሳይሆን ለመጥፎ ምርጫቸዉ ጥሩ የሆነ ቅጣት ነዉ። እነዚህ ሰዎች ሙጭጭ ያሉት መራራ ነገር ላይ እና የሚያላምጡትም ችግርን ስለሆነ ህይወታቸዉ ደስታ የራቀዉ ነዉ። ሌሎች ደግሞ አስደሳች የሆነ ምርጫ አላቸዉ። ይህም የሆነዉ ከሽህ መጥፎ ነገሮች ባጋጣሚ የተጣለች መልካም ነገርን ማግኘት ስለሚችሉ ነዉ።


ጎበዝ፣ በብልህነት መንገድ እንጓዝ፣ ብልሆችም እንሁን! :mrgreen:

Meleket
Member
Posts: 1109
Joined: 16 Feb 2018, 05:08

Re: ‘የብልህነት መንገድ’ - ምርጥ መጠሓፍ በምርጥ ተርጓሚ - ይዘቷን እንካችሁ አጣጥሙ!

Post by Meleket » 19 Apr 2019, 10:58

የዛሬዎቹን 10 የብልህነት መንገዶች፡ ከዘመናት በፊት ፊደላትን ቀርጸዉ ላቆዩልን ብልሆቹ አባቶቻችን ክብር የምንጋራቸዉ ናቸዉ። ይህን ስናደርግም የህዝቦችን ስሞታ ሰምታ እንዳልሰማች የምትመስለዉ፣ “ሐቅ፣ ፍትህ፣ ይግባኝ የለለዉ ብይን ወይ ፍርድ ” የሚል ቃል ስትሰማ መስቀል እንዳየ ሰይጣን የሚያደርጋትን :lol: ፣ ርህራሄ ቢሷና ጨካኟ ህወሃት በኤርትራ ህዝብና በወንድሙ የኢትዮጵያ ህዝብ የተባበረ ክንድ የተደሰቀችበትንና ሳትባንን እያዛጋች ‘ትልቁንና ዋና” ምሽጓን አድዋና አኽሱም ላይ፡ ጊዚያዊ ምሽጓንና የመከላከያ ወረዳዋን ደግሞ በራያ በተንቤንና በእንደርታ በማድረግ መቀሌ እንድትሸጎጥ የተገደደችበትን 1ኛ ዓመት የድል በዓል እያከበርን ነዉ። :mrgreen:

141. ከራስህ ድምጽ ጋር ፍቅር እንዳይዝህ። ሌሎችን ሳታስደስት ራስህን ብታስደስት ምን ጥቅም ኣለዉ? ራስን ማርካት የሚያጭደዉ ስድብን ብቻ ነዉ። ራስህን ስታደንቅ በሌሎች ዘንድ ባለእዳ ትሆናለህ። እየተናገሩ ራስን ማድመጥ ደግሞ አስቸጋሪ ነገር ነዉ። ለራስ መናገር እብደት ሲሆን፤ በሌሎች ፊት ራስን ማድመጥ ደግሞ እጥፍ ጊዜ እብደት ነዉ። አንዳንድ ሰዎች “ትክክል ነኝ?” ወይም “ታዉቃለህ?” በሚሉ አረፍተነገሮች ጆሮአችንን ያደነቁራሉ። እነዚህ ሰዎች የሌላዉን ሰው ሙገሳ ወይም ስምምነት ለማግኘት ሲሉ ሰዉን ያበሳጫሉ፤ ይህ ደግሞ የማመዛዘን ችሎታቸዉን ጥያቄ ውስጥ ያስገባዋል። ከንቱ ሰዎችም በገደል ማሚቶ መልክ ማዉራት ይወዳሉ፤ ንግግራቸዉ ያለድጋፍ መቀጠል ስለማይችል ለያንዳንዱ ቃል ቂላቂል የሆነ “ጥሩ ብለሀል” የሚል ማበረታቻን ይፈልጋሉ

142. ባላንጣህ አንተን ቀድሞ መልካም የሆነዉን ነገር በመምረጡ ምክንያት ብቻ እልህ ዉስጥ ገብተህ ስህተት ከሆነ ነገር ጋር ሙጭጭ እንዳትል። ይህ የሆነ እንደሆን ወደ ግብግቡ የምትገባዉ ሲጀመር ተሸንፈህ ሲሆን ውድቀትህ ደግሞ የዉርደት ይሆናል። ባላንጣህ መልካሙን ነገር መምረጡ ብልጠቱን ሲያሳይ ያንተ ከመጥፎዉ ጎን መቆም ደግሞ ደደብነትህን ያሳያል። ከመናገር ይልቅ መተግበር የበለጠ አደጋ ስላለዉ፤ በንግግር ግትር ከሆኑት ይልቅ በተግባር ግትር የሆኑት የበለጠ ለአደጋ የተጋለጡ ናቸዉ። ስድ በሆነ ድንቁርናቸዉ ምክንያት ችኮ ሰዎች ከእዉነት ይልቅ ሀሰትን፤ ከጥቅማቸዉ ይልቅ ተቃርኖን እንዲመርጡ ያደርጋቸዋል። ነገሩ መጀመሪያዉን ስለሚገለጥላቸዉ ወይም በኋላ አቋማቸዉን ስለሚያስተካክሉ አስተዋይ ሰዎች ከስሜታዊነት ይልቅ ለምክንያታዊነት ተገዥ ናቸዉ። ባላንጣ ደግሞ ሞኝ ከሆነ ሞኝነቱ ጎራዉን እንዲቀይር ያደርገዉ እና ከመጀመሪያዉ የባሰ ኣቋም እንዲይዝ ያደርገዋል። እናም መልካሙን ነገር እንዲለቅልህ ብትፈልግ አንተም መልካሙን ያዝ። በዚህ ጊዜ ሞኝነቱ መልካሙን እንዲተዉ ያደርገዉ እና ግትርነቱ ደግሞ ዉድቀቱን ያመጣለታል

143. ስድነትን እንዳያመጣብህ ቄንጠኛ አትሁን። ከልክ በላይ የሆኑ ነገሮች ሁሉ በሰዉ ዘንድ ዝቅተኛ ግምት ያሰጡሀል። ለክብራችን አስጊ የሆነ ነገር ሁሉ እንደሞኝነት ስራ ይቆጠራል። እንቆቅልሽ መጀመሪያ እዉነት የምትመስል የማታለያ ስራ ስትሆን አጓጊ በሆነዉ ዉበቷ ደግሞ ትኩረታችንን ይስባል። ሆኖም ግን በኋላ ሀሰተኝነቷ ሲጋለጥ ዉርደትን ትከናነባለች። እንቆቅልሽ የሆነ ዉበት ሲኖራት፤ በፖለቲካዉ አለም ደግሞ የሀገራት መጥፊያ ልትሆን ትችላለች። በችሎታቸዉ መልካም ነገር ማድረግ የማይችሉት ወይም ችሎታዉ እያላቸዉ ድፍረቱ የሌላቸዉ ሰዎች እንቆቅልሽን ይጠቀማሉ። ይህ ስራቸዉ በሞኞች ዘንድ አድናቆትን ሲያስገኝላቸዉ፤ ለብልሆች ደግሞ ማስጠንቀቂያ ይሆናቸዋል። እንቆቅልሽ የሚያሳየዉ ችግር ያለበትን የማመዛዘን ችሎታ እና የማስተዋል ጉድለትን ነዉ። የተመሰረተዉ ደግሞ በሀሰት ወይም በኢ-እርግጠኝነት ላይ ስለሆነ መልካም ለሆነዉ ነገር ሁሉ ጠንቅ ነዉ።

144. የሌሎችን እቅድ የምታሳካ መስለህ ግባ እና የራስህን እቅድ አሳክተህ ዉጣ። ይህ መርህ የምትፈልገዉን ለማግኘት ፍቱን የሆነ ዘዴ ነዉ። በሰማያዊዉ ነገር እንኳ ክርስቲያናዊ አባቶቻችን ይህን የተቀደሰ ህግ ይመክሩናል። ይህ ጠቃሚ የሆነ ማስመሰያ ሲሆን የሌላዉን ሰዉ መልካም ፈቃድም ያስገኝልናል። ማለትም ለእርሱ ጥቅም የምታስጠብቅ ትመስላለህ ግን ለራስህ ጥቅም ትደክማለህ። ምንም ነገር ግራ በመጋባት እንዳትጀምር፤ በተለይ ደግሞ ጉዳዩ በጣም ብርቱ ከሆነ። መጀመሪያ የሚወጣቸዉ ቃል “እንቢ” የሆኑ ሰወችን ተጠንቀቃቸዉ። በተለይ ደግሞ አንገራጋሪነታቸዉን ቀድመህ የተረዳህ እንደሆን “እሽ” ማለት እዳይከብዳቸዉ የምትፈልገዉን ነገር አትግለፅ። ይህ መርህ ድብቅ አላማወችን ይመለከታል፤ ታላቅ ብልጣብልጥነትንም ይጠይቃል።

145. የቆሰለችዉን እጣትህን ደብቃት፤ አለዚያ ሰዎች ይረጋግጧታል። ስለቁስልህ በፍጹም አታማርር። ክፉ ነገር ሁሌም የሚያነጣጥረዉ ከሚያመን ወይም ከሚያዳክመን ነገር ላይ ነዉ። የተናደድክ ብትመስል ሌሎች የበለጠ እንዲያላግጡብህ ታደርጋቸዋለህ። ክፋት ሁሌም ደካማ ጎንህን ለማግኘት እንደተጣጣረ ነዉ። በአሽሙር የሚያምህን ነገር ለማግኘት ጥረት ያደርጋል፤ ወደ ቁስልህ እንጨት ለመስደድ ደግሞ ሽህ መንገዶችን ያዉቃል። ብልህ ብትሆን ክፉ አሽሙሮችን ትተዋለህ፤ ያለብህን የግል ሆነ የቤተሰብ ችግርም ትደብቃለህ። ለዚህ ምክንያቱ ዕጣ ፋንታ እንኳ ልትመታህ የምትፈለገዉ በጣም ከሚያምህ ቦታ ላይ በመሆኑ እና ሁሌም በቀጥታ የምታመራዉ ወደ ስስ ጎንህ በመሆኑ ነዉ። ስለዚህ የሚያስፈራህን እና የሚያስደስትህን ነገር እንዳትገልፅ ተጠንቀቅ። ይህን የምታደርገዉ ክፉዉ እንዲያልፍልህና መልካሙ ደግሞ እንዲሰነብትልህ ነዉ።

146. በጥልቀት ተመልከት። ነገሮች አብዛኛዉን ጊዜ ከዉጭ እንደሚታዩ ሆነዉ አይገኙም። ለዚህ ነዉ ከቅርፊቱ ዉጭ ምንም የማያየዉ ድንቁርና ወደ ነገሮች ዘልቆ ሲገባ ብዙዉን ጊዜ ድንግርግር ውስጥ የሚገባዉ። በማንኛዉም ስፍራ ማለቂያ በሌለዉ ስድነቱ ብዙ ሞኞችን ከኋላዉ እያስከተለ ቀድሞ የሚደርሰዉ ሀሰት ነዉ። እዉነት ጊዜ ወስዶ እየተሟዘዘ ሁሌም ዘግይቶ በመጨረሻ ነዉ የሚደርሰዉ። አስተዋይ ስዎች ደግሞ ተፈጥሮ ሁለት ጆሮ ስለሰጠቻቸዉ እያመሰገኑ አንደኛዉን ጆሮአቸዉን ለእዉነት ማዳመጫ ያስቀምጡታል። ሀሰት ግብታዊ ስለሆነ ግብታዊ ሰዎች ፈጥነዉ ወደ ሀሰት ይጠጋሉ። ማስተዋል ብልሆች እና አስተዋዮች ያከብሯት ዘንድ ገለል ብላ ትመሽጋለች።

147. የቅርብ ሩቅ አትሁን። የፈለክ ጎበዝ ብትሆን እንኳ አንዳንዴ ምክር ያስፈልግሃል። ሰዎችን የማያዳምጥ ተስፋ የሌለዉ ቂላቂል ነዉ። እጅጉን ራሳችዉን ችለዉ የሚኖሩ ሰዎች እንኳ የጓደኝነት ምክርን ማዳመጥ አለባቸዉ። እንዲሁ ከሁሉ በላይ የሆኑት ባለስልጣናት እንኳ ከሌሎች መማርን ይወዳሉ። አንዳንድ ሰዎች ከሰዉ የራቁ ስለሆኑ ሊታረሙ አይችሉም ሌሎች ደግሞ ማንም ሊደግፋቸዉ ስለማይፈቅድ ይወድቃሉ። እርዳታ ሊገባበት ስለሚችል በጣም ደረቅ የሚባለዉ ሰዉ እንኳ በሩን ለጓደኝነት ምክር ክፍት አድርጎ መተዉ አለበት። ሁላችንም ሊመክረን እና ሊገስፀን ነፃነት ያለዉ ጓደኛ ያስፈልገናል።ለዚህ ሰዉ ይህን ስልጣን የምንሰጠዉ በታማኝነቱና በአስተዋይነቱ ላይ ባለን አመኔታ ከማንኛዉም ሰዉ ላይ መጫን የለብንም። እንደ መስታዉት የሚያገለግለን ታማኝ ሰዉ ካጠገባችን ሊኖር ይገባል። ይህን መስታወት ከተጠቀምንበት ከስህተት ያርመናል

148. በንግግር የተካንክ ሁን። የንግግር ጥበብ የታላቅ ሰዉ ምልክት ነዉ። የትም ቦታ የሚያስፈልግ ነገር ስለሆነ እንደ ንግግር አስተዋይነትን የሚጠይቅ ነገር የለም። እነሆ ሽንፈታችን ሆነ ዉድቀታችን እዚህ ላይ ነዉ። በደንብ ታስቦበት የተጻፈ ንግግር በመሆኑ ደብዳቤ መጻፍ አስተዋይነትን ይጠይቃል፤ ንግግር ደግሞ ችሎታችንን በፍጥነት ግምት ዉስጥ ስለሚያስገባዉ የበለጠ አስተዋይነትን ይጠይቃል። ይህ የሚሆነዉ አዋቂዎች ምላስህን መርምረዉ የብስለትህን ደረጃ ስለሚያደርሱበት ነዉ። “ተናገር እና ትታወቃለህ” ነበር ጠቢቡ ያለዉ። ለአንዳንዶች የንግግር ጥበብ ማለት ምንም ጥበብ ሳይጠቀሙ ንግግርን እንደ ልብስ ለቀቅ አድርጎ በመተዉ የተመሰረተ ነዉ። ይህ አባባል በጓደኞች መሀከል ለሚደረግ ንግግር ሊሰራ ይችላል በታላላቅ ታዳሚወች ዘንድ ግን ንግግር ኮስተር ያለ ሆኖ የተናጋሪዉን ታላቅ ችሎታ ማሳየት አለበት። በተሳካ ሁኔታ ለመነጋገር ራስህን ከአድማጮች ፀባይና እዉቀት አንፃር ማስተካከል አለብህ። ግን የቃላት ሳንሱር የምታካሂድ ሆነህ እንዳትገኝ፤ ይህ የሆነ እንደሆነ እንደ ሰዋስዉ እብድ ወይም ከዚህ ባነሰ ሁኔታ እንደ አረፍተነገር አስጨናቂ ያስቆጥርሃል። እንዲሁ ሌሎች እንዲያርቁህ እና ንግግርህም በሰዎች ዘንድ ተቀባይነትን እንዲያጣ ያደርገዋል። በንግግር ጊዜ ከአንደበተ ርቱእነት ይልቅ፤ የንግግሩ ብስለት የበለጠ ቦታ ኣለዉ።

149. ጥፋትህን በሌላዉ ላይ ማላከክ እወቅበት። ይህ ለአስተዳዳሪወች አስተማማኝ የሆነ ፖሊሲ ሲሆን ከሰዎች ቁጣም የሚጠብቅህ መርህ ነዉ። ክፉዎች እንደሚያስቡት ጥፋትን በሌላዉ ማላከክ እና የሚከተለዉን አሉባልታም እንዲሸከም ማድረግ የሚመነጨዉ ከችሎታ ማነስ ሳይሆን ከታላቅ ችሎታ ነዉ። ሁሉም ነገርህ መልካም ዉጤት ሊኖረዉ አይችልም እንዲሁ ሁሉንም ሰዉ ማስደሰት አትችልም። እናም ማንም ዝናህን በተወሰነ ቢጎዳዉም የእሮሮወች ማከማቻ የሚሆንህ የራሱ ሩጫ እና ጉጉት ጥሩ አላማ የሚያደርገዉ ማላከኪያ ሰዉ ፈልግ።

150. ራስህን መሸጥ እወቅበት። የዉስጥ ችሎታ ብቻ በቂ አይደለም። ሁሉም ሰዉ ነገርን ገለጥ አድርጎ ወይም በጥልቀት አይመለከትም። ሰዎች መንጋዉን ተከትለዉ መግተልተል ይወዳሉ፤ አንዱ ቦታ የሚሄዱትም ሌሎች ሲሄዱ ስላዩ ነዉ። ያንድን ነገር ዋጋ መግለፅ ታላቅ ችሎታን ይጠይቃል። ፍላጎትን ስለሚቀሰቅስ ማሞገስን ልትጠቀም ትችላለህ። ሌላ ጊዜ ደግሞ በጣም ጥሩ ስም ልትሰጠዉ ትችላለህ (ሆኖም ግን ከአስመሳይነት ፍፁም መራቅን አስታዉስ)። ሌላዉ ዘዴ ደግሞ አንድ ነገር የቀረበዉ ለስልጡኖች ብቻ ታስቦ እንደሆነ መግለጽ ነዉ። ይህ ሲሆን ሁሉም ሰዉ ራሱን የሰለጠነ አድርጎ ስለሚቆጥር እና ያልሰለጠነ መሆኑን ከተረዳ ደግሞ ስልጡን ለመሆን በማሰብ በሸቀጡ ላይ ፍላጎት ያድርበታል። የታይታ እና ዋጋ የለሽ ስለሚያስመስላቸዉ ነገሮችን ተራ ወይም ቀላል ናቸዉ እያልክ እንዳታሞግስ።

ጎበዝ፣ በብልህነት መንገድ እንጓዝ፣ ብልሆችም እንሁን! :mrgreen:

Meleket
Member
Posts: 1109
Joined: 16 Feb 2018, 05:08

Re: ‘የብልህነት መንገድ’ - ምርጥ መጠሓፍ በምርጥ ተርጓሚ - ይዘቷን እንካችሁ አጣጥሙ!

Post by Meleket » 20 Apr 2019, 10:48

የዛሬዎቹን አስር የብልህነት መንገዶችን ደግሞ “ትግራይ-ትግርኚ” የተባለዉን አስተሳሰብና የተወላገደ የቦለቲካ ፈሊጥ መቀመቅ ውስጥ ለከተቱት ለጀግኖቹ ላገሬ አርበኞች ክብር እዚህ እንጋራዋለን ይህን ስንካፈልም ‘የትግራይ ትግርኚን ሆነ የዓባይ ትግራይ ማለትም ታላቋ ትግራይ’ የሚል ስስታም የፖለቲካ ቀመር ከከሓዲዋ ሕወሐት ጋር እንጦርጦስ የወረደበትን የኤርትራ ህዝብና የኢትዮጵያ ህዝብም አንደኛ ዓመት የጋራ የድል በዓላቸዉን በሚያከብሩበትና ሲሻቸዉ የዳዊት ልጅ ወደ ቅድስቲቱ ከተማ የገባበትን የሆሳዕና በዓል አሊያም በያሉበት የትንሳኤዉን በዓል በጋራ በማክበር ነዉ!!!! :lol:

151. አርቀህ አስብ፤ ዛሬ ለነገ-ከተቻለ ለብዙ ቀናት ወደፊት። አስተዋይነት የተሞላበት ጥንቃቄ ጊዜን መጠቀም ነዉ። ቀድመዉ ለተዘጋጁት መጥፎ እድል፤ ለተጠነቀቁት ደግሞ አደጋ የሚባል ነገር የለም። ምክንያታዊነትን ለችግር ጊዜ ከመጠቀም ይልቅ ችግሮቹን ለመተንበይ ተጠቀምበት። አስቸጋሪ ነገሮች መለስ ብሎ በብርቱ ማሰብን ይጠይቃሉ። ነገሮች ከተደራረቡብህ በኋላ እንቅልፍ ከማጣት መጀመሪያዉኑ ሳይደራረቡብህ ብትፈታቸዉ የተሻለ ነዉ። አንዳንዶች መጀመሪያ ይተገብሩ እና በኋላ ያስባሉ፤ ይህ ስለወሰዱት እርምጃ ራስን መደለያ ምክንያት ከማፈላለግ ዉጭ አድራጎታቸዉን ተከትለዉ ስለሚመጡት ነገሮች ለማወቅ አይጠቅምም። ሌሎች ደግሞ አንድን ነገር ከማድረጋቸዉ በፊት ሆነ ካደረጉ በኋላ አያስቡም። መልካሙን ነገር ለማግኘት ይጠቅምህ ዘንድ ህይወትህ በሙሉ በማሰብ የተሞላ ሊሆን ይገባል። ለህይወት ነፃነትን የሚያጎናጽፏት አርቆ ማሰብ እና ማሰላሰል ናቸዉ።

152. ታላቅ ወይም ታናሽ በመሆናቸዉ ምክንያት አሳንሰዉ ሊያስገምቱህ ከሚችሉ ሰዎች ጋር አትወዳጅ። አንድ ሰዉ በጣም ላቅ ባለ መጠን ታላቅ ከበሬታን ያገኛል። ይህ ታላቅ ሰዉ የመሪ ተዋናይነቱን ቦታ ይይዝ እና አንተ ግን ከሱ ስር ስለምትሆን ከበሬታን ብታገኝ እንኳ ከፍርፋሪ እና ከትርፍራፊ የበለጠ አይሆንም። ጨረቃ ብቻዋን የሆነች ጊዜ የምትወዳደረዉ ከከዋክብት ጋር ነዉ፤ ሆኖም ግን ፀሀይ በወጣች ጊዜ ጨረቃ ትጠልቃለች ወይም አትወጣም። ስለዚህ አሳንሶ ሊያሳይህ ወደሚችል ሰዉ ሳይሆን የተሻልክ አድርጎ ሊያቀርብህ ወደሚችል ሰዉ ብቻ ተጠጋ። አንድ ሰዉ መጥፎ ጓደኛን በመጠጋት ራሱን ችግር ላይ አለመጣል ብቻ ሳይሆን የራሱን ክብር እየጎዳ የሌላዉን ክብርም ከፍ ከፍ ማድረግ የለበትም። እናም በሙያህ መካን ከፈለግክ ከተካኑት ተጠጋ፤ ከተካንክ ደግሞ ብዙም ያልተካኑትን ተጠጋ።

153. ሌላዉ ትቶት ወደሄደዉ ታላቅ ክፍተት እንዳትገባ ተጠንቀቅ። ይህን ስታደርግ ከበቂ በላይ የሆነ ችሎታ መያዝህን አረጋግጥ። የቀደመህን ሰዉ እኩሌታ ለመሆን እንኳ ችሎታህ ከእርሱ በእጥፍ የበለጠ መሆን አለበት። ሰዎች ከቀደመዉ ሰውየ ይልቅ አንተን እንዲመርጡ ማድረግ ግሩም ዘዴ ነዉ፤ በቀደመህ ሰዉ ጥላ ስር አለመዉደቅ ደግሞ ብልጠትን ይጠይቃል። ሁሌም የድሮዉ የተሻለ ስለሚመስል የቀደመህን ሰዉ ክፍተት መሙላት ከባድ ነዉ። ቀድሞ የተገኘዉ ሰዉ ካንተ የተሻለ አጋጣሚ ስላለዉ አንተ በተመሳሳይ ችሎታ እርሱን ተከትለህ ብትመጣ ከእርሱ ጋር እኩል ልትሆን አትችልም። እናም እርሱን በሰዎች ዘንድ ከያዘዉ ታላቅ ስፍራ ለመፈንቀል ተጨማሪ ችሎታ ያስፈልግሃል

154. ለማፍቀር ሆነ ለማመስገን አትፍጠን። በሰል ያለ ማመዛዘን ነገርን ለማመን ይዘገያል። ሀሰት ነገር የየእለቱ ተራ ነገር ስለሆነ አምኖ መቀበል ብርቅየ ይሁን። ሆኖም ግን ሌሎች በሚናገሩት ነገር ላይ ያለህን ጥርጣሬ በግልጽ አታሳይ። አንድን ሰዉ እንደ ዉሸታም ስትቆጥር ወይም እንደተሸወደ ስታስረዳዉ ንቀት ብቻ ሳይሆን ስድብም ሊሆን እንደሚችል አስተዉል። ከዚህ የበለጠዉ አደጋ ደግሞ ሌሎችን እንደ ሀሰተኛ ስትቆጥር አንተም ሀሰተኛ መሆንህን ልታመለክት እንደምትችል ተረዳ። ሀሰተኛ ሁለት ጊዜ ይቀጣል፤ አንደኛዉ ባለማመኑ ምክንያት ሌላኛዉ ደግሞ ባለመታመኑ። አስተዋዮች ባዳመጡት ነገር ላይ ፍርድን ከመስጠት ይቖጠባሉ። ሌላዉ ምክር ደግሞ ለማፍቀር መፍጠን እንደሌለብን ነዉ። አንዳንድ ሰዎች በቃላት ሲዋሹ ሌሎች ሰወች በተግባር ይዋሻሉ፤ የተግባር ውሸት ደግሞ የበለጠ ጉዳትን ያስከትላል።

155. ስሜትህን መቆጣጠር ቻል። ይህ ለአስተዋዮች ከባድ ባለመሆኑ በተቻለህ መጠን በስሜት ከመገንፈል ይልቅ ብርቱ ማሰላሰልን ተጠቀም። እንደተናደድክ መጀመሪያ ማድረግ ያለብህ ነገር ቢኖር መናደድህን መገንዘብ ነዉ፣ እናም ስሜትህን በመቆጣጠር የበለጠ ስሜታዊ ላለመሆን መጣር አለብህ። ይህን ታላቅ ጥንቃቄ ከወሰድክ ቁጣን በቶሎ ታበርዳለህ። እየሮጥን እያለ ከባድ የሆነዉ ነገር ማቆም መቻል ነዉ። ነገርን ደግሞ ማቆም መቻል ብቻ ሳይሆን በትክክለኛዉ ሰአት ማቆምንም እወቅበት። በእብደት ሰአት መረጋጋት መቻል ስለ ማመዛዘን ችሎታህ ብዙ ይናገራል። ሁሌም ከልክ ያለፈ ስሜታዊነት ከምክንያታዊነት ያርቃል፤ ይህን ከተገነዘብክ ደግሞ በቁጣ አለመጥለቅለቅ ብቻ ሳይሆን ማስተዋልም አይሳንህም። ከስሜታዊነት መልካም ነገርን ማግኘት ብትሻ በአስተዋይነት ተቆጣጠረዉ።

156. ጓደኞችህን ምረጥ። ጓደኞችህ የጓደኝነትን ቦታ መያዝ ያለባቸዉ በፍቅር ብቻ ሳይሆን በማስተዋል ተገምግመዉ እና በክፉ ቀን ተፈትነዉ መሆን አለበት። የህይወት ስኬት መሰረት ቢሆንም ሰዎች ለጓደኛ ምርጫ የሚሰጡት ጥቂት ትኩረትን ነዉ። አንዳንዴ እንዲሁ በመገናኘት ሌላ ጊዜ ደግሞ በአጋጣሚ ጓደኝነት ይመሰረታል። ብልሆች ከቂላቂሎች ጋር እንደማይገጥሙ የታወቀ ስለሆነ ጓደኞቻችን በሰዉ ዘንድ መገምገሚያችን ናቸዉ። ከአንድ ሰዉ ጋር ስትሆን ትደሰታለህ ማለት በራሱ ጓደኝነትን ለመመስረት በቂ ምክንያት አይደለም። አንዳንዴ ያንድን ሰዉ ችሎታ ብዙም ሳንተማመንበት ተጫዋችነቱን ግን እንወድለታለን። አንዳንድ ጓደኝነቶች ተገቢ ሲሆኑ ሌሎች ደግሞ ህገወጦች ናቸዉ። ተገቢ የሆኑት ለደስታ ሲያገለግሉን፤ ህገወጦች ደግሞ ስኬትን ለመጎናጸፍ ይጠቅሙናል። አብዛኛወቹ ጓደኞችህ ወዳጅነታቸዉ ከስኬትህ ጋር ሲሆን ጥቂቶች ደግሞ ያንተነትህ ጓደኞች ናቸዉ። የልብ ጓደኛህ ማስተዋል ከብዙ ባልንጀሮችህ መልካም ምኞት የበለጠ ነዉ። እናም ጓደኞችህን ስትይዛቸዉ በምርጫ እንጅ በአጋጣሚ እንዳይሆን። ብልህ ጓደኞች ችግራችንን ሲያቃልሉልን ቂል ጓደኞች ደግሞ ችግር ይደራርቡብናል። ጓደኝነታችሁን ጠብቀህ ለማቆየት ብትፈልግ ለጓደኛህ ሀብትን አትመኝለት።

157. የሰዎችን ባህሪ መረዳት እንዳያዳግትህ። ምክንያቱም ይህ ቀላል ግን አደገኛ የሆነ ስህተት ስለሆነ ነዉ። በሸቀጡ ከመሸወድ በዋጋዉ መሸወድ የተሻለ ነዉ። ነገሮችን ገለጥ አድርጎ ማየትን የሚያህል ነገር የለም። ነገሮችን እና ሰዎችን ማወቅ ልዩነት ሲኖራቸዉ፤ የሰዎችን ባህሪ ጠለቅ ብሎ መረዳት መቻል እንዲሁ ቀልዳቸዉንም መገንዘብ ታላቅ ጥበብ ነዉ። ስለዚህ የሰዎችን ባህሪ ጠለቅ ብሎ እንደ መጽሀፍት ማጥናት ያስፈልጋል

158. ጓደኞችህን መጠቀም እወቅ። ይህ ሙያን እና አስተዋይነትን ይጠይቃል። አንዳንዶች በቅርብ ሌሎች ደግሞ በሩቅ ሲሆኑ ጠቃሚወች ናቸዉ። እንዲሁ ለፊት ለፊት ንግግር የማይበጅ ጓደኛ በሩቁ ሲላላኩት ጠቃሚ ሊሆን ይችላል። ለዚህ ምክንያቱ መራራቅ በቅርቡ ሆነን ልንቋቋማቸዉ የማንችላቸዉን እክሎች ስለሚያጸዳልን ነዉ። ከጓደኞችህ ደስታን ብቻ ሳይሆን ጥቅምንም መፈለግ አለብህ። ጓደኝነት ሁሉም ነገር በመሆኑ በጎ የሆኑ ነገሮች ሁሉ ያሏቸውን ሶስት ጸባያት ይዟል፤ እነሱም፡ አንድነት፣ መልካምነት እና ሀቅ ናችዉ። ለእዉነተኛ ጓደኝነት ምቹ የሆኑ በጣም ጥቂት ሰዎች ናቸዉ፤ ጓደኛን መምረጥ ያላወቅንበት እንደሆን ደግሞ የእነዚህ ሰዎች ቁጥር የበለጠ አናሳ ይሆንብናል። አዲስ ጓደኛን ከመያዝ ይልቅ ነባር ጓደኛን ጠብቆ ማቆየት የበለጠ ጠቃሚ ነዉ። እስከመጨረሻዉ ሊዘልቁ የሚችሉ ጓደኞችን ፈልግ፤ አዲስ ጓደኛ ስትይዝ ደግሞ አንድ ቀን የረዢም ጊዜ ጓደኛ ሊሆን እንደሚችል እያሰብክ ተደሰት። ከሁሉም ላቅ ያሉት ጓደኞች በደንብ በሰል ያሉት እና ከእኛ ጋርም ብዙ ነገርን አብረዉ ያሳለፉት ናቸዉ። ጓደኝነት ያልታከለባት ሕይወት ምድረ በዳ ናት። ጓደኝነት መልካሙን ነገር ሲያበዛልን መከራን ደግሞ ይጋራልናል። ጓደኝነት ለመጥፎ እጣ ፈንታ ልዩ መድሃኒት ስትሆን ለመንፈሳችን ደግሞ ጣፋጭ እፎይታን ትሰጣለች

159. ቂሎችን መታገስ ቻል። ማወቅ ትእግስታቸዉን ስላጠበበዉ ጠቢቦች ታጋሽነታቸዉ ዝቅተኛ ነዉ። ብዙ ያወቀን ማርካት በጣም አስቸጋሪ ነዉ። ፈላስፋዉ ኢፒክቴተስ እንደሚያስረዳን ከሆነ ጠቃሚዉ የህይወት ህግ ሁሉንም ነገሮች መታገስ መቻል ነዉ። እንዲያዉም ጨምሮ እንዳስረዳዉ ከሆነ ይህ ህግ የጥበብ ግማሹ ክፍል ነዉ። ጅላጅልነትን መቋቋም ታላቅ ትእግስትን ይጠይቃል። አንዳንዴ በጣም የሚያሰቃዩን ሰዎች እጅጉን ጥገኛ የሆናቸዉ ሰዎች ናቸዉ። ይህ ደግሞ ራስ መግዛት ያስተምረናል። ታጋሽነት መለኪያ የሌለዉ የዉስጥ ሰላምን ያላብሳል። ይህም በምድር ላይ እንደመባረክ ይቆጠራል። እናም ሌሎችን መታገስ የማያዉቅበት ግለሰብ ለብቻዉ ሊኖር ይገባዋል፤ በርግጥ ይህ እንኳ ሊሆን የሚችለዉ ሰውየዉ እራሱን እንኳ መታገስ የሚችል ከሆነ ነዉ

160. ንግግርህ በማስተዋል ይሁን። ባላንጣዎችህን ስታናግር በጥንቃቄ፤ ለተቀሩት ሰዎች ደግሞ በጨዋነት መሆን አለበት። አንድን ቃል ለመትፋት ሁሌም ጊዜ አለህ መልሶ ለመዋጥ ግን ጊዜ የለህም። ጥቂት ቃላት በተናገርክ ቁጥር ጥቂት ክሶች ስለሚቀርቡብህ ንግግርህ እንደ ወንጌል ይሁን። ጠቃሚ ለሆነዉ ነገር ስትዘጋጅ ጠቃሚ ባልሆነዉ ነገር ላይ ተለማመድ። ከንግግር መቆጠብ የመለኮታዊነት ባህሪ አለዉ። ለመናገር ፈጣን የሆነ ሰዉ ደግሞ ተንደፋድፎ ይወድቃል

ጎበዝ፣ በብልህነት መንገድ እንጓዝ፣ ብልሆችም እንሁን! :mrgreen:

Meleket
Member
Posts: 1109
Joined: 16 Feb 2018, 05:08

Re: ‘የብልህነት መንገድ’ - ምርጥ መጠሓፍ በምርጥ ተርጓሚ - ይዘቷን እንካችሁ አጣጥሙ!

Post by Meleket » 23 Apr 2019, 10:58

ጎበዝ የዛሬዎቹን አስር የብልህነት መንገዶች፡ ዘራቸው ሆነ ዜግነታቸዉ፣ የፖለቲካ አላማቸዉ ሆነ ሃይማኖታቸዉ ምንም ይሁን ምን ነገር ግን በመላው ዓለምና በየአካባቢያቸዉ ጭቆናን፣ አድልዎን፣ ዘረኝነትን እየተጠየፉ “ግሪካዊ አይሁዳዊ” ብለዉ ሳይለያዩ ለፍቅር ለሰላም ለወንድማማችነት ሌተቀን ለሚተጉት አካሎች ሁሉ ክብር እዚህ እንጋራለን። ይህን ስናደርግ ደግሞ የኤርትራ ህዝብና የኢትዮጵያ ህዝብ በፊታቸዉ ተጋርጦ ከነበረው ጥልቅ ጉድጓድ ላይ የሰላም ድልድይን የገነቡበትን:lol: “ድልድይ አፍራሾችንም” እየነቀሱና እየመነጠሩ ጥጋቸዉንና እንዲይዙ፡ ልካቸዉንም እንዲያዉቁ፡ ለሕግ የበላይነትም መገዛት እንዳለባቸዉ ቁልጭ አድርገዉ ያስተማሩበትን፡ የሁለቱን ህዝቦች 1ኛ ዓመት የድል ጉዞም በጋራና በመረዳዳት መንፈስ እየተጓዝን ነዉ:mrgreen:

161. ጥቃቅን ድክመቶችን አስወግዳቸዉ። በጣም ላቅ ያለ የሚባለዉ ሰው እንኳ ጥቃቅን ጉድለቶች አሉበት። እናም እንዲህ አይነቱ ሰዉ ከድክመቶቹ ጋር ተቆራኝቶ ወይም ደባል ሆኖ ይኖራል። የማስተዋል ጉድለቶች ያሉን እንደሆን ደግሞ በጣም ብርቱ ናቸዉ ወይም ሰዉ በቀላሉ ያስተዉላቸዋል። እነዚህ ድክመቶች ሊኖሩ የቻሉት ደግሞ ባለቤቱ ስለሚወዳቸዉ እንጅ ስለማያዉቃቸዉ አይደለም። ይህ ደግሞ ሁለት ስህተት እንደመስራት ይቆጠራል፤ ለዚህ ምክንያቱ ባለቤቱ ምክንያታዊ ያልሆነ ወዳጅነት የያዘዉ ከተሳሳተ ነገር ጋር በመሆኑ ነዉ። ጥቃቅን እንከኖች ላቅ ያለ ነገር ላይ እንደተሰነቀሩ ጉድፎች ይቆጠራሉ። እነዚህ ነገሮች ሰዎችን ቢያርቁም ለባለቤቱ የቁንጅና ምልክት መስለዉ ይታዩታል። እነዚህን እንከኖች ማጥፋት እራስህን ለማሸነፍ እና ተሰጥዖወችህንም የበለጠ ለማጉላት ጥሩ አጋጣሚ ሊሆንህ ይችላል

162. ክፋተኞችን እና ምቀኞችን አሸንፋቸዉ። ምንም ትህትና ጠቃሚ ቢሆንም እነዚህን ሰዎች ንቆ ማለፍ ብቻ በቂ አይደለም። ስላንተ መጥፎ ነገር ስለሚያወራ ሰዉ መልካም ማዉራትን የመሰለ የተከበረ ተግባር የለም። በችሎታ ሆነ በብቃት ቅናተኞችን እንደማሰቃየት የመሰለ በቀል የለም። እያንዳንዱ ስኬትህ መጥፎ ነገርን ለሚመኙልህ ሰዎች ስቃይ ሲሆን፤ ለባላንጣወችህ ደግሞ የምትጎናጸፈዉ ክብር ሲኦል ይሆንባቸዋል። ስኬትን ወደ መርዝነት መለወጥ፣ ይህ ነዉ እንግዲህ ታላቁ ቅጣት። ቅናተኛ የሚሞተዉ አንዴ ሳይሆን በባላንጣዉ ስኬት ቁጥር ነዉ። የቅናተኛዉ ባላንጣ ዘላቂ ዝናን አገኘ ማለት ለቅናተኛዉ ዘላለማዊ ስቃይ ማለት ነዉ። ባላንጣዉ በክብር ለዘላለም ሲኖር፤ ቅናተኛ ደግሞ ከቅጣቱ ጋር ዝንተ አለም ይኖራል። የዝና ጥሩምባ ለአንዱ ዘላለማዊነትን ስትለፍ፤ ቅናተኛን ደግሞ በጭንቀት ተፈጥርቆ ይሞት ዘንድ ትፈርድበታለች።

163. ለእድለ ቢሶች ያለህ ርህራሄ ከእድለ ቢሶች እንዳይጨምርህ ይሁን። የአንደኛዉ መጥፎ እድል የሌላኛዉ መልካም እድል ሊሆን ይችላል። ምክንያቱም ብዙ ሰዎች ለመጥፎ እድል ካልተዳረጉ በስተቀር አንድ ሰው እድለኛ ሊሆን ስለማይችል ነዉ። ደስተኛ ያልሆኑ ሰዎች አብዛኛዉን ጊዜ የሰወችን ርህራሄ ይስባሉ። ለዚህም ነዉ እጣ ፋንታ የረገመቻቸዉን ሰዎች ርባና በሌለዉ ትብብር ልንክሳቸዉ የምናስብ። በጣም ተመችቶት እያለ ሰዉ ሁሉ የጠላዉ ግለሰብ በዉድቀቱ ጊዜ የሁሉንም ሀዘን ይስባል። ለዚህ ምክንያቱ ውድቀቱ በቀልን ወደ ርህራሄ ስለሚለዉጣት ነዉ። ብልጥ የሆነ እጣ ፋንታ ካርታዋን እንዴት እንደምትሸከሽክ ይወቅ። አንዳንድ ሰዎች መልካም እድል ላይ ያሉ ሰዎችን ያርቋቸው እና ሰዎቹ መጥፎ እድል ሲያጋጥማቸዉ ይጠጓቸዋል። ይህ ተግባር ምግባረ ጨዋነትን ቢያመለክትም የማስተዋል ስራ ግን አይደለም።

164. የአንድ ነገር ስኬታማነት ወይም በሰዎች ዘንድ ተቀባይነት ስለማግኘቱ ፈትነዉ። ይህ መርህ አንድን ነገር ወደ መልካም ፍፃሜ ለማድረስ እና በያዝከዉ ተግባር መግፋት ወይም ማቆም እንዳለብህ ለመወሰን ይረዳሃል። ስለዚህ አስተዋይ ሰዉ የሰዎችን ፍላጎት በመፈተን አያያዙን ይገነዘባል። ይህ ነገር ለመጠየቅ፤ ለመመኘት፤ ሆነ ለማስተዳደር የሚጠቅም ታላቅ መርህ ነዉ።

165. ጦርነትህ የጨዋ ይሁን። ጠቢብ ሰዉ ጦርነት ሊዘምት ቢችልም የሚዘምትበት ጦርነት ግን የዉርደት ነገር አይደለም። ጸባይህ ማንፀባረቅ ያለበት አንተነትህን እንጅ የሌሎችን ተጽዕኖ መሆን የለበትም። ባላንጣዎችህን በጨዋነት መቅረብ የሚያስመሰግን ተግባር ነዉ። ስትዋጋ ደግሞ ዉጊያህ የሀይል ሚዛንን ወዳንተ ለመቀልበስ ብቻ ሳይሆን ታላቅ ተዋጊ መሆንህንም ለማሳየት ጭምር መሆን አለበት። ጨዋነት በጎደለዉ መንገድ ማሸነፍ እንደ ሽንፈት ይቆጠራል። መልካም ሰዉ ወዳጅን ሲጣሉ የሚያገኟቸዉን አይነት የተከለከሉ መሳሪያወችን ለግጥሚያ አይጠቀምም። ምንም ወዳጅነትህ በጥላቻ ቢፈርስም ጓደኝነት የጣለብህን እምነት ለራስህ ጥቅም ማዋል የለብህም። ከሀዲነት የተቀላቀለበት ነገር ሁሉ ለስምህ እጅግ መጥፎ ነዉ። ጨዋ ሰዎች አንዳች ታህል የወራዳነት ተግባር አይገኝባቸዉም። እንዲሁ ጨዋነት መጥፎነትን ይጠየፋል። እነሆ ጨዋነት፤ ለጋስነት ሆነ ታማኝነት በአለሙ ላይ ሁሉ ቢጠፋ እንኳ አንተ ጋር ግን እንደሚገኙ አዉቀህ ልትኩራራ ይገባል።

166. የወሬን እና የተግባርን ሰዉ ለይተህ እወቅ። ይህ ነገር አንተነትህን ወይም ስልጣንህን ብለዉ በሚፈልጉህ ጓደኞችህ መካከል እንዳለዉ ልዩነት ረቂቅ የሆነ ነዉ። መጥፎ ተግባር ባይከተላቸዉም እንኳ መጥፎ ቃላት መጥፎ ከመሆን አያመልጡም። ሆኖም ግን መጥፎ ቃላትን ባትናገር እንኳ መጥፎ ነገር ከሰራህ ነገሩ የበለጠ ክፉ ነዉ። አንድ ሰዉ ትንፋሽ ብቻ ስለሆኑ ቃላትን አይመገብም፤ ጮሌነት የታከለባቸዉ ማጭበርበሪያዎች በመሆናቸዉ ምክንያት ደግሞ በትህትና ብቻ አይኖርም። ወፎችን በመስታወት ተጠቅሞ መያዝ አደገኛ ወጥመድ ነዉ። በባዶ ቃላት ሚረኩ ቂሎች ብቻ ናቸዉ። እናም ቃላት ዋጋቸዉን ጠብቀዉ እንዲቆዩ ከተፈለገ በተግባር መደገፍ አለባቸዉ። ከቅጠል ውጭ ፍሬ የማይሰጡ ዛፎች ልብም ስለሌላቸዉ አንድ ሰዉ የትኛዉ ጠቃሚ የትኛዉ ደግሞ ለጥላነት እንደሚያገለግል መለየት አለበት።

167. ራስህን በራስህ መረዳት ቻል። በክፉ ቀን ከጠንካራ ልብ የበለጠ ወዳጅ አይገኝም። ልብ ከደከመች ደግሞ ባቅራቢያዋ ባሉት አካላት መረዳት አለባት። በራሳቸዉ የሚተማመኑ ሰዎች ጭንቀትን በደንብ ይቋቋማሉ። ለመጥፎ እድል እንዳትሸነፍላት፤ አለዚያ በጣም ትፀናብሃለች። አንዳንድ ሰዎች ሸክማቸዉን ማቅለል ስለማይችሉበት መከራቸዉ እጥፍ እጅ ይጨምራል። እራሱን የሚያውቅ ሰው ያሉበትን ድክመቶች በማሰላሰል ያሸንፋቸዋል። አስተዋዮች ሁሉንም ያሸንፋሉ - ከዋክብትን እንኳ ሳይቀር

168. የጅላጅልነት አጋንንት እንዳትሆን ተጠንቀቅ። ይህ አዉሬነት የሚመነጨዉ፤ ግብዞችን፣ አይን አዉጣዎችን፣ እልኸኞችን፣ ግልፍተኞችን፣ ትምክህተኞችን፣ አባካኞችን፣ የማይረቡትን፣ ልከበር ባዮችን . . . እና የመሳሰሉትን የስድነት ደቀመዛሙርት ነዉ። ታላቅ የሆነዉን ውበት ስለሚጻረር የመንፈስ አዉሬነት ከስጋዊ አዉሬነት የበለጠ ነዉ። ሆኖም ግን ይሄንን ሁሉ መጃጃል ማን ሊያርመዉ ይችላል? እነሆ ማስተዋል በጠፋበት ምክር እና እርማት ቦታ የላቸዉም። እንዲህ አይነት ሰዎች በአሽሙር እየተሰደቡ የተጨበጨበላቸዉ ይመስላቸዋል።

169. አንዴ እንኳ አለመሳት መቶ ጊዜ ኢላማን ከምታት የተሻለ ነዉ።ግርዶሽ ያጠላበት ጊዜ ሁሉም ወደ ፀሀይ ቢመለከትም፤ በደንብ እያበራች እያለ ምንም ቀና ብሎ ሊመለከታት አይደፍርም። ስዶች በጣም ብዙ ከሆነዉ ስኬትህ ይልቅ አንዷ ድክመትህ ላይ ሙጭጭ ይላሉ። መጥፎ ነገሮች በጣም ይታወቁ እና ከመልካም ነገር የበለጠ አሉባልታን ይጭራሉ። ብዙ ሰዎች ሀጢኣት እስኪሰሩ ድረስ በሰዉ ዘንድ አይታወቁም፤ ሀጢአት ከፈጸሙ በኋላ ግን እነሆ ስኬታቸዉ ሁሉ ተደምሮ እንኳ ቅንጣት ታህል ስህተታቸዉን ለመሸፈን አይበቃም። ስለዚህ ክፋት ሁሉንም ስህተቶችህን እንደሚያይ እና በጎ ነገሮችህ ላይ ደግሞ ፊቱን እንደሚያዞር ልብ በል

170. ለሁሉም ነገር መጠባበቂያ ይኑርህ። ይህን ብታደርግ ተፈላጊነትህን ማስጠበቅ ይቻልሃል። ሁሉንም ክህሎቶችህን ሆነ ሀይልህን ባንዴ አትጠቀም። በእዉቀት እንኳ መጠባበቂያ ሊኖርህ ይገባል፤ ይህን ብታደርግ ልቀትህ እጥፍ እጅ ይሆናል። ሁሌም አደጋ ባጋጠመህ ጊዜ የሚደርስልህ መጠባበቂያ ሊኖርህ ይገባል። በተገቢዉ አጋጣሚ የሚገኝ ድነት፤ ከግልጽ ማጥቃት ይበልጥ ዋጋ ያለዉ እና የተከበረ ነገር ነዉ። የአስተዋይነት እንቅስቃሴም ከአደጋ ርቆ ነዉ። እዚህ ላይ ግማሹ ከሙሉዉ ይበልጣል የሚባለዉን ለየት ያለ አባባል መቀበል እንችላለን።

ጎበዝ፣ በብልህነት መንገድ እንጓዝ፣ ብልሆችም እንሁን!
:mrgreen:

Meleket
Member
Posts: 1109
Joined: 16 Feb 2018, 05:08

Re: ‘የብልህነት መንገድ’ - ምርጥ መጠሓፍ በምርጥ ተርጓሚ - ይዘቷን እንካችሁ አጣጥሙ!

Post by Meleket » 25 Apr 2019, 09:16

የዛሬ 10 የብልህነት መንገዶች ደግሞ የምንጋራዉ ልክ እንደ 'እንትና' በተግባር የተከታዮቻቸዉን፡ የዜጎቻቸዉንና በስራቸዉ ያሉ የሰራተኞቻቸዉን፡ እግር ለሚያጥቡ ለተከታዮቸ፣ ለዜጎቸ፣ በስሬ ላሉ ሰራተኞች ምን ላድርግላቸዉ በምን ላግዛቸዉ በምንስ አርአያ ልሁናቸዉ ወዘተ እያሉ ለሚያስቡትና በተግባርም ይህንን ለሚያራምዱ መሪዎችና አለቆች ክብር እዚህ እንጋራቸዋለን። :lol: ይህንን ስናደርግም እንደ ይሁዳ ለገንዘብና ለግዚያዊና ቁሳዊ ብልጽግና ብለዉ ኢሰብኣዊ ተግባር በመፈጸም አጋሮቻቸዉንና ወንድሞቻቸዉን እንደሸጡትና እንደከዱት ሕወሓቶች፡ መታሰሪያ ወይ መታ-- ገመዳቸዉን ይዘዉ መቐሌ የተወሸቁበትን 1 ዓመት የኤርትራ ህዝብና የኢትዮጵያ ህዝብ የድል በዓል በጋራ እያከበርን ነዉ።

171. በሌሎች ሰዎች ላይ ያለህን ዉለታ አታባክነዉ። ጠቃሚ ጓደኞችን ለወሳኝ ጊዜ አስቀምጣቸዉ። ስለዚህ እዉቂያህን እና የሰዎችን መልካም ፈቃድ ለጥቃቅን ነገሮች አታዉል። አደጋ ዉስጥ እስካልገባህ ድረስ ጠመንጃህ እንዳይጮህ። ምክንያቱም ብዙውን በጥቂት ከለወጥከዉ በኋላ ምን ይተርፍሃል? ከሰዎች እርዳታ እና ትብብር ይበልጥ ዉድ የሆነ አንዳች ነገር የለም። ሰዎች ሊሰሩህ ወይም ሲያፈርሱህ ይችላሉ፤ ብልጠትን እንኳ ሊሰጡህ ሆነ ሊነሱህ ይቻላቸዋል። ጠቢብ ሰዎች ምንም የተፈጥሮ እና የዝናን ይሁንታ ቢያገኙም በእጣ ፋንታ ዘንድ ግን የተጠሉ ናቸዉ። በነገሮች ከመተማመን ይልቅ በሰዎች መተማመን ይበልጣል።

172. ምንም የሚያጣዉ ነገር ከሌለዉ ሰው ጋር አትወዳደር። እንዲህ አይነቱ ዉድድር እኩልነት የሰፈነበት አይደለም። ለዚህ ምክንያቱ አንደኛዉ ተወዳዳሪ መድረክ የገባዉ ሁሉንም ነገር አጥቶ ያለምንም ፍርሀት በመሆኑ ነዉ። ይህ ሰዉ ሁሉንም ነገር በማጣቱ እና በተጨማሪ የሚያጣዉ አንዳች ነገር ስለሌለ ያገኘዉን ነገር ሁሉ ፊት ለፊት ለመጋፈጥ ዝግጁ ነዉ። እናም መልካም ስምህን በእንዲህ አይነት ሰዉ ምክንያት እንዳታጣዉ ተጠንቀቅ። ስምህን ለመገንባት አመታትን ቢወስድብህም ከመቅጽበት ልታጣት ትችላለህ፤ ያዉም እዚህ ግባ በማይባል ጉዳይ። አንዲት ፍሬ ነዉር ብዙ አመታት የተደከመለትን ክብር ልታደበዝዝ ትችላለች። አስተዋይ ሰዉ እፊቱ የተደቀነዉን አደጋ ይረዳል። ይህ ሰዉ ስሙን የሚያጎድፈዉን ነገር ያዉቃል፤ ነገርን ሲቀርብ ደግሞ በማስተዋል እና በእርጋታ በመሆኑ ማስተዋል መልካም ስሙን ታድንለት ዘንድ በቂ ጊዜ ይሰጣታል። ምንም ቢያሸንፉ እንኳ ራስን ለሽንፈት በማጋለጥ የታጣዉን ነገር ማስመለስ አይችልም።

173. ከሌሎች ጋር ባለህ መስተጋብር ከመስታዉት የተሰራህ አትሁን። አንዳንድ ሰዎች በቶሎ ይሰበሩ እና ስስነታቸዉን ያሳያሉ። እነዚህ ሰዎች በማማረር ይሞሉና ሰዎችን ያበሳጫሉ። እንዲሁ ከአይን ብሌን የበለጠ ቁጡ በመሆናቸዉ በቀልድ ሆነ በቅንነት ሊነኳቸዉ አይቻልም። ጥቃቅን ነገር ስለሚያበሳጫቸዉ እነዚህን ሰዎች ለማናደድ ብርቱ ነገር አያስፈልግም። እናም ከእንዲህ አይነት ሰዎች ጋር መስተጋብር የሚያደርግ እጅግ ጥንቁቅ ሊሆን ይገባዋል። ሰዎቹ ራስ ወዳድ እና የስሜት ተገዥ ሲሆኑ በዚህ ድክመታቸዉ ምክንያት ደግሞ ሁሉንም ነገር መስዋእት የሚያደርጉ የአጉል ከበሬታ አምላኪዎች ናቸዉ።

174. በችኮላ አትኑር። ነገሮችን በየስፍራቸዉ ማደራጀት ከቻልህ በነሱ መደሰትን ትማራለህ። ብዙ ሰዎች እድላቸዉን ሁሉ ከህይወታቸዉ በፊት ጨርሰዉት ያርፋሉ። እነዚህ ሰዎች መደሰት ስለማይችሉ ሀሴትን ያጣሉ። አስደሳች የሆነዉን ጊዜያቸዉን ሁሉ ያባክኑ እና አመሻሽተዉ ወዳለፈዉ ነገር መመለስ ይከጅላቸዋል። ለነዚህ ሰዎች ጊዜ ዝግተኛ ስለሚሆንባቸዉ፤ በችኩል ባህሪያቸዉ ሊያፈጥኑት ይፈልጋሉ። እንዲሁ ሕይወታቸውን በሙሉ ሊፈጽሙት የማይችሉትን ነገር በአንድ ቀን ካልጨረስን ይላሉ። ስኬታቸውን እያሰቡም አመታትን ወደፊት ይጓዛሉ፤ ፈጣን በመሆናቸዉ ምክንያት ደግሞ ሁሉንም ነገር ባጭር ጊዜ ይፈጽሙታል። እዉቀትን ስትመኝ እንኳ ባታዉቃቸዉ የሚሻሉ ነገሮችን እንዳታዉቅ ይረዳህ ዘንድ በልክ መሆን አለበት። የምትደሰትባቸዉ ቀናት ከእድሜህ ያጠሩ በመሆናቸዉ ስትደሰት በቀስታ ይሁን፤ ስራህን ስትፈጽም ግን በፍጥነት። ለዚህ ምክንያቱ የእለቱ ስራ ሲጠናቀቅ በደስታ ቢሆንም የእለቱ ሀሴት የሚጠናቀቀዉ ግን በተመሳሳይ መልክ ስላልሆነ ነዉ።

175. ቁም ነገረኛ ሰዉ ሁን። ቁም ነገረኛ ብትሆን በማይረቡ ሰዎች አትደሰትም። ቁም ነገር ላይ ያልተመሰረተ ታላቅነት ሀሴት የራቀዉ ነዉ። በትክክል እዉነተኛ የሆኑት ሰዎች ቁጥር ከዉጭ ሲታዩ እውነተኛ ከሚመስሉት ሰዎች ያነሰ ነዉ።የማይሆነዉን የሚያቅዱ ከዚያም ሀሰትን የሚወልዱ አስመሳዮች አሉ። እነዚህን ሰዎች የሚያበረታቱ ሌሎች ሰዎች ደግሞ በተግባራቸዉ እያበረታቱ አነስተኛ ከሆነዉ ከእዉነተኛ ነገር ይልቅ የማይጨበጠዉን የሀሰት ነገር ይመርጣሉ። በሀቅ ላይ ያልተመሰረተ ስለሆነ የእነዚህ ሰዎች አምሮት ሁሉ ፍፃሜዉ ከንቱ ነዉ። ትርፍን የሚያስገኝ የቁም ነገር ስራ ሲሆን፤ እዉነተኛ ዝናን የሚያላብስ ደግሞ እዉነተኛ ተግባር ብቻ ነዉ። አንድ የሀሰት ተግባር ሌላ የሀሰት ተግባርን ስለሚወልድ፤ በሀሰት የተገነባ ነገር ሁሉ ብዙም ሳይቆይ ይፈራርሳል። መሰረት የሌላቸዉ ነገሮች ሁሉ እድሜ አይኖራቸዉም። ብዙ ተስፋ የሚሰጥ ጥርጣሬ ዉስጥ እንደሚከተን ሁሉ ከልክ በላይ ማስረጃ የሚያቀርበዉን ደግሞ አሌ እንለዋለን።

176. ወይ እወቅ ካላወቅክ ደግሞ የሚያዉቅን አዳምጥ። ለመኖር የራሳችን ወይም የሌላ ሰው እውቀት ያስፈልገናል። ሆኖም ግን ብዙ ሰዎች ስለምንም ነገር አለማወቃቸዉን አያዉቁም፤ ሌሎች ደግሞ ሳያዉቁ የሚያዉቁ ይመስላቸዋል። እነሆ የጅልነት ነቀርሳ መድሀኒት የለዉም። ደንቆሮወች እራሳቸዉን ስለማያዉቁ የጎደላቸዉን ነገር ለማፈላለግ አይወጡም። አንዳንዶች ደግሞ ብልህ መሆናቸዉን ቢያውቁ ኖሮ ጠቢብ ይሆኑ ነበር። የማስተዋል ጠቢቦች በጣም ብርቅየ ቢሆኑም የሚያማክራቸዉ ስለሌለ ስራ ፈትተዉ ይዉላሉ። ምክርን መጠየቅ ክብርን አይጎዳም፤ እዉቀትህንም ጥርጣሬ ዉስጥ አይከተዉም። ይልቅስ ዝናህን ያሳድግልሃል። እናም መጥፎ እድልን ለመዋጋት ምክንያታዊ ምክርን ተቀበል

177. አንተም ከሌሎች ጋር በጣም አትላመድ እነሱም ካንተ ጋር እንዲላመዱ አትፍቀድላቸዉ። ከሰዉ ጋር በጣም የተዋወቅክ እንደሆነ ያለህን ክብር እና ታላቅነት ታጣለህ። ከዋክብት እኛን ባለመታከካቸዉ ምክንያት ዉበታቸዉን ጠብቀዉ መቆየት ተችሏቸዋል። መለኮት ክብርን ይፈልጋል፤ መተዋወቅ ደግሞ መናናቅን ይወልዳል። ሰብአዊ የሆኑ ነገሮች ሁሉ በጣም ጥቅም ላይ የዋሉ እንደሆን በሰው ዘንድ ያላቸዉ ክብር ይቀንሳል። ለዚህ ምክንያቱ ቁጥብነት የደበቃቸዉን ጉድለቶች ቅርርብ ስለሚገልጣቸዉ ነዉ። ስለዚህ ከማንም ጋር እጅጉን አትቀራረብ። በጣም መቀራረብ ከበላዮችህ ጋር ሲሆን አደገኛ ነዉ፤ ከበታቾችህ ጋር የሆነ እንደሆነ ደግሞ ነዉር ነዉ። በድንቁርናቸዉ ምክንያት ባለጌዎች ስለሆኑ ከመንጋወች ጋር አትቀራረብ። መንጋወች ዉለታ እየዋልክላቸዉ መሆኑን ስለማይረዱ የምታደርግላቸውን ነገር እንደ ግዴታህ አድርገዉ ይወስዱታል። በጣም መተዋወቅ እና ስድነት ኩታ ገጠም ናቸዉ

178. በተለይ ጠንካራ ልብ ካለህ ልብህን ተማመንበት። በጣም አስፈላጊ የሆኑ ነገሮችን መለየት ስለሚችል ልብህን አትቃረነዉ። ልባችን አንደ ቤት በቀል ጠቢብ ይቆጠራል። ብዙወች የጠፉት በሚፈሩት ነገር ነዉ፤ ሆኖም ግን መከላከያ እርምጃ ሳይወስዱ መፍራት ብቻ ምን ጥቅም አለዉ? አንዳንዶች ቀድሞ ነገርን የሚተነብይላቸዉ እና ማስጠንቀቂያ እየሰጠ ከዉድቀት የሚያድናቸዉ ተፈጥሮ የቸረቻቸዉ ታማኝ ልብ አላቸዉ። ወደ ችግር መገስገስ ምክንያታዊነት አይደለም፤ መገስገስ ካለብህ ግን ችግሩን ግማሽ መንገድ ላይ ለመግጠም እና ድል ለመንሳት መሆን አለበት።

179. ቁጥብነት የችሎታ መገለጫ ነዉ። ቁጥብነት የሌላት ልብ እንዳልታሸገ ደብዳቤ ትቆጠራለች። ሚስጥርህን የምትደብቅበት ጥልቀት ይኑርህ፤ ይህ ደግሞ ነገሮች የሚሰምጡበትን እና የሚደበቁበትን ሰርጦች እና ዳርቻወች ያስገኝልሀል። ቁጥብነት ራስን ከማሸነፍ የሚመጣ በመሆኑ ቁጥብነት እዉነተኛ ድል ነዉ። ራስህን ለገለፅክለት ሰዉ ሁሉ ግብርን መክፈል ይጠበቅብሃል። የማስተዋል ጤንነት የሚገለጸዉ በዉስጣዊ ሰላም ነዉ። ቁጥብነት ችግር ላይ የሚወድቀዉ በሌሎች ጥቃት ነዉ። ሰዎች የተቃረኑህ ጊዜ ቁጥብነትህን ግልፍት ዉስጥ ይከቷታል፤ አሽሙርን በመጠቀም ደግሞ ብልጥ የሚባለዉን ሰዉ እንኳ የዉስጡን እንዲገልጽ ያደርጉታል። እናም የምታደርገዉን አትናገር፤ አደርጋለሁ ያልከዉንም አታድርግ።

180. ጠላትህ በሚያደርገዉ ነገር እንዳትሸወድ ሞኝ ጥቅሙን ስለማይረዳ ብልህ ያደርጋል ብሎ የሚጠብቀዉን ነገር አያደርግም። ብልጥ ደግሞ ያደርጋል የተባለዉን የማያደርገዉ አላማዉ እንዳይታወቅበት ከሰዎች ለመሰወር ነዉ። ሁሌም ነገሮችን ከሁለት አቅጣጫ ተመልከታቸዉ፤ ኋላ እና ፊታቸዉንም አስተዉል። በነገሮች ላይ ገለልተኛ ለመሆን ሞክር። ማሰላሰል ያለብህ ሊሆን ይችላል ስለምትለዉ ሳይሆን ስለሚሆነዉ መሆን አለበት

ጎበዝ፣ በብልህነት መንገድ እንጓዝ፣ ብልሆችም እንሁን!
:mrgreen:

Meleket
Member
Posts: 1109
Joined: 16 Feb 2018, 05:08

Re: ‘የብልህነት መንገድ’ - ምርጥ መጠሓፍ በምርጥ ተርጓሚ - ይዘቷን እንካችሁ አጣጥሙ!

Post by Meleket » 27 Apr 2019, 03:35

የዛሬዎቹን 10 የብልህነት መንገዶች የፈለገዉን ያህል ግዙፍ በደል፣ ጭቆና፣ እንግልት፣ አድልዎና በምድር ዉስጥ አሉ የተባሉ ስቃዮችን ሁሉ ተቋቁመዉ ተስፋ ሳይቆርጡ በድልና በትንሳኤ አሸብርቀዉ፤ ልክ እንደ ‘እንትና’ ከሞት ጋር ተጋፍጠዉ ሞትንም ድል ነስተዉ፡ የሓቅንና የእውነትን አሸናፊነት ለሚያበስሩ የሰዉ ልጆች ሁሉ ክብር እዚህ እንጋራቸዋለን። :lol: ይህንም ስናደርግ የኤርትራ ህዝብና የኢትዮጵያ ህዝብ ለዘመናት ካሳለፉት እንግልት አድልዋዊ ስራና ሴራ እየተገላገሉ፣ ዳግም አሸብርቀዉ በመነሳት ሰላምን እየዘመሩ አሻጥረኛንና በሰዉ ሃብትና ትከሻ በሰዉ ላብና ወዝ ሊንቀባረር የሚሻን ወስላታ ሁሉ በተለይም የሕወሓት ውርንጭሎችን በአክሱም ሆቴል ጋጥ ውስጥ የከተቱበትን አንደኛ ዓመት የድል በዓል፡ ወደር ከሌለዉ ትልቁ በዓላችን ከበዓለ ትንሳኤ ጋር በድምቀትና በፍስሓ መንፈስ በጋራ እያከበርን ነዉ! :mrgreen:

181. አትዋሽ፤ እዉነትንም ሙሉ በሙሉ አትናገር። ልብን እንደ መብጣት ስለሚቆጠር የእዉነትን ያህል ጥበብን የሚጠይቅ ነገር የለም። አንዲት ቅንጣት ሀሰት ስለታማኝነትህ ያለህን ዝና ልታጎድፈዉ ይቻላታል። ማታለል እንደ ክህደት ስራ ሲቆጠር አታላዩ ደግሞ በባሰ ሁኔታ እንደ ከሀዲ ይቆጠራል። እዉነት ሁሉ በዘፈቀደ ሊነገር አይገባም፤ ይህ የሚሆነዉ አንዳንዴ ለራስህ ሲባል ሌላ ጊዜ ደግሞ ለሌሎች ሰዎች ሲባል በዝምታ ሊታለፍ ስለሚገባዉ ነዉ።

182. በሁሉም ነገር የተወሰነ ድፍረትን መጨመር ጠቃሚ ነዉ። ስለሌሎች ያለህን ግምት ልትቀይር ይገባል፤ ይህም ሌሎችን እስከምትፈራቸዉ ድረስ ታላቅ አድርገህ ማየት እንደሌለብህ ነዉ። ምናብህ በፍጹም ለልብህ እንዳይሸነፍ። ብዙ ሰዎች ታላቅ የሚመስሉት እስክትጠጋቸዉ ድረስ ነዉ፤ ለዚህም ነዉ መቀራረብ አብዛኛዉን ጊዜ ከከበሬታ ይልቅ ቅሬታን የሚወልደዉ። ማንም ቢሆን ከሰዉ ልጅ የታናሽነት ተፈጥሮ በላይ ሊሆን አይችልም። የእያንዳንዱ ሰው እዉቀት ሆነ ጸባይ “ዉይ እንዲህ ቢሆን ኖሮ. . .” የሚያስብል ነገር አይጠፋዉም። ማዕረግ በተወሰነ ደረጃ የበላይነትን ያላብሳል፤ ሆኖም ግን ዕጣ ፋንታ ከፍተኛ ቦታ ላይ ያለን ሰው አነስተኛ ችሎታ በመስጠት ስለምትቀጣዉ አብዛኛዉን ጊዜ ማዕረግ እና ችሎታ ሆድና ጀርባ ናቸዉ። ምናባችን አብዛኛዉን ጊዜ ችኵል በመሆኑ ምክንያት ነገሮች በትክክል ከሆኑት በላይ አጋኖ ይመለከታቸዋል። በዚህ ምክንያት ምናባችን ሲመለከት ያለዉን ብቻ ሳይሆን ሊኖር የሚችለዉን ጭምር ነዉ። እናም ልምድን መሰረት በማድረግ ነገሮችን በጠራ አይን መመልከት እና ምናብንም መገሰጽ አስፈላጊ ነዉ። ይህ ደግሞ ጅላጅልነት በጣሙን ደፋር፤ ጨዋነት ደግሞ ፈሪ እንዳይሆን ይረዳል። በራስ መተማመን ለሞኞች እና ለመደዴወች ከሰራላቸዉ፤ በራስ መተማመን ለሚገባቸዉ ለጠቢቦች እና ለብርቱዎች ምን ያህል በጠቀማቸው!?

183. ምንም ነገር ላይ ሙጭጭ እንዳትል። ሞኞች ግትር ናቸዉ፤ ግትሮችም ሞኞች። የእነዚህ ሰዎች ሙጭጭ ባይነት በተሳሳተዉ ግምታቸዉ ልክ የገዘፈ ነዉ። ትክክለኛነትህን እርግጠኛ የሆንክ ጊዜ እንኳ ለድርድር ዝግጁ መሆን ተገቢ ነዉ። ይህን ካደርግክ ሰዎች በስተመጨረሻ ትክክለኝነትህን ይረዱና ትህትናህን ያደንቁልሃል። በማሸነፍ ከምታተርፈዉ ይልቅ በክርክር ብዙ ታጣለህ። ሰዉ ግትር ሲሆን ዘብ የቆመዉ ለስድነት እንጅ ለእዉነት አይደለም። እነሆ ለማሳመን አስቸጋሪ እና ተስፋ በሚያስቆርጥ ሁኔታ ችኮ የሆኑ ዲንጋይ ራስ ሰዎች አሉ። ግልፍተኝነት እና ችኮነት የተገናኙ እንደሆን ዘላለማዊ የሆነ የሞኝነት ትዳርን ይመሰርታሉ። በአስተያየትህ ሳይሆን በማድረግ ፍላጎትህ ብርቱ ሁን። እርግጥ አንድ ሰዉ ሁለቴ መሸነፍ የሌለባቸዉ ብቅርየ አጋጣሚወች አሉ። እነሱም አንደኛዉ በአስተያየት ሌላኛዉ ደግሞ በአፈጻጸም ናቸዉ።

184. በስነስርኣት ወይም በአከባበር የተጠመድክ እንዳትሆን። ይህ የማስመሰል ስራ በንጉሶች ላይ ሲታይ እንኳ ከተለመደው ወጣ እንዳለ ተግባር ይቆጠራል። ጥንቁቅነት መንፈስን የሚያሳምም ቢሆንም በዚህ ተግባር የተጠመዱ ሀገሮች አሉ። የክብራቸዉ አምላኪ የሆኑት የሞኞች ልብስ የተጠቀመዉ በቂላቂል ስፌት ሲሆን፤ ማንኛዉም ነገር ክብራቸዉን ስለሚነካዉ ክብራቸዉ በጥቂት ነገሮች ላይ የተቆለለ መሆኑን ያሳያሉ። ክብርን መፈለግ አግባብ ቢሆንም፤ የአስመሳይነት ተምሳሌት መሆን ግን አግባብ አይደለም። እርግጥ እዉነት ነዉ ስነስርአት አከባበርን የማያዉቅ ሰዉ ለስኬት ለመብቃት ታላቅ ችሎታ ያስፈልገዋል። መልካም ነገርን ማስመሰል አግባብ ባይሆንም መልካም ነገር ግን ሊጠላ አይገባዉም። በጥቃቅን ነገሮች ላይ ማተኮር ደግሞ የታላቅነት ምልክት አይደለም።

185. ክብርህን በሙሉ በአንድ ጨዋታ ብቻ እንዳታንጠለጥላት። ለዚህ ምክንያቱ የተሸነፍክ እንደሆን ጉዳቱ ሊፋቅ የማይችል ስለሆነ ነዉ። በተለይ የመጀመሪያህ ከሆነ በቀላሉ ትሳሳታለህ። ሁሌም በመልካም ሁኔታ ልትገኝ አትችልም፤ ሁሉም ቀን ደግሞ ያንተ ሊሆን አይችልም። እናም ሁሌም የመጀመሪያዉን ማረሚያ ይሆንህ ዘንድ ሁለተኛ እድል እንዲኖርህ አድርግ . . . ምክንያቱም የመጀመሪያዉ መልካም ሆነ አልሆነ ሁለተኛዉ ስለሚያድነዉ ነዉ። እናም ሁሌ ለይግባኝ ሆነ ለማሻሻል እድል እንዲኖርህ አድርግ። ነገሮች በብዙ አጋጣሚወች ላይ የተመረኮዙ ናቸዉ፤ እድል ደግሞ እኛን ወደ ስኬት የምትወስድባቸዉ አጋጣሚወች በጣም ጥቂት ናቸዉ።

186. መልካም ነገር ቢመስል እንኳ ችግር ያለበትን ነገር እወቀዉ። መጥፎ ነገር ተሸፋፍና ብትቀርብ እንኳ አስተዋይ ሰው ሊለያት ይገባል። ምንም አንዳንዴ የወርቅ ተክሊል ደፍቶ ቢቀርብም እንኳ የባርነት ስርአት መጥፎነቱ አይለወጥም። መጥፎ ነገርን የፈለገ ከፍከፍ ብናደርገዉ ማንነቱን አይቀይርም። አንዳንዶች አንድ ችግር ያለበት ታላቅ ሰው ይመለከቱ እና ታላቅ የሆነዉ ባለበት ችግር ምክንያት አለመሆኑን መረዳት ያዳግታቸዋል። ታላቅ ሰዎችን እንደምሳሌ መዉሰድ ደግሞ የተንሰራፋ በመሆኑ ምክንያት ሌሎች የእነዚህን ታላቅ ሰወች መጥፎ ምግባር ጭምር ለመቅዳት ይጣጣራሉ። ታዲያ በታላቅነት የተደበቀ መጥፎ ነገር ታላቅነት በሌለበት እጅጉን አስፀያፊ መሆኑን ባለመረዳት አድናቆት መልከ ጥፉነትን እንኳ ትቀዳለች።

187. አንድ ነገር ሌሎችን የሚያስደስት ከሆነ እራስህ ስራዉ፤ አስደሳች ካልሆነ ደግሞ ሌሎች እንዲሰሩት አድርግ። ይህ ዘዴ የሰወችን በጎነት ወደ አንተ ሲስብልህ፤ ጥላቻቸዉን ደግሞ ወደ ሌሎች ሰወች ያስተላልፍልሃል። ታላላቆች እና ጨዋወች በጎ ከሚደረግላቸዉ ይልቅ በጎ ማድረግ ያስደስታቸዋል። በቁጭት ወይም በርህራሄ ስሜት ምክንያት እራስህን ችግር ውስጥ ሳትጨምር በሌሎች ላይ ችግር መፍጠር አትችልም። የሽልማት ወይም የካሳ ነገር ከሆነ ነገሩ ወዲያዉኑ እንዲፈጸም አድርግ፤ መጥፎ የሆነ እንደሆነ ግን እንደ ሽማግሌ እንዲያገለግልህ ሌላ ሰው ይፈጽመዉ። ሰወች ቅሬታቸዉን በጥላቻ እና በአሉባልታ መልክ የሚቀስሩበትን አንዳች ነገር ልትሰጣቸዉ ይገባል። የኮልኮሌወች ቁጣ ልክ እንደ ውሻ እብደት በመሆኑ ቃታ ስቦ ያቆሰላቸዉን ሳይመለከቱ አፈሙዙን ይነክሳሉ። ምንም አፈሙዙ ከደሙ ነፃ ቢሆንም በፍጥነት ይቀጡታል

188. የምታሞግሰው አንዳች ነገር ይኑርህ። ይህ መልካም ጣእም እንዳለህ፤ ሌላ ቦታ ያለዉን መልካም ነገርም እንደምታዉቅ እና እዚህ ስላለዉ ነገር ደግሞ አስተያየት ትሰጣለህ ተብሎ እንዲታመንብህ ያደርጋል። አንድ ሰዉ ልቀትን ካወቃት በተገኘችበት ሁሉ የሚገባትን ክብር ይሰጣታል። ሙገሳ ለጭዉዉት እና ለአርአያነት በርን ሲከፍት፤ በዙሪያህ ላሉ ደግሞ ትህትና የምታሳይበት የጨዋነት ተግባር ነዉ። ሆኖም ግን አንዳንድ ሰዎች እፊታቸዉ ያሉትን ለመሸንገል ሲሉ ባቅራቢያቸዉ የሌሉትን ሰዎች በማጣጣል ተቃራኒዉን ይፈፅማሉ። የእነዚህ ሰዎች ዘዴ ተቀባይነት የሚገኘዉ ጓደኛህን ሲያማ ለኔ ብለህ ስማ መሆኑን በማይረዱ ቂሎች ዘንድ ነዉ። አንዳንድ ሰዎች ደግሞ ከትላንትናዉ ታላቅ ነገር ይልቅ የዛሬዉን ተራ ነገር ማድነቅ ይቀናቸዋል። እናም አስተዋይ ሰዉ የተጠቀሱትን ማጭበርበሪያወች ይገንዘብ እና ለማጋነን ሆነ ለሽንገላ የማይደለል ይሁን። እንዲሁ እነዚህ አጉል ሀያሲወች በሁሉም ሰው ዘንድ የሚጠቀሙት አንድ አይነት ዘዴ መሆኑን ይረዳ።

189. የሌላዉን ችግር ለራስህ ጥቅም አዉለዉ። ችግር ፍላጎትን የወለደ ጊዜ ሌሎችን እንደልባችን የምናደርግበትን በር ይከፍትልናል። ፈላስፋወች እጦት ምንም አይደለም አሉ፤ ፖለቲከኞች ደግሞ እጦት ሁሉም ነገር ነዉ አሉ - እነሆ ፖለቲከኞች ትክክል ናቸዉ። አንዳንዶች የሌሎችን ፍላጎት ተጠቅመዉ የራሳቸዉን ጉዳይ ያሳካሉ። እነዚህ ሰዎች በፍላጎት መጠመድ በማግኘት ከሚመጣዉ እርካታ የበለጠ መሆኑን ይረዳሉ። የምንፈልገዉን ነገር ማግኘት በጣም አስቸጋሪ እየሆነ በሄደ ቁጥር ፍላጎታችን የበለጠ ይጨምራል። የምትፈልገዉን የሚያስገኝልህ የብልጠት መንገድ ሌሎችን ጥገኛህ ማድረግ ነዉ።

190. ከሁሉም ነገር መጽናኛን አግኝበት። እርባና የለሾች እንኳ በዘላለማዊነታቸዉ ይጽናናሉ። መጽናኛ የማይገኝበት ችግር የለም። አባባሉ እንደሚያስረዳዉ “ቆንጆወች እንደ መልከ ጥፉወች እድለኛ በሆን እያሉ ይመኛሉ” ይላል። ለሞኞች መጽናኛቸዉ እድል ነች። ብዙም ጠቃሚ አለመሆን ብዙ ለመኖር ይበጃል። የተሰነጠቀ ብርጭቆ የሚያናደን ሙሉ በሙሉ ባለመሰበሩ ምክንያት እድሜው ረዥም ስለሆነ ነዉ። መልካም እድል ታላቅ ሰዎችን የምትቀናባቸዉ ትመስላለች። ጥቅም የለሾችን በዘላቂነት ትሸልማቸው እና አስፈላጊዉን ነገር ደግሞ ታሳጥረዋለች። በጣም ዋጋ ያላቸዉ ነገሮች ባጭሩ ሲቀጩ፤ ፍሬ ቢሶች ደግሞ ዘላለማዊ ይሆናሉ ወይም ለዘላለሙ የሚኖሩ ይመስላሉ። መጥፎ እድል ያለዉን ሰዉ መልካም እድል ሆነ ሞት አድማ ይመቱ እና ይረሱታል።

ጎበዝ፣ በብልህነት መንገድ እንጓዝ፣ ብልሆችም እንሁን!
:mrgreen:

Meleket
Member
Posts: 1109
Joined: 16 Feb 2018, 05:08

Re: ‘የብልህነት መንገድ’ - ምርጥ መጠሓፍ በምርጥ ተርጓሚ - ይዘቷን እንካችሁ አጣጥሙ!

Post by Meleket » 30 Apr 2019, 11:17

ጎበዝ የዛሬዎቹን 10 የብልህነት መንገዶች፣ ነጩን ነጭ ጥቁሩንም ጥቁር ብለዉ ሓቅን በመግለጥ የህዝብ ወገንተኝነታቸዉን ላስመሰከሩ በዓለም ዙርያ ለሚገኙ እዉነተኛ የሃይማኖት ኣባቶች ክብር በተለይም ለኤርትራዉያን የካቶሊኽ ኃይማኖት ጳጳሶች ክብር እዚህ እንካፈላለን። :lol: እርግጥ ነዉ ግፍ እየተፈጸመ እያዩ፣ ስሕተት ሲፈጸም ባይናቸዉ እያዩ ምንም እንዳላዩ የሚሆኑትን በዓለም ዙርያ በተለይም በአፍሪካ ቀንድ የሚገኙ “ካህናተ-ደብተሮችን” ይህ ክብር አይመለከታቸዉም ይህንም ስናደርግ በተንኮል ስራዋ በተለያዩ የጎረቤታችን “ክልሎች” እኩይ መርዧን ረጭታ፡ ንጹሓን እናቶችንና ህጻናትን ከምድረገጽ ለማጥፋት ብሄር ተኮር ዘመቻ በማካሄድ “የቀስት” ሰለባ በማድረግ በቀቢጸ ተስፋ እርምጃ ላይ የምትገኘዉን ሟቿ ህወሓት ኢምንትነቷን የተረዳችበትን 1 ዓመት የኤርትራ ህዝብና የኢትዮጵያ ህዝብን የድል በዓል እያከበርን ነዉ

191. ክፍያህን በትህትና መልክ እንዳትወስድ። ይህ ማጭበርበር ነዉ። ሰውን ለማፍዘዝ አስማት የማያስፈልጋቸዉ አንዳንድ ሰዎች አሉ። እነዚህ ሰዎች ባርኔጣቸዉን እያወለቁ እጅ በመንሳት ከንቱ የሆኑትን ቂሎች ያታልላሉ፤ እንዲሁ ከበሬታን እየሸጡ ደግሞ እዳቸዉን ትንፋሽ በሆኑት ቃላት ይከፍላሉ። እነሆ ለሁሉም ቃል የገባ ለማንም ቃል አልገባም። ተስፋ መስጠት የቂሎች ወጥመድ ናት። እዉነተኛ ትህትና የግድ ነዉ፤ ሀሰተኛ ትህትና አጭበርባሪነት፤ ከልክ ያለፈ የሚያሳዩ ሰወች የሚያጎነብሱት ለሰውየዉ ሳይሆን ለሀብቱ እና ለተሸንጋይነቱ ነዉ። በተጨማሪውም ትህትናቸዉን የሚያሳዩት ለመልካምነቱ ሳይሆኖ ይሰጣል ብለዉ ለሚጠብቁት ችሮታዉ ነዉ።

192. ሰላማዊ ሰው እድሜው ረዥም ነዉ። ሰላማዊ ሰዎች መኖር ብቻ ሳይሆን ይነግሳሉ (ይሰፍናሉ)። አዳምጥ እንዲሁ ተመልከት፤ ድምጽህን ግን አጥፋ። ከጭቅጭቅ የጸዳ ቀን ማለት በእረፍት የተሞላ ምሽት ማለት ነዉ። ብዙ መኖር እና በህይወት መደሰት ማለት ሁለት ጊዜ መኖር ማለት ነዉ። ይህ ደግሞ የሰላም ፍሬ ነዉ። ለማይጠቅመዉ ነገር ብዙም ካልተጨነቅክ የምትፈልገዉን ሁሉ ታገኛለህ። ሁሉንም ነገር እንደ ቁምነገር መቁጠርን የመሰለ ሞኝነት የለም። በማያገባህ ነገር ማዘን ሆነ ለሚመለከትህ ነገር ትኩረትን አለመስጠት ሁለቱም ቂልነት ናቸዉ።

193. የሌላዉን ጥቅም ለማስጠበቅ ብሎ መጥቶ የራሱን ጥቅም አስጠብቆ የሚሄደዉን ሰዉ ተጠንቀቀዉ። የተንኮል መከላከያዉ ንቃት ነዉ። ሌሎች ብልጣብልጥ ሲሆኑ አንተ ደግሞ የበለጠ ብልጥ ሁን። አንዳንዶች የራሳቸዉን ስራ ከራስህ ጋር እንድትፈጽም ያደርጉሃል። የእነዚህን ሰወች ዉጥን በቶሎ ካልደረስክበት እራስህን እጅህ እስኪቃጠል ድረስ የእነርሱን ለዉዝ እሳት ውስጥ እየጠበስክ ታገኛለህ።

194. ስለራስህ እና ስለጉዳይህ ያለህ ግምት ጥርት ያለ ይሁን። በተለይም ገና መኖር መጀመርህ ከሆነ። ሁሉም ሰው ለራሱ ትልቅ ግምትን ይሰጣል፤ በተለይ ታናሾች ስለራሳቸዉ ያላቸዉ ግምት በጣም ከፍተኛ ነዉ። ሁሉም ሰው ስለእድለኝነቱ ያልማል፤ እራሱንም ተሰጥኦ ያለዉ አድርጎ ይቆጥራል። ተስፋ አንዳች ነገር ላይ ሙጭጭ ቢልም፤ እዉነታ ግን ተስፋ የሚጠብቀዉን ነገር መዉለድ ይሳነዋል። እዉነታን በጠራ አይን መመልከት ለከንቱ ምናብ ስቃይን ይፈጥራል። ምክንያታዊ ሁን። ማንኛዉንም ነገር በመረጋጋት ትቀበል ዘንድ ክፉዉን እየጠበቅክ መልካሙን ተመኝ። በጣም ከፍ አድርጎ ማለም አላማን ሊያስት ይችላል። ስራህን ስትጀምር ስለስራዉ ያለህን ግምት አስተካክል። ልምድ ያልታከለበት ግምት አብዛኛዉን ጊዜ በስህተት የተሞላ ነዉ። አቅምህን እና ሁኔታህን በደንብ እወቅና ምናብህን ከእዉነታዉ ጋር አዛምደዉ።

195. ማድነቅን እወቅበት። ሁሌም ሌላዉን የሚበልጥ ሰዉ አለ፤ እንዲሁ ይህን ሰዉ የሚበልጥ ደግሞም ሌላ ሶስተኛ ሰዉ አለ። በእያንዳንዱ ሰዉ መደሰት መቻል በጣም ጠቃሚ ነዉ። የሁሉንም መልካምነት ስለሚረዳ እና ነገሮችን በደንብ መፈጸም ምን ይህል ከባድ ነገር እንደሆነ ስለሚያዉቅ ጠቢብ ሁሉንም ያከብራል። በከፊል ከድንቁርናዉ የተነሳ በከፊል ደግሞ ሁሌም መጥፎዉን ነገር ስለሚመርጥ ሞኝ ሌሎችን ይጠላል

196. ኮከብህን እወቅ። ኮከብ የሌለዉ ሰዉ የለም። በመጥፎ እድል የተለከፍክ ከሆነ ደግሞ ኮከብህን አላወቅካትም ማለት ነዉ። አንዳንዶች እንዴት እና ለምን እንደሆነ ሳያዉቁት በእድለኝነታቸዉ ብቻ የልዑላን እና የሀይለኞችን መልካም ፈቃድ ያገኛሉ። እነዚህ ሰዎች የሚያስፈልጋቸዉ ነገር ቢኖር እድላቸዉን በደንብ መንከባከብ ነዉ። ሌሎች ደግሞ በጠቢቦች ዘንድ ተወዳጅነትን ያገኛሉ። አንዳንድ ሰወች ካንድ ሀገር ይልቅ በሌላኛዉ ተቀባይነትን፤ ወይም ደግሞ በሌላ ከተማ ታዋቂነትን ያገኛሉ። እንዲሁ እኩል ወይም ተመሳሳይ በሚመስሉ አገልግሎቶች እንኳ አንደኛዉ ስፍራ ከሌላኛዉ ላቅ ያለ እርካታን ያስገኛል። ወይዘሮ እድል ካርዶቿን የምትሸከሽካቸዉ እንዳስፈለጋት ነዉ። እናም ማሸነፍን ወይም መሸነፍን ስለሚወስን እያንዳንዱ ሰዉ እድሉን እና ችሎታዉን ይወቅ። የእድል ኮከብን መከተልም ይወቅበት።

197. ከሞኞች ጋር እንዳትቀላቀል። ሞኝ ማለት ሞኝ የሆነን ሰው መለየት የማይችል ሲሆን፤ ከዚህ የባሰዉ ደግሞ ሞኝን መለየት የሚችል ሆኖ እያለ ሞኙን የማይርቀዉ ነዉ። ሞኞች ላይላዩን ብትቀርባቸዉ እንኳ በጣም አደገኞች ናቸዉ፤ የተማመንክባቸዉ እንደሆን ደግሞ ብዙ ጥፋት ያደርሳሉ። እንዲሁ ለጊዜዉ የራሳቸዉ ቡከናምነት ወይም የሌላ ሰዉ ተዉ ባይነት ቢያግዳቸዉም እንኳ ዉለዉ አድረዉ የጅል ስራን መስራታቸዉ አይቀርም። መልካም ስም የሌለዉ ሰዉ ያንተን መልካም ስም ያጎድፍብሀል። ሁሌም የሞኞች ዕጣ ፈንታ መጥፎ ሲሆን፤ ይህም ለእነሱ እንደ ሸክም ነዉ። ታዲያ እጥፍ የሆነዉ መጥፎ እጣ ፋንታቸዉ ከሚጠጉት ሰዉ ጋር ሁሉ በመለካለክ ይተላለፋል። ቂሎች መጥፎ ያልሆነ አንድ ነገር ብቻ አላቸዉ፤ እሱም ምንም ጠቢብ ለቂሎች ጠቃሚ ባይሆንም ቂሎች ግን ለጠቢብ እንደመጥፎ ምሳሌ ስለሚያገለግሉት ጠቃሚ ናቸዉ።

198. ተሻግሮ መሄድን እወቅበት። ያሉበትን አካባቢ ከለቀቁ በኋላ ከበሬታን የሚያገኙ ብዙ ሰወች አሉ። በተለይ በታላላቅ ሹመቶች ዘንድ ጠረፍን ካልተሻገሩ ከበሬታን የማያገኙ ብዙ ሰወች አሉ። ለታላላቆች እናት ሀገር ልክ እንደ እንጀራ እናት ናት። ይህ የሆነዉ ቅናት ማስታወስ የምትፈልገዉ አንድ ሰው የተነሳበትን እንጅ በኋላ የደረሰበትን ስላልሆነ ነዉ። ከሩቅ ቦታ የመጣ ደግሞ ሰወች የሚያዩት ተሰርቶ ካለቀ በኋላ እና ላቅ ካለ በኋላ ስለሆነ በሰወች ቢሰደቡም በአለም ዙሪያ ክብርን አግኝተዋል። እነዚህ ሰወች በህዝባቸዉ ዘንድ ከሩቅ ቦታ ስለመጡ ይከበራሉ። ጫካ ዉስጥ እንጨት እያለ በሚያዉቀው ሰዉ ዘንድ የጣኦት ቅርጽ ከበሬታን አያገኝም

199. ከበሬታን ለማግኘት ስትጥር በማስተዋል እንጅ በአይን አዉጣነት እንዳይሆን። ወደ ከበሬታ የሚወስደን ትክክለኛዉ መንገድ ችሎታ ነዉ፤ ችሎታ ከተግባራዊነት ጋር ከተጣመረ ደግሞ መንገዱ አጭር ይሆናል። ባዶ መልካምነት ብቻዉን በቂ አይደለም፤ ተጋፊነት እና ሙጭጭ ባይነት ደግሞ ስምህን ያጎድፉታል። ምክንያቱም እነዚህን ነገሮች ያደረግክ እንደሆን ነገርን ስለምታበላሽ ጥላቻን ታተርፋለህ። እናም አማካኙን መንገድ ተከተል እና ችሎታ ይኑርህ እንዲሁ ራስህን በሰዉ ፊት ማቅረብንም እወቅበት።

200. ከልክ ያለፈ ደስታ እንዳያሸንፍህ በተስፋ የምትጠብቀዉ አንዳች ነገር ይኑርህ። ሰውነታችን አየርን እንደሚፈልገዉ ሁሉ መንፈሳችንም የራሷ ምኞቶች አሏት። አሁንም ነገሮች በእጃችን የገቡ እንደሆን ቅሬታና የደስታ እጦትን ይፈጥሩብናል። ተስፋ እንዲሰጠን እና የማወቅ ፍላጎታችንን ያረካልን ዘንድ እዉቀትን በተመለከተ እንኳ በሂደት የምንማረዉ ተጨማሪ እዉቀት ሊኖር ይገባል። ተስፋ ህይወትን ሲያላብሰን ከልክ ያለፈ ደስታ ደግሞ የህይወት ጠንቅ ነዉ። ሌሎችን ስትሸልም በፍጹም እንዳይረኩ አድርገህ መሆን አለበት። ሰወች ምንም ነገር የማይፈልጉ ጊዜ ሁሉንም ነገር ልትፈራ ይገባሃል። እነሆ ፍርሃት የሚጀምረዉ ምኞት ሲያልቅ ነዉ።

ጎበዝ፣ በብልህነት መንገድ እንጓዝ፣ ብልሆችም እንሁን! :mrgreen:

Meleket
Member
Posts: 1109
Joined: 16 Feb 2018, 05:08

Re: ‘የብልህነት መንገድ’ - ምርጥ መጠሓፍ በምርጥ ተርጓሚ - ይዘቷን እንካችሁ አጣጥሙ!

Post by Meleket » 04 May 2019, 05:11

ጎበዝ ተጠፋፋን አይደል፣ ያዉ ምን የመሰለ “የእርቀ-ሰለም ጥሪ” የሚል የአገሬ ኤርትራን ሁኔታ የሚገልጥ ጥሁፍ አግንቸ እሱን ሳጣጣም ነው። ለማንኛዉም የዛሬ አስር የብልህነት መንገዶችን ይህን “ብርቅ የእርቀ-ሰላም ጥሪ” በመልካም መንፈስ ተገንዝበው ለስኬቱ ሳያሰልሱ ጥረት ለሚያደርጉ አካላት ክብር እዚህ እንካፈለዋለን። ይህንን ስናደርግም የነዚህን መንፈሳዊ አባቶች ጥሪ በማድመጥ እንትናም እንዳለዉ “መጥፎውን በመጥፎ ሳይሆን በመልካም ለማሸነፍ” አንድየ ራሱ ብርታቱን እንዲሰጠን እየተማጸንን ነው! :lol:

201. ሞኞች ማለት ሞኝ የሚመስሉት በሙሉ እና፤ ሞኝ የማይመስሉት እኩሌታወች ናቸዉ። ቂላቂልነት በአለም ላይ ነግሷል፤ ጠቢብነት የቀራት ነገር ቢኖር በመለኮት ፊት ቂላቂል መሆን ነዉ። ከሁሉም የበለጠዉ ሞኝ ሌሎች እንጅ እርሱ ሞኝ እንዳልሆነ የሚያስበው ሰዉ ነዉ። ጠቢብ ለመሆን ጠቢብ መምሰል ብቻ በቂ አይደለም፤ በተለይም ደግሞ በራስህ አይን። አለማወቁን የሚያዉቅ ያዉቃል፤ ሌሎች እንደሚመለከቱ የማያስተዉል ደግሞ እየተመለከተ አይደለም። አለም የተሞላችው በሞኞች ቢሆንም፤ አንዳቸዉም እራሳቸዉን እንደሞኝ አይቆጥሩም፥፡ ሞኝ ላለመሆንም ጥረት አያደርጉም።

202. ቃላት እና ተግባር ባንድ ላይ ሙሉ ሰዉን ይፈጥራሉ። መልካም ተናገር፤ ተግባርህም የጨዋ ይሁን። የመጀመሪያዉ መልካም አእምሮን ሲያሳይ፤ ሁለተኛዉ ደግሞ ላቅ ያለ ልብን ያሳያል፤ ሁለቱም የሚመነጩት ከታላቅ መንፈስ ነዉ። ቃላት የተግባር ጥላወች ናቸዉ። ቃላት ሴት ሲሆኑ ተግባሮች ደግሞ ወንድ ናቸዉ። ሌሎችን ከማመስገን ራስ መመስገን። መናገር ቀላል ቢሆንም መስራት ከባድ ነዉ። ተግባር የህይወት ቁም ነገር ሲሆን፤ ጥበብ የተሞሉ ንግግሮች ደግሞ ጌጧ ናቸዉ። የቃላት ታላቅነት ጠፊ ሲሆን፤ የምግባር ታላቅነት ግን ዘላቂ ነዉ። ተግባር ከማስተዋል የሚወጣ ፍሬ ነዉ። ቃላት ጠቢብ ሲሆኑ፤ ተግባር ደግሞ ታላቅ ነዉ።

203. በዘመንህ ያሉትን ታላቅ ሰዎች እወቃቸዉ። እንዲህ አይነት ሰወች በቁጥር ብዙም አይደሉም። እንደ ፎኒክስ ከአለሙ ሁሉ ያለዉ አንድ ታላቅ ካፒቴን፤ አንድ ታላቅ ተናጋሪ፤ አንድ ክፍለዘመን አንድ ብልህ፤ እና አንድ ታላቅ ንጉስ ነዉ። ፍጹም የሆነ ልቀትን ስለሚጠይቅ ታላቅነት በጣም ብርቅየ ነዉ። ተግባሩ ታላቅ በሆነ ቁጥር ደግሞ ወደ ልቀት ለመድረስ የሚያስፈልገዉ ጥረት ያንኑ ያህል ታላቅ ነዉ። አብዛኛዎች “ታላቅ” የሚለዉን ቃል ከሲዛር እና ከአሌክሳንደር እየተዋሱ ራሳቸዉን ጠርተዉበታል፤ እነሆ ይህ ነገር የከንቱ ተግባር ነዉ፤ ተግባር ያልታከለባቸዉ ቃላት የነፋስ ሽውታ እንጅ ሌላ አይደሉም። የነበሩት በጣም ጥቂት ሴኔካወች ሲሆኑ፤ ዘላቂ ዝናን ያገኘ ደግሞ ኦፔሊስ* ብቻ ነው። (* ይህ ሰዉ በጥንታዊት ሮም የክርስትና ሀይማኖት አንጃን ያስፋፋ ነዉ።)

204. ከልክ በላይ እንዳትኩራራ ወይም ተስፋ እንዳትቆርጥ ይረዳህ ዘንድ ቀላል የሆነዉን እንደ ከባድ፤ ከባድ የሆነዉን ደግሞ ቀላል እንደሆነ አስበህ ፈጽመዉ። አንድን ነገር መስራት ባትፈልግ፤ እንደተሰራ አድርገህ ቁጠረው። ጥንቁቅነት ታላቅ ሰዉ የማይቻለዉን ሁሉ ያሸንፋል። ታላቅ አደጋ በሆነበት ቅጽበት ዝም ብለህ ፈጽም እንጅ ብዙም አታስብ። እንቅፋቶች ላይ ሙጭጭ አትበል።

205. ስድብን መጠቀም እወቅ። ነገሮችን የማግኛዉ አንዱ መንገድ ነገሮቹን መስደብ ነዉ። ስትፈልጋቸዉ አይመጡም ያልፈለግካቸዉ ጊዜ ደግሞ ምንም ጥረት ሳታደርግ እየሮጡ ይመጡልሃል። እነሆ ምድራዊ ነገሮች የሰማያዊ ጥላ በመሆናቸዉ ምክንያት ፀባያቸዉም እንደ ጥላ ነዉ። ስትቀርባቸዉ ይፈረጥጣሉ፤ ስትርቃቸዉ ደግሞ ይከተሉሃል። እንዲሁ ስድብ ብልጠት የታከለበት የበቀል መንገድ ነዉ። ጠቢብ የሆነ መርህ ቢኖር ባላንጣዎችህን በጥፋታቸዉ ከመቅጣት ይልቅ ክብርን ስለሚያላብሳቸዉ እና አሻራንም ትቶ ስለሚያልፍ ራስህን በጽሁፍ (በብዕር) አትከላከል። ርባና የለሽ ሰዎች በብልጠት ታላቆችን እየተቃወሙ የማይገባቸዉን ዝና በተዘዋዋሪ ያገኛሉ። ታላቆች ባላንጣዎቻቸዉን ከቁብ ሳይቆጥሩ ቢተዋቸዉ ኖሮ ብዙ ሰዎች ታዋቂነትን አያገኙም ነበር። በጅላጅልነታቸዉ ሰዎችን እንደሚቀብረዉ እንደ አለመታወቅ ያለ ታላቅ በቀል የለም። ባለጌ ቂሎች የአለማችንን እና የክፍለ ዘመኑን ታላቅ ነገር በማርከስ ዘላለማዊነትን ለመላበስ ይጥራሉ። ስድ የሆነ ጉምጉምታን ጸጥ ማስባያዉ አንዱ መንገድ ናቅ አድርጎ መተዉ ነዉ። እተቻለሁ ያልክ እንደሆን ግን ትጎዳሃለች፤ ዋጋ ከሰጠሃት ደግሞ ዋጋ ታሳጣሃለች። ምንም ትንፋሻቸዉ ላቅ ያለዉን ነገር ባያጠቁረዉ እንኳ ማወየቡ ባይቀርም ሰዎች አንተን ለመምሰል ጥረት በማድረጋቸዉ ልትደሰት ይገባል።

206. ስድ ሰዎች የትም ቦታ መኖራቸዉን ተረዳ። ታላቅ ከሚባሉት ቤተሰቦች ዉስጥ እንኳ እንዲህ ኣይነት ሰዎች አሉ። እንዲሁ እያንዳንዱ ሰው በቤቱ ውስጥ ያገኛቸዋል። ስዶች ብቻ ሳይሆን በጣም የባሰባቸዉ ታላቅ ስዶች አሉ። እነዚህ ሰዎች እንደ መስታወት ስባሪ ተራ የሆነ ነገርን አንፀባራቂ ሲሆኑ የሚያደርሱት ጥፋት ግን ከመስታወቱ በባሰ ሁኔታ ከፍተኛ ነዉ። ሲናገሩ እንደ ሞኝ ሲሆን ሌሎችንም በማጣጣል የብልግና ተግባር ይፈጽማሉ። እንዲህ አይነት ግለሰቦች በአጠቃላይ የድንቁርና ደቀመዛሙርት እና የደደብነት ባላባቶች ሲሆኑ፤ አፋቸዉ ደግሞ ለአንቋሻሽ አሉባልታ ያሞጠሞጠ ነዉ። ስለዚህ ለሚናገሩት በተለይ ደግሞ ለስሜታቸዉ ምንም ትኩረትን እንዳትሰጥ። እነሆ እነዚህን ሰዎች ትርቃቸዉ ዘንድ እወቃቸዉ፤ በስድነታቸዉ እንዳትሳተፍ፤ እንዲሁ አንተንም ለስድነታቸዉ እንዳያዉሉህ ተጠንቀቅ። ማንኛዉም አይነት ስድነት ሞኝነት ሲሆን፤ ስዶች ደግሞ በሞኝነት የተሞሉ ናቸዉ

207. ራስህን ተቆጣጠር። በተለይ ባጋጣሚ በሚከሰቱ ነገሮች ላይ። ድንገተኛ የሆነ የስሜት ዥዋዥዌ ማስተዋልን ይጎዳታል፤ እናም ይሄኔ ነዉ ልትስት የምትችል። ያንዲት ደቂቃ የስሜት መገንፈል ወይም በራስ መርካት መዘዛቸዉ ከብዙ ሰአታት ግዴለሽነት የበለጠ ነዉ። ያንዲት አፍታ ስህተት ደግሞ የእድሜ ልክ ቁጭት ልታስከትል ትችላለች። ብልጣብልጥ ሰዎች የባላንጣዎቻቸዉን ማስተዋል ለመፈታተን ወጥመድ ያዘጋጁና የባላንጣወቻቸዉን አስተሳሰብ ይገመግማሉ። ሚስጥርንም መንጥረዉ በማዉጣት ታላቅ የሚባለዉን ሰዉ ውስጥ ይረዳሉ። ለዚህ መፍትሄዉ ምንድን ነዉ? ራስህን ተቆጣጠር፤ በተለይ ደግሞ ከግልፍታ። ስሜት እንደ ፈረስ እንዳይበረግግ መቆጣጠር መቻል ታላቅ የራስ መግታት ችሎታን ይጠይቃል፤ ከፈረስ ጀርባ ብልህ ከሆንክ (ደራሲዉ ግራሽያን እዚህ ላይ “ከፈረስ ጀርባ ላይ ተቀምጦ ብልህ መሆን አይቻልም” የሚለዉን የእስፓኝ ሀገር ምሳሌያዊ አባባል ማመልከቱ ነዉ።) ደግሞ፤ በሁሉም ነገር ብልህ ነህ። ችግር ከፊቱ እንደተደቀነ የሚያዉቅ በጥንቃቄ ይጓዛል። በስሜት የተወረወረ ቃል ለተናጋሪዉ ቀላል ብትሆንም ተቀብሎ ለሚያብሰለስላት ሰዉ ግን ከባድ ነች።

208. በቂልነት በሽታ እንዳትሞት። ብልህ ሰዎች አብዛኛዉን ጊዜ የሚሞቱት በአእምሮ በሽታ ነዉ። ሞኞች ደግሞ በምክር ታንቀዉ ይሞታሉ። በሞኝነት የምትሞተዉ ከልክ በላይ ምክንያታዊ የሆንክ እንደሆን ነዉ። አንዳንዶች የሚሞቱት ሁሉንም ነገር ስለሚረዱ እና ስለሚሰማቸዉ ሲሆን፤ ሌሎች ደግሞ ስለማይረዱ ወይም ምንም ስለማይሰማቸዉ ነዉ። አንዳንዶች ሞኝ የሆኑት ስለሚፀፀቱ፤ ሌሎች ደግሞ ስለማይፀፀቱ። ከልክ ባለፈ እዉቀት መሞት ሞኝነት ነዉ። አንዳንዶች ብዙ በማወቃቸዉ ሲጠፉ፤ ሌሎች ደግሞ ምንም ባለማወቃቸዉ ይኖራሉ። ምንም እንኳ ብዙወች በቂልነት ቢሞቱም፤ ከቂሎች መሀከል መኖር ጀመሩ የሚባሉት በጣም ጥቂቶቹ ስለሆኑ፤ በትክክል ሞቱ የሚባሉትም በጣም ጥቂቶቹ ናቸዉ

209. ተራ ከሆነ ቂላቂልነት ነፍስህን አጽዳ።ይህ ለየት ያለ ጤነኝነትን ይተይቃል። የልምድ ቂላቂልነትን ባህል ስላጸደቀዉ የግለሰቦችን ድንቁርና መቋቋም የሚችሉ ሰዎች የመንጋዎችን ድንቁርና መቋቋም ያቅታቸዋል። ስዶች እድላቸዉ መልካም ሆኖ እያለ እንኳ ደስተኛ አይደሉም፤ እዉቀታቸዉ መጥፎ እያለ ደግሞ ሀዘን ብሎ ነገር የለባቸዉም። እንዲሁ በራሳቸዉ ሀሴት መደሰት ያቅታቸዉ እና በሌሎች ይቀናሉ። ሌላዉ ቂልነት ደግሞ የዛሬ ሰወች የትላንቱን መናፈቃቸዉ እና እዚህ ተቀምጠዉ ደግሞ ማዶ ያለዉን መሻታቸው ነዉ። በተጨማሪም ያለፈዉ የተሻለ ሲመስል፤ ማዶ ያለዉ ደግሞ ተወዳጅ ይሆናል። በሁሉም ነገር የሚስቀዉ ደግሞ በሁሉም ነገር እንደሚያለቅሰዉ ሁሉ ቂላቂል ነዉ

210. እዉነትን መቻል ያዝ። እዉነት አደገኛ ናት፤ ይህም ቢሆን መልካም ሰዉ ሊናገራት አያዳግተዉም። ይህን ማድረግ ደግሞ ጥበብን የሚጠይቅ ነገር ነዉ። እዉነት ስህተትን ለማረም ስትዉል አይነተኛ መሪር ስለሆነች ሙያተኞች የእዉነት ኪኒንን ማጣፈጫ ፈጥረዋል። ይህ ደግሞ ታላቅ ችሎታን እና የታረመ ምግባርን ይጠይቃል። እነሆ ተመሳሳይ እዉነታ እየተናገሩ አንድን ሰዉ ማደንቆር ወይም ማስደሰት ይቻላል። የአሁን ጉዳዮች እንዳለፉ ተደርገዉ ሊነገሩ ይገባቸዋል። ለሚገባዉ ወይም ሊረዳ ለሚችል ሰዉ ነገርን እንዲሁ መጠቆም ብቻ በቂ ነዉ ይህ በቂ ካልሆነ ግን ድምጽህን አጥፋ። መራራ መድሀኒት ለልዑላን በፍጹም መሰጠት ስለሌለበት ያፈጠጠዉን እዉነት በዘዴ ማለስለስ ያስፈልጋል።

ጎበዝ፣ በብልህነት መንገድ እንጓዝ፣ ብልሆችም እንሁን! :mrgreen:

Meleket
Member
Posts: 1109
Joined: 16 Feb 2018, 05:08

Re: ‘የብልህነት መንገድ’ - ምርጥ መጠሓፍ በምርጥ ተርጓሚ - ይዘቷን እንካችሁ አጣጥሙ!

Post by Meleket » 10 May 2019, 04:03

ጎበዝ የዛሬ አስር የብልህነት መንገዶችን ፍቅርን ያልተላበሰ ፍቅርን እንዲላበስ፣ ርሕራሄን ያልተላበሰ ርህራሄን እንዲጎናጸፍ፣ የይቅርታ መንፈስ የሌለበት የይቅርታ መንፈስን እንዲላበስ እየተመኘን፤ በጭካኔ መንገድ ብቻ የሚጓዝ ቆም ብሎ እንዲያስብ፣ ስፍር ቁጥር የሌላቸው እስርቤቶችን የሚሰራ ስፍር ቁጥር የሌላቸውን የችግኝ ጣቢያዎችን እንዲመሰረት፣ እስር ቤቶችንም ወደ ችግኝ ጣቢያነት እንዲቀይር እየመከርንና እየተመኘን፣ ለአፍሪካ ቀንድ የፖለቲካ መሪዎች ክብር እንጋራለን። ይህን ስናደርግም አገሬ ኤርትራን ከጨቋኞች መንጋጋ ፈልቅቀው ነጻነትን እንድትጎናጸፍ ያደረጓትን መጻኢዋ ኤርትራም ስደት የሚባል አውሬ ያጠላባት እንዳትሆን፣ ልጆቿም በሃገራቸው ያለ አንዳች ስጋት በፍቅርና በወንድማማችነት መንፈስ የሚጎማለሉበትን ሁኔታ ለመፍጠር እየተመኙ ክቡር ህይወታቸዉን ለገበሩላት ያገሬ ልጆች ማለትም ለ“ስዉአት” ክብር እንጋራለን።

211. በገነት ሁሌም ሀሴት፤ በገሀነም ሁሌም ሀዘን፤ በሁለቱ መሀከል በሆነችዉ ምድር ደግሞ ሁለቱንም እናገኛለን። ምድር ላይ በሁለት ተቃራኒ ነገሮች መሀከል ስለምንኖር ሁለቱንም እንቋደሳለን። እድል ተለዋዋጭ ነች እናም ሁሌም ደስታ ሆነ ሁሌም መከራ ብሎ ነገር የለም። ሕይወት ዜሮ እና በራሷ ምንም ባትሆንም ገነትን ስንጨምርባት ግን የበዛች ትሆናለች። ለእጣ ፋንታህ ግዴለሽ መሆን አስተዋይነት ሲሆን፤ በእጣ ፋንታህ አለመገረም ደግሞ ጠቢብነት ነዉ። ብዙ በቆየን ቁጥር ሕይወታችን ልክ እንደ ቲያትር እየተወሳሰበች ስለምትሄድ መደምደሚያዋ መልካም ይሆን ዘንድ ተጠንቀቅ።

212. ፍጹም ላቅ ያሉትን ችሎታዎችህን ለራስህ እንጅ ለሰዎች እንዳትገልጽ። ታላላቅ መምህራን ብልጠታቸዉን ሲገልጹ በብልጠት ነዉ። ለዚህ ምክንያቱ ይህን ካላደረጉ ታላቅ አስተማሪ ሆነዉ ሊቀጥሉ ስለማይችሉ ነዉ። ጥበብህን ስትገልጽ በጥበብ መሆን አለበት። የምትሰጠዉ ሆነ የምታስተምረዉ ነገር እንዳያልቅብህ ይሁን። ይህን ያደረግክ እንደሆን ሰዎችን ያንተ ጥገኛ ማድረግ ይቻልሃል ዝናህንም ጠብቀህ መዝለቅ ትችላለህ። ስታስተምር እና ለሰዎች የሚፈልጉትን ስትሰጥ የሰዎችን አድናቆት እያተረፍክ እና ልቀትህን በጥቂት በጥቂቱ በመግለጽ መሆን አለበት። ቁጥብነት ለማሸነፍ ሆነ ለመኖር ታላቅ መርህ ነዉ በተለይ ደግሞ እጅግ አስፈላጊ በሆኑ ጉዳዮች ላይ

213. መቃወምን እወቅበት። ይህ አንተ ሳትጠላለፍ ሌሎችን ግን ጥልፍልፍ ዉስጥ የምትከትበት እና ሆድ ያመላለሰዉን የምታናግርበት መንገድ ነዉ። ተቃዉሞ ሌላኛዉ ሰዉ ስሜቱን እንዲዘረግፍ ማድረጊያ መንግድ ነዉ። ጥርጣሬን ወይም አለመተማመንን መግለጽ ሰዎች በሆዳቸዉ የቋጠሩትን ሚስጥር ሽቅብ አስብሎ ማዉጫ ሲሆን፤ ይህ በጣም ሚስጥር ጠባቂ የሆኑ ሰዎችን ለማዉጣጣት ፍቱን የሆነ ዘዴ ነዉ። ታላቅ ብልጠት ከታከለበት የሰዎችን የማድረግ ፍላጎት ጥልቀት እና የማመዛዘን ችሎታ መፈተን ይቻላል። አንድ ሰዉ በማለባበስ ወይም ቅኔ አዘል በሆነ መንገድ የሚወረዉራቸዉን ቃላት በብልጠት ኣጣጥላቸዉ እና በሆዱ የያዛቸዉን ጥልቅ ሚስጥሮች ቀስ በቀስ እንዲተፋ ማድረግ ይቻልሃል። የአስተዋይ ሰዉ ቁጥብነት ሌሎችን ቁጥብነታቸዉን እንዲያጡ ያደርጋቸዋል። ይህ ደግሞ ለመመርመር ያስቸገረን ልብ ስሜት ለማወቅ ይረዳል። የፈለገችዉን ነገር ሁሉ ለማግኘት ስለምትችል በማለባበስ የምትወረወር ጥርጣሬ ነገርን ለማወቅ የምትረዳ ቁልፍ ነች። በትምህርት እንኳ ጎበዝ የሆነዉ ተማሪ መምህሩን በመቃወም በደንብ እንዲያስተምር እና ለእዉቀት ጠበቃ እንዲቆም ያደርገዋል

214. አንዴ ብትሞኝ፤ ሁለቴ ግን እንዳትሞኝ። አብዛኛዉን ጊዜ አንድ ስህተት ለማረም አራት ስህተቶችን እንሰራለን። አንድ ዉሸት ወደ ሌላ ያዉም ታላቅ ወደሆነ ዉሸት እንደሚያመራ ይነገራል፤ እነሆ ይህ አባባል ለሞኝነት ተግባርም ይሰራል። ስህተት ያለበት ነገር መከተል መጥፎ ሲሆን፤ ከዚህ የባሰው ደግሞ ይህን ስህተት መሸፈን አለመቻል ነዉ። ስህተት ማለት ባህሪዋ እንደ ግብር ነዉ፤ ከተከላከልካት ወይም ከጨመርክባት ክፍያዋም በዛዉ ልክ ያድጋል። ታላቅ የሚባለዉ ጠቢብ አንድ ስህተት ሊሰራ ቢችልም፤ ስህተቱን ግን አይደግማትም። እንዲሁ ስህተት ዉስጥም ሊገባ ይችል ይሆናል፤ ግን እግሮቹን አጣጥፎ ስህተት ላይ ኣይቀመጥም።

215. ድብቅ ኣላማ ያለዉን ሰዉ ተጠንቀቀዉ። ብልጣብልጥ ሰዉን የሚያጠቃ በማስቀየስ ነው። አንዴ ካስቀየሰ በኃላ ደግሞ ማጥቃት ቀላል ነው። እንዲህ አይነት ሰዎች የሚፈልጉትን ለማግኘት አላማቸዉን ይደብቃሉ፤ መጀመሪያ ለመሆን ደግሞ ሁለተኛ ሆነዉ ይቀርባሉ። የእነዚህ ሰዎች አላማ በደንብ የሚሳካዉ ሰዎች ትልማቸውን ያልደረሱበት እንደሆን ነዉ፣ ስለዚህ ዉጥናቸዉን በንቃት ተከታተል። ሰዎች አላማቸዉን የደበቁ ጊዜ ደግሞ አሰሳህን በደንብ አጠናክር። የሌሎች ዉጥን ዉስጥ ሰርገህ ልትገባ ይገባል፤ የሚፈልጉትን ለማግኘት ጅራታቸዉን ሲቆሉም በደንብ ተመልከት። እነዚህ ሰዎች የማይፈልጉትን እንፈልጋለን እያሉ አዙሪት መንገድን በመከተል የሚፈልጉትን ይቀልባሉ። ስለዚህ ለነዚህ ሰዎች የምትፈቅደዉን ነገር እወቅ፤ አንዳንዴም አላማቸዉን እንደደረስክበት እንዲያዉቁ ማድረግ መልካም ነዉ።

216. ራስህን መግለጽ ቻል፤ ራስህን ስትገልጽ ደግሞ እንዲሁ ሳይሆን ፍንትዉ አድርገህ መሆን አለበት። አንዳንድ ሰዎች በደንብ መጸነስ ቢችሉም ሲገላገሉ ግን አጉል ናቸዉ። መንፈስ እንደወለዳቸዉ የምንቆጥራቸዉ ሃሳቦች እና ዉሳኔዎች በጥራት ካልተገለጹ ለታዳሚ ሳይደርሱ ይቀራሉ። አንዳንድ ሰዎች እንደ ታላቅ ገንዳ ብዙ መጠጣት ቢችሉም የሚሰጡት ግን በጣም ጥቂት ሲሆን፤ ሌሎች ደግሞ ከሚሰማቸዉ በላይ ይናገራሉ። ዉሳኔ ለማድረግ ፍላጎትህ፤ ጥረት ደግሞ ለእዉቀትህ ታላቅ ስጦታዎች ናቸዉ። ጥርት ያለ እዉቀት ያላቸዉ ሰዎች ታዋቂ ሲሆኑ፤ ግራ የገባቸዉ ደግሞ ለመረዳት አስቸጋሪ በመሆናቸዉ ምክንያት ክብርን አግኝተዋል። በርግጥ ስድ ላለመሆን ሲባል አንዳንዴ ግልጽ አለመሆን መልካም ነዉ። ሆኖም ግን የምናወራዉ ነገር ለእኛ እራሱ ግልጽ ሳይሆንልን ለሚያዳምጠን ሰዉ እንዴት ግልጽ ሊሆንለት ይችላል?

217. እስከመጨረሻዉ አትዉደድ፤ እስከመጨረሻዉም አትጥላ። ጓደኞችህን ነገ በጣም አደገኛ ጠላቶችህ ሊሆኑ እንደሚችሉ እያሰብክ ቅረባቸዉ። ይህ ነገር ደርሶ የታየ ነገር ስለሆነ ቀድመህ ተዘጋጅበት እና ጓደኞችህ የከዱህ እለት አንተን በጽኑ የሚዋጉበትን መሳሪያ እንዳትሰጣቸዉ ይሁን። በተቃራኒዉ ደግሞ ለጠላቶችህ የዕርቅን በር እንዳትዘጋባቸዉ። ይህ ደግሞ የጨዋነት መንገድ በመሆኑ ከአደጋ የራቀ ነዉ። የመበቀል ሀሴት ብዙውን ጊዜ ወደ ስቃይ ሲያመራ፤ አንድን ሰዉ በመጉዳታችን የምናገኘዉ ደስታ ደግሞ ወደ ህመም ይቀየራል

218. አስቦ ከማድረግ ዉጭ ምንም ነገር በግትርነት እንዳትፈጽም። ማንኛዉም አይነት ግትርነት ስሜታዊነት የወለደዉ ነገር በመሆኑ ሁሌም በስህተት የተሞላ ነዉ። በሁሉም ነገር ጦርነትን ማወጅ የሚወዱ እና በሚሰሩት ሁሉ ሌላዉን ማሸነፍ የሚፈልጉ የአማጺነት ባህሪ የተጠናወታቸዉ ሰዎች አሉ። እነዚህ ሰዎች በሰላም መኖር የሚባል ነገር አያዉቁም፣ የመሪነት ቦታ የያዙ እንደሆን ደግሞ በጣም አደገኞች ናቸዉ። መንግስታቸዉን በአንጃ ይከፋፍሉ እና እንደ ህጻን ልጅ በታዛዥነት የሚያገለግሏቸዉን ሰዎች ሁሉ ወደ ጠላትነት ይቀይሯቸዋል። ሁሉንም ነገር መፈጸም የሚፈልጉት በድብቅ ሲሆን፤ ያገኙት ስኬት ሁሉ በራሳቸዉ ጥረት መሆኑ ይሰማቸዋል። ሌሎች ሰዎች ይህን እንቆቅልሽ የሆነ ባህሪያቸዉን የተረዱት ጊዜ በንዴት ይሞሉ እና የእነዚህን ትምክህተኞች ቁሳዊ ኣላማ ሁሉ ስለሚያደናቅፉት አንዳች ነገር እንኳ መፈጸም ያዳግታቸዋል። እናም ብቻቸዉን ምንም አይነት ችግርን መፍታት አቅቷቸዉ ሆዳቸዉ ሲያር ተመልካቾች ይደሰታሉ። እንዲህ አይነት አረመኔዎች የሚበጃቸዉ ስልጡኑን አለም ትቶ ከሰው በላዎች ጋር መኖር ነዉ። ምክንያቱም የሰዉ በላወች አረመኔነት ከእነዚህ አረመኔወች ሰዉ በላነት የተሻለ ስለሆነ ነዉ።

219. ምንም እንኳ ባሁኑ ዘመን ሳያታልሉ መኖር ባይቻልም፤ በአታላይነት እንዳትታወቅ ይሁን። ብልጣብልጥ ከመሆን ይልቅ አስተዋይ መሆን የተሻለ ነዉ። እያንዳንዱ ሰው ባግባቡ እንዲስተናገድ ቢፈልግም፤ ማንም ሰው ሌሎችን ባግባቡ ማስተናገድ አይፈልግም። ትህትናህ ወደ ተራነት እዉቀትህ ደግሞ ወደ አታላይነት እንዳይቀየር ተጠንቀቅ። በሽራቢነት (ቀበሮነት) ከመፈራት ይልቅ በጠቢብነት መከበር የበለጠ ነዉ። ትሁት ሰዎች ተወዳጅነትን ቢያተርፉም አብዛኛዉን ጊዜ እንደተታለሉ ናቸዉ። ዘዴኛነት እንደ አታላይነት ስለሚተረጎም ላቅ ያለዉ ዘዴኛነት ዘዴን መደበቅ ነዉ። ግልጽነት በወርቅ ዘመን ሲነግስ፤ አሁን ባለንበት በብረት ዘመን ደግሞ ብልጣብልጥነት ነግሷል። የሰዎችን እምነት ስለሚያስገኝ ችሎታ ያለዉ ሰው ነዉ መባል ክቡር ነገር ነዉ። ብልጣብልጥ ነዉ መባል ግን መጥፎ ስም ከመሆኑ በላይ በሰዎች ዘንድ ጥርጣሬን ያጭራል።

220. የአንበሳን ለምድ መልበስ ካቃተህ፤ የቀበሮን ለምድ ልበስ። ጊዜን መከተል ማለት ጊዜን መቅደም ነዉ። የምትፈልገዉን ካገኘህ ዝናህን ጠብቀህ መቆየት ትችላለህ። ጥንካሬ ካነሰህ፤ ዘዴን ተጠቀም። ከሁለት አንዱን ተጠቀም፤ ታላቅ የሆነዉን የብርታት መንገድ ወይም አቋራጭ የሆነዉን የዘዴኛነት መንገድ። እዉቀት ከጥንካሬ በላይ ብዙ ነገርን ይፈጽማል፤ ብልሆችም ብዙ ጊዜ አሸንፈዋል። ፈልገህ ያላገኘህዉን ነገር ልትጠላዉ ይገባል።


ጎበዝ፣ በብልህነት መንገድ እንጓዝ፣ ብልሆችም እንሁን! :mrgreen:

Meleket
Member
Posts: 1109
Joined: 16 Feb 2018, 05:08

Re: ‘የብልህነት መንገድ’ - ምርጥ መጠሓፍ በምርጥ ተርጓሚ - ይዘቷን እንካችሁ አጣጥሙ!

Post by Meleket » 15 May 2019, 09:34

ጎበዝ የዛሬዎቹን አስር የብልህነት መንገዶች ባገሬ በኤርትራ እንዲሁም ድንበር ሳይገታቸዉ በማንኛዉም አገር የሚኖሩ ሰዎች በያሉበትም አካፋና ዶማ ይዘዉ በተግባር መሬት ላይ ችግኞችን ለሚተክሉ የአለማችን ዜጎች በሙሉ ክብር እዚህ እንጋራለን። :lol: ይህን ስናደርግም ቆፍጣኖቹ ያገሬ ወጣቶች በሰርጋቸዉ ቀንም እድምተኞቻቸዉን ሁሉ አስከትለዉ እስከ 500 ችግኝ የመትከል ልማድን በተግባር እያሳዩ ይገኛሉ፣ በመሆኑም ከሰው ልጅ ክብር አልፈው የእጽዋት ክብርና ጥቅም ለገባቸዉ ያገሬ ወጣቶች እንዲሁም በዓለም ዙርያ ላሉ ሰዎች፣ እንስሶችና እጽዋት ሁሉ ክብር እነዚህ አስር የብልህነት መንገዶችን ስንካፈል የሃገራችን የኤርትራ ነጻነት “ወደቡንም ድንበሩንም” ሳይሸራረፍ ያስከበረ፣ ልዑላዊ መሬቱን አየሩንና ባሕሩንም ሙሉ በሙሉ የተቆጣጠረና ያስተዳደረ ይሆን ዘንድ ያለንን ሙሉ ተስፋ እየገለጥን ነው!! :mrgreen:

221. ራስህን ሆነ ሌሎችን አደጋ ውስጥ ልትጨምር ስለምትችል ግልፍተኛ አትሁን። አንዳንድ ሰዎች ለራሳቸዉ ሆነ ለሌሎች ክብር ጠንቅ ናቸዉ። እነዚህ ሰዎች ሁሌም ከሞኝነት አፋፍ ላይ ነዉ ያሉት። እንዲህ አይነት ሰዎች በቀላሉ ማግኘት ብንችልም መወዳጀቱ ግን በጣም ይከብደናል። በአንድ ቀን መቶ መበሳጫወች በቂያቸዉ አይደሉም። የተጠጉትን ሰው ሁሉ ከመቃረናቸዉ በላይ፤ ምንም የሚመቻቸዉ ነገር የለም። ሆኖም ግን ከሁሉም በላይ ትዕግስታችንን የሚፈታተኑት ምንም መልካም ነገር ሳይሰሩ ያገኙትን ሁሉ የሚያጣትሉ ሰዎች ናቸዉ። የቅሬታ ርስት በጣም ሰፊ ከመሆኑ በላይ በብዙ አዉሬወች የተሞላ ነዉ።

222. ጥንቃቄ የተሞላበት ማመንታት የአስተዋይነት ምልክት ነዉ። ምላስ የመንፈሳችን ትርታ ነች፤ እንደ ዱር አውሬ በመሆኗ ደግሞ አንዴ መስፈሪያዋን ከፍታ ከወጣች በኋላ መልሶ መያዝ በጣም ከባድ ነዉ። ጠቢቦች ጤነኝነታችንን ለመገምገም፤ ንቁዎች ደግሞ ልባችንን ለማዳመጥ ምላስን ይጠቀማሉ። የሚያሳዝነዉ ነገር በጣሙን መጠንቀቅ የሚገባቸዉ ሰዎች ግድ የለሽ መሆናቸዉ ነዉ። ጠቢቦች አደገኛ እና አስቸጋሪ ከሆኑ ነገሮች በመራቅ ራሳቸዉን መግዛት እንደሚችሉ ያሳያሉ

223. የግድየለሽነት ሆነ በልምሰል ባይነት ምክንያት ባህሪህ ወጣ ያለ እንዳይሆንየታላቅነት ምልክት ከመሆን ይልቅ የጎደሎነት ምልክት የሆኑ ግብታዊ ተግባሮችን በመፈጸም የታወቁ ወጣ ያለ ባህሪ ያላቸዉ ሰዎች አሉ። አንዳንድ ሰዎች የሚታወቁት ለየት ባለ የፊት ጉድፍ ሲሆን፤ ወጣ ያለ ባህሪ ያላቸዉ ሰዎች ደግሞ በሚያደርጉት ነገር ሁሉ ከልክ በማለፍ ይታወቃሉ። ወጣ ያለ ባህሪ ዝናህን ያጎድፈዋል። የብልግና ተግባር በተወሰኑ ሰዎች ዘንድ ሳቅን ሲቀሰቅስ በተቀሩት ደግሞ ብስጭትን ይፈጥራል።

224. የነገርን አያያዝ እወቅበት። በስለታቸዉ በኩል የሚሰጡህን ነገሮች በፍጹም እንዳትቀበል። ሁሉም ነገሮች ሁለት ገጽታ አላቸዉ። በስለቱ ከጨበጥከዉ መልካም የሚባለዉ ነገር ሳይቀር ይጎዳሃል፤ በእጀታዉ ከያዝከዉ ደግሞ በጣም አደገኛ የተባለዉ ነገር እንኳ መከታ ይሆንሃል። ብዙ ህመምን ያስከተሉ ነገሮች ያላቸዉ መልካም ጎን ቢታወቅ ኖሮ ሀሴትን ይፈጥሩ ነበር። ሁሉም ነገር መልካም እና መጥፎ ጎን ሲኖረው ጨዋታዉ ያለው ነገሮችን በመልካም ጎናቸዉ መጠቀሙ ላይ ነዉ። የአንድ ነገር ገጽታ እንደተመለከትንበት አቅጣጫ ይወሰናል። ስለዚህ ነገሮችን በመልካምነት ተመልከታቸዉ፤ መልካሙን ነገርም በክፉ አትለዉጠዉ። እነሆ ለዚህ ነዉ አንዳንድ ሰዎች ከሁሉም ነገር ደስታን ሲያገኙ ሌሎች ደግሞ ሀዘንን የሚያጭዱት። ይህ የመጥፎ እድል መከላከያ ሲሆን፤ ለመኖር ደግሞ በማንኛዉም ዘመን ሆነ በየትኛዉም ሙያ የሚያገለግል ታላቅ መርህ ነዉ

225. ዋናዉን እንከንክን እወቀዉ። ማንኛዉም ችሎታ እንከን ያለበት ሲሆን፤ ለዚህ እንከን ከተሸነፍክለት ደግሞ በአንተ ላይ ይነግስ እና መጫወቻ ያደርግሃል። ይህን እንከንህን ትኩረት በመስጠት ማዳከም ትችላለህ፤ ለይተህ ያወቅከዉ እንደሆን ደግሞ ማሸነፍ ትችላለህ። ለሚሰድቡህ ሰዎች የምትሰጣቸዉን ያህል ትኩረት ለእንከንህም ስጣት።ራስህን መግዛት ብትፈልግ ራስህን መርምር። ይህን ዋናዉን እንከንህን ካንበረከከዉ በኋላ ሌሎች ይከተላሉ

226. የሰዎችን ድጋፍ የምታገኝ ሁን። የብዙዎች አድራጎት ሆነ ወሬ የታይታ እንጅ ከዉስጣቸዉ የመነጨ ነገር አይደለም። ምንም እንኳ አንዳንዴ ለማመን የሚከብድ ቢመስልም መጥፎ ነገር በቀላሉ ስለሚታመን ማንም ሰዉ መጥፎ ነገርን ቢነግረን አምነን እንቀበላለን። እነሆ አለን የምንለዉ መልካም እና ታላቅ ነገር ሁሉ የተመሰረተዉ ሰዎች ስለኛ ባላቸዉ ክብር ነዉ። ምንም አንዳንዴ ሰዎች ትክክል በመሆናቸዉ ቢደሰቱም ጥንቃቄ ካልተጨመረበት ትክክለኝነት ብቻዉን በቂ አይደለም። ሌሎችን ማስደሰት ጥቂት ነገር ቢጠይቅም ዋጋዉ ግን ላቅ ያለ ነዉ። ተግባር የሚሸመተዉ በቃላት ነዉ። የፈለገ ታናሽ ቢሆንም በአለማችን ጓዳ በአመት ቢያንስ አንዴ እንኳ የማይፈለግ ነገር የለም፤ ዋጋዉ የፈለገ ታናሽ ቢሆን እንኳ ከሌለ መታጣቱ አይቀርም። ሰዎች ስለነገሮች ሲናገሩ ስሜታቸዉን እንደሚከተሉ አስታዉስ

227. ለመጀመሪያ እይታ እንዳትሸነፍ። አንዳንድ ሰዎች መጀመሪያ ከሰሙት ነገር ጋር ይጋቡ እና ዘግይቶ የደረሰባቸዉን ዉሽማ ያደርጋሉ። ሀሰት ሁሌም ቀድሞ ስለሚደርስ ዘግይቶ ለሚደርሰዉ እዉነት ቦታ አይገኝለትም። በማድረግ ፍላጎትህ ሆነ በእዉቀትህ ዘርፍ መጀመሪያ የተገለጸልህን ነገር እንዳትከተል፤ ይህን ብታደርግ ግብታዊ መሆንህን ታሳያለህ። አንዳንድ ሰዎች ጸባያቸዉ እንደ እንስራ ሲሆን፤ መጥፎ ይሁን መልካም የሚያስቡት መጀመሪያ የቀረበላቸዉን መጠጥ ነዉ። እናም ይህን ባህሪያቸዉን የሚያዉቁ ሰዎች ክፋትን ይሸርቡባቸዋል። አንድን ነገር ሁለት ጊዜ መመርመር ያስፈልጋል። ታላቁ አሌክሳንደር ለምሳሌ የሌላዉን ወገን ሀተታ በሁለተኛዉ ጆሮዉ ያዳምጣል።

228.አሉባልተኛ እንዳትሆን ተጠንቀቅእንዲሁ የሌሎችን ዝና በማርከስም እንዳትታወቅ ተጠንቀቅ፤ የሌሎችን ስም እያጎደፍክ ደግሞ ቀልድ አዋቂ እንዳትባል። ይህን ብታደርግ ሁሉም ሰዉ ይበቀልሃል፤ መጥፎ ነገርም ይወራብሃል፤ አንተ አንድ ራስህን ስትሆን ያስቀየምካቸዉ ሰዎች ግን ብዙ በመሆናቸዉ ምክንያት በቀላሉ ትሸነፋለህ። ሀሜተኛ ሰዉ ሁሌም የተጠላ ነዉ። ይህ ሰዉ ታላላቅ ሰዎችን ቢቀርብም ተቀባይነት የሚያገኘዉ ለመዘበቻነት እንጅ ለአስተዋይነቱ አይደለም። መጥፎ ነገርን የሚያወራ ሰዉ ከተናገረዉ የበለጠ መጥፎ ነገርን ይሰማል

229. ሕይወትህን በእቅድ ምራዉ። ይህ መሆን ያለበት በመቻኮል እና ግራ በመጋባት ሳይሆን አርቆ በማሰብ እና በማመዛዘን ነዉ። ሕይወት እረፍት ያልተጨመረባት እንደሆን በጣም አድካሚ ናት። ሕይወትን ጣፋጭ የሚያደርጋት የተለያዩ ነገሮችን መማር ነዉጣፋጭ ለሆነ ህይወት የመጀመሪያዉ ተግባርህ ከሙታን ጋር መነጋገር መሆን አለበትየተወለድነዉ እንድንማር እና ራሳችንን እንድናዉቅ ሲሆን፤ ወደ ሰዉነት ደረጃ የሚለዉጡን ደግሞ መጽሀፍት ናቸዉሁለተኛዉ ተግባርህ ደግሞ ከህያዋን ጋር ይሁን እና በዚህ አለም መልካም የተባለዉን ነገር ሁሉ ለማየት እና ለመገንዘብ መዋል አለበት። ሁሉም ነገር ባንድ አካባቢ ሊገኝ አይችልም። ፈጣሪ በረከቱን ሲያከፋፍል ብዙ ሀብትን የሰጣት መልከ ጥፉ ለሆነችዉ ልጅ ነዉ። ሶስተኛዉ ተግባርህ ግን ሙሉ በሙሉ የግልህ ሲሆን፤ ከሁሉም በላይ አስደሳች የሆነዉ ነገር ደግሞ መፈላሰፍ ነዉ

230. አይንህን በጊዜዉ ክፈት። የሚመለከቱት ሁሉ አይናቸዉን የገለጡ አይደሉም፤ እንዲሁ የሚያዩት ሁሉ እየተመለከቱ አይደለም። ነገርን ዘግይቶ መረዳት የሚያመጣዉ እፎይታ ሳይሆን ሀዘንን ነዉ። አንዳንዶች የሚታየዉ ነገር ሁሉ ካለቀ በኋላ ይባንኑና ቤታቸዉን እና የኔ የሚሉትን ነገር ሁሉ ካጡ በኋላ ማስተዋል ይጀምራሉ። ማስተዋልን ፍላጎት ለሌለዉ ሰው መስጠት ከባድ ሲሆን፤ የበለጠ ከባድ የሆነዉ ደግሞ ማስተዋል ለጎደለዉ ሰዉ ፍላጎትን መስጠት ነው። እንዲህ አይነት ግለሰቦችን ሰዎች ይከቡ እና መሳቂያ ያደርጓቸዋል። ጆሯቸዉ ለምክር የተደፈነ ሲሆን፤ አይኖቻቸዉን ደግሞ ለመመልከት አይጠቀሙባቸዉም። መኖር የቻሉት በዕዉርነታቸዉ በመሆኑ እዉርነትን የሚያበራታቱ አንዳንድ ሰዎች አሉ። ቆንጆ መሆን ስለማይችል ባለቤቱ አይን የሌለዉ ፈረስ ያልታደለ ነዉ

ጎበዝ፣ በብልህነት መንገድ እንጓዝ፣ ብልሆችም እንሁን!
:mrgreen:

Meleket
Member
Posts: 1109
Joined: 16 Feb 2018, 05:08

Re: ‘የብልህነት መንገድ’ - ምርጥ መጠሓፍ በምርጥ ተርጓሚ - ይዘቷን እንካችሁ አጣጥሙ!

Post by Meleket » 20 May 2019, 10:09

የዛሬ አስር የብልህነት መንገዶችን ሃገሬ ኤርትራን ከጭቆና ለማገላገል በቀና መንፈስ ከቤታቸዉና ከማጀታቸዉ ወጥተዉ በንጽሕና ለታገሉ ኤርትራዉያን ታጋዮች (አንበሶች) በሙሉ ክብር እንጋራለን። ይህን ስናደርግም ባለፉት ዘመናት ሁሉ ለዚህ ክቡር ዓላማ ከቤታቸዉ ወጥተዉ ያልተመለሱትን ማለትም የተሰዉትን የናቕፋ ኣንበሶች፣ የዓላ ኣንበሶች፣ የባረንቱ ኣንበሶች፣ የመስሓሊት ኣንበሶች፣ የአሶሳ አንበሶች፣ የኣፍዓበት ኣንበሶች፣ የምጽዋ ኣንበሶች፣ የደቀምሓረ ኣንበሶች፣ የሽሬ ኣንበሶች፣ የቤይሉል ኣንበሶች፣ የኣዉገት ኣንበሶች፣ የዓሰብ ኣንበሶች፣ የባድመ ኣንበሶች፣ የእግሪመኸል ኣንበሶች ወዘተ እያስታወስን፣ ሃገረ ኤርትራን ከምድር ገጽ መደምሰስ ከትላንት በስቲያ ሆነ ትላንት እንዳልተቻለ ሁሉ ዛሬም ነገም ከነገወዲያም ለዘለዓለሙ የማይቻል መሆኑን ‘ለኤርትራዉያን ኣንበሶች’ ማለትም ‘ለተሰዉት ታጋዮቻችን’ ዛሬም በ28ኛዉ የነጻነት በኣል ወቅት ዳግም እያረጋገጥን ነው። እንደሚታወቀዉ ሃገሬ ኤርትራ አንበሳ የምትለዉ ሕይወቱን ሳይሳሳ በተግባር ገብሮ መስዋእት የሆነላትን ዜጋ ብቻ ነው

231. ያላለቁ ነገሮችን ለሰው አታሳይ። ነገሮች ካለቁ እና ላቅ ካሉ በኋላ እንዲታዩ አድርግ። ሁሉም ጅማሬዎች ዉበት የለሽ በመሆናቸዉ መጨረሻ ላይ ለተመልካች የሚታየዉ ያ የተነሱበት ዉበት የለሽነታቸዉ ነዉ። አንድን ነገር ሳያልቅ ያየነዉ እንደሆን ካለቀ ኋላ የምናገኘዉን ደስታ ይቀንሰዋል። ትልቅ ነገርን በአንድ ጊዜ መመልቱ ያቀፋቸዉን ነገሮች እንዳናስተዉል ቢያደርገንም እርካታን ግን ይፈጥርልናል። አንድ ነገር ከመሆኑ በፊት ምንም አይደለም፤ እንዲሁ መሆን ሲጀምር እንኳ ላለመሆን የቀረበ ነዉ። እጅ ያስቆረጥማል የተባለዉን ምግብ እንኳ ሲዘጋጅ ማየት ያስመልሳል እንጅ የምግብ ፍላጎትን ኣይከፍትም። ታላላቅ የተባሉት መምህራን ስራቸዉ ጽንስ ላይ እያለ እንዳይታይ ያደርጋሉ። ከተፈጥሮ ተማር እና ስራዎችህ ዉበት እስኪጎናጸፉ ድረስ ለሰዎች አትሳይ።

232. ተግባራዊነትን ልትላበስ ይገባል። ሁሉም ነገር በመላምት መቅረት ስለሌለበት ተግባር አስፈላጊ ነዉ። የህይወትን ታላላቅ ጉዳዮች ቢያዉቅም ተራ የሆኑትን ነገሮች ስለማያዉቅ ጠቢብን ማታለል ቀላል ነዉ። ጠቢብ ታላላቅ ነገሮችን ሲያሰላስል ታናናሽ እና ቀላል የሆኑትን ጉዳዮች ይዘነጋል። በዚህ ምክንያት ሌሎች ምላጭ የሆኑበትን የኑሮ ዘዴ እርሱ ስለሚያቅተዉ ግብታዊ በሆኑት በመንጋዎች ዘንድ አንድም መሳለቂያ ሌላም መገረሚያ ይሆናል። ስለዚህ ብልህ ለማታለል ሆነ ለመዘበቻ የተመቸ እንዳይሆን ቢፈልግ ተግባራዊነትን ይማር። ምንም ታላቅ ነገር ባይሆኑ እንኳ አስፈላጊ በመሆናቸዉ ምክንያት ተራ የሆኑ የሕይወት ጉዳዮችን ማስፈጸም ቻል። ተግባራዊነት ያልተጨመረበት እዉቀት ምን ጥቅም አለዉ? እነሆ በዚህ ዘመን እዉነተኛ እዉቀት ማለት የኑሮ ዘዴን ማወቅ ነዉ

233. ሰዎች ስለሚፈልጉት ነገር እንዳትስት፣ ይህን ብትስት ከደስታ ይልቅ ስቃይን ትፈጥርባቸዋለህ። አንዳንዶች የሰዉን ባህሪ ስለማይረዱ ድጋፍን ለማግኘት ሲጣጣሩ ብስጭትን ይቀሰቅሳሉ። ተመሳሳይ ነገር ቢሆንም እንኳ አንዱን ያበሳጨዉ ሌላዉን ሊያስደስተዉ ስለሚችል ባልንጀራህን እጠቅም ብለህ ያደረግከዉ ጎጅ ሊሆን ይችላል። አንዳንዴ ሰዉን ከማስቀየም ይልቅ ማስደሰት ያላወቅክበት እንደሆን ዉለታህንና ስጦታህን ታባክናለህ። ባህሪዉን ያልተረዳኸዉን ሰዉ ልታረካዉ አትችልም። እናም ለዚህ ነዉ የአንዳንድ ሰዎች ያመሰገኑ እየመሰላቸዉ ግን እየተሳደቡ የሚገኙት፤ ይህ ደግሞ የሚገባ ቅጣት ነዉ። ሌሎች ደግሞ በአንደበተ ርቱዕነታቸዉ ያስደሰቱን እየመሰላቸዉ ግን መንፈሳችንን ይመርዙታል

234. ያንተ ክብር ያለዉ በሌላ ሰዉ እጅ ከሆነ የዚያ ሰዉ ክብርም ባንተ እጅ መሆኑን እርግጠኛ ሁን። እንዲሁ ብዙ የማዉራት ሆነ ዝም የማለት ጥቅሙ ሆነ ጉዳቱ ለሁለታችሁም መሆን አለበት። የክብር ነገር የተነሳ እንደሆነ ሁሉም ሰዉ ተቆርቋሪ ሊሆን ይገባዋል፤ እናም እያንዳንዱ ለራሱ ክብር ሲል የሌላዉን ክብር መጠበቅ ኣለበት። ለሌሎች ሚስጥር አለማካፈል የተሻለ ቢሆንም፤ ሚስጥርህን ካካፈልክ ግን ሚስጥረኛህ ሚስጥርህን የሚጠብቃት በአስተዋይነት ብቻ ሳይሆን በጥንቃቄም ጭምር እንዲሆን አድርግ። ሚስጥሩን ያወጣ እንደሆነ ደግሞ ኪሳራዉ ለሁለታችሁም መሆን አለበት፤ ይህ የሆነ እንደሆን ደግሞ ሚስጥረኛህ ሚስጥርህን የሚደብቃት ለራሱ ጥቅም ሲል ጭምር ይሆን እና በፍርድ ቤት ፊት እንኳ ባንተ ላይ መመስከር ይከብደዋል።

235. እንዴት መጠየቅ እንዳለብህ እወቅ። ይህ ነገር ለአንዳንዶች በጣም ከባድ ቢሆንም ለሌሎች በጣም ቀላል ነዉ። አይሆንም ማለትን ለሚያዉቁ ሰዎች ጥያቄህን ማቅረብ ብዙም ድካም የሚያስፈልገዉ ነገር አይደለም። ሌሎች ደግሞ ከመቅጽበት አይቻልም ስለሚሉ ብዙ መልፋት ያስፈልግሃል። እነዚህን ሰዎች መቅረብ ያለብህ ከመዝናኛ ድግስ የቆዩ ጊዜ እና መንፈሳቸዉ በታደሰበት ወቅት ነዉ። ይህ ሲባል በርግጥ አላማህን ለመረዳት ትኩረት አይሰጡም ብለን በማሰብ ነዉ። የደስታ ቀን የሚባሉት ደግሞ የሰዎች መልካምነት የሚገለጽባቸዉ ቀናት ናቸዉ። ባልንጀራህን አይሆንም ብለዉ እየመለሱት እያየህ ጥያቄህን እንዳታቀርብ ይሁን፤ ለዚህ ምክንያቱ በእንደዚህ አይነት ጊዜ ለእነዚህ ሰዎች አይቻልም ማለት ቀላል ስለሆነ ነዉ። በሀዘን ከተሞሉ ሰዎች ደግሞ ምንም ነገር ማግኘት አትችልም። ርካሽ ካልሆኑ እና ዉለታህን ለመመለስ ግድ የማይላቸዉ ካልሆነ በስተቀር ሰዎችን አስቀድመህ በዉለታህ ማሰር በጣም ጠቃሚ ነዉ።

236. ሽልማቱ የሚገባዉ ቢሆንም ዉለታ እንደዋልክለት አድርገህ ስጠዉ። ላንድ ሰዉ የሚገባዉን ከምናደርግለት ይልቅ ዉለታ ብንዉልለት ስልጡንነታችንን ያሳያል። በፍጥነት የሚዋሉ ዉለታወች በጣም ላቅ ያሉ ሲሆኑ፤ በቶሎ የተደረገ ነገር ደግሞ የተደረገለትን ሰዉ በዉለታ ያሰራል። ይህ ብልጠት የተሞላበት ግዴታን መወጫ መንገድ ነዉ። ይህ ሲሆን አንደኛዉ እዳዉን እየተወጣ እያለ ቢሆንም አበዳሪዉን ግን አዙሮ እዳ ዉስጥ ይከተዋል። ይህ ዘዴ ለጨዋዎች እንጅ ለወሮበላወች አይሰራም

237. ሚስጥርህን ለበላዮችህ እንዳታካፍል። ይህን ስታደርግ ፍሬዉን እየተካፈልክ ቢመስልህም እየተካፈልክ ያለኸዉ ግን ልጣጩን ነዉ። ብዙዎች የጠፉት ሚስጥራቸዉን በማካፈል ነዉ። እንዲህ አይነት ሰዎች ከዳቦ ድርቆሽ እንደሚሰሩ ማንኬያዎች ስለሆኑ ፍጻሜያቸዉ ፈጣን ነዉ። የልዑልን ሚስጥር መካፈል ሸክም እንጅ መልካም ነገር አይደለም። ብዙዎች መልከ ጥፉነታቸዉን የሚያሳያቸዉን መስታወት ይከሰክሱታል። በተመሳሳይ ሁኔታ መጥፎነታቸዉን የሚያስታዉሳቸዉን ሰዉ ደግሞ ማየት አይፈልጉም። ማንንም ቢሆን ታላቅ እዳ ዉስጥ ልትከተዉ አይገባም፤ በተለይ ደግሞ ታላላቅ ሰዎችን። እነዚህን ሰዎች ያንተ ልታደርጋቸዉ የሚገባህ አንተ ባደረግክላቸዉ ዉለታ እንጅ እነሱ ባደረጉልህ ዉለታ መሆን የለበትም። አደገኛ የሆኑት ነገሮች ደግሞ ለጓደኞቻችን የምነግራቸዉ ሚስጥሮች ናቸዉ። ለሌላ ሰዉ ሚስጥርህን አሳልፈህ የሰጠህ ጊዜ የዚያ ሰዉ ባሪያ ትሆናለህ። ይህ ነገር በተለይ በልዑላን ዘንድ ምንም ተቀባይነት የለዉም፤ ለዑል ያጣትን ነፃነቱን ለማስመለስ ሲል መልካምነትን እና ምክንያታዊነትን ጨምሮ ሁሉንም ነገር ከመደፍጠጥ ወደ ኋላ ኣይልም። ስለዚህ የራስህን ሚስጥር አለመናገር ብቻ ሳይሆን የሰዉንም ሚስጥር አትስማ

238. የጎደለህን ነገር እወቅ። አንዳንዶች የጎደላቸዉን ነገር ቢያገኙ ኖሮ ወደ ታላቅነት ደረጃ ይሸጋገሩ ነበር። እንዲሁ ሌሎች ደግሞ ያለችባቸዉን ትንሽ ጉድለት ቢያርሙ ኖሮ ከፍ ወዳለ ደረጃ ይሸጋገሩ ነበር። አንዳንድ ሰዎች ቅንነት ይጎድላቸዉ እና ተሰጥኦዋቸዉን ያደበዝዙታል፤ ሌሎች ደግሞ በተለይ ስልጣን የያዙ ጊዜ ጨዋነት ይጎድላቸዉ እና የቤተሰቦቻቸዉ ልብ በቶሎ ይነካል። አንዳንድ ሰዎች ቅልጥፍና የተሞላበት አፈጻጸም ሲጎድላቸዉ ሌሎች ደግሞ ቆሞ ማሰላሰል ይጎድላቸዋል። ጥንቃቄ ልማድን ሊቀይር ስለሚችል እነዚህ ሰዎች ጉድለቶቻቸዉን ቢገነዘቧቸዉ በቀላሉ ሊያርሟቸዉ ይችላሉ

239. ከልክ በላይ ብልጣብልጥ አትሁን። ከብልጣብልጥነት ይልቅ ጠቢብነት የበለጠ ነዉ። ከልክ በላይ ጮሌ የሆንክ እንደሆን ወይ ነገር ትስታለህ ወይም ደግሞ ነገር ታበላሻለህ። ይህን ነዉ እንግዲህ የተለመደዉ የብልጣብልትነት እጣ ፋንታ። አመዛዛኝነት ከችግር የራቀ ነዉ። አዋቂ መሆን መልካም ቢሆንም፤ ፀጉር ሰንጣቂነት ግን መልካም ነገር አይደለም። ከልክ በላይ ምክንያታዊ መሆን እንደ ክርክር ስለሚቆጠር የሚያስፈልገዉን ያህል ምክንያት ብቻ የሚጠቀም አመዛዛኝነት የተሻለ ነዉ

240. አላዋቂ መምሰልን እወቅበት። አንዳንዴ ታላቁ እዉቀት የማያዉቁ መስሎ መቅረብ የሚሆንበት ጊዜ አለ። ይህን መርህ ታላላቅ ጠቢቦች እንኳ ይጠቀሙበታል። በእንደዚህ አይነት አጋጣሚወች ደደብ መምሰል እንጅ ደደብ መሆን ግዴታህ አይደለም። ጥበብ ለቂሎች ምናቸዉም አይደለችም። እናም እያንዳንዱን ሰዉ እንደ ምላሱ አናግረዉ። ጥበብ ባለበት ሞኝነት ስለሌለ ሞኝ ማለት ሞኝ መስሎ የሚቀርበዉ ሳይሆን በትክክል ሞኝ የሆነዉ ሰዉ ነዉ። በሌሎች ዘንድ ለመወደድ ብትፈልግ የአህያን ለምድ ለብሰህ ቅረብ

ጎበዝ፣ በብልህነት መንገድ እንጓዝ፣ ብልሆችም እንሁን!
:mrgreen:

Meleket
Member
Posts: 1109
Joined: 16 Feb 2018, 05:08

Re: ‘የብልህነት መንገድ’ - ምርጥ መጠሓፍ በምርጥ ተርጓሚ - ይዘቷን እንካችሁ አጣጥሙ!

Post by Meleket » 23 May 2019, 03:50

የዛሬዎቹን አስር የብልህነት መንገዶች ኤርትራ ህዝብ ክብር እንጋራዋለን፤ ወንድም የሆነዉ የኢትዮጵያ ህዝብንም በዚህ በኤርትራ የነጻነት ቀን በወንድማዊ የሃሴት መንፈስ የደስታችን ተጋሪ እንዲሆን ስንጠይቅ ወጣቱን ጠቅላይም “እንትናን አያረሳሱን፣ ባገራችን ልዑላዊ መሬት ውስጥ ያለዉን ያገርዎን ሰራዊት ያዉጡ፣ ልዑላዊ መሬታችንን በሙሉ እናስተዳድርበት፣ ያገርዎ 'ቦለቲከኞች' የወረሱትን የንጹሓን ኤርትራዉያንን ንብረትም መልሱ ወይ ካሱ” እያልን አሁንም ደግመን ደጋግመን ዋናዉ ጉዳያችን እንዳይድበሰበስ ልናስታዉሳቸዉ እንወዳለን። :mrgreen: ይህን ስናደርግም ጋዜጠኛዉን ኤልያስ ክፍሌን ማንም እንደልቡ እዚህ መጥቶ እንዲፈነጭ ‘ይሉኝታቢሶችና ክፍትኣፎችም’ ሰው ይታዘበናል ሳይሉ እንዳሻቸዉ እንዲሰዳደቡ ሳይቀር ሙሉ እድልና መብት በመስጠቱ እጅግ እያመሰገንን፣ የብልግና ተሳዳቢዎችን ቖንጠጥ እንዲያደርግ እየመከርን ነው። አያይዘንም ይህን ምርጥ የባልታሳር ግራሽያንን መጠሐፍ እንድንጋራ በምርጥ አማርኛ መጠሓፉን የተረጎመዉን አያሉ አክሊሉንም፡ “የናንተ አይነቶችስ ይብዙልን፣ ኑሩልን እደጉ ተመንደጉ” እያልን ደግመን ደጋግመን እጅግ እያመሰገንና እየመረቕን ነዉ። እነ ‘እንቶኔን’ ግን መፈጠራቸዉንም ረስተናል መሰል! :mrgreen:

241 ሲቀልድቡህ ቻለዉ፤ አንተ ግን በሌሎች ላይ እንዳትቀልድ። የመጀመሪያዉ ትህትና ቢሆንም ሁለተኛዉ ግን ችግር ውስጥ ይጨምርሃል። ፌሽታ ላይ መጥፎ ቀልድ የሚወረዉር ሰዉ ከምናስበዉ በላይ አዉሬነት የተጠናወተዉ ነዉ። ላቅ ያሉ ቀልዶች አስደሳች ሲሆኑ፤ እንዲህ አይነት ቀልዶችን ማስተናገድ መቻል ደግሞ የችሎታ ምልክት ነዉ። የተናደድክ መስለህ የታየህ እንደሆን ሰዎች የበለጠ እንድትናደድ ጥረት ያደርጋሉ። ቀልድን ደግሞ ማቆም የሚያስፈልግባቸዉ ጊዜያት አሉ። አደገኛ የሚባሉ ችግሮች መነሻቸዉ ዘበት በመሆኑ እንደ ቀልድ ጥንቃቄን የሚጠይቅ ነገር የለም። እናም ቀልድ ከመጀመርህ በፊት አንድ ሰዉ ምን ያህል ሊያስኬድህ እንደሚችል እወቅ።

242 ጅምርህን ዳር አድርሰዉ። አንዳንድ ሰዎች ለመጨረስ ምንም ሳይጨነቁ ለመጀመር ግን የማይፈነቅሉት ድንጋይ የለም። ይጀምራሉ ግን አይጨርሱም፤ እነሆ እንዲህ አይነት ሰወች እንቆቅልሽ ናቸዉ። ምስጋናን የማያገኙት ደግሞ መጨረስ ስለማይችሉ ነዉ። ለእነዚህ ሰዎች ሁሉም ነገር የሚያልቀዉ ከመደምደሚያዉ በፊት ነዉ። ቤልጅጋዊዉ በትዕግስቱ እንደሚታወቀዉ ሁሉ እስፓኛዊዉ ደግሞ በችኩልነቱ የታወቀ ነዉ። ቤልጅጋዊዉ ጉዳዩን ሲፈጽም፤ እስፓኛዊዉ ጀምሮ ይተዋል። የሁለተኛዉ ለጊዜዉ እንቅፋቱን እስኪያልፍ ድረስ ብዙ ይለፋል ሆኖም ግን ምንም ጉዳዩን ማሸነፍ ቢያስደስተዉም እስከመጨረሻዉ ድል ማድረስን አያዉቅበትም። እናም የማድረግ ችሎታ እንዳለዉ ቢያስመሰክርም ማድረግ ግን አይፈልግም። እንዲህ ኣይነት ባህሪ የሚያሳየዉ በችኮላ መጀመርን ወይም ተለዋዋጭነትን በመሆኑ ሁሌም ደካማ ጎንን ያሳያል። እነሆ መጀመር ያለበት ነገር ከሆነ የሚጠናቀቅ ነገርም መሆን አለበት፤ ፍፃሜ መድረስ የማይገባዉ ከሆነ ለምን ቀድሞዉኑ ተጀመረ? ጠቢቦች ታዳኙን ማሳደድ ብቻ ሳይሆን በትክክል ያድኑታል።

243 ሁሌም እርግብ አትሁን። የእርግብን የዋህነት ከእባብ መሰሪነት ጋር እያቀያየርክ ተጠቀም። ዉሸትን የማያዉቅ ሰዉ ሌሎች የሚነግሩትን በቀላሉ ይቀበላል፤ ማታለልን የማያዉቅ ደግሞ ሌሎችን ያምናል፤ ለዚህም ነዉ መልካም ሰዉን ማታለል ቀላል የሆነዉ። አንዳንዴ መልካምነትን ሊያሳይ ስለሚችል መሞኘት ሁሌም የሞኝነት ምልክት አይደለም። ሁለት አይነት ሰዎች አደጋን ቀድሞ ማሽተት ይችላሉ፤ አንደኛዉ ከራሱ ስህተት የተማረ ሰዉ ሲሆን፤ ሁለተኛዉ ደግሞ ከሌሎች ስህተት የተማረ ነዉ። ከገባህበት አደጋ ራስህን ማዉጣት ብቻ ሳይሆን አደጋዉን ቀድመህ መተንበይን ጭምር ማወቅ አለብህ። በጣም መልካም ከሆንክ ለሌሎች መጥፎ የመሆን እድልን ትከፍትላቸዋለህ። ስለዚህ በግማሹ የእባብን በግማሹ ደግሞ የእርግብን ባህሪ ያዝና አዉሬ ሳይሆን ባለተሰጥኦ ሁን።

244 ሌሎችን በዉለታ እሰራቸዉ። አንዳንድ ሰዎች ራሳቸዉን እየጠቀሙ ሌሎችን የሚጠቅሙ ይመስላሉ። እንዲሁ የሰጡ እየመሰሉ ለራሳቸዉ ይወስዳሉ። ሌሎች ደግሞ ብልጥ ከመሆናቸዉ የተነሳ ለራሳቸዉ እየጠየቁ ሰዉን ያከበሩ ይመስላሉ፤ ራሳቸዉን ጠቅመዉ ደግሞ ሌሎችን ያከበሩ ይመስላሉ። ቅሉ ሌሎች እየሰጧቸዉ ቢሆንም የሰዎችን ትህትና በመጠቀም ሰጭዎች ግዴታቸዉን እየተወጡ እንዲመስል ያደርጋሉ። እናም ከልክ በላይ ብልጥ ከመሆናቸዉ የተነሳ ማን ምን እንደሰጠና ማን ምን እንደተቀበለ ለመለየት እስኪያስቸግር ድረስ ነገሮችን ያዘበራርቋቸዋል። በቀላል አድናቆት ደግሞ ምርጥ የተባለዉን ነገር ይገዛሉ። አንድ ነገር እንዳስደሰታቸዉ በመግለጽ ደግሞ ሽንገላን እና ክብርን ያሳያሉ። እንዲሁ የሰውን ይሉኝታ በመጠቀም እነሱ እራሳቸዉ ስለተደረገላቸዉ ነገር ማመስገን ሲገባቸዉ ሌሎች ዉለታ የተዋለላቸዉ እንዲመስል ያደርጋሉ። እንደዚህ አይነት ሰዎች ግዴታ የሚባለዉን ነገር በብቃት በመጠቀም ከሰዋስዉ ባለሙያነት ይልቅ የተሻሉ ፖለቲከኞች መሆናቸዉን ያሳያሉ። እነሆ ይህ ተግባር ታላቅ ብልጠት ነዉ። እንዲህ የሚያደርግን ሰዉ መያዝ ብሎም የሰጠንን ክብር መመለስ እና የወሰደዉን ጥቅም ማስመለስ መቻል የበለጠ ላቅ ያለ ብልጠት ነዉ።

245 አንዳንዴ ከተለመደዉ ወጣ ብለህ ማሰብ አለብህ። ይህ ታላቅ ችሎታን ያሳያል። አንተን ሳይሆን ራሱን እንደሚወድ የሚያሳይ በመሆኑ የማይቃወምህን ሰዉ ትልቅ አድርገህ ልትቆጥረዉ አይገባም። በፍጹም በሽንገላ እንዳትሞኝ፤ ሽንገላን ገስጻት እንጂ እንዳታበረታታት። ስለመልካም ሰዎች መጥፎን በሚያወሩ ሰዎች መታማትን ደግሞ እንደክብር ልትቆጥረዉ ይገባል። ታላቅነት ለጥቂቶች ብቻ የተገባ በመሆኑ ነገርህ ሁሉንም ሰዉ ያስደስትልኝ በማለት ጭንቀት እንዳይገባህ።

246 ሳትጠየቅ ማብራራያ ኣትስጥ። ማብራሪያ ብትጠየቅ እንኳ በችኮላ መስጠት ቂልነት ነዉ። ጤነኛ እያለህ ገላህን መብጣት ራስን ለበሽታ መጋበዝ እንደሆነዉ ሁሉ ሳትጠየቅ ገለጻን መስጠት ደግሞ ራስን እንደመወንጀል ይቆጠራል። ቀድሞ ማብራሪያ መስጠት በሰዎች ዘንድ አላስፈገላጊ ጥርጣሬን ይቀሰቅሳል። በምን ችግር ልፍጠር እንደማለት ስለሆነ አስተዋይ ሰዉ የባልንጀሮቹን ጥርጣሬ ግብረገብነትን በተሞላ መንገድ ለማስቀየስ መሞከር እንጅ ሊንበረከክ አይገባዉም።

247 በጥቂት በጥቂቱ እወቅ፤ አነስ አድርገህ ኑር። አንዳንዶች ደግሞ ተቃራኒዉን እንድናደርግ ይመክሩናል። በእዉነት ከጊዜ ዉጭ የኛ ነዉ የምንለዉ አንዳች ነገር የለም። ምንም ነገር ባይኖረን እንኳ ጊዜ ይኖረናል። ሕይወት በጣም ዉድ ነገር በመሆኗ ከልክ በላይ አድካሚ በሆኑ ተግባሮች ወይም ታላላቅ ጉዳዮች ላይ ልናዉላት አይገባም። ስለዚህ ከልክ በላይ በቅናት ሆነ በስራ የተጠመድክ እንዳትሆን፤ ይህን ብታደርግ ሕይወትህን ታላግጥባታለህ መንፈስህንም ታስጨንቃታለህ። አንዳንድ ሰዎች ይህ አባባል ለእዉቀትም ይሰራል ቢሉም አንድ ሰዉ ካላወቀ መኖር ስለማይችል አባባሉ ትክክል አይደለም።

248 በአዳዲስ ነገሮች ልብህ እንዳይሰረቅ። ስድነት ወደ ነገሮች ልኬታ ጫፍ መድረስ ስለሚወድ በቅርቡ የሰሙትን ማመን የሚወዱ ሰዎች አሉ። ሌላኛዉ ስህተት ደግሞ መጀመሪያ የሰሙትን ማመን ነዉ። የነዚህ ሰዎች ፍላጎት የተሰራዉ ከሰም በመሆኑ “አዲስ” የተባለዉ ነገር ልባቸዉን ይሰርቀዉ እና ቀደም ብሎ የመጣዉን ነገር ሁሉ አሽቀንጥረዉ ይጥሉታል። እንዲህ አይነት ሰዎች ሁሉንም ነገር በፍጥነት ስለሚተዉት ምንም ነገር ማስቀረት አይችሉም። ማንኛዉም ሰዉ ደግሞ የፈለገዉን ቀለም ይቀባቸዋል። እነዚህ ሰዎች እድሜልካቸዉን ህጻንነት የተጠናወታቸዉ በመሆኑ ለሚስጥረኛነት የተመቹ አይደሉም። በዚህ የስሜት ተለዋዋጭነታቸዉ ምክንያት ደግሞ በማመዛዘን እና በሀሳብ ዥዋዥዌ ይዘፈቁ እና እድሜ ልካቸዉን ሰንካላ ሆነዉ ይቀራሉ።

249 ከህይወት ማብቂያ ላይ መኖር እንዳትጀምር። አንዳንዶች በደስታ ይጀምሩ እና ጭንቀትን ለነገ ያቆዩታል። ትክክል የሆነዉ ተርታ ግን ዋናዉን ነገር ማስቀደም እና ድጋፍ ሰጪዉን ማስከተል ነዉ። አንዳንዶች ደግሞ ሳይገጥሙ ማሸነፍ ይፈልጋሉ። እንዲሁ ሌሎች ሰዎች ደግሞ ጥቃቅን የሆኑ ነገሮችን መጀመሪያ ይማሩ እና ጠቃሚ የሆነዉን እና ዝና የሚያቀዳጃቸዉን ትምህርት ወደ ህይወታቸዉ መጨረሻ ይገፉታል። ሌላኛዉ ደግሞ ልክ መልካም እድል ሊዘንብለት ሲል ከቦታዉ ይሰወራል። ስለዚህ ለመማር ሆነ ለማወቅ ዘዴን መጠቀም አስፈላጊ ነዉ።

250 ተቃራኒዉን ማሰብ ያለብን መቸ ነዉ? በክፉ ያናገሩን ጊዜ ነዉ። አንዳንዶች ሁሉንም ነገር ተቃራኒ ያደርጉት እና እሽ እንቢ፤ እንቢ ደግሞ እሽ ይሆናል።አንድን ነገር ካጣጣሉት ደግሞ ያመሰግኑታል ማለት ነዉ። ነገሩን ለራሳቸዉ ስለሚፈልጉት ለሌሎች ያጣጥሉባቸዋል። ስለዚህ ሁሉም አድናቆት መልካም አስተያየትን ያዘለ አይደለም። አንዳንድ ሰዎች ደግሞ መልካሙን ነገር ላለማመስገን ሲሉ መጥፎዉን ያመስግናሉ። እነሆ መጥፎዉን መለየት ያልቻለ ሰዉ መልካሙንም ሊለይ አይቻለዉም።


ኤርትራዉያን በሙሉ እንዲሁም ኣፍቃሬ ኤርትራዉያንም ጭምር እንኳን ላገሬ የነጻነት በዓል ፈጣሪ በሰላም አደረሰን!!!
ጎበዝ፣ በብልህነት መንገድ እንጓዝ፣ ብልሆችም እንሁን! :mrgreen:

Abaymado
Member
Posts: 3282
Joined: 27 Sep 2017, 21:56

Re: ‘የብልህነት መንገድ’ - ምርጥ መጠሓፍ በምርጥ ተርጓሚ - ይዘቷን እንካችሁ አጣጥሙ!

Post by Abaymado » 23 May 2019, 08:53

ይሄን ምክር የሚከተሉ ሁሉ ሽባ መሆን አለባቸው:: ሁሉንም ሰው እየመከረ እንዴት ሁሉንም ጮሌ : አራዳ : መሪ ሊያረግ ይችላል:: አንድ ሰው የራሱ መመርያ መንገድ አለው: ሌላው የሚሄድበት መንገድ ለእሱ አይሆንም:: ይሄ ሰው(ፀሐፊው ) ይሄን ሁሉ ምክር ከየት ነው ያመጣው? ከራሱ ተሞክሮ ወይስ ከየት?
የዛሬ ሶስት መቶ ዓመት የነበረ ህይወት አሁን ሊሰራ ይችላል?

Meleket
Member
Posts: 1109
Joined: 16 Feb 2018, 05:08

Re: ‘የብልህነት መንገድ’ - ምርጥ መጠሓፍ በምርጥ ተርጓሚ - ይዘቷን እንካችሁ አጣጥሙ!

Post by Meleket » 25 May 2019, 03:45

Abaymado wrote:
23 May 2019, 08:53
ይሄን ምክር የሚከተሉ ሁሉ ሽባ መሆን አለባቸው::
ምክሩን የማይከተሉትስ? :lol:
Abaymado wrote:
23 May 2019, 08:53
ሁሉንም ሰው እየመከረ እንዴት ሁሉንም ጮሌ : አራዳ : መሪ ሊያረግ ይችላል::
መች ሁሉን ሰዉ ሆነና የሚመክረዉ፣ የሚከተሉትን እንጂ! :lol: ደራሲዉ ደግሞ "ሰዉን ሁሉ ጮሌ፣ አራዳ፣ መሪ ማድረግ እችላለዉ" አላለም እኮ፤ ይልቅስ በእይታዉ የብልህነት መንገድን ነው መጠቆም የሞከረዉ። :mrgreen:
Abaymado wrote:
23 May 2019, 08:53
አንድ ሰው የራሱ መመርያ መንገድ አለው: ሌላው የሚሄድበት መንገድ ለእሱ አይሆንም::
እርግጥ ነዉ ላንዱ 'የብልህነት መንገድ' ሆኖ የሚታየዉ፡ ለሌላኛዉ 'የሽባነት መንገድ' ሆኖ ሊታየዉ ስለሚችል፣ ያንዱ መንገድ ለሌላኛዉ ተመራጭ መንገዱ ላይሆን ይችላል!!! :lol:
Abaymado wrote:
23 May 2019, 08:53
ይሄ ሰው(ፀሐፊው ) ይሄን ሁሉ ምክር ከየት ነው ያመጣው? ከራሱ ተሞክሮ ወይስ ከየት?
ወዳጄ “ይሄ ሁሉ ምክር” መሆኑ ገብቶሃላ!!! ከየት እንዳመጣዉማ “የትም ፍጪዉ ዱቄቱን አምጪዉ” ሲባል አልሰማህም ማለት ነዉ! :mrgreen:
Abaymado wrote:
23 May 2019, 08:53

የዛሬ ሶስት መቶ ዓመት የነበረ ህይወት አሁን ሊሰራ ይችላል?
እንዴ ዴ ዴ! ይሄንማ የሚያውቁት ብልሆች ብቻ ናቸው እኮ! እስቲ አሁን የመጨረሻዋን ምክር ደግሜ ላጣጥማት!!!

ኤርትራዉያን በሙሉ እንዲሁም ኣፍቃሬ ኤርትራዉያንም ጭምር እንኳን ላገሬ የነጻነት በዓል ፈጣሪ በሰላም አደረሰን!!!
ጎበዝ፣ በብልህነት መንገድ እንጓዝ፣ ብልሆችም እንሁን!
:mrgreen:

Meleket
Member
Posts: 1109
Joined: 16 Feb 2018, 05:08

Re: ‘የብልህነት መንገድ’ - ምርጥ መጠሓፍ በምርጥ ተርጓሚ - ይዘቷን እንካችሁ አጣጥሙ!

Post by Meleket » 06 Jun 2019, 08:35

ጎበዝ የዛሬዎቹን 10 የብልህነት መንገዶች ፋሽስት ጣልያንን ቁምስቅል በማሳጣት፡ ሆድ አደር ባንዶችንና ኃይለሥላሴንም ሆነ መኳንንቶቻቸዉን በግልጽ በመተቸት፡ የወቅቱን የጦቢያን ሁኔታ በብስለት በመተንተን ለኅሊናው ሲል ለኖረው አንድ ኤርትራዊ ድንቅ አባት አርበኛ ክብር እንካፈለዋለን። ይህ ተስፋሚካኤል ትኩእ የተባለዉ አርበኛ ከመብራህቱ (ሎሬንሶ) ታእዛዝ ጋር ባንድላይ ፊደል ቆጥሮ ተምሮ ቀጥሎም በኤርትራ፣ በሱማሌ፣ በሊቢያ፣ በኢጣልያ፣ በኢትዮጵያና በሱዳን ድንቅ ታሪክን የሰራ የዛሬ መቶ አመት የነበረን የፖለቲካ ሁኔታ ልብ በሚመስጥ አኳኋንና ፖለቲካዊ ብስለት “ሃገሬ የህይወቴ ጥሪ” በሚል አርእስት ታሪኩን ጽፎ ለመጭው ትውልድ ያበረከተ “ርእሰ መዃንንንት” የሆነ ጀግናችንን እየዘክርን እንካፈለዋለን። :lol: ይህንን ስናደርግም አሁን በግዚያችንም ታሪክ ሰርተናል ብለው ግን ደግሞ ታሪካቸዉን በተገቢዉ ሁኔታ ያልጻፉ አካላትን መነቃቃት እንደሚገባቸው ከአባት አርበኛዉ ከተስፋሚካኤል ትኩእ ታሪክን መዝግቦ ማለፍ ያለዉን ፋይዳ መማር እንደሚገባቸዉም እያስገነዘብን ነዉ። :mrgreen:

251. ሰብኣዊ የሆነዉን ነገር መለኮታዊ ነገር እንደሌለ አድርገህ፤ መለኮታዊ የሆነዉን ነገር ደግሞ ሰብአዊ ነገር እንደሌለ አድርገህ ተጠቀምበት። ይህን ምክር የሰጠን ታላቅ መምህር (የእየሱሳዊያንን ማህበር የመሰረተዉ የልዩላዉን ቅዱስ ኢግናጢየስ ነው) ሲሆን ምክሩ ምንም ማብራሪያ አያስፈልገዉም

252. ሙሉ በሙሉ ለራስህ ብቻ ሳይሆን ሙሉ በሙሉ ለሌሎችም አትኑር። ሁለቱም በስድነት የተሞሉ ስቃዮች ናቸዉ። ሙሉ በሙሉ የራስህ ብቻ ከሆንክ ሁሉንም ነገር ለኔ ትላለህ። እንዲህ አይነት ሰዎች ጥቃቅን በሆኑት ነገሮች እንኳ ለመሸነፍ አይፈልጉም ወይም ምቾታቸዉ በጥቂቱ እንኳ እንዲቀንስ አይፈቅዱም። እጣ ፈንታቸዉን ተስፋ እያደረጉ ደግሞ ሀሰት በሆነ የራስ መተማመን ይሞላሉ። ሆኖም ግን አንዳንዴ ሌሎች ለኛ ይሉ ዘንድ እኛም ለሌሎች ማለት መልካም ነገር ነዉ። የህዝብ ስልጣን ከያዝክ የህዝብ አገልጋይ ልትሆን ይገባል። ይህ ካልሆነ ስልጣኑን ከነኮተቱ ልቀቅ። ሞኝነት ከልክ በላይ ማለፍ ስለሚወድ አንዳንዶች ሙሉ በሙሉ ለሰዎች ያድሩ እና አሳዛኝ የሆነ የሞኝነት ተግባር ይፈጽማሉ። እነዚህ ሰዎች ራሳቸዉን ሙሉ በሙሉ ለሌሎች ሰዉተዉ ያርፉና የኛ ነዉ የሚሉት ቀን ቀርቶ የእኛ ነዉ የሚሉት ሰአት እንኳ የላቸዉም። አንዳንድ ሰዎች ደግሞ ለሌሎች ብዙ እያወቁ ለራሳቸዉ ግን ምንም ስለማያዉቁ ቀደም ብለዉ ከተጠቀሱት ሰዎች ጋር ተመሳሳይነት አላቸዉ። አስተዋይ ብትሆን ሰዎች የሚፈልጉህ ላንተ ሳይሆን ለራሳቸዉ ጥቅም መሆኑን ትረዳለህ። በዚህ ምክንያት ትኩረታቸዉ ያለዉ ልታደርግላቸዉ ከምትችለዉ ነገር ላይ ነዉ።

253. ሀሳቦችህን ፍጹም ግልጽ አታድርጋቸዉ። ብዙ ሰዎች የሚያዉቁትን ነገር ይንቁታል፤ ለመረዳት የሚከብዳቸዉን ግን ያከብሩታል። ነገሮች በሰዎች ዘንድ ዋጋ እንዲያገኙ ከተፈለገ አስቸጋሪ መሆን አለባቸዉ። ሰዎች ሊረዱህ ካልቻሉ ከበሬታን ይቸሩሀል። ከበሬታን ለማግኘት ብትፈልግ አብሮህ ከሚሰራዉ ባልንጀራህ ጋር ለመስራት ከሚያስፈልግዉ በላይ እዉቀት እንዳለህ ሆነህ ቅረብ። ይህን ስታደርግ ግን ከልክ እንዳታልፍ ተጠንቀቅ። ለአስተዋይ ሰዎች ጠቢብነት ሁሉም ነገር ቢሆንም ከዚህ ዉጭ ላሉት ግን የተናገርከዉን ለመረዳት ሲፍጨረጨሩ ለነቀፋ ጊዜ እንዳያገኙ ለማድረግ ተናጋሪ ልትሆን ይገባል። ይህ ሲሆን ብዙወች ምክንያት ማቅረብ ባይችሉም አድናቆታቸዉን ይቸራሉ። ሰዎች ሚስጥራዊ ወይም ድብቅ የሆነ ነገርን ያከብራሉ፤ ሲደነቅ የሰሙትን ደግሞ ያደንቃሉ።

254. ክፉ ነገር እንደ መልካም ነገር ሁሉ የሚመጣዉ ተከታትሎ በመሆኑ የፈለገ ትንሽ ብትሆን እንኳ ክፉ ነገርን በንቀት አይን እንዳትመለከታት። መጥፎ ሆነ መልካም ነገሮች የሚሰበሰቡት አምሳያዎቻቸዉ ወደሚገኙበት ስፍራ ነዉ፣። ብዙ ሰዎች መጥፎ እጣ ፈንታ ያጋጠመዉን ሰዉ እየተዉ መልካም እድል ወዳጋጠመዉ ሰዉ ይነጉዳሉ። በዛ ቅንነታቸዉ እርግቦች እንኳ መጠጋት የሚወዱ ነጭ የሆነዉን ግድግዳ ነዉ። መጥፎ እድል ውስጥ ያለ ሰዉ ምንነቱን፤ ምክንያታዊነቱን እና መጽናኛዉን ሁሉ የተነፈገ ሰዉ ነዉ። ስለዚህ መጥፎ ነገርን ነካክተህ እንዳትቀሰቅሳት ይሁን። ትንሽ ስህተት ወዲያዉኑ ምንም ባትመስልም እርሷን ተከትሎ የሚመጣዉ ግን ማብቂያ የሌለዉ ውድቀት ነዉ። ሙሉ በሙሉ የሚከናወን መልካም ነገር እንደሌለ ሁሉ ሙሉ በሙሉ የሚያበቃ መጥፎ ነገር የለም። መጥፎ እጣ ፈንታ ከሰማይ የወረደ ከሆነ በትዕግስት፤ ምድራዊ ከሆነ ደግሞ በአስተዋይነት ተጋፈጠዉ።

255. መልካም ነገር ማድረግን እወቅበት። መልካም ስታደርግ በጥቂቱ እና ኣዘዉትረህ መሆን አለበት። እንዲሁ አንድ ሰዉ ሊመልሰዉ ከሚችለዉ በላይ ከሆነ አትዋልለት። እነሆ ብዙ የሚሰጥ እያከናወነ ያለዉ ሽያጭ እንጅ ስጦታ አይደለም። የተጠየቁትን ማድረግ እንደማይቻላቸዉ ያወቁ ጊዜ ስለሚያርቁህ ዉለታ የዋልክላቸዉን ሰዎች ከልክ በላይ አትጠይቃቸዉ። ሰዎችን ብርቱ ባለእዳህ ያደረግካቸዉ እንደሆነ ታጣቸዋለህ። ሰዎች ዉለታህን መመለስ ሲያቅታቸዉ ያንተ ባለእዳ ከመሆን ይልቅ ጠላትህ ቢሆኑ ስለሚመርጡ ወዳጅነታችሁ ይፈርሳል። ጣኦቱ ቀራጩን ማየት እንደማይፈልግ ሁሉ፤ ዉለታ የተዋለለት ሰዉም ባለዉለታዉን ማየት አይፈልግም። እናም ስለመስጠት ይህን ትምህርት ተማር፤ ስጦታዉ ምስጋናን እንዲያስገኝልህ ከፈለግክ በጣም የሚፈለግ ግን ብዙም ወጭ የማያስወጣ ስጦታ አበርክት።

256. ለባለጌዎች፤ ለከንቱዎች እና ለሁሉም አይነት ቂሎች ተዘጋጅ። እንዲህ አይነት ሰዎች በጣም የበዙ በመሆናቸዉ ከእነዚህ ሰዎች ጭራሹን መራቅ የአስተዋይነት ተግባር ነዉ። በየቀኑ ከእነዚህ ሰዎች ጥቃት ራስህን እንዴት እንደምትከላከል ትኩረት ሰጥተህ አስብ። ለክስተቱ ቀድመህ ተዘጋጅ እንጅ ክብርህን ለስድ አጋጣሚወች አሳልፈህ አትስጣት። አስተዋይነት የታጠቀን ሰዉ ቂልነት ሊያጠቃዉ አይችልም። የሰዉ ልጅ መስተጋብራዊ ጉዞወች በእንቅፋት የተሞሉ በመሆናቸዉ ምክንያት ክብርህ ሊጎድፍ ስለሚችል የተሻለዉ አማራጭ በብልጠት አቅጣጫህን መለወጥ ነዉ። እዚህ ላይ ነዉ ጥበብ የተሞላበት ሽወዳ የሚያገለግለዉ። ከሁሉም በላይ ደግሞ ከችግር በፍጥነት ለመዉጣት የሚያገለግሉትን ለጋስነትን እና ግብረገብነትን ተጠቀም።

257. ነገሮች እስኪበላሹ ድረስ አትጠብቅ። ማንኛዉም ሰዉ ጠላት መሆን ቢችልም እንኳ ሁሉም ሰዉ ጥሩ ወዳጅ ሊሆን አይችልም። ጥቂቶች መልካም ማድረግ ቢችሉም አብዛኞች መጥፎ ነገርን ይፈጽማሉ። ድብቅ ጠላቶች በጠላታቸዉ እጅ እሳት የሚያቀጣጥሉበትን አጋጣሚ እያደቡ ይጠባበቃሉ። ጓደኞቻችን የተጣላናቸዉ እንደሆን አደገኛ ጠላት ይወጣቸዋል፤ የራሳቸዉን ጥፋትም በሌሎች ጥፋት ይሸፋፍናሉ። ሰዎች ከባልንጀራችን ጋር ስንጣላ ሲያዩን የሚናገሩት ስሜታቸዉን እየተከተሉ ሲሆን፤ የሚሰማቸዉ ደግሞ እንደፍላጎታቸዉ ነዉ። የጓደኝነታችንን ጅምር ማስተዋል የጎደለዉ ነዉ ይላሉ፤ ፍፃሜዉን ደግሞ ለምን እስካሁን አብራችሁ ቆያችሁ እናም ዘግይቷል እያሉ ይነቅፋሉ። ጓደኝነትህን ማቋረጥ ካለብህ በቀስታና በይቅርታ እንዲሁ ዉድጅትህን በማርገብ እንጅ በነዉጥና በሁካታ እንዳይሆን። በግሩም ሁኔታ ስለማቆም የጠቀስነዉ መርህ እዚህ ላይ ጠቃሚ ነው[38ኛዉ ኣባባል ነዉ።]።

258. መከራህን የሚጋራልህ ሰዉ ፈልግ። በአደገኛ አጋጣሚወች እንኳ ብቻህን ስለማትሆን የሌሎችን ጥላቻ ብቻህን መቀበል የለብህም። አንዳንድ ሰዎች ሁሉንም ነገር ብቻቸዉን መቆጣጠር ቢፈልጉም እያደረጉ ያሉት ግን የሰወችን ነቀፋ ሙሉ በሙሉ መረከብ ነዉ። እናም ይቅርታ የሚያደርግልህ ወይም መከራህን የሚካፈልልህ ሰዉ እንዲኖር አድርግ። መጥፎ እድል እና ኮልኮሌዎች ሁለት የሆኑትን ማጥቃት ይከብዳቸዋል። ሀኪሞች እንኳ መድሀኒቱ ጠፍቷቸዉ በሽታዉን ማዳን ሳይችሉ ቢቀሩ እንኳ ሬሳዉን በመሸከም የሚረዳቸዉን አማካሪ መጥራት አይጠፋቸዉም። ይህን ሲያደርጉ ክብደቱን እና ሀዘኑን ለሌሎች ያጋራሉ ማለት ነዉ። ብቻዉን በቆመ ሰዉ ላይ የመከራ እጅ በጣም ብርቱ ነዉ።

259. ስድብን ከመቀበል ይልቅ መከላከል የበለጠ በመሆኑ ስድብ ሊከተል መሆኑን ቀድመህ እወቅ እና ወደ ምስጋና ቀይረዉ። ጠላት ሊሆን የነበረን ሰዉ ወዳጅ ማድረግ ታላቅ ችሎታ ነዉ። በዚህ መንገድ ክብርህን ሊያጎድፉት የነበሩ ሰዎችን የክብርህ ጠባቂ ታደርጋቸዋለህ። በተጨማሪም ስድብን ወደ ዉለታ መቀየር እና ሌሎችን በዉለታህ ማሰርን ማወቅ ጠቃሚ ነገር ነዉ። ሀዘንን ወደ ደስታ መቀየር መቻል ደግሞ የኑሮ ዘዴን ማወቅ ነዉ። ስለዚህ ክፋትን ራሱ ወደ ወዳጅነት ቀይረዉ።

260. አንተ ሙሉ በሙሉ የሌሎች መሆን እንደማትችለዉ ሁሉ ሌሎችም ሙሉ በሙሉ ያንተ ሊሆኑ አይችሉም። ፍቅርን በመስጠት እና እራስን በመስጠት መካከል ሰፊ ልዩነት ስላለ የስጋ ዝምድና ሆነ ጓደኝነት ወይም በጣም ከባድ የሚባል ግዴታ እንኳ ይህን ህግ ሊገስሱት አይቻላቸዉም። በጣም ጥብቅ የሚባል ወዳጅነት እንኳ የማይሰራባቸዉ ጊዜያት አሉ። ለዚህም ነዉ ጓደኛ ለራሱ የሚደብቃቸዉ ሚስጥሮች እንዳሉት ሁሉ ልጅም ከአባቱ የሚደብቀዉ ነገር ያለዉ። እናም ለአንዳንድ ሰወች የምትናገረዉን ነገር ለሌሎች የምትደብቅበት ጊዜ ስላለ የሚስጥረኛህን አይነት እያየህ ሁሉንም ነገር ትገልጻለህ ወይም ትደብቃለህ ማለት ነዉ።

ጎበዝ፣ በብልህነት መንገድ እንጓዝ፣ ብልሆችም እንሁን! :mrgreen:

Meleket
Member
Posts: 1109
Joined: 16 Feb 2018, 05:08

Re: ‘የብልህነት መንገድ’ - ምርጥ መጠሓፍ በምርጥ ተርጓሚ - ይዘቷን እንካችሁ አጣጥሙ!

Post by Meleket » 15 Jun 2019, 02:16

ጎበዝ የዛሬ አስር የብልህነት መንገዶችን ወርሃ ሰኔ እውነተኞቹ ኤርትራዉያን አንበሶች ይበልጥ የሚዘከሩበት ግዜ እንደመሆኑ መጠን ለፍትህ ለእኩልነት ለነጻነት ሲሉ ሕዝባቸውንም ከግፈኞችና ጨካኞች መንጋጋ ለማላቀቅ በቅን ልቦና ሕይወታቸውን ያለማወላወል ለገበሩ ለኤርትራዉያን እውነተኛ አንበሶች ማለትም ለ“ሰማእታት” ክብር እንዲሁም በመሰሪዎች ተደናግረው ጦርነት ውስጥ ገብተው ሕይወታቸው ላለፈ ኢትዮጵያዉያን ወንድሞቻችን ክብር ጭምር እንካፈለዋለን። ይህን ስናደርግም የነዚህን እውነተኛ ኤርትራዉያን አንበሶች መካነ መቃብር በማፈራረስ ድርብ በደል የፈጸሙ፣ በኤርትራ ልዑላዊ መሬት ውስጥ እስከ አሁኗ ደቂቃ በማን አለብኝነት ሰፍረው የሚገኙትን፣ ኤርትራም ልዑላዊ መሬቷን ያላንዳች መሸራረፍ እንዳታስተዳደር እንቅፋት የሆኑትን ወራሪ የትግራይ ወያኔዎችን በጨዋ ደንብ አሁንም ደግመን ደጋግመን በኤርትራ ህዝብ ስም “ዓገብ” በማለት ነው። አያይዘንም ወጣቱን የኢትዮጵያ ጠቅላዪንም “ቃልህን ተግብር” እያልን ከኤርትራ ምድር የሚገኙ ያገርህን ሠራዊት እንድታስወጣ በሰማእታቶቻችን ስም ደግመን ደጋግመን እየጠየቅን ነው።

261. በሞኝነት ተግባር አልሞት ባይ ተጋዳይ እንዳትሆን። አንዳንድ ለስህተታቸዉ ታማኝ የሆኑ ሰወች ስህተት ከፈጸሙ በኋላ በስህተታቸው መቀጠልን እንደ እርጋታ ወይም ጽናት አድርገው ይቆጥሩታል። እነዚህ ሰዎች በዉስጣቸው ራሳቸውን ቢወቅሱም ለሰዎች ግን ትክክል መሆናቸዉን ይናገራሉ። እንዲህ አይነት ግለሰቦች የሞኝነት ተግባር የፈጸሙ ጊዜ ሰዎች ግዴለሽ ናቸዉ እያሉ ያስባሉ፤ በዛ ተግባራቸዉ የገፉበት እንደሆነ ደግሞ ሞኝ ናቸዉ ይላሉ። በስህተት በገባነዉ ቃልኪዳን ሆነ በስህተት በወስደነው ዉሳኔ ለዘላለሙ ልንታሰር አይገባም። አንዳንዶች ደደብነታቸዉን ያራዝሟትና ታማኝ ጅሎች ለመሆን ይሞክራሉ።

262. መርሳትን እወቅ። ይህ ነገር ከችሎታ ይልቅ እድልን ይጠይቃል። በጣም መርሳት ያለብን በቀላሉ የማናስታዉሳቸዉን ነገሮች ነዉ፣ ትዝታ ባለጌነቱ ስንፈልገዉ አለመምጣቱ ሲሆን፤ ጅልነቱ ደግሞ መምጣት በሌለበት ጊዜ መምጣቱ ነዉ። ትዝታ ስቃይን ሲፈጥርብን አሰልች፤ ሀሴትን ሲፈጥርብን ደግሞ ግድ የለሽ ነዉ። አንዳንዴ የችግሮች መድሀኒታቸዉ መርሳት ቢሆንም መድሀኒቱን እንረሳዋለን። ትዝታ ሕይወታችንን ሲኦል ወይም ገነት ልታደርገዉ ስለምትችል ትኩረት ሰጥተን ልንኮተኩታት ይገባል። በራሳቸዉ የሚደሰቱ ሰወች ግን በቂላቂል የዋህነታቸዉ ሁሌም ደስተኞች ስለሆኑ ይህ ነገር አያስጨንቃቸዉም።

263. ብዙ መልካም ነገሮች በሌሎች ሰዎች እጅ ቢሆኑ የተሻለ ነዉ። በደንብ ልትደሰትባቸዉ የምትችል ይህ የሆነ እንደሆነ ነዉ። በመጀመሪያዉ ቀን ደስታዉ የባለቤቱ ሲሆን በኋላ ግን ለሌሎች ነዉ። ይጠፉብናል ብለን ስለማንሰጋ እና አዲስ ስለሚሆኑብን የሰዉ የሆኑ ነገሮችን እጥፍ ጊዜ እንደሰትባቸዋለን። የተከለከሉት ነገር ሁሉ ስለሚጣፍጥ የሌላ ሰዉ ዉሀ እንኳ ማር ማር ይላል።

264. ግዴለሽ የምትሆንባቸዉ እለታት እንዳይኖሩህ። እጣ ፋንታ ባልተዘጋጀንበት አጋጣሚ እኛን የምታስደነግጥበትን አጋጣሚ እንደተጠባበቀች ነዉ። እናም ለዚህ የፍርድ ቀን እዉቀታችንን፤ ማስተዋላችንን እና ብርታታችንን ብቻ ሳይሆን ዉበታችን እንኳ መዘጋጀት አለባት። እነሆ እነዚህ ነገሮች እንዝላል የሆኑበት ቀን የዉርደታችን ቀን ነዉ። ጥንቃቄ ሁሌም የሚጠፋዉ በጣም በሚያስፈልግበት ጊዜ ነዉ። ሀሳብ የለሽነት ለዉርደት ይዳርጋል። በደንብ የሚከታተሉን ሰዎች ደግሞ ይህን ህግ ስለሚረዱ ችሎታችንን የሚፈታተኑት ባልተዘጋጀንበት ሰአት ነዉ። እነዚህ ሰዎች ችሎታችንን በደንብ የምናሳይባቸዉን ቀናት በመተዉ ባልጠበቅነዉ ቀን ፈተና ላይ ይጥሉናል

265. የበታቾችህን አጣብቂኝ ዉስጥ መክተት እወቅበትዋና የምትለምደዉ እየሰጠምክ እያለህ ስለሆነ በተገቢዉ ጊዜ የተከሰተ አደገኛ ሁኔታ ብዙ ታላቅ ሰዎችን ፈጥሯል። እንዲ አይነቱ አጋጣሚ ብዙ ሰዎችን ምን ያህል እንደሚያዉቁ ብቻ ሳይሆን ትክክለኛ ዋጋቸዉንም እንዲረዱ አስችሏቸዋል። እነሆ አደገኛዉ አጋጣሚ ባይኖር ኖሮ የእነዚህ ሰዎች ችሎታ በፍርሀታቸዉ ዉስጥ ተቀብሮ ይቀር ነበር። አስቸጋሪ ሁኔታዎች ታላቅ የምንሆንበትን አጋጣሚ ያቀርቡልናል። ታላቅ ሰዉ ክብሩ አደጋ ላይ መዉደቁን የተረዳ እንደሆን ሽህ ሰዎች ሊሰሩ ከሚችሉት በላይ ሊያከናዉን ይችላል። እንግዲህ ታላቅ ሰዎች የሚፈጠሩት በዚህ መንገድ ነው።

266. በጣም መልካም በመሆን መጥፎ አትሁን። የማትቆጣ ከሆነ ደግሞ መጥፎ ትሆናለህ። በእዉነት ምንም የማይሰማቸዉ ሰዎች ከሰዉ አይቆጠሩም። እነሆ የእነዚህ ሰዎች ባህሪ እንደዛ የሆነዉ ደደብ በመሆናቸዉ እንጅ ምንም ስሜት ስለማይሰማቸዉ አይደለም። ስለዚህ በተገቢዉ አጋጣሚ በስሜት መሞላት እዉነተኛ ሰዉ ያደርጋል። ወፎች እንኳ ወፈከልክል ምንም ስሜት ባለማሳየቱ ያላግጡበታል። ጣፋጭ ብቻ ለሞኞች እና ለህጻናት የተገባ በመሆኑ ጣፋጩን ከመራራዉ ጋር ማፈራረቅ ችሎታን ያሳያል። እራስን እስኪስቱ ድረስ እጅግ መልካም መሆን ታላቅ ሀጢአት ነዉ።

267. ቃላቶችህ ለስላሳ ምግባሮችህ ደግሞ ገራገር ይሁኑ። ቀስት ሰዉነታችንን ሲወጋ ቃላት ደግሞ መንፈሳችንን ይወጋሉ። ጣፋጭ ኬክ ለአፋችን መልካም ሽታን ይሰጠዋል። ንፋስን መሸጥ መቻል ታላቅ ችሎታ ነዉ። ብዙ ነገሮች በቃላት ስለሚከፈሉ በቃላት ብቻ ከባድ የሚባሉ ነገሮችን ማለፍ ይቻላል። እናም ሰዎች የተወጣጠሩብህ ወይም የፈዘዙብህ ጊዜ በአየር አስተናግዳቸዉ። ዘዉዳዊ ትንፋሽ በተለየ ሁኔታ የማሳመን ችሎታ አለዉ። አፍህ በማር የተሞላ ይሁን እና ጠላቶችህ እንኳ እስኪወዷቸዉ ድረስ ቃላቶችህን ወደ ከረሜላ ለዉጣቸዉ። ለመወደድ ብቸኛዉ መንገድ ገራገር እና ሰላማዊ መሆን ነው።

268. ሞኝ በመጨረሻ የሚሰራዉን ብልህ በቅድሚያ ይሰራዋል። ሁለቱም ተመሳሳይ ነገር እየፈጸሙ ቢሆንም እንኳ የሚለያዩት በሚፈጽሙበት ጊዜ ነዉ፤ አንደኛዉ በትክክለኛዉ ሰአት ሲፈጽም ሌላኛዉ በአጉል ሰአት ይፈጽማል። በተሳሳተ እሳቤ ከጀመርክ ሁሉንም ነገር የምትፈጽመዉ በተሳሳተ መንገድ በመሆኑ አናትህ ላይ ልታደርገዉ የሚገባዉን በእግርህ ትረግጠዋለህ፤ ቀኝ የሚሆነዉን ግራ ታደርገዋለህ፤ እናም ስራህ በሙሉ ብስለት የጎደለዉ ይሆናል። በዚህ አጋጣሚ ለእንዲህ አይነቱ ሰዉ ያለዉ መፍትሄ በተቻለ ፍጥነት ወደ ትክክለኛዉ አቅጣጫ ማምራት ነዉ። ይህ ባይሆን ግን በዉዴታ ሊሰራ የነበረዉን በግዴታ ይሰራዋል። ብልሆች ወዲያዉኑ ወይም ቆይተዉ መፈጸም ያለባቸዉን በፍጥነት ለይተዉ ደስ እያላቸዉ በማከናወን ዝናቸዉን ከፍ ያደርጋሉ።

269. አዲስ መሆንህን ተጠቀምበት። አዲስ እስከሆንክ ድረስ ከበሬታን ታገኛለህ። በሚያመጣዉ ለዉጥ ምክንያት ስለሚያስደስት እና መንፈስን ስለሚያድስ አዲስ የሆነ ተራ ነገር ከተላመድነዉ ታላቅ ነገር ይበልጥብናል። ላቅ ያሉ ነገሮች ከኛ ጋር ሲቀላቀሉ ቶሎ ያረጃሉ። ሆኖም ግን የአዲስነት ግርማ ሞገስ የሚቆየዉ ለጥቂት ጊዜ በመሆኑ በአራት ቀናት ዉስጥ ሰዎች ላንተ ያላቸዉን ክብር ያጣሉ። እናም በመጀመሪያወቹ ቀናት የምታገኘዉን መከበር በተቻለህ መጠን ተጠቀምበት እና መኮብለል ሲጀምር ደግሞ የተቻለህን ያህል ለማስቀረት ሞክር። የአዲስነት ሞቅታ እንዳበቃ ስሜት ይቀዘቅዛል፤ ደስታም ወደ ንዴት ይቀየራል። ሁሉም ነገሮች የራሳቸዉ ጊዜ እንዳላቸዉ እና እንደሚያልፍባቸዉም ጠንቅቀህ እወቅ።

270. ብዙዎችን እያስደሰተ ያለዉን ነገር ብቻህን እንዳትነቅፍ። ሊገለጽ ባይችል እንኳ እንዲህ አይነቱ ነገር ብዙዎችን ሊያስደስት የቻለበት አንዳች ነገር አለዉ። ለየት ብሎ መታየት ሁሌም አስጠሊታ ሲሆን፤ ለየት ያልከዉ በስህተት ከሆነ ደግሞ አስቂኝ ነዉ። ብዙ ሰዉ የሚወደዉን ነገር ስደበዉ እና አንተዉ ራስህ ትሰደብና ከአጉል ምርጫህ ጋር ብቻህን ትቀራለህ። ምርጫ አለማወቅ የሚወለደዉ ከደደብነት ስለሆነ መልካም የሆነዉን ነገር መለየት ካልቻልክ አለማወቅህን ደብቅ እንጅ ነገሮችን በጥቅሉ አትኮንን። ሁሉም ሰዉ ነዉ የሚለዉ ነገር በትክክል ነዉ፤ ይህ ካልሆነ ደግሞ ነገሩ ሊሆን ነው።

ጎበዝ፣ በብልህነት መንገድ እንጓዝ፣ ብልሆችም እንሁን!
:mrgreen:

Maxi
Member+
Posts: 5926
Joined: 06 Mar 2014, 04:33

Re: ‘የብልህነት መንገድ’ - ምርጥ መጠሓፍ በምርጥ ተርጓሚ - ይዘቷን እንካችሁ አጣጥሙ!

Post by Maxi » 15 Jun 2019, 04:35

Meleket, 30 more to go!! :P

You are doing great job. God bless you!!

Meleket
Member
Posts: 1109
Joined: 16 Feb 2018, 05:08

Re: ‘የብልህነት መንገድ’ - ምርጥ መጠሓፍ በምርጥ ተርጓሚ - ይዘቷን እንካችሁ አጣጥሙ!

Post by Meleket » 15 Jun 2019, 05:13

Maxi wrote:
15 Jun 2019, 04:35
Meleket, 30 more to go!! :P

You are doing great job. God bless you!!
ወዳጄ Maxi

ከተቀመጥኩበት ተንስቼ ጎንበስም ብዬ “አሜን” ብያለሁ!

ሐቅን በመግለጥ፣ ትምህርት ሰጪ የሆኑ ጽሑፎችንም በማጋራት፣ አጉራዘለሎችን ለመግራት በምናደርገዉ ትግል የትውልድ ሚናችንን እየተወጣን እንዳለን ጠንቅቀው የሚያዉቁ የወዳጄ Maxiና የሌሎች ቅን ሰዎች ሞራል ስላልተለየን በእጅጉ እናመሰግናለን!!! በትግርኛም ከልባችን “ክብረት ይሃበልና” ብለናል!!!
:D

Post Reply