Ethiopian News, Current Affairs and Opinion Forum
Meleket
Member
Posts: 3059
Joined: 16 Feb 2018, 05:08

ሰብእና ገደላ (ገጽታ ገደላ) _ የምስጋናው አንዱዓለም እዪታ

Post by Meleket » 07 Nov 2022, 10:53

ቢያነቡት ዕውቀት ከመገብዬት ሌላ የሚከስሩት ነገር የለም። ለትንታኔው ምስጋናው አንዱዓለምን አመስግነናል። :mrgreen:
ሰብእና ገደላ (ገጽታ ገደላ) _ የምስጋናው አንዱዓለም እዪታ

የተቃዋሚ ዋና መሳሪያ የሆነው ሰብእና ገደላ በዚህ የአማራነት እንቅስቃሴ ውስጥ ሳይጠቀስ መታለፍ የሌለበት ነው፡፡ ብዙዎችን ደህና ሰዎች ደጋግሞ እያደናቀፈ አላሰራ ያለ፡፡ ሰብእና ገደላ፤ ወይም ገጽታ ገደላ፡፡ ሰብእና (ገጽታ) ገደላ በተለይ በፖለቲካው ዓለም የፖለቲካ ተቋማትን እድሜ የሚተካከል ነው፡፡ ይሄ ዘዴ ሰውን ከስራው ለማደናቀፍ፣ በሰዎች ዘንድ ተቀባይነቱ እንዲሳሳ፣ ትግሉን ተስፋ ቆርጦ እንዲተው፣ ሞራሉ እንዲነካ እና ሁለተኛ አያሳየኝ ብሎ ከሚወደው ስራው ወይም ህዝብ እንዲነጠል ማድረጊያ ስልት ነው፡፡

ገጽታ ገደላ የደካሞች መሳሪያ ነው፡፡ በአካል የማይገድሉትን በምላሳቸው ይገድሉታል፡፡ በተግባርና በሀሳብ የላቃቸውን በአሉባልታና ሀሜት ሊያወርዱት ይሞክራሉ፡፡ ጀግናውን ፈሪ ያደርጉታል፡፡ ሰውን አውሬ ያስመስሉታል፡፡
በታሪካችን ከሚታወቁት ገጽታ ገደላዎች አንዱ አጼ ቴዎድሮስ ላይ የደረሰው ነው፡፡ አጼ ቴዎድሮስን በምላስ ለማሸማቀቅ “የኮሶ ሻጭ ልጅ” አሏቸው፡፡ እስካሁን የካሳ እናት ኮሶ ስለመሸጣቸው በአራት ነጥብ የደመደመ የታሪክ ምስክር የለም፡፡ ቢሆን እንኳ የእናቱ ኮሶ መሸጥ በምንም መልኩ ካሳን ሊገድለው አይችልም ነበር፡፡ አይሻል፣ ጉራምባና ሌሎችም የጦር አውድማዎች ላይ ያንበረከካቸው በኮሶ ማውራ (ዋንጫ/ቅል) ሳይሆን በጦርና በጎራዴ ነበር፡፡ ደካሞች ጦርና ጎራዴን በክንዳቸው መግጠም ሲያቅታቸው በምላሳቸው የኮሶ ማውራን ገጠሙት፡፡

አጼ ፋሲል ሰውነቱ ሁሉ ጸጉር ነው፣ ሴት አብሮ አሳድሮ ያንን እንዳትናገርበት ወደውሀ ይጥል ነበር፣ ለዛ ንስሀ ነው ሰባት ድልድይ እና 44 አብያተ ክርስቲያናት ያሰራው ይሉት ነበር፡፡ ይህ ገጽታ ገደላ ነው፡፡ ንጉሱ ሰው አልነበሩም ወይም የተለዩ ፍጥረት ነበሩ ለማለት ነው፡፡ ያሰሩት ያ ሁሉ የስልጣኔ አሻራ ከንጉሱ ረቂቅ አእምሮ የመነጨ እቅድ እና ፍላጎት እንዳልሆነ በመናገር ስራውን ሲያዳፍኑት ነው፡፡ የጎንደርን ስልጣኔ የዝሙት ንስሀ ፍሬ ሲያደርጉት ነው፡፡ የፋሲል አባት አጼ ሱስንዮስ ብርቱው ጦረኛ ዜና መዋእሉ እንደሚያስረዳው ለ28 አመታት ያለረፍት የተዋጋ ሰው ነው፡፡ ሰበቡ ምንም ሀይማኖት ቢሆንም ቅሉ ምላሱ ተጎልጉሎ ሞተ እየተባለ ነው አሙሟቱ እንኳ የሰው እንዳልሆነ ሲነገር የቆየው፡፡ ያ ሁሉ የዋለው ውለታ በሀይማኖት ባለመስማማቱ ብቻ በምላስ መጎልጎል መሞት ብቻ ነው የተዘጋው፡፡ አጼ ምኒልክን የተፈጥሮ ጥበባቸውንና የመሪነት “ካሪዝማቸውን” ለመካድ ስንት እና ስንት ነገር ይሏቸው ነበር፡፡ አሉላ አባ ነጋን በአጼ ዮሐንስ ዙሪያ የተሰባሰቡ ምላሰኞች “ወዲ ቁቢ” ወይም የደሀ/ገበሬ ልጅ እያሉ እስከማሳሰርና ማሻርም ደርሰው ነበር፡፡ አጼ ሀይለ ስላሴን የንጉሱን ጥበብና ማስተዋል ለመካድ ሲባል ቆሪጥ ምናምን እያሉ ስሙን የሚያጠፉበትም ምክንያት ያው የገጽታ ገደላ ስራ ነው፡፡ ልጅ ኢያሱ ያ ሁሉ ያደረገውንም ያላደረገውም ተጠቅሞ ስሙን በማጉደፍ ከጨዋታ ውጭ የተደረገው በዚሁ በገጽታ ገደላ ስራ ነው፡፡ ልጅ ኢያሱ በወቅቱ ከጀርመንና ቱርክ ጋር ወዳጅነት መመስረቱ ያንገበገባቸው እንግሊዝና ፈረንሳዮች ሴራ ሸረቡበት የሚሉም አሉ፡፡ እንግሊዞች በተለይ ከሱማሌ ሴቶች ጋር ሆኖ የሚያሳይ የሀሰት የፎቶ ቅንብር ግብጽ ውስጥ በ20 ሽህ ኮፒ አባዝተው አምጥተው በተኑ የሚሉ አሉ፡፡ ወግ አጥባቂው የወቅቱ ህዝብም ልጅ ኢያሱን ተቀየመ፡፡ የተባለውን ነገር ልጅ ኢያሱ አድርጎ ሊሆን ይችላል፡፡ ግን ለዛ የሚያበቃው አልነበረም፡፡ ያው ገጽታ ገዳዮች ከባዶ ነገር ገጽታ መግደያ ንጥረ ነገር የሚቀምሙትን ያህል ከትንሽ እውነት ላይ ተራራ የሚያክል ገጽታ ገዳይ ቁልል ይፈጥራሉ ለማለት ነው፡፡

ገጽታ ገደላ የነፍስያ ገደላ ምዕራፍ አንድ ነው፡፡ ገጽታውን ሲገድሉ አልሞትላቸው ያለውን በአካል ለመግደል ይሞክራሉ፡፡ ብርቱዎች ግን ያንን ገጽታ ገደላ ተቋቁመው ያልፉታል፡፡ ወደ እውነተኛ እና ታሪክ አይሽሬ ሰብእናም ይቀይሩታል፡፡
ቴዎድሮስ ኮሶ ሻጭ ለተባለው ሰብእና ገደላ ተነበርክኮ በቋራ በረሀዎች ቀርቶ ቢሆን ዛሬ የማይሞተውን ዋናውን ሰብእና ለታሪክ አያስተላልፍም ነበር፡፡ አጼ ምኒልክ ለተነሳባቸው ሰብእና ገደላ ተነብርክከው ቢሆን ኖሮ ዛሬ “ያለምጣም” አይሆኑም ነበር፡፡ ይሄ የጥንት በሽታ አሁንም አለ፡፡ ሲሻው በግላጭ፣ እንዲያ ሲል ከሀሳዊ ማንነት ጀርባ ሆኖ፡፡ ለዚህ በሽታ ዘመናዊ ቴክኖሎጅው የበለጠ ጥንካሬ ሰጥቶታል፡፡ የዛሬ መቶ አመታት ገደማ ግብጽ ድረስ የውሸት ፎቶ በማቀናበር የተጀመረው የገጽታ ገደላ ዛሬ ቴክኖሎጂውን ተጠቅሞ የት እንደደረሰ በየእለቱ የምናየው ነው፡፡ ነገር ግን ገጽታ ገደላን ያላለፈ እውነተኛውን ሰብእና ለታሪክ አያወርስም፡፡

የኮሶ ሻጭ ልጅ እየተባለ ስሙ የጠፋው ቴዎድሮስ ግን በዘመኑ ከነበሩት መሳፍንት ሁሉ የላቀ የፖለቲካ ራእይ የነበረው ሰው ነው፡፡ ለምሳሌ ለ21 ወራት የንጉሱ እስረኛ የነበረው እንግሊዛዊ ሄንሪ ብላንክ ስለሀበሻ አገር የእስራት ዘመኑ ሲያትት እንዲህ ይላል፡ - በሚቀጥለው የዘመቻ እለት ንጉሱ አስተርጓሚ የነበረውን ሳሙኤልን አሁንም አሁንም ጥያቄ እያስያዘ ይልከው ነበር፡፡ ከጥያቄዎቹም፡- የአሜሪካ ጦርነት አበቃ እንዴ? ምን ያህሉ ሞቱ? ምን ያህል ወታደሮች ነበሯቸው? እንግሊዞች ከአሻንቴዎች ጋር ተዋግተዋል እንዴ? ተዋግተው ወረሯቸውን? አገራቸው ችግር አለበት? እንደዚህ እንደኛ አገር ነው? የዳሆሜ ንጉስ ለምንድነው የራሱን ዜጎች እንደዛ የጨፈጨፋቸው? ምን ነበር ሀይማኖቱ?

ቴዎድሮስ በዚሁ በሄንሪ ማስታወሻ እንደምናነበው በቆራጣ በኩል ጣና ላይ ጀልባዎች እንዲሰሩለት ብዙ ደከመ፡፡ ፈረንጆቹም ችሎታ አልነበራቸውም፡፡ “ማንም የሚረዳው እንደሌለ ሲያውቅ ራሱ ግሩም የሆነ ከወደመደቡ ጠፍጣፋ በጣም ወፍራም የደንገል ታንኳ ሰራ፡፡ በሁለት ሰዎች እጆች የሚሽከረከሩ እንደ ኃይል መስጫ መርገጫ አይነት እጀታዎች ከጎንና ጎን ሰራለት፡፡ በእርግጥ የጋዝ መቅዘፊያ ፈልስፎ ሰራ-- የማሽከርከሪያው ክፍል ብቻ ችግር ቢኖርበትም፡፡ ውሀው ላይ ለረጅም ጊዜ አየነው፡፡ ይሁንና በደንብ ተሸከርካሪ እጀታዎቹ በደንብ እንዲቀዝፉ ወደ መቶ ሰዎች ያስፈልጉት ነበር፡፡ በሚያሳዝን ሁኔታ ግን ይህንን ብዙም ጥቅም ሊሰጠው የማይችለው ስራ ላይ ጊዜውን ሲያጠፋ ከሰፈረበት ካምፕ አራት ማይሎች በማይርቅ ቅርበት በአመጸኛ ሽፍቶች መከበቡን ዘንግቶት ነበር” ይላል ሄንሪ፡፡ ስለመቅደላው መንገድ ሲጽፍም “ቀስ በቀስ መንገዱን ሰራው፡፡ መንገዱ በአውሮፓዊ መሀንዲስ አይን እንኳ ትልቅ ግምት የሚሰጠው ነበር፡፡ በዛም መንገድ ሞርታሮቹን እና መድፎቹን አጓጓዘበት” ብሏል፡፡ ይሄንን ባለ ራእይ ግን በኮሶ ሻጭ ልጅነት ከመንገዱ ለማሰናከል ብዙ ተብሎበት ነበር፡፡

ገጽታ ገደላ የመጀመሪያውን የአማራ ድርጅት መስራችና መሪ እንዲሁም መስዋእት ፕ. አስራት ወልደየስንም አልለቀቃቸው፡፡ ፕ. አስራት ዘለፋ፣ ስድብና አድማ የገጠማቸው ከራሳቸው ወገን እንደሆነ ዛሬ ብዙዎቹ በቁጭት ይናገሩታል፡፡ አማራ እየታደነ በገደል እየተጣለ በነበረበት ወቅት አማራ ለምን ይነካል በማለታቸው ብቻ በህብረ-ብሄር ኢትዮጵያዊያን እና አማራ-ጠል የ60ው ትውልድ አባላት “አክራሪ፣ ዘረኛ” እየተባሉ ይወነጀሉ ነበር፡፡ አስራት ግን ከትምህርትም እጅግ የተማሩ፣ ከዝናም ዝና የነበራቸው ሰው ነበሩ፡፡ በእርሳቸው ዘመን “እኔ አማራ አይደለሁም፤ ኢትዮጵያዊ ነኝ” እያሉ ይኮፈሱ የነበሩት ሁሉ ሲያሳብቡ የነበሩት ተማርኩ ባይነትን እና ሁለንተናዊ ሰውነትን ነው፡፡ ነገር ግን ከአስራት አይደርሱም ነበር፡፡ አስራት እውነተኛ ትምህርት ስለነበራቸው እውነተኛ የህዝብ ፍቅር ነበራቸው፡፡ ከእውነተኛ እውቀትና ትምህርት የህዝብ ፍቅር፣ የሰው ፍቅር ይመነጫል፡፡ ከይስሙላ እውቀትና ትምህርት ግን ሌብነት፣ ሀሜተኝነት፣ ጨካኝነት፣ አሉባልተኝነትና ግብዝነት ይወጣሉ፡፡

የሀበሻ ትምህርት በእውነት ወይም ሀሰት ሞዴል መስራቱ ራሱ ሌላው ችግር ነው፡፡ መሀል አልባ የኢትዮጵያዊያን ህይወት እንግዲህ መቸም ከ66ቱ አብዮት ፍንዳታ ጊዜ የበለጠ የተንጸባረቀበት ጊዜ የለም፡፡ ጤዛ ፊልም ላይ ፕሮፍ. ኃይሌ ገሪማ የጭብጥ መሪም አድርገውታል፡፡ ተስፍሽ “ወይ ከእኛ ነህ ወይ ከዛኛው ነህ፣ መሀል ላይ መሆን አትችልም፤ መሀል ሰፋሪ በሁለት ጥይት ይመታል ይሉሃል” ብሎ ለአንበርብር የሚያስረዳበት ቦታ ማለት ነው፡፡ ይህ ምን ያመለክታል? በኢትዮጵያ ውስጥ የሰው ልጅ መሀል ላይ መኖር አይችልም፡፡ ዳር እና ዳር ሆነህ ትጓተታለህ፡፡ ኃይል ያገኘው ጎትቶ ወደመሀል ያመጣህና ይከሰክስሀል፡፡ መሀሉ የምትከሰከስበት እንጅ በሰላም የምታርፍበት አይደለም፡፡

ይህን በሽታ የምናድግበት ሸፋፋ የትምህርት ስርዓት ያባባሰው ይመስላል፡፡ ለተማሪዎች ከመዋእለ ህጻናት እስከ ዩኒቨርሲቲ ድረስ “እውነት/ሀሰት” የሚል ፈተና ብቻ ነው የሚቀርበው፡፡ ይህም ማለት ለኢትዮያዊ ሁሉም ነገር እውነት ነው ወይም ሀሰት ነው ማለት ነው፡፡ መሀል ላይ ለአከራካሪ ሀሳብ ቦታ የለም፡፡ አከራካሪ ሀሳብ በኢትዮጵያዊያን አእምሮ የለም፡፡ ሁሉም ነገር እውነት ወይ ውሸት ከሆነ ለምን ክርክር ያስፈልጋል!! እውነትነቱን የሚጠራጠር የግድ እውነት ወይ ሀሰት ማለት ስላለበት አንዱን ይመርጣል፡፡ አንተ እውነት እንዲል ፈልገህ እሱ ውሸት ካለ በዱላ ብለህ እውነት እንዲል ታስገድደዋለህ፡፡

በዚህ እውነት/ሀሰት የአእምሮ ስሪት ላደገ ማኅበረሰብ መከራከር አዲስ፣ መፈረጅ ግን ልማድ (“ኖርማል”) ነው፡፡ አእምሮአችን በጥንዳዊ አስተሳሰብ የሚሰራ ነው፡፡ ሌቪ ስትራውስ የተባለ ፈረንሳዊ አንትሮፖሎጅስት/ሶሲዮሎጅስት “ባይናሪ ኦፖዚሽን” ይለዋል፡፡ ምን ማለት ነው? የሰው ልጅ አእምሮ የአሰራር ስርዓት ጥንትም አሁንም በሁሉም ቦታ ተመሳሳይ ነው፡፡ ማለትም በጥንድ ተቃራኒ ዘዴ ነው የሚያስበው ይላል፡፡ ለምሳሌ የሰው ልጅ አእምሮ ጨለማ ካለ ብርሀን አለ ብሎ ያምናል፡፡ ሞት ካለ ህይወት አለ ብሎ ያምናል፡፡ መሄድ ካለ መምጣት አለ፤ ጥሬ ካለ የተቀቀለ አለ ብሎ ያስባል፡፡ ነገር ግን ይሄንን ጥንዳዊ የአእምሮ ስሪት ባህል (ስልጣኔ) ከጥንዳዊነት ወደ ተተንታኝ አሳብነት ቀይሮታል፡፡ በብርሀን እና በጨለማ መካከል ጸሀይ ግባት፣ ምሽት፣ ውድቅት፣ ወጋገን፣ ንጋት፣ ጠዋት፣ ቀን እየተባለ የሚተነተን ብዙ አሀድ አለ፡፡ በሌላውም ሁሉ አስተሳሰብ እንደዛው፡፡

የኢትዮጵያ የትምህርት ስርዓት ግን ያው የጥንቱ የአእምሮ ስሪት ውስጥ እንደተወሸቀ ነው፡፡ እውነት ወይ ውሸት በሚል አስተሳሰብ፣ ወይም ነው ወይም አይደለም በሚል አስተሳሰብ የተቃኘ ነው፡፡ በእውነት እና በውሸት መካከል ገና እውነት እና ውሸትነቱ ያልለየ፣ ያልተጠና፣ ያልተረጋገጠ አስተሳሰብ መኖሩን አይረዳም፡፡ አንዳንድ በማህረሰቡ እንደ እውነት የተወሰደ ነገር ግን ቆይቶ ውሸት የሚሆን፤ አንዳንድ በማህበረሰቡ እንደውሸት የተወሰደ ግን እውነት የመሆን እድል ያለው አስተሳሰብ መኖሩን አያውቅም፡፡ ለምሳሌ የዚህ ጥንዳዊ አስተሳሰብ ውጤቶችን እንይ፡፡ ምኒልክ ጨቋኝ ነው ወይ አይደለም፡፡ ከነው እና አይደለም ውጭ ሌላ ምርጫ የለህም፡፡ ነው ብለህ ትስማማለህ ወይም አይደለም ብለህ ትጣላለህ፡፡ አማራ አለ ወይም የለም ይልሀል፡፡ ለምን ብለህ ብትጠይቅ መልስ አታገኝም፡፡ አለ ብለህ ትወገዛለህ (አሁን መፈራት ነው በእርግጥ)፤ ወይም የለም ብለህ ገልፍጠህ ይገለፈጥልሀል፡፡ የአማራ ብሄረተኝነት አለ ወይም የለም ተብለህ ትጠየቃለህ፡፡ አእምሮህ በተሰራበት የእውነት/ሀሰት ጥንዳዊ አሰራር መሰረት የለም ወይ አለ ብለህ ትመልሳለህ፡፡ ለምን ብሎ የሚጠይቅህ የለም፡፡ ቢጠይቅህም የምትመልስለትን ሊረዳው አይችልም፡፡ ምክንያቱም አእምሮው ለጥንዳዊ ድምዳሜ እንጅ ለመካከለኛው ትንተና ስላልሰለጠነ፡፡ አማራ ጨቋኝ ነው ወይስ አይደለም ተብለህ ትጠየቃለህ፡፡ አይደለም ብለህ ትጣላለህ ወይም ነው ብለህ ይጨበጨብልሀል፡፡

[ “ግዮናዊነት የአማራ መነሻ እና መድረሻ” ምስጋናው አንዱዓለም (መለክ ሐራ) ከጻፈው መጸሐፍ ገጽ 311-314 የተቀነጨበ]

Assegid S.
Member
Posts: 936
Joined: 11 Aug 2013, 07:11
Contact:

Re: ሰብእና ገደላ (ገጽታ ገደላ) _ የምስጋናው አንዱዓለም እዪታ

Post by Assegid S. » 07 Nov 2022, 12:11

ወንድም መለከት ... አስተማሪ ለሆነው ፅሑፍ ደራሲውም አንተም ብዙ ምስጋና ይገባችኋል። ሌላው እንዲማርበት ኣራት የመፅሐፍ ገፅ "type" ማድረግ ቀላል አስተዋፆ አይደለም።

Thank you again, Brother Meleket.

Abe Abraham
Senior Member
Posts: 14412
Joined: 05 Jun 2013, 13:00

Re: ሰብእና ገደላ (ገጽታ ገደላ) _ የምስጋናው አንዱዓለም እዪታ

Post by Abe Abraham » 07 Nov 2022, 12:15

Assegid S. wrote:
07 Nov 2022, 12:11
ወንድም መለከት ... አስተማሪ ለሆነው ፅሑፍ ደራሲውም አንተም ብዙ ምስጋና ይገባችኋል። ሌላው እንዲማርበት ኣራት የመፅሐፍ ገፅ "type" ማድረግ ቀላል አስተዋፆ አይደለም።

Thank you again, Brother Meleket.
teret teret ye lam ...?

አጼ ፋሲል ሰውነቱ ሁሉ ጸጉር ነው፣ ሴት አብሮ አሳድሮ ያንን እንዳትናገርበት ወደውሀ ይጥል ነበር

Meleket
Member
Posts: 3059
Joined: 16 Feb 2018, 05:08

Re: ሰብእና ገደላ (ገጽታ ገደላ) _ የምስጋናው አንዱዓለም እዪታ

Post by Meleket » 08 Nov 2022, 05:40

ወንድም Assegid S. ስለ ቀጣዩ ማበረታታትህ ከልብ አመስግነናል። እርግጥ ነው የጽሑፉ ኣላማ፡ ይዘቱን በመመልከት አስተማሪ ሆኖ ስላገኘነው ነው ለአንባቢ ያካፈልነው።

ምስጋናው አንዱዓለም ምሕሬትም፡ አንዳንድ ቦታዎች ላይ ከእርሱ ጋር ባንስማማም፡ የአማራውን ህዝብ ትግል ለማስተባበር የጻፈውን ይህን በትንታኔ ዬታጨቀ መጸሐፉን ግን አለማድነቅ ኣይቻልም።

አማራው ማኅበረሰብ ብርቅ ኢትዮጵያውያን አማራ ጸሐፊዎቹንና ምሁሮቹን እነ ፕሮፌሰር ጌታቸው ኃይሌን በማጣቱ ዬከሰረ ቢመስለንም፤ እነ ምስጋናው አንዱዓለም እና እንዳንተም ዓይነቱ ዕንቁ ጸሐፊዎች ስላላችሁት ፈለጋችሁን ይከተል ዘንድና በአላፊኣግዳሚው እንዳይሸማቀቕ ይልቁንም ለህልውናው ይተጋ ዘንድ ሊበረታታ ይገባል።

Assegid S.
Member
Posts: 936
Joined: 11 Aug 2013, 07:11
Contact:

Re: ሰብእና ገደላ (ገጽታ ገደላ) _ የምስጋናው አንዱዓለም እዪታ

Post by Assegid S. » 08 Nov 2022, 08:49

Meleket wrote:
08 Nov 2022, 05:40
ወንድም Assegid S. ስለ ቀጣዩ ማበረታታትህ ከልብ አመስግነናል። እርግጥ ነው የጽሑፉ ኣላማ፡ ይዘቱን በመመልከት አስተማሪ ሆኖ ስላገኘነው ነው ለአንባቢ ያካፈልነው።

ምስጋናው አንዱዓለም ምሕሬትም፡ አንዳንድ ቦታዎች ላይ ከእርሱ ጋር ባንስማማም፡ የአማራውን ህዝብ ትግል ለማስተባበር የጻፈውን ይህን በትንታኔ ዬታጨቀ መጸሐፉን ግን አለማድነቅ ኣይቻልም።

አማራው ማኅበረሰብ ብርቅ ኢትዮጵያውያን አማራ ጸሐፊዎቹንና ምሁሮቹን እነ ፕሮፌሰር ጌታቸው ኃይሌን በማጣቱ ዬከሰረ ቢመስለንም፤ እነ ምስጋናው አንዱዓለም እና እንዳንተም ዓይነቱ ዕንቁ ጸሐፊዎች ስላላችሁት ፈለጋችሁን ይከተል ዘንድና በአላፊኣግዳሚው እንዳይሸማቀቕ ይልቁንም ለህልውናው ይተጋ ዘንድ ሊበረታታ ይገባል።
ወንድም መለከት ... ለመልካም አስተያየትህ እኔም በጣም አመሰግናለሁ

መልካም ቀንም ይሁንልህ!

Post Reply