Ethiopian News, Current Affairs and Opinion Forum
Assegid S.
Member
Posts: 936
Joined: 11 Aug 2013, 07:11
Contact:

ያልተቀበሩ አቶ … .

Post by Assegid S. » 18 Apr 2022, 12:32

https://www.eaglewingss.com/



ያልተቀበሩ አቶ … .

በምክንያት ራቅ ብዬ ከነበረበት የህይወት ውሎ ስመለስ፥ እራሴን ከወቅታዊው የሀገራችን ፖለቲካዊ አየር ጋር ለማላመድ ያልፉኝን ዜናዎች በጨረፍታም ቢሆን መዳሰሱ ግድ ነበር። እናም፦ ከዚህም ከዚያም ዓይኔ ውስጥ የገቡትን የኣጭር ጊዜ ክስተቶች በወፍ-በረር ስማትር … የኣማራ ክልል ምክር ቤት 6ኛ ዙር መደበኛ ጉባዔ ላይ ደረስኩ። ተመለከትኩ - አደመጥኩ፦ አቶ ዮሐንስ ቧያለው የኣማራውን ብሶት ያወሳሉ፣ አትክልተኛው ተሽቀዳድመው በግርድፉ ሳያኝኩ የዋጡት ጥሬ ሰሊጥ ልባቸው ላይ ቆሞባቸዋል መሰለኝ፥ እንደ ከብት አፋቸውን ዘግተው የዋጡትን መልሰው ያመነዥካሉ። እንደ ተቀቀለ ፓስታ እየተልመጠመጠ አላስቆም ያላቸውን የጀርባ አጥንት እንደምንም የቋጠሩበትን ወፍራም ቆዳ ይዘው መድረክ ላይ የወጡት የክልሉ ፕሬዚዳንትም፥ አእምሮና ልባቸውን ከቤተመንግስት ደጃፍ አንጥፈውት እንደመጡ ፍዝዝ ድንዝዝ ያለው የዘወትር ህይወት አልባ ገፅታቸው ያሳብቃል … .

ሰከንዶች እያለፉ በርካታ ደቂቃዎች ቆየሁ፥ የሚሰማ ቀርቶ የሚታይ ነፍስ ያለው ነገር ግን አጣሁ። ድሮውንም ከሙታን ጉባኤ ቁምነገር በመፈለጌ እራሴን ወቅሼ ተንቀሳቃሽ ምስሉን ለመዝጋት ጣቴን ሳንቀሳቅስ ግን ድንገት ኣንድ ቃል ዓይኔ ውስጥ ገባ … "የተከበሩ"

የተከበሩ አቶ … የተከበሩ ወይዘሮ … ተብሎ ጠረፔዛ ላይ የተቀመጠ የስም መለያ (Name Plate.) ስምንተኛው ሺህ ይልሀል ይህን ጊዜ ነው፤ "ድንቄም!” አሉ ወይዘሮ ብርቄ … ገድገድ ቢያድርጋቸው ኣንድ ጠርሙስ አረቄ። ስብዕናውን የሸጠ ነፍስ-አልባ ሙት "የተከበረ" ብለው ሲያሞካሹት። እንደ-እኔ እንደ-እኔ፦ ከነዚህ ሙታን ገባሮች ፊት "የተከበሩ" ሳይሆን ያልተቀበሩ የሚል የስም ታግ ነበር መቀመጥ የሚገባው።

አእምሮውን ለሆዱ ያስገዛ … የወከለውን ህዝብ እንባ ኣንድ ጉንጭ ለማትሆን የአምቦ ውሃ፣ የገዛ ወገኑን አበሳ ጭብጥ ለማትሞላ ጨጨብሳ የረሳን ኣሳማ … በማዕረግ መጥራት ቀርቶ እንደ ተራ የሰው ዘር መቁጠር በራሱ አማሳሉን ያካፈለ እግዚአብሔር አብን እንደ መስደብ ነው።

እውነት ለመናገር፦ ይህ የመረረ ጥላቻ አቻ-ምክንያት አልባ እንዳይሆን በማሰብ ብቻም ሳይሆን፥ ወደ ከፋ ደረጃም እንዳይሻገርብኝ ጭምር … ለብኣዴን ያለኝን እጅግ በጣም መራራ ስሜት ለማለዘብ በተደጋጋሚ ብዙ ጥሬያለሁ፤ በጎ ምግባራቸውን ፍለጋ ብዙ ሞክሬያለሁ። ነገር ግን፦ በየትኛውም ወቅት፥ የብኣዴንን አባላት ተግባርና እንቅስቃሴ … በነጠላም ይሁን በቡድን በመረመርኩ ጊዜ … ውስጤን ቁጭትና ንዴት አልቦት እንጂ ስሜቴን አለዝቦት አያውቅም።

የንጉሱ ኣፍ ሆነው ካገለገሉት የቀድሞ ባለስልጣን እስከ ሰሞነኛው የከንቲባዋ ዣንጥላ፥ ሁሉም ግዑዝ መገልገያ ዕቃ እንጂ ትኩስ ደም ያላቸው ክቡር ሰብዓዊ ፍጥረቶች መስለው አይታዩኝም። ሌላው ቀርቶ፦ በፆታ ተዋፆ በፌደራል መንግስቱ ውስጥ ስልጣን የነበራቸውንና ያላቸውን የህወሃትንም ሆነ የኦህዴድን እንስት ባለስልጣናት (ወይዘሮ ኬሪያ ኢብራሒምን፣ ወይዘሮ ፈትለወርቅ ገ/እግዚአብሔርን፣ ወይዘሮ አዳነች አበቤን፣ ወዘተን) እንደ ምሳሌ በመውሰድ፥ ብሔራዊ መንግስቱ የሰጣቸውን ሀገራዊ ስልጣን በኣደባባይ በማሾር፥ ፍትሐዊ ያልሆነ ጎሳዊ መብትና ጥቅምን ለማስከበር የሄዱበትንና እየሔዱበት ያለውን ርቀት ተመልክቼ ፊቴን ወደ ብኣዴን ሳዞር እጅግ አፍራለሁ። የወከላቸውን ህብረተሰብ ፍትሐዊ ጉድለትና ፍላጎት ለመግለፅ ሳይሆን እራሳቸውን ለመሸጥ እንደተዘጋጁ የመጠጥ ቤት ባልቴቶች፥ ፊታቸው ላይ ደምቆ በተሰመረ ኩል ሞገስ ገዝተው ከፊት የሚደረደሩትን የብኣዴን ተወካዮች በተመለከትኩ ቁጥር፥ ምክር ቤቱም ይሁን የጠቅላይ ሚንስትሩ ጽ/ቤት የቺቺኒያ መሸታ ቤት መስሎ ያምታታኛል።

ከዚህ ቀደም፦ የኦሮምያ ክልል ፕሬዚዴንት የሆኑት አቶ ሽመልስ አብዲሣ በመስቀል አደባባይ "የነፍጠኛውን አከርካሪ ሰብረነዋል" ብለው በፎከሩበት ወቅት:

እውነት ለመናገር፥ በምክትል ጠቅላይ ሚንስትሩ እግር ኣንድ የሱማሌ ወይንም የትግራይ ክልል ባለስልጣን ቢሆን ኑሮ፥ አቶ ሽመልስ አብዲሳ በጓዳቸው እንኳ ለትዳር አጋራቸውም ደፍረው በጆሮዋ የማይተነፍሱትን ስድብ በብሔሩ ላይ እንደወረደ በአደባባይ አያወርዱበትም ነበር ስል ትዝብቴን መግለፄን በሚገባ አስታውሳለሁ … ( የሰው ልጣጭ! October 19, 2019 )

ይኸው ዛሬ፦ ጉንቱው የብኣዴን ባለስልጣን አቶ ዮሐንስ ቧያለው … በተረኛው የኦህዴድ መንግስት ሚዛን የኣማራ መሪዎች የሱማሌን፣ የኣፋርን፣ ወይንም ደግሞ የቤንሻንጉልን ክልል መሪዎች ያክል እንኳ ክብደት እንደሌላቸው በአፋቸው ሲመሰክሩ ሰማን። የኣማራ ክልል ባለስልጣናት "ለእግር ወኃ አቅርቡ ሲባሉ … እኔ ነኝ የማጥብህ!” የሚሉ ስልብ አሽከሮች ናቸው ሲሉ በስተመጨረሻም ቢሆን እውነትን ተንፍሰዋታል። (source: Utopia Cable TV )

ብኣዴን እና ባለስልጣናቱ አንሰው ያሳነሱትን ትልቅ ህዝብ ሳስብ ልጓም የሚበጥሰው ንዴቴ፥ የወረዱበት ሸለቆ ድረስ ወርጄ ምንነታቸውን ለመግለፅ የምጠቀምበት ቃላት፥ የእነርሱን ስብዕና ሳይሆን የራሴን ግብረገባዊ ፍልስፍና እጅግ የሚያጎድፈው መስሎ እየተሰማኝ፥ ቀላል የማይባል ቁጥር ያለውን መጣጥፌን አየር ላይ ከማዋል አግዶብኛል። ዛሬ ግን … የአቶ ዮሐንስ ቧያለውን ምስክርነት ከሰማን ዘንዳ፥ ሌላው ቢቀር እንኳ ከብሔራዊው ምርጫ ጥቂት ቀናት በፊት ከሞነጫጨርኩት ግጥም ቢያንስ በመጠኑም ቢሆን ጠየም ያሉትን ስንኞች ልቆንጥርና የዛሬ ጽሑፌን ልቋጭ። ልብ በሉ! ተፅፎ ለመለጠፍ እጅግ የሚቸግረው ሐረግ … ብኣዴን በአደባባይ የሚጠራበት ማዕረግ ነው። ህወሃትና ኦህዴድ ዳቦ ሳይቆርሱ ያወረሱት የስም ቅርስ!

ኣዴፓ ነህ … ኣማራ?
ንገረኝ ሳትፈራ
ምን ብዬ … ማን ሆነህ
ድምፄን ልጣልልህ?

ብአዴን ነህ … በድኑ?
ትራፊ ቀለቡ?
ኩሊነት ኩል ሆኖ የሚያደምቅህ*
አሽከርነት የማይሻክርህ?

በአንገትህ ስብ ቢዋጥ ማተብህ
ቢያጡ ቅናት ከደመህ
ያኔም ዛሬም ቢጎድልህ ወኔ
ማን ነበር ያሉህ እነ እንቶኔ?

እምብርት የለሽ … እንስሳ
ቅል አእምሮ … አንካሳ
ዘር አሰዳቢ … ሽንታም
እንዳሉህ ከሆንክ … ለሀጫም

እራፊ ጨርቅ እንጂ ዳይፐር
ከአንገት መቀመጫህ 'ሚታሰር
ካርድ ወረቀት ምን ሊፈጥር?
ፈሳሽ ላይመጥ … ላይቋጥር?

ንገረኛ ማን ልበልህ?
ሰው ነው ኣሳማ … ምልክትህ?
በምን ሒሳብ ቀኜን ልስጥህ
እንደ ራሴ ልወክልህ?

ለሆድህ ብለህ ሆድ ያስባስከው
ኣማራን በጅምላ ያዋረድከው
አንተው ከሆንክ ያ የሰው ልጣጭ
ተመርጠህ የሆንከው ምራጭ

እርጉሙን ስላሉህ ጥሩ
ደም አልባውን ደማቁ
ድምፄን ብሰጥህም አታወራ
አፍህ የሚከፈተው ለእንጀራ

አጥንት አልባ ልፍስፍስ
ስለ መብት እኩልነት ላተነፍስ
ይቅር …
ጦሙን ይዋል ኦናው ዝግባ
ባዶ ወንበር ይሻላል ከወኔ-አልባ

* የኩልን ትርጉም፦ የእርሳሱን ኩል ወይንም ደግሞ የእንግሊዝኛውን ቃል “cool” መርጦ … አንባቢ በገባው ይፍታው።

ግንጥል ግጥሙ መታሰቢያነቱ ለአቶ ተመስገን ጥሩነህ እና ለአቶ ደመቀ መኮንን ይሁንልኝ።