Ethiopian News, Current Affairs and Opinion Forum
Assegid S.
Member
Posts: 936
Joined: 11 Aug 2013, 07:11
Contact:

ኣብን ሲያድግ ብኣዴን ነው

Post by Assegid S. » 14 Feb 2022, 17:42

https://www.eaglewingss.com/



ኣብን ሲያድግ ብኣዴን ነው

በድኑ ብአዴን እንደ በሶቢላ እየሸመጠጠ የበላውን ብር "ብድር" ነው ብሎ መቷል። ጎበዝ … እንግዲህ የእኛም ነባር የትግል መፈክር ይቀየር ... ከ"ሙስናን እንዋጋ!" ወደ "ብድርን እንዋጋ!" ሰው … ከዚህም ከዚያም እየተፈናቀለ - ከእርጉዝ እስከ እመጫት በጋ ክረምት ሳይል ላስቲክ ተጠልሎ ባዶ ሆዱን ውሎ - ባዶ ሆዱን ያድራል፥ ኣሳማ ጠግቦ ለግብረ አበሮቹ ሚልዮን ብር ያሻማል።

ኢትዮዽያዊነት በዘር መዘርዘር ከጀመረበት ዘመነ-ህወሃት አንስቶ እስከ ዛሬዋ ዕለት ድረስ እንቆቅልሽ የሆነብኝ ብሔር ኣማራ ነው። ለአቅመ-ሔዋን ያልደረሱ ህፃናት ልጆቹና ልጃገረዶቹ ይደፈራሉ፣ ጎበዛዝቱ በንቀትና ጥላቻ ይተፋባቸዋል፣ አዛውንቶቹ በሽምግልናቸው ከቅዬያቸው ይፈናቀላሉ፣ በኣጠቃላይ "ሀገሬ" በሚላት ኢትዮዽያ ጎረቤት የሆነውን የኬንያን ህዝብ ያክል እንኳን ክብር ሳያገኝ በኣራቱም መዓዘን እንደ አጋዘን እየታደነ ይታረዳል … ዛሬም ድረስ ግን የበሰበሰውን ቀንበር ብአዴንን ከጫንቃው ላይ አውርዶ ለመጣል ሞራልና ድፍረት አጥቷል። ለምን? ኣማራ ውስጥ "ይህ አይሆንም!” የሚል ደፋር ወንድ የለም ማለት ነው? አቶ ተመስገን ጥሩነህን የመሰለ ዘር-አስነዋሪ... ምሳውን እየበላ እራቱ የሚርበው - የማይጠግብ ባንዳ ጅብን የሚተካ የካሣ ዘር ጠፋ?

እራሴን እንደ ኢትዮዽያዊ - ከዚያም እንደ ኣማራ የምቆጥር ዜጋ ብሆንም፥ ኣማራ ወይንም የሌላ ብሔር ተወላጅ ከሆኑ ጎደኞቼ ጋር ስመክርም ሆነ ስከራከር ግን ለኣንዲት ሰከንድ እንኳ በብአዴን የፖለቲካ ድርጅትነት ተስማምቼ አላውቅም። ይህ ደግሞ የእኔ ብቻ ሳይሆን የኣብዛኛው ኣማራ፥ በተለይም ከመሐል ሀገር የተገኘነው የብሔሩ ተወላጆች የጋራ አመለካከት ነው። ብአዴን ለእኔ ጋጣ ነው - የኣህያና ፈረስ ማጐሪያ! ይህን ስል ግን የጭነት እንስሳቱን አገልግሎት እያሳነስኩ አይደለም። ከወይዘሮ ዳግማዊት ሞገስ ይልቅ የአፄ ሚንልክ ፈረስ ለኢትዮዽያም ሆነ ለኣማራ ትልቅ ውለታ እንደሰራ ጠንቅቄ አውቃለሁ። ሌላው ቢቀር ንጉሱን ተሸክሞ ከጦሩ ሜዳ አድርሷል።

ወደ ዋናው ሐሳቤና አልፈታ ወዳለኝ ቋጠሮ ስዞር ... ኣማራ፦ በዚህ ሁሉ የማያባራ የመከራ ቸነፈር እየተመታ በድኑን ብአዴን ለመቅበር የቸገረው ምንድነው? ወንድ ወይንስ ጉድጓድ? የኣማራ ብአዴንን አፈር ለማልበስ ያለመቻል ሚስጢር ምንድነው?

በኢትዮዽያዊነት ስነ-ልቦና ለተገራ ግለሰብ "ከባልደራስና ከብአዴን ለኣማራ ማን ይቀርባል?" ብሎ መጠየቅ ስንፍና ይሆናል፤ አልፎም ኢሰብአዊነት። በመንግስት አስተዳደር ውስጥ ወሳኝ ሥፍራ እንዳለው ድርጅት ስንመለከተው ግን፥ ለኣማራው የታፈነ የመከራ ጩኸት ቀድሞ ድምፅ-ማጉያ መሆን የነበረበት ማን ነው? ብአዴን ወይንስ ባልደራስ? መቼም አንዴ ... ብአዴን እምብርት የሌለው አልቅት ነው፥ ህያው ሆኖ ሳለ ዘላለሙን እንደ ሙት አፈር ውስጥ ተቀብሮ የሚኖር ትል ... ካልን፤ ሌላው ቢቀር፦ ሰሞኑን የምናየውንና የምንሰማውን የኣማራ ማህበረሰብ ዋይታ መፍታት ቢያቅተው እንኳ ለአቤቱታ እግሩ እስኪቀጥን መጓዝ የነበረበት - በቅርብ ከማረሚያ ቤት የወጣው አቶ እስክንድር ነጋ ነበር ወይንስ በቅርብ ከማዕረጉ ማዕድ የጐረሰው አቶ በለጠ ሞላ? ያልታደለ ኣማራ! ጎበዝ ... ሥልጣንም እንደ ስትሮክ (stroke) ድንገት ሲመታ አንደበትን ይቆልፋል እንዴ?

ነገሩ የከረመ እንቆቅልሽ ሆኖብኝ ብዙ ጠየኩኝ እንጂ ... እውነት ለመናገር ... ከእንግዲህ ቦኃላ ለኣማራው ለቅሶም ሆነ ሳቅ መጠየቅ ያለበት ተወካዮቹ ሳይሆኑ እራሱ ወካዩ ማህበረሰብ ነው። ሰማይ-ዳር ያለን ፈጣሪ "ወይ ውረድ - ወይ ፍረድ!" ብሎ ከሞገተ፥ ባህር-ዳር ያለን ኣቃጣሪ አንስቶ ለመፈጥፈጥ ወኔም ሆነ ሞራል ሊያንሰው አይገባም። ንሥሩ አብን ግን "chicken" እየመሰለ መጥቷል። ብዙዎቻችን ... ኣብን ሲያድግ ብኣዴን ነው ... ወደሚለው ድምዳሜ እየተሳብን ነው።