Ethiopian News, Current Affairs and Opinion Forum
MatiT
Senior Member
Posts: 11549
Joined: 16 Feb 2013, 10:18

በደርግ ዘመን ኢሳይያስ አፈወርቂ የሚታውቁትን ያህል በኢትዮጵያ ሕዝብ ውስጥ ሌላ የሚታወቅ የዓመጽያን መሪም አልነበረም፣^ስለ ጦርነት ሲወሳ አርዕስት የነበሩት ኢሳይያስ አፈወርቂ ብቻ ነበሩ።

Post by MatiT » 15 Oct 2020, 21:11

This truth should be known to all Ethiopians.
This truth when the TPLF is in the desert to secede from Tigray....

#ጸሓፊ:፟፟_ ሲሳይ ኣገና Sisay Agena From # ESAT TV

“ኢሳይያስ አፈወርቂ ለኢትዮጵያ የሰጣት የመቶ ዓመት የቤት ሥራ”
" . . . ሻዕቢያ ይበልጥ ያበሳጨን የብሄር ብሄረሰብ መብት እስከመገንጠል የሚለውን አንኳር አቋማችንን አለመቀበሉ ነበር" ገብሩ አሥራት ገጽ 116
". . .ሻዕቢያ እና ምዕራባውያን መቼም ቢሆን የኦነግን የመገንጠል አጀንዳ ሲደግፉ አይቼ አላውቅም" ዶ/ር ነጋሶ ገጸ 152
. . . More importantly, the very systems of government established in Ethiopia and Eritrea after the fall of the Derg were significantly different and not much appreciated in each other’s capital. Isaias especially thought Meles’ concept of ethnic federalism was misguided. . .
David Shinn
የኤርትራው ፕሬዜዳንት ኢሳይያስ አፈወርቂ "ለኢትዮጵያ የመቶ ዓመት የቤት ሥራ ሰጥታናታል" ብለዋል የሚለውን ከሩብ ክፍለዘመን በፊት ጀምሮ አብዝተን ሰምተነዋል።በአንድ በኩል ይህን የሚገልጹልንን በማመን፥በሌላም በኩል በኢትዮጵያ የሆነውን እና የታየውን የልዩነትና የጥላቻ ፖለቲካ በመመርመር በርግጥም ይህ የሻዕቢያ ዕኩይ ዕቅድ ሊሆን እንደሚችል ያመንን ጥቂቶች አልነበርንም።ይህ ሁኔታ በአንድ በኩል ሕወሓትን ያለልክ ዝቅ አድርጎ ከመመልከት እና ሻዕቢያን ከማግዘፍም ይመነጫል።
በእርግጥም ሕወሃት አዲስ አበባ ገብቶ ንግስናውን እስኪጭን “ወያኔ” እንደ አማጺ ቡድን በሕዝብ ውስጥ ቢታወቅም፥መሪው አቶ መለስ ዜናዊ ግን አይታወቁም ነበር። አዲስ አበባ ገብተው የኢትዮጵያ ግዚያዊው መንግስት ፕሬዚዳንት መሆናቸው ሲነገር በሕዝቡ ዘንድ ገጻቸውም፣ ስማቸውም እንግዳ ነበር። በትግሉ ወቅት በመንግስት ሚዲያዎችም ስማቸው አይነሳም። በደርግ ዘመን ኢሳይያስ አፈወርቂ የሚታውቁትን ያህል በኢትዮጵያ ሕዝብ ውስጥ ሌላ የሚታወቅ የዓመጽያን መሪም አልነበረም፣ ስለ ሰሜን ጦርነት፣ ስለ አማጽያኑ ሲወሳ በስም የሚታወቁ እና የመንግስት ሚዲያም አርዕስት የነበሩት ኢሳይያስ አፈወርቂ ብቻ ነበሩ።
የሕወሃት/ኢሕአዴግ ሃይል መሃል ሃገር ገብቶ አምቦን ተሻግሮ ወደ አዲስ አበባ ሲገሠግሥ የደርግ መንግስት አብዛኛውን እና ጠንካራ ሰራዊቱን ኤርትራ ለማቆየት መገደዱ በጦር ባለሙያዎች ዓይን ምን ማለት እንደሆነ ባላውቅም ፥የደርግ መንግስት ለሕወሓት የነበረው ዝቅተኛ ግምት እስከመቃብርም አለመለወጡን ከማሳየቱም ባሻገር፣ይህ የደርግ መንግስት አስተሳሰብ በሕብረተሰቡም ዘንድ እንዲንጸባረቅ ምክንያት ሆኗል። ቤተ መንግስቱን ሊነጥቅ ያሰፈሰፈ ሃይል እየገፋ መጥቶ ከመቶ ባነሰ ኪሎ ሜትር ተጠግቶ ባለበት ሁኔታ አብዛኛውን ጠንካራ ሰራዊት ኤርትራ ማስቀመጥ ምን ማለት ነው? ማዕከሉን ሰጥቶ ፣ቤተመንግስቱን ተነጥቆ የዳሩን መጠበቅስ ይቻላልን ? ጥያቄዬ ለወቅቱ የሃገሪቱ መሪና የጦር ሃይሎች ጠቅላይ አዛዥ ኮሎኔል መንግስቱ ኃ/ማርያም ነው። (ዕድሉን ባገኝ ለኮሎኔል መንግስቱ የማነሳቸው ሌሎች በርካታ ጥያቄዎችም አሉኝ።ከፈቀዱ ዚምቧቤ ሄጄም ቃለምልልስ ለማድረግ ዝግጁ ነኝ)
ወደ ጉዳያችን ወደ አቶ ኢሳይያስ አፈወርቂ እንመለስ።በአጠቃላይ ሕወሓት ከሻዕቢያ በኋላ መፈጠሩና እስከ አዲስ አበባ በተደረገው ጉዞ የሻዕቢያ ድጋፍ እንዳልተለየው መነገሩም ፣ሕወሓትን ያለሻዕቢያ ድጋፍ ማሰብ ለብዙዎች አስቸጋሪ ሆነ። ሑለቱ ቡድኖች አዲስ አበባ እና አስመራ ላይ ስልጣን ከያዙም በኋላ በኢትዮጵያ የንግድ እንቅስቃሴ የሻዕቢያ ተጽዕኖ እየጎላ መምጣቱ መሰማት ጀመረ፣ ቡና የማታመርተው ኤርትራ የኢትዮጵያን ቡና በብር እየገዛች ኤክስፖርተሮች ዝርዝር ውስጥ ገብታ ዶላር የማፈሷ ዜና ጎልቶ መወጣቱ ሕወሃት ራሱን ችሎ የቆመ መንግስት ሳይሆን፣ በኢትዮጵያ የሻዕቢያ ጉዳይ አስፈጻሚ ነው የሚለውም ገዢ ሃሳብ ወደ መሆን ተሸጋገረ።
ኢትዮጵያ ውስጥ ሻዕቢያ ተጽዕኖ ፈጣሪ መሆኑ ስላላጠራጠረም ሃገራችን የገባው የልዩነትና የጥላቻ ፖለቲካ የሻዕቢያ አጀንዳ መሆኑም ጥቂት በማይባሉ ወገኖች ዘንድ ታመነ ። ፕሬዚዳንት ኢሳይያስ አፈወርቂ “ለኢትዮጵያ የመቶ ዓመት የቤት ሥራ ሰጥተናታል” ያሉትም ይህንን የልዩነትና የጥላቻ ፖለቲካ መሆኑም ይተነተን ጀመር።
በኋላ ላይ የኢትዮ ኤርትራ ጦርነት መጀመሩ ተረት እና ዕውነቱን ለማበጠር ፣ ስለ ሁለቱ ሃይሎች ይበልጥ ለመርመር አይን ገላጭ ክስተት ሆነ።
ሻዕቢያ እና ሕወሓት በግንቦት ወር 1990 ጦርነት ውሳጥ ሲገቡ፣ ደም እየፈሰሰም ጦርነቱ የምር መሆኑ ብዙዎችን አጠራጠረ።ነፍሳቸው ይማረውና የአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲው መመህር ዶ/ር መኮንን ቢሻው የመቀሌው አይደር ት/ቤት በቦምብ እስኪደበደብ ጦርነቱ የዕውነት አልመሰለኝም ሲሉ በወቅቱ ለ”ኢትኦጵ” ጋዜጣ የገለጹት የጥርጣሬው ስሜት የተራው ሕዝብ ብቻ እንዳልነበር የሚያሳይ ነው። ሕወሃትን ያለሻዕቢያ ማሰብ ምን ያህል ከባድ እንደነበርም የሚያስረዳን ዶ/ር መኮንን ቢሻው በዚያው ቃለ ምልልስ “ያም ቢሆን መጣላታቸውን መቶ በመቶ አላመንኩም ፣ገና 60 በመቶ ላይ ነኝ “ ማለታቸው ስናስታውስ ነው።
ሕወሃትና ሻዕቢያን ለያይቶ መመልከት በወቅቱ ምን ያህል ከባድ እንደነበር ወቅቱን እና ግኑኝነታቸውን ለሚያስታውስ ግልጽ ነበር። በነገራችን ላይ ዛሬም ድረስ አልተጣሉም ብለው የሚያምኑ “የፖለቲካ ሊቆች” መኖራቸውን በዚሁ አጋጣሚ ማስታወሱና እግዚአብሄር እንዲምራቸው መመኘቱም ተገቢ ነው።
ጦርነቱ ሲቀጥል ፣ እንዲሁም ከጦርነቱ በኋላ ችግሩ እንዴት ጀመረ የሚለውን መመርመር እና መጠየቅ ማንበብ እና መረጃ መቆፈር የግድ ይላል። ለምን ተጣሉ? የቀደመ ግኑኝነታቸውስ ምን ነበር የሚለውን ስመረምር ግን የኢሳይያስ “የመቶ አመት የቤት ሥራ “ የሕወሃት ሆኖ ጠበቀኝ።ሻዕቢያና አቶ ኢሳይያስ ከሕወሃት ጋር ግጭት ውስጥ የገቡበት የጸቡ አንዱ ሰበዝ እኛ የምንታመምበትን የዘር ፖለቲካ ሻዕቢያ በመቃወሙ እንደሆነ አሜሪካዊው ዲፕሎማት ኽርማን ኮኽን ጽፈው ሲያስነብቡን ፥ ሻዕቢያ የትግራይ እና የኦሮሞን መገንጠል በአጠቃላይ የኢትዮጵያን መበታተን አይደግፍም ብለው የኦነጉ አቶ ሌንጮ ለታ እና የሕወሃቱ አቶ ገብሩ አስራት እንዲሁም ዶ/ር ነጋሶ ጊዳዳ እና አቶ መለስ ዜናዊ ሲመሰክሩና በዚህም ከሻዕቢያ ጋር መቀያየማቸውን በኩራት ሲነግሩን ሻዕቢያ በሕወሃት የአገዛዝ ዘመን የክፉ ቀን ከለላ ስለሆነን ብቻ ሳይሆን፣ በዘላቂነትም ወዳጃችን መሆኑ ይገለጥልናል።27 ዓመታት ያሳመሙን ፣ዛሬም ከሸሹ በኋላ በዘሩት በሽታ የሚያሰቃዩን የሕወሃት መሪዎች መሆናቸውም ይከሰትልናል። የሁሉም ምስክርነት በጽሁፍ፣በመጽሃፍ እና በቪዲዮ የተደገፈ በመሆኑ በዝርዝር እንመለከተዋለን። ጦርነቱ ሲጀመር የነበረውን ሁኔታ ግን በቅድሚያ እናስታውስ ።
የዛሬ 22 ዓመት ከ 5 ወር ግንቦት 4 ቀን 1990 ዓ.ም በወቅቱ የመከላከያ ሚኒስትር የነበሩት አቶ ተፈራ ዋልዋ በኢትዮጵያ ፓርላማ ቀርበው የመስሪያ ቤታቸውን የአንድ ዓመት አፈጻጸም ሪፖርት አቀረቡ።በዚህም ኢትዮጵያ ከጎረቤት ሃገራት ጋር ያላት ግኑኙነት ሰላማዊ መሆኑንም ገለጹ። የኢትዮጵያ ቴሌቪዥንም የአቶ ተፈራን መግለጫ በምስል አስደግፎ ዕለቱኑ ዘገበ።
በማግስቱ ግንቦት ቀን 5/1990 ዓ/ም ፍጹም ያልተጠበቀ ፥የአቶ ተፈራ ዋልዋን መግለጫ የሻረ እና ኤርትራ በኢትዮጵያ ላይ ወረራ መፈጸሟን የሚገልጽ ያልተጠበቀ ዜና በዚያው በኢትዮጵያ ቴሌቪዥን ተላለፈ።
አቶ ተፈራ ዋልዋ ዙሪያው ሰላም ነው የሚል መግለጫ በሰጡ ማግስት የመጣው ይህ ዜና ለኢትዮጵያውያንም ሆነ ለዓለም አቀፉ ማህበረሰብ እንግዳ ቢሆንም፥ መንግስታዊዎቹ ሚዲያዎች የመንግስት ባለስልጣናትን ጠቅሰው እንደዘገቡት ትንኮሳው የታየው እና በታንክ የተደገፈው ጥቃት የጀመረው ከሳምንት በፊት ሚያዚያ 28/1990 ነበር።
ያው እንግዲህ አቶ ተፈራ ዋልዋ መከላከያ ሚኒስትር ቢሆኑም ብአዴን እንጂ ህውሃት ባለመሆናቸው፣ የሆነውንም እየሆነ ያለውንም የሰሙት ያው ከኛው ጋር ነበር ማለት ነው።
የወቅቱ ፕሬዚዳንት ዶ/ር ነጋሶ ጊዳዳም ጦርነቱ እስከተከሰተበት ግዜ ድረስ በኢትዮ ኤርትራ ግኑኝነት ዙሪያ ተሳታፊ እንዳልነበሩ "ዳንዲ-የነጋሶ መንገድ" በተባለው መጽሃፋቸው ገጽ 174 ላይ አስፍረዋል። "እስከ ኢትዮ ኤርትራ ጦርነት በኤርትራ ጉዳይ ላይ ሲካሄዱ በነበሩት ውይይቶች ላይ አልተሳተፍኩም" ብለዋል።
ዶ/ር ነጋሶ በዚህም ቅር ይላቸው እንደነበር በዚሁ መጽሃፋቸው ገጽ 222 ላይ አስፍረዋል።ከኤርትራ ጋር ግኑኝነት እንዲያደርግ በተዋቀረው ኮሚቴ ውስጥ ሁሉም የሕወሃት አባላት እንደነበሩ ያስታወሱት ዶ/ር ነጋሶ ጊዳዳ የፈጠረባቸውን ስሜት ሲገልጹም
" ጦርነቱ ሲቀሰቀስ ቅሬታ ነበረኝ። እኛን ደብቀው ውስጥ ውስጡን ሲሰሩ ቆይተው አሁን የሚነግሩን እንዴት ነው የሚል ቅሬታም በውስጤ ተፈጥሮ ነበር" ብለዋል።
እርግጥ ነው በኢትዮ ኤርትራ ግኑኝነት ዙሪያ ኢትዮጵያን ወክለው ሲሳተፉ የነበሩት ሁሉም የሕወሓት አባላት እንደነበሩ የሕወሃት ሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባል የነበሩት አቶ ገብሩ አስራትም ግልጽ አድርገዋል።አቶ ገብሩ አሥራት "ሉዓላዊነትና ዲሞክራሲ በኢትዮጵያ" በተባለው በ2006 በታተመው መጽሃፋቸው በገጽ 268 እንዳሰፈሩት ጦርነቱ እስኪፈነዳ ኢትዮጵያን ወክለው ከኤርትራ ልኡካን ጋር ይነጋገሩ የነበሩት ሶስቱ የህወሃት ሰዎች ጄነራል ጻድቃን ገብረተንሳይ፣ አቶ ተወልደ ወልደማርያም እና አቶ ክንፈ ገብረመድህን ነበሩ።
ሕወሃት እና ሻዕቢያ በግንቦት ወር 1990 የጀመሩት እና ሁለት ዓመታት የዘለቀው ጦርነት በይፋ የሚታወቀው ምክንያቱ የባድመ ይገባኛል ቢሆንም፣ የተጠራቀሙ ችግሮች እንዲሁም በኢትዮጵያ የተዘረጋው የጎሳ ፌደራሊዝም የልዩነት ነጥብ ሆኖ መገኘቱን ፕሮፌሰር ዴቪድ ሺን ይገልጻሉ።በኢትዮጵያ የአሜሪካ አምባሳደር የነበሩት ፕሮፌሰር ዴቪድ ሺን የዛሬ 7 ዓመት January 2014 ጽፈው እንዳስነበቡን በኢትዮጵያ የተዘረጋው የጎሳ ወይንም የብሄር ፌደራሊዝም በኤርትራውያን በተለይም በፕሬዚዳንት ኢሳይያስ ዘንድ ጥያቄን አስነስቷል፣የተሳሳተ መንገድ ስለመሆኑም ፕሬዚዳንቱ አሳስበዋል።
Time to Bring Eritrea in from the Cold (But It’s Harder than It Sounds) – By David Shinn
. . . While the Tigrayan People’s Liberation Front (TPLF) of Meles Zenawi and the Eritrean People’s Liberation Front (EPLF) of Isaias Afewerki often cooperated in their battle to remove the Derg regime from Ethiopia, they also periodically had tactical and strategic differences. In the post-Derg euphoria, these earlier disagreements were usually overlooked by outsiders. More importantly, the very systems of government established in Ethiopia and Eritrea after the fall of the Derg were significantly different and not much appreciated in each other’s capital. Isaias especially thought Meles’ concept of ethnic federalism was misguided. . .
(አርቲክሉን ሙሉን በዚህ ሊንክ ያገኛሉ)
https://africanarguments.org/.../time-to-bring-eritrea.../
ይህንን የዲፕሎማቱን ትንተና የሕወሃት ፖሊት ቢሮ አባል የነበሩት አቶ ገብሩ አስራት "ሉዓላዊነት እና ዲሞክራሲ በኢትዮጵይ" በተባለው እና በ2006 በታተመው መጽሃፋቸው ገጽ 236 ላይ ይህንኑ በማጠናከር የሁለቱ ቡድኖች ልዩነት ወይንም ቅራኔ ከወሰን ይገባኛል የተለየ እንደሆንም በሚከተለው መልክ ይገልጹታል።
" ሻዕቢያዎች ከሕወሀት/ኢሕአዴግ ጋር የተወሰኑ የፖለቲካ ልዩነት እንዳላቸው፥ ከስትራቴጂ አንጻር ግን ምንም ዓይነት ልዩነት እንደሌላቸው ይገልጹልን ነበር።ልዩነት የሚሏቸውንም በሥጋት ደረጃ ብቻ የሚያነሷቸውን ኢሕአዴግ የሚያራምደውን የብሄር ብሄረሰብ መብት እስከመገንጠል አቋምና ይህንን መሰረት ያደረገውን አወቃቀር ነበር።ይህ በኢትዮጵያ የተቋቋመው የፌደራል ሥርዓት ለግጭት እና ለኢፍትሃዊ የሃብት ክፍፍል ሊዳርግ ይችላል የሚል ሥጋት እንደነበራቸውም በግልጽ ይነግሩን ነበር።ከዚያ ውጭ ሌላ የፖለቲካ ልዩነት እንደሌላቸው እና ከኛ ጋር የሚኖራቸው ግኑኝነትም ስትራቴጂካዊ ሊሆን እንደሚችል ይገልጹልን ነበር”
አቶ ገብሩ አሥራት ይህንን በመጽሃፋቸው ገጽ 116 ላይ ሲያጠናክሩም
" ሻዕቢያ ይበልጥ ያበሳጨን የብሄር ብሄረሰብ መብት እስከመገንጠል የሚለውን አንኳር አቋማችንን አለመቀበሉ ነበር"
አቶ ገብሩ በመጽሃፋቸው እንዳሰፈሩት ሻዕቢያዎች የልዩነት ነጥብ በማለት የሚያነሱት እና እንደ ሥጋት የሚጠቅሱት የኢሕአዴግን የራስን ዕድል በራስ መወሰን መብት እስከመገንጠል የሚለውን እና ይህንን መሰረት ያደረገውን የፌደራል ሥርዓት አወቃቀር ነበር።ሻዕቢያዎች ይህ ሁኔታ ለግጭት እና ለኢፍትሃዊ የሃብት ክፍፍል ይዳርጋል የሚል ሥጋታቸውን ይገልጹ እንደነበርም የሕወሃቱ አቶ ገብሩ አሥራት በመጽሃፋቸው ያስታውሳሉ። ይህንን የሻዕቢያ አቋም ሕወሃት መጨረሻ ላይ ከደረሰብት ውድቀት እና ሃገሪቱ ላይ ጥሎ ካለፈው መከራ አንጻር በመመዘን በእርግጥም የኢትዮጵያ ጠላት ማነው የሚለውን ጥያቄም አድምቆ ማስመር ያስፈልጋል።
ሟቹ የቀድሞ የኢፌድሪ ፕሬዚዳንት የቀድሞው የኦነግ አባል ዶ/ር ነጋሶ ጊዳዳም በኦነግ እና በሻዕቢያዎች መካከል ስለነበረው ግኑኝነት ሲጠቅሱም ሻዕቢያ ኦነግን የሚረዳው ደርግን ለመጣል እንዲያግዘው ነው ይላሉ። ሻዕቢያ የኦነግን የቅኝ ግዛት ጥያቄ እንደማይቀበል እና በኦሮሚያ ያለው የፊውዳል መስፋፋት እንጂ ቅኝ ግዛት አይደለም እንደሚል የዳንዲ መንገድ በተባለው መጽሃፋቸው ገጽ 115 ላይ አስፍረዋል።ዶ /ር ነጋሶ ይህንኑ በገጽ 152 ላይ ሲያጠናክሩም፦"ሻዕቢያ እና ምዕራባውያን መቼም ቢሆን የኦነግን የመገንጠል አጀንዳ ሲደግፉ አይቼ አላውቅም" ብለዋል። ዶ/ር ነጋሶ በዚሁ መጽሃፋቸው በገጽ 172 ላይ ደግሞ
"ሻዕቢያ በኢትዮጵያ ውስጥ ተጽዕኖ የማሳረፍ ውጥኑን ለማሳካት ሲል ሕወሃትም ሆነ የኦሮሞ ድርጅቶች ተባብረው ደርግን እንዲጥሉ ቢፈልግም የእሱ ዓይነት የነጻነት ጥያቄ እንንዲያነሱ ግን አይሻም ነበር”
ሟቹ የቀድሞ ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊም የኤርትራ ሕዝብ ትግል ከየት ወዴት በተባለውና በአቶ አብርሃም ያየህ ከትግርኛ ወደ አማርኛ በተመለሰው መጽሃፍቸው ገጽ 170 "የራስን ዕድል በራስ መወሰን ጥያቄ ላይ የተነሳ ልዩነት" በሚል ንዑስ ርዕስ ሻዕቢያ በኢትዮጵያ የብሄረሰቦች የመገንጠል መብትን በመቃወም ሕወሃት ለሃገራዊ አንድነት እንዲታገል ያቀረበውን ጥያቄ አንስተው ይተቻሉ።በዚህም ግኑኝነታቸው መሻከሩን በኋላም መቋረጡን ያብራራሉ።
የኦነግ መስራች እና ጸሃፊ የነበሩት አቶ ሌንጮ ለታም በኢሳት ቴሌቪዥን March 2016 ባደረጉት ቃለምልልስ ሻዕቢያ የሕወሃትንም ሆነ የኦነግን የመገንጠል ጥያቄ እንደማይቀበል ይልቁንም ለአንዲት ኢትዮጵያ እንዲሰሩ ግፊት ያደርግ እንደነበር በድምጽ እና በምስል መስክረዋል። (ከተያያዘው ቪዲዮ ከ15 ኛው ደቂቃ ጀምሮ የአቶ ሌንጮን ምስክርነት ይስሙ)

ሌሎች የጽሁፍ እና የድምጽ ምስክርነቶችም ከላይ የተዘረዘረውን የሚያጠናክሩ ሆነው አግኝቺያለሁ።ፕሮፌሰር መስፍን ወልደማርያም በNovember 2015 ከኢሳት ጋር ያደረጉት ቃለምልልስ ፣ዶ/ር ካሳ ከበደ October 2015 ዋሺንግተን ዲሲ ውስጥ በተካሄደው የኢትዮ ኤርትራ ኮንፈረንስ ላይ ያደረጉት ንግግር ወዘተ ተረቱን የሚደፍቁ ፣የነ አቶ ገብሩ አስራትን ምስክርነት የሚያረጋግጡ ናቸው። በአጠቀላይ የኢሳይያስ አፈወርቂን “ጸረ ኢትዮጵያ አጀንዳ” እና “የመቶ ዓመት የቤት ሥራ” ስፈልግ ያገኘሁት ዕውነታ ይህ ነው።
ይህም ብቻ አይደለም።ሰለ ኢትዮጵያም ሆነ ስለ ብሄራቸው መብት የተከራከሩና ፍትህ የጠየቁ በወህኒ በሚሰቃዩበት፣የሸሹም ከጎረቤት ሃገራት ጭምር በሚታፈኑበት ፣ ሕወሃት ምድሩንም ሰማዩንም በተቆጣጠረበት በዚያ ጨለማ ዘመን ብቸኛ መሸሻ ፣ለመታገልም መንደርደሪያ እና መጠጊያም የነበረችው በፕሬዚዳንት ኢሳይያስ የምትመራው ኤርትራ ነበረች፣ከለውጡም በኋላም ሕወሃቶች የነርሱ ጸጥታ መዋቅሩ ከመጽዳቱ በፊት ያበጠው ይፈንዳ ብለው የግልበጣ ሙከራ ያላደርጉት ቀውሱ አሳስቧቸው ወይንም የምዕራባውያኑ ተግሳጽ አስጨንቋቸው ብቻ ሳይሆን፣የኤርትራን መንግሥት በመፍራት ጭምር መሆኑንም መጠራጠር ይቻላል።
ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ እና ቡድናቸው ከኤርትራ መንግሥት ጋር ሊወዳጁ እንደሚችሉ የሕወሃት መሪዎች አስቀድመው ቢገምቱ ኖሮ መጋቢት 24/2010 የጠቅላይ ሚኒስትር አብይ በዓለ ሲመት መሆኑ ቀርቶ፣ሁለት ዓመታት የቀጠለው ቀውስ ወደ ከፋ ዕልቂት የሚያመራበት ምዕራፍ መጀመሪያም ይሆን ነበር። ሓምሌ 1 ቀን 2010 ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ ወደ አስመራ፣ሃምሌ 7 /2010 ፕሬዚዳንት ኢሳይያስ ወደ አዲስ አበባ ያደረጉት ጉዞ የሕወሃት መሪዎች እጃቸውን እንዲሰበስቡ እና አርፈው እንዲቀመጡ ግልጽ መልዕክት አስተላልፏል ተብሎም ይታመናል።የለውጡን ሃይል በቀጥታ ከመታገል ይልቅ በየክልሉ ቀውስ ስፖንሰር ማድረግ የመረጡት ፊትለፊት ከግንብ ጋር መላተሙ ስለማያዋጣ እና ተራራውን መግፋት እንደማይቻል በማመናቸው ጭምር ነው። . . . አዎን ትርክቶችን አምነን ፣ መጽሃፉን ስንገልጥ ያገኘነው ዕውነትና ዛሬ ያለንበት ሁኔታ ይህ ነው።የቀረው ተረት ነው።
ፕሬዚዳንት ኢሳይያስም ሆኑ፣ የኤርትራ መንግስት ትናንትም ሆነ ዛሬ የኢትዮጵያ ጠላት አለመሆናቸውን እንዳረጋገጥን ሁሉ ነገም ጥሩ ወዳጀ እና ወንድም ሆነው እንደሚቀጥሉ እናምናለን።ከኢትዮጵያም ሆነ ኤርትራ ለትውልድ የሚቀርበው ትልቁ ገጸ በረከት የትናንትን ፋይል ዘግቶ፣ ለነገ የተደላደለ ጥርጊያ መዘርጋት ነው።
ጥቅምት 5/2013 October 14/2020
Time to Bring Eritrea in from the Cold (But It's Harder than It Sounds) – By David Shinn | African Arguments
AFRICANARGUMENTS.ORG
Time to Bring Eritrea in from the Cold (But It's Harder than It Sounds) – By David Shinn | African Arguments

quindibu
Member
Posts: 3279
Joined: 31 Dec 2010, 13:17

Re: በደርግ ዘመን ኢሳይያስ አፈወርቂ የሚታውቁትን ያህል በኢትዮጵያ ሕዝብ ውስጥ ሌላ የሚታወቅ የዓመጽያን መሪም አልነበረም፣^ስለ ጦርነት ሲወሳ አርዕስት የነበሩት ኢሳይያስ አፈወርቂ ብቻ ነ

Post by quindibu » 15 Oct 2020, 21:42

Sisay Agena is the only Ethiopian journalist who consistently disproves my long held view that there are no journalists, but cadres, in Ethiopia!

My hats off to you, Sir!


Post Reply