Ethiopian News, Current Affairs and Opinion Forum
Bashuu
Member
Posts: 6
Joined: 15 Jul 2023, 21:32

The Horror On Addis Residents Continues In The Name Of Limat

Post by Bashuu » Yesterday, 13:24

የካዛንቺስ ቤት ፈረሳና የእናቶች ጩኸት

አበበ ፍቅር
ቀን:

September 18, 2024

አዲሱን ዓመት በጭንቀትና በፍርኃት ያሳለፉት የካሳንቺስ አካባቢ ነዋሪዎች ዛሬም የሚጠጉበት ጥግ አጥተው ልጆቻቸውን ይዘው ጎዳና ላይ ለመውጣት ነገ ዛሬ እያሉ እንደሆነ ተናግረዋል፡፡

የአሮጌው ዓመት መጠናቀቂያ የአዲሱ ዓመት መባቻ ነበር ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ፣ ሁለተኛውን ዙር የኮሪደር ልማት በይፋ ያስጀመሩት፡፡ አዲሱ ኮሪደር እስካሁን ከተሠራው የሰፋ እንደሆነ በመግለጽ፣ አካባቢው በጣም ያረጀ በመሆኑ ፈርሶ በአዲስ መተካት እንዳለበት መልዕክት ማስተላለፋቸው ይታወሳል፡፡

ታላቁ ቤተ መንግሥት ጀርባ ካሳንቺስ አካባቢ፣ ከመስቀል አደባባይ እስከ መገናኛ፣ ከጣሊያን ኤምባሲ ጀርባ ጀምሮ ግንፍሌ ቀበናና አዋሬን ይዞ የሚሄደውን የወንዝ ፕሮጀክት፣ ከአፍሪካ ኮንቬንሽን ሴንተር እስከ ጎሮ ያለው ቀጣና፣ ከአራት ኪሎ በሽሮ ሜዳ እስከ እንጦጦ፣ ከእንጦጦ ወደ በፒያሳ በፍሬንድሺፕ ወደ ፒኮክ የሚወስደውን የወንዝ ፕሮጀክት አጠቃሎ እንደሚይዝ ጠቅላይ ሚኒስትሩ የተናገሩት በቅርቡ ነበር፡፡

ቤተ መንግሥት ጀርባ ካሳንቺስ አካባቢ የከተማዋ ከንቲባ ወ/ሮ አዳነች አበቤ በበላይነት እንዲመሩት የተሰጣቸው ሲሆን፣ ሕዝብን አወያይተው እንደሚያከናውኑ ተስፋ ጥለውባቸው ነበር፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትሩ በተናገሩ ማግሥት ‹‹ቤታችሁ ሊፈርስ ነው በአጭር ጊዜ እንድትለቁ›› በመባላቸው የአዲስ ዓመት በዓልን በጭንቀት ማሳለፋቸውን ነዋሪዎቹ ተናግረዋል፡፡

አካባቢው እንደሚፈርስ ከተነገራቸው ጊዜ ጀምሮ በጭንቀትና በፍርኃት ውስጥ እንደሆኑ የተናገሩት ነዋሪዎቹ፣ ከአዲሱ ዓመት ጀምሮ ባሉት 21 ቀናት ውስጥ ቤታቸውን ለቀው እንዲወጡ እንደተነገራቸው ገልጸዋል፡፡

‹‹ቤታችሁ ለልማት ሊፈርስ ነው ነገ ዛሬ ሳትሉ በአጭር ቀን ለቃችሁ እንድትወጡ›› ስለመባላቸው በዕንባ ታጅበው የሚናገሩት ነዋሪዎቹ፣ የልጆቻቸው ትምህርትና ሠርተው የሚተዳደሩበት ሥራ ከሁሉም በላይ ረሃብና ጥማታቸውን፣ ገመናቸውንም የሚሸፍኑበት፣ ሲደክማቸው የሚያርፉበት ደስታም ሆነ ሐዘናቸውን የሚወጡበት ቤታቸው በድንገት ከላያቸው ላይ ሊፈርስባቸው እንደሆነ በሐዘን ተውጠው እየተናገሩ ነው፡፡

ሪፖርተር ተዘዋውሮ ካዛንችስ አካባቢ ቤታቸው የሚፈርስባቸውን ነዋሪዎች ባነጋገረበት ወቅት ባደረገው ምልከታም፣ ነዋሪዎቹ በአስከፊ ሁኔታ አዛውንትና ሕፃናት ሴቶች በለቅሶ ታጅበው በከፋ ችግር ውስጥ እንደሚኖሩ ለመረዳት ችሏል፡፡

ከ20 ዓመት በላይ እንደኖሩበት የሚናገሩት ለደኅንነታቸው በመሥጋት ስማቸውን መግለጽ ያልፈለጉ አንዲት እናት፣ እስከ መስከረም 21 ድረስ ቤታቸውን ለቀው እንዲወጡ መባላቸው በጣም እንዳስጨነቃቸው ተናግረዋል፡፡ የሦስት ልጆች እናት የሆኑት እኚህ እናት፣ ‹‹በዕንቅርት ላይ ጆሮ ደግፍ›› እንዲሉ ሁለቱ ልጆቿ በሕመም ላይ ናቸው፡፡ አንዷ የስኳር ታማሚ ስትሆን በመድኃኒት የዕለት ተዕለት ኑሮዋን የምትገፋ፣ እንዲሁም ሌላኛዋ ሕፃን ልጇ ደግሞ የአካል ጉዳተኛ ናት፡፡ ሦስት ልጆቿን መንገድ ዳር ችፕስ በመሸጥ የሚያስተዳድሩ ሲሆኑ ዛሬ ላይ ግን ቤትም ሆነ ሥራ እንድትለቁና ከአካባቢው እንዲነሱ መደረጉ በእጅጉ እንዳስጨነቃቸው ተናግረዋል፡፡

‹‹ከዚህ በኋላ የት ነው የምገባው ልጆቼንስ ወዴት ነው የማደርጋቸው›› የሚሉት እኚህ እናት፣ ከወረዳ እስከ ክፍለ ከተማ እግራቸው እስኪቀጥን ቢሄዱ የሚሰማቸውና መፍትሔ የሚሰጣቸው አካል ማጣታቸውን ያክላሉ፡፡

‹‹ክፍለ ከተማ ስጠይቅ ወረዳ ሂጂ ይሉኛል፣ ወረዳ ስሄድ ነገ ዛሬ ነይ እያሉ ከማመላለስ የዘለለ ችግሬን የሚሰማልኝ አካል አላገኝሁም፤›› በማለት በሽተኛ ልጆችን ይዘው ችግር ላይ መውደቃቸውን ተናግረዋል፡፡

‹‹ነገ ነይ የሚለኝን የወረዳ ሠራተኛ በቀጠረኝ ቀን ስሄድ ተቀይሯል ይሉኛል፤›› የሚሉት ቅሬታ አቅራቢዋ፣ ታማሚ ልጆቻቸውን ይዘው ጎዳና ላይ ለመውጣት እንደሚገደዱ ተናግረው፣ ልጆቻቸው የሚወስዱት መድኃኒት በመቋረጡ ሕይወታቸው አሥጊ ደረጃ ላይ ነው፡፡

ዕንባቸው ከዓይናቸው ሞልቶ እየፈሰሰ ብሶታቸውንና ሥጋታቸውን የሚናገሩት እናት አባታቸው ወደ ቤት ከሚመጣበት የማይመጣበት ቀን ይበዛል፣ ልጆቼን ብቻዬን መንገድ ዳር ችፕስ በመሸጥ ብቻ ነው የማስተዳድራቸው ይላሉ፡፡

ከክፍለ ከተማ የመጡ አመራሮች ቤታቸውንና ያሉበትን የኑሮ ሁኔታ አይተው ቤት ይሰጣችኋል ብለው መሄዳቸውን የተናገሩት እኚህ እናት፣ ነገር ግን ይሰጣችኋል ከሚል ባዶ ተስፋ ውጭ የሚጨበጥ ነገር ጠፍቶባቸው ወረዳ እየተመላለሱ የሚያናግራቸው አጥተው እንደሚገኙ ነው የተናገሩት፡፡

‹‹ዕድሜ ልካችንን ሠርተን ለሆዳችንና ለቤት ኪራይ ብቻ በመክፈል ነው፤›› ኑሯችንን የገፋነው የሚሉት ሌላኛዋ እናት ናቸው፡፡ ለብዙ ዓመታት የቀበሌ ቤት ተከራይተው ይኖሩ የነበሩት እኚህ እናት፣ ቤቱ ሊፈርስ በመሆኑ ከልጆቻቸው ጋር ጎዳና መውጣት ብቸኛ አማራጫቸው ስለመሆኑ በሐዘን ውስጥ ሆነው ነው የሚናገሩት፡፡ ወደ ወረዳ በመሄድ ወዴት እንድረስ ልጆች ይዘን ምን እንሁን ብለን ስንጠይቅ፣ ‹‹ተከራይ ምን አፍ አለው እንደለመዳችሁት ሌላ ቦታ ሄዳችሁ ተከራይታችሁ መኖር ትችላላችሁ፤›› የሚል ምላሽ እንደሚሰጧቸው ተናግረዋል፡፡

‹‹ባለቤቴ የቀን ሥራ ነው የሚሠራው፣ የቀን ሥራ ደግሞ አንዴ ሲታጣ ሌላ ጊዜ ሲገኝ ነው፤›› የሚሉት ሌላኛዋ አስተያየት ሰጭ፣ ቤታቸው ሊፈርስ በመሆኑ ከአዛውንት እናታቸውና ከሦስት ልጆቻቸው ጋር አብረው በጠባብ ቤት ክፉውንም ደጉንም ያሳለፉ መሆኑን ገልጸው፣ ዛሬ ለዓመታት የኖሩበት የቀበሌ ቤት ሊፈርስ መሆኑን ሲሰሙ በእጅጉ መጨነቃቸውን ያስረዳሉ፡፡

‹‹መንግሥት ለእናቶችና ለሕፃናት የተሻለ ጊዜ ይሆናል ሲለን ቆይቶ ዛሬ ላይ ግን ልጆቻቸውን ከትምህርት ተለያዩ እኛም እንዳቅማችን ሠርተን እየከፈልን ከምንኖርበት ቤት ተባረርን፤›› የሚሉት እኚህ እናት፣ ቤት ለመከራየት እንኳን ልጆቻችንን ቆጥረው ፈቃደኛ እንደማይሆኑ ከወዲሁ ያለባቸውን ሥጋት ያክላሉ፡፡

‹‹ምን ሠርቼ ነው ልጆቼን የማበላው? ምንስ ሠርቼ ነው የቤት ኪራይ የምከፍለው ሁለት ሕፃናት ልጆቼን ይዤ ወዴት እገባለሁ፤›› በማለት ጭንቀታቸውን ይናገራሉ፡፡

ትምህርት ቤት ለመማር ተመዝግበው የነበሩ ተማሪዎች ወደ ትምህርት ቤት የመሄድና የመማር ፍላጎት እንደሌላቸው ተናግረዋል፡፡