Ethiopian News, Current Affairs and Opinion Forum
sarcasm
Senior Member
Posts: 10186
Joined: 23 Feb 2013, 20:08

በብሔር ማንነት ላይ የተመሰረተ ሕገ ወጥ የዘፈቀደ እስር ለ7 ወር በአፋር ክልል ያሉ 9ሺ የትግራይ ተወላጆች በአፋጣኝና ያለቅድመ ሁኔታ ሊለቀቁ ይገባል - የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን

Post by sarcasm » 29 Jun 2022, 19:12

በአፋር ክልል ሰመራ ከተማ ሰመራና አጋቲና ካምፕ ውስጥ ተይዘው የሚገኙ ሰዎች በአፋጣኝና ያለቅድመ ሁኔታ ሊለቀቁ ይገባል
June 29, 2022
Report


በብሔር ማንነት ላይ የተመሰረተ ሕገ ወጥ እና የዘፈቀደ እስር በመሆኑ በአፋጣኝ ሊለቀቁ ይገባል፤ ወደ መኖሪያ አካባቢያቸውም እስኪመለሱ ድረስ በካምፑ ውስጥ ለመቆየት የሚፈልጉ ሰዎች ቢኖሩ በሙሉ ፈቃደኝነትና ያለ ማናቸውም ዓይነት የእንቅስቃሴ ገደብ ሊሆን ይገባል

የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) ጋዜጣዊ መግለጫ
ሰኔ 22 ቀን 2014 ዓ.ም.

የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) ከግንቦት 15 እስከ 20 ቀን 2014 ዓ.ም. በአፋር ክልል ሰመራ ከተማ በሚገኙ ሰመራ እና አጋቲና ካምፖች በመባል በሚታወቁ ቦታዎች ውስጥ በሰሜን ኢትዮጵያ ከተካሄደው ጦርነት ጋር ተያይዞ “ለደኅንነታቸው ጥበቃ እና በወንጀል ጥርጣሬ የሚፈለጉ ሰዎችን ለመለየት” በሚል ምክንያት ከትግራይ ክልል አዋሳኝ ከሆኑ 3 የአፋር ክልል ወረዳዎች፣ ማለትም ከአባላ፣ ከኮነባ እና ከበረሃሌ፣ በታኅሣሥ ወር 2014 ዓ.ም. ተይዘው የቆዩና በሁለቱ ካምፖች የሚገኙ ወደ 9 ሺህ የሚጠጉ የትግራይ ተወላጆች ያሉበትን ሁኔታ በቦታው በመገኘትና በማነጋገር፣ የመንግሥት አካላት እና አገልግሎት ሰጪዎችን እንዲሁም ሌሎች መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶችን በማነጋገር ክትትል ሲያደርግ ቆይቷል።

በሁለቱም ቦታዎች በመጠለያ ጣቢያ ስም ተይዘው የሚገኙት ሰዎች ወደእነዚህ ስፍራዎች እንዲመጡ የተደረገው የአፋር ክልል የፀጥታ ኃይሎች በዞንና ወረዳ ደረጃ ካሉ ሲቪል አመራሮች ጋር በመሆን በወሰዱት እርምጃ፣ ከዚህ በላይ ከተጠቀሱት አካባቢዎች የትግራይ ተወላጆችን ለይተው በመሰብሰብ ከታኅሣሥ ወር 2014 ዓ.ም. ጀምሮ በተለያዩ ቀናት በመኪና በማጓጓዝና አሁን ወደሚገኙበት ካምፖች በማምጣት ነው፡፡

ኮሚሽኑ ያነጋገራቸው በካምፖቹ ውስጥ የሚገኙት ሰዎች ከመኖሪያቸው አካባቢ እንዲወጡና በነዚህ ቦታዎችም እስካሁንም ድረስ እንዲቆዩ የተደረጉት ከፍቃዳቸው ውጪ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

በሁለቱ ካምፖች በኢሰመኮ የክትትል ጉብኝት ወቅት 8,560 ሰዎች የነበሩ ሲሆን፣ ወንዶች እና ሴቶች ተለያይተው የተያዙ በመሆናቸው የአንድ ቤተሰብ አባላት ተለያይተው ለመኖር ተገድደዋል። በካምፖቹ ውስጥ የሰብአዊ እርዳታና የሕክምና አገልግሎት አቅርቦት እጅግ ውስን በመሆኑና በካምፑ በተከሰተ ወረርሽኝ መሰል በሽታ ለሕይወት መጥፋት ጭምር ምክንያት ሆኗል፡፡ በወሊድ ምክንያት ካልሆነ በስተቀር በአካባቢው ወደሚገኝ የጤና ተቋም ሄዶ ለመታከም ባለመፈቀዱ ችግሩን አባብሶታል፡፡

ባለፉት 5 ወራት ውስጥ በሰመራ ካምፕ ብቻ በበሽታ ሕይወታቸው ያለፉ ሰዎች፣ እንዲሁም ካምፑ ውስጥ በወሊድ ወቅት ልጅ የሞተባት እናት መኖራቸውን ተይዘው የሚገኙት ሰዎች ለኮሚሽኑ አስረድተዋል። ቤተሰቦቿ የአእምሮ መረበሽ (የማኅበረ ሥነ ልቦና ጉዳት) ደርሶባታል በሚል በሰንሰለት አስረው ያስቀመጧት ወጣት ሴት፣ እስከ 10 የሚደርሱ ከባድ ቁስል ያለባቸው ሰዎች፣ የአእምሮ እድገት ውስንነት ያለባቸው 5 ሕፃናት እንዲሁም የቆዳ በሽታ ወረርሽኝ ነው በተባለ በሽታ የተጠቁ ከ4-5 ዓመት ዕድሜ መካከል የሚገኙ ሕፃናት በእነዚሁ ካምፖች ውስጥ ይገኛሉ። ኮሚሽኑ ያነጋገራቸው ሰዎች ወቅታዊ እና ተገቢ ሕክምና ባለማግኘታቸው የቆዳ ወረርሽኝ የተባለው በሽታ ወደ ሌሎች ሰዎች በመዛመቱ አጠቃላይ ደኅንነታቸውና ሕይወታቸው ጭምር አደጋ ላይ መውደቁን ለመረዳት ተችሏል።

ኢሰመኮ ያነጋገራቸው ጉዳዩ የሚመለከታቸው የክልሉ መንግሥት አካላት “የእንቅስቃሴ ገደብ የተጣለው ለሰዎቹ ደኅንነት ጥበቃ እና ከፀጥታ ስጋት ጋር በወንጀል ጥርጣሬ የሚፈለጉ ሰዎችን የመለየት ስራ መስራት በማስፈለጉ” መሆኑን ይናገራሉ። የኢሰመኮ ዋና ኮሚሽነር ዶ/ር ዳንኤል በቀለ “በአፋር ክልል ሰመራ ከተማ ሰመራና አጋቲና ካምፕ ውስጥ ተይዘው የሚገኙት ሰዎች ሁኔታ በመጠለያ ጣቢያ ስም የተፈጸመ፣ በብሔር ማንነት ላይ የተመሰረተ ሕገ ወጥ እና የዘፈቀደ እስር በመሆኑ በአፋጣኝ ሊለቀቁ ይገባል፤ ወደ መኖሪያ አካባቢያቸውም እስኪመለሱ ድረስ በካምፑ ውስጥ ለመቆየት የሚፈልጉ ሰዎች ቢኖሩ በሙሉ ፈቃደኝነትና ያለ ማናቸውም ዓይነት የእንቅስቃሴ ገደብ ሊሆን ይገባል” ብለዋል፡፡ ዶ/ር ዳንኤል አክለውም “በፈቃዳቸው ወደ መኖሪያ አካባቢያቸው ለመመለስ ወይም አሁን ባሉበት ቦታ ለመቆየት ወይም ወደ ሌላ ቦታ ለመሄድ ለሚፈልጉ ሰዎች ሁሉ አስፈላጊው ድጋፍና እርዳታ ሊሰጣቸውም ይገባል፤ እንዲሁም በምክንያታዊ ሁኔታ በወንጀል የተጠረጠሩ ሰዎች ካሉ በመደበኛው የወንጀል ፍትሕ አስተዳደር ሥርዓት ከሚታይ እና በፍርድ ቤት ትእዛዝ ብቻ ከሚፈጸም በስተቀር፤ የአሁኑ አያያዝ የሕግ መሰረት የሌለው ከመሆኑም በተጨማሪ በካምፑ የሚገኙትን ሰዎች ለተደራረበ የሰብአዊ መብቶች ጥሰት እያጋለጠ በመሆኑ በአፋጣኝና ያለምንም ቅድመ ሁኔታ ሊያበቃ ይገባል” በማለት አሳስበዋል፡፡


https://ehrc.org/%E1%89%A0%E1%8A%A0%E1% ... %E1%8A%93/