Ethiopian News, Current Affairs and Opinion Forum
Revelations
Senior Member+
Posts: 33669
Joined: 06 Jan 2007, 15:44

በጊምቢው ጭፍጨፋ በተገደለችው እናቷ እቅፍ የተገኘችው የ15 ቀኗ ጨቅላ ሕጻን

Post by Revelations » 27 Jun 2022, 12:10

27 ሰኔ 2022

አይሻ ሰይድ የተወለደችው በደቡብ ወሎ ዞን፣ አርጎባ ወረዳ ውስጥ ነው። እዚያ ትወለድ እንጂ እድገቷ ግን በምዕራብ ወለጋ፣ ጊምቢ ወረዳ ፣ ቶሌ ቀበሌ ውስጥ ነው።

ወደዚያ ያቀናችው በ1990 ዓ.ም ነበር። ያኔ ነፍስ ያላወቀች ሕጻን ነበረች ።

አይሻ አልተማረችም። በግብርና ሥራ የሚተዳደሩ አባቷን እያገዘች ነበር የምትኖረው።

እድሜዋ ከፍ ሲልም እዚያው ባደገችበት ቶሌ ቀበሌ ትዳር መሰረተች። የራሷን ጎጆ ቀለሰች። ሕይወት እንዲህ እያለ ቀጠለ።

ልጆችን አከታትላ ወለደች። በሚያማምሩ ሁለት ሴት ልጆች ተባረከች።

ከዚያም ከአራት ዓመታት ቆይታ በኋላ የመጨረሻዋ የሆነችውን ሴት ልጇን ተገላገለች። ግን እንደ ሌሎቹ ሁሉ ልጇ ድክድክ ስትል ለማየት አልታደለችም። የሚኮላተፈውን አፏን ለማጣጣምም አልበቃችም።

አይሻ ሰይድ ቅዳሜ፣ ሰኔ 11 2014 ዓ.ም በኖረችበት ቀዬ ከሌሎች በርካታ ሰዎች ጋር ስትገደል ልጇ የ15 ቀናት ዕድሜ ብቻ ነበር የነበራት።

የ25 ዓመቷ አይሻ፣ እናቷ በአቅራቢያዋ የለችም። እንደ አራስ ይህንን ነው የምመገበው ብላ አላማረጠችም። ባለው የፀጥታ ችግርም አራስ ቤቷ የምቾትና የድሎት ሳይሆን የሰቀቀን ነበር።

“በአካባቢው የሚኖሩ የአማራ ተወላጆች በታጣቂዎች ማስፈራሪያና ዛቻ ስለሚደርስባቸው ኑሯችን በስጋት የተሞላ ነበር” ይላሉ ታሪኳን ያካፈሉን የአይሻ የቅርብ ዘመድ።

በስጋት ብቻ ግን አላበቃም።

ለደኅንነታቸው ስንል ስማቸውን የማንጠቅሳቸው የአይሻ ዘመድ የቅርብ ጎረቤቷም ነበሩ።

የስድስት ዓመት፣ የአራት ዓመት እና የአስራ አምስት ቀን ሴት ልጆች እናት የነበረችው አይሻ፣ ያማጠችበት ወገቧ አልጠናም። እግሮቿም ቢሆን ለማምለጥ ብርታት አልነበራቸውም ። ጡቶቿ እንዳጋቱ ነበር።

የ15 ቀን እርጥብ አራስ።

ዕለቱ ቅዳሜ ፣ ሰኔ 11፣ 2014 ዓ.ም ጠዋት። ታጣቂዎች ከተኛችበት ይዘዋት ሲሄዱ ገና ደሟ ያልደረቀ ጨቅላ ልጇን በእቅፏ ይዛለች።

ልትተዋት ብታስብስ ለማን? ወይ ደግሞ አራስ ልጇን ሲያዩ አይጨክኑብንም ብላ ይሆናል።

“ታጣቂዎቹ እርሷን ጨምሮ ከየቤቱ ሕጻናትን እና ሴቶችን እየለቀሙ ጨፌ ወደሚባል ጫካ ይዘዋቸው ሄዱ። ከዚያም ረሸኗቸው” ይላሉ።

አራሷ አይሻ ጨቅላ ልጇን እንዳቀፈች እዚያው አሸለበች።

ጥቃቱ የተፈፀመው በቶሌ ቀበሌ የአማራ ተወላጆች በሚኖሩበት አምስት መንደሮች ውስጥ ነው።

ግለሰቡ እንደሚሉት ለሰዓታት የዘለቀው ጥቃት ሲፈፀም የፀጥታ አካላት አልነበሩም፤ ፈጥነውም አልደረሱም።

የፀጥታ አካላት ቦታው የደረሱት በጣም ዘግይተው እንደሆነ ቢቢሲ ያነጋገራቸው ነዋሪዎች ተናግረዋል።

እሁድ ዕለት ከጥቃቱ የተረፉት ነዋሪዎች፣ በየቤቱና በየመንገዱ የወደቁ የሕጻናት፣ የሴቶችና የሽማግሌዎች አስክሬን እየሰበሰቡ መቅበር ያዙ።

ጨፌ የሚባል ጫካ ውስጥ ግን የሆነውን የሰማ አልነበረም። ሁሉም ድንጋጤና ሐዘን ውስጥ ነበር።

እሁድ ረፋድ ላይ ያገኙትን ሲቀብሩ ከዋሉ በኋላ በዚያው ዕለት ከቀኑ 7፡00 ገደማ ሌላ መርዶ ተሰማ። ታግተው ጨፌ የሚባል ጫካ ውስጥ የተገደሉ አሉ ተባለ።

“በመከላከያ ኃይል ታጅበን ወደዚያው አመራን” ይላሉ የአይሻ ዘመድ።

ሁሉም ሰው የራሱን ዘመድ አስክሬን እያየ ያነሳል።

የአይሻ ዘመድም ዐይኑ ከዘመናት ጎረቤቱ እና ዘመዱ አስክሬን ላይ አረፈ።

“አይሻ አራስ ልጇን በፊቷ አድርጋ፣ የ15 ቀን ጨቅላ ልጇን ደገፍ ብላ አሸልባለች። ጀርባዋ ላይ ነው በጥይት የተመታችው” ይላሉ።

ወጣቷ አይሻ ሦስት ልጆቿን ሜዳ ላይ በትና በሰቀቀን የምትኖርባትን ጊምቢንና ይህችን ዓለም ተሰናብታለች።

“እኛ አይሻን ስናነሳት ልጅቷ በሕይወት ተርፋለች የሚል ሃሳብ አልነበረንም” የሚሉት የቅርብ ዘመዷ፣ ትረፊ ያላት ነፍስ ኾኖ አራሷ የአይሻ ልጅ ትንፋሽ ነበራት ይላሉ።

'ትንሿ አይሻ' አሁን ከእናቷ ጉያ ብትወጣም በዘመድ እቅፍ ውስጥ ትገኛለች።

አይሻ ይህችን ዓለም የተሰናበተችው ብቻዋን አይደለም። የ14 ዓመት እህቷን አስከትላ ነው። ታላቅ እህቷም ቢሆን በጥይት ተመትታ ነቀምት ሆስፒታል በሕክምና ላይ ትገኛለች ብለዋል።

አባቷ፣ ባለቤቷ እና ልጆቿ ግን በሕይወት ተርፈውላታል።

የበቆሎ ማሳ ውስጥ ገብተው የተረፉት ሁለቱ ታዳጊ ልጆቿ፣ የእናታቸውን ሞት በውል ሳይረዱት፣ የሆነውንና እየሆነ ያለው ሳይገባቸው አሉ።

እንደ አይሻ ሁሉ አሚናት ሰይድ የተባለች እናትም የስምንት ወር ልጇን ትታ ከሦስት ሕጻናት ልጆቿ ጋር ተገድላለች።

የ35 ዓመቷ አሚናት ከ10 ዓመት፣ ከ7 ዓመት እና ከ4 ዓመት ልጆቿ ጋር ቤቷ ውስጥ ነው የተገደለችው። የ8 ወር ልጇ ግን ብትቆስልም ከሞት ተርፋለች።

“አስክሬን ለመሰብሰብ ቤት ከፍተን ስንገባ ሁሉም ወድቀዋል። እናቲቱን ስናነሳት የ8 ወር ልጇን. . . በሕይወት አገኘናት” ይላሉ እኝሁ የዐይን እማኝ ።

ሕጻኗ ሕክምና ተደርጎላት ወደ ቤት ተመልሳለች።

የዐይን እማኙ እንዳሉት ጉዳቱ ለክፉ የሚሰጣት አይደለም።

ከአሚናት ቤተሰብ ውስጥ በሕይወት የተረፉት ባለቤቷ እና የ15 ዓመት ልጃቸው ብቻ ናቸው። አሁን በመሪር ሐዘን ውስጥ ሕጻኗን ይዘው ተቀምጠዋል።

ሌላኛዋ እናት ሃሊማ ሷድቅም በወለደች በስምንተኛ ቀኗ ነው የተገደለችው። ሃሊማም እንደ አይሻ ደሟ ያልደረቀ አራስ ነበረች። የጥይት ሩምታው የ8 ቀኗን ሕጻንም አልማረም። አንድ እጇን አሳጥቷታል።

ይህ የእነዚህ እናቶች ብቻ ታሪክ አይደለም። ይህ ዘገባ በቶሌ ቀበሌ፣ ስልሳው በሚባለው መንደር የሆነውን ብቻ ለማሳየት የሞከረ ሽራፊ ታሪክ ነው።

የዐይን እማኙ እንደሚሉት እርሳቸው በሚኖሩበት ጊምቢ ወረዳ፣ ቶሌ ቀበሌ፣ ስልሳው የሚባለው መንደር ውስጥ 120 ሰዎች ተገድለዋል። ከእነዚህ መካከል 97ቱ ሴቶችና ሕጻናት ናቸው። ከ97ቱ ውስጥ ደግሞ 62ቱ ከአስር ዓመት በታች ያሉ ሕጻናት ናቸው።

የአካባቢው ነዋሪዎች እንደሚሉት በጥቃቱ ወላጆቻቸው ተገድለውባቸው ብቻቸውን የቀሩ በርካታ ህጻናት እንዳሉ ይናገራሉ።

አሁን ላይ በአካባቢው የመከላከያ፣ የፌደራል ፖሊስና የኦሮሚያ ክልል ልዩ ኃይል ተሰማርተዋል። አካባቢው የተረጋጋ ይመስላል። ቢያንስ የሞቱትን እንደ ወጉም፣ አንደ ሃይማኖቱም ባይሆን አፈር ማቅመስ ችለዋል።

ከጥቃቱ የተረፉት ቤተሰቦችም በእሳት በወደመውና በተዘረፈው ኦና ቤታቸው በጥይት ሩምታ የተሳቀቁ ልጆችን ይዘው የዕለት ጉርስ የሚጥልላቸውን እየጠበቁ ነው።

የቶሌ ቀበሌው ጭፍጨፋ

ቅዳሜ፣ ሰኔ 11፣ 2014 ዓ.ም በምዕራብ ወለጋ፣ ጊምቢ ወረዳ፣ ቶሌ ቀበሌ ውስጥ በሚገኙት ጉቱ፣ ጨቆርሳ፣ ስልሳው፣ በገኔ፣ ጫካ ሰፈር እና ሀያው በተባሉ መንደሮች (ጎጦች) ሰኔ 11 ቀን 2014 ዓ. ም. በታጣቂዎች በተፈጸመ ጥቃት ከ300 የሚልቁ ንጹሀን ሰዎች መገደላቸውን የዐይን እማኞች ተናግረዋል።

ምን ያህል ሰዎች እንደተገደሉ ይፋዊ ቁጥር በመንግሥት በኩል ባይነገርም፣ የዐይን እማኞች እንዲሁም የተለያዩ መገናኛ ብዙኃን የሟቾችን ቁጥር ከ500 በላይ አድርሰውታል።

አሶሽየትድ ፕረስ በአሜሪካ የአማራ ማኅበርን ጠቅሶ እስካሁን በጥቃቱ 503 ሰዎች መገደላቸውን በትናንት ዘገባው አስነብቧል።

የአስክሬን ፍለጋው አሁንም የቀጠለ ሲሆን የሟቾቹ ቁጥር ከዕለት እለት እየጨመረ እንደሆነ ቢበሲ ያነጋገራቸው የዐይን እማኝ ተናግረዋል።

በዚህ ታሪክ ውስጥ ያነጋገርናቸው የዓይን እማኞች እርሳቸው በሚኖሩበት ስልሳው መንደር ውስጥ ዛሬ አራት ተጨማሪ አስክሬን ማግኘታቸውን ለቢቢሲ ገልጸዋል።

ቢቢሲ ያነጋገራቸው የዐይን እማኞች እንዲሁም መንግሥት ጥቃቱን የፈጸመው ‘ሸኔ’ በመባል የሚታወቀው ታጣቂው የኦሮሞ ነፃነት ሠራዊት እንደሆነ ሲገልጹ፣ ቡድኑ ግን ለጥቃቱ የመንግሥት ኃይሎችን ተጠያቂ አድርጓል።

የኦሮሞ ነጻነት ሠራዊት ባወጣው መግለጫ፣ ታጣቂዎቹ በሰላማዊ ሰዎች ላይ ጥቃት እንደማይፈጽሙና የጊምቢው ጥቃትም መንግሥት አደራጅቶታል ባለው ኢ-መደበኛ ኃይል እንደተፈጸመ ገልጾ፣ ክስተቱ በገለልተኛ ወገን እንዲጣራ ጠይቋል።

የተባበሩት መንግሥታት የሰብአዊ መብቶች ከፍተኛ ኮሚሽንም በምዕራብ ወለጋው ጥቃት ወቅት ቁጥራቸው ያልታወቀ ሰዎች በታጣቂዎቹ ታግተው መወሰዳቸውን ገልጾ፣ የኢትዮጵያ መንግሥት ባለሥልጣናት በጥቃቱ ዙሪያ ፈጣን፣ ገለልተኛና ዝርዝር ምርመራ እንዲያደርጉ ጠይቋል።

ኮሚሽኑ በአብዛኛው የአማራ ብሔር አባላት በሚኖሩበት ቶሌ ላይ ተፈጽሞ በመቶዎች የሚቆጠሩ በዋናነት ሴቶችና ህጻናት ስለተገደሉበት ጥቃት እማኞችን ማናገሩን አመልክቶ፣ ታጣቂዎቹ በርካታ ቤቶችን በማቃጠላቸው ቢያንስ 2000 ሰዎች ከቤታቸው ተፈናቅለዋል ብሏል።

ተቃዋሚ ፓርቲዎች፣ የመብት ተሟጋቾችና ሌሎችም ጥቃቱን ያወገዙ ሲሆን መንግሥት የሕዝቦችን ደህንነት እና ሰብዓዊ መብታቸውን እንዲያስጠብቅ አሳስበዋል።

በመቶዎች የሚቆጠሩ ሰላማዊ ሰዎች በተገደሉበት እለት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይን ጨምሮ ከፍተኛ ባለሥልጣናት የአረንጓዴ አሻራ ፐሮግራም ችግኝ በመትከል ላይ በማተኮራቸው በማኅበራዊ ሚዲያ ክፍተኛ ቁጣን ቀስቅሷል። በአገር ውስጥና በውጭ አገራት የተቃውሞ ድምጾች እየተሰሙ ነው።

ጥቃቱ ከተፈፀመ ከአምስት ቀናት በኋላ በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ስብሰባ ላይ የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ (አብን) ተወካዮች ይኸው ጉዳይ በአጀንዳ እንዲያዝ በዶ/ር ደሳለኝ ጫኔ በኩል ጥያቄ ቢያቀርቡም ተቀባይነት ባለማግኘቱ ስብሰባውን አቋርጠው ወጥተዋል።

ይህንን ተከትሎም የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) በምዕራብ ወለጋ ዞን ከተከሰተው በተጨማሪ በጋምቤላ ክልል “በንፁሃን ዜጎች ላይ የተፈጸመውን አሰቃቂ የሰብዓዊ መብት ጥሰት አጣርቶ እንዲያቀርብ” ማዘዙ ተገልጿል።

በተጨማሪም በሚገኘው ውጤት መሠረት ውሳኔ እና ምላሽ ለመስጠት የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አፈ ጉባዔ አቶ ታገሠ ጫፎ ከምክር ቤት አባላት የተውጣጡ ሁለት ቡድኖችን ማቋቋማቸውንና ውጤቱ ለሕዝብ ይፋ ይደረጋል ተብሏል።

* የእናቶቹን ታሪክ ያጋሩን ለደህንነታቸው ስንል ስማቸውን የማንጠቅሳቸው በቶሌ ቀበሌ፣ ስልሳው መንደር ነዋሪ የሆኑት የአይሻ ሰይድ የቅርብ ዘመድና ጎረቤት ናቸው። ነዋሪው አስክሬን በማሰባሰብ ሲቀብሩ ከነበሩ ግለሰቦችም አንዱ መሆናቸውን ለቢቢሲ ተናግረዋል።









Right
Member
Posts: 2723
Joined: 09 Jan 2022, 13:05

Re: በጊምቢው ጭፍጨፋ በተገደለችው እናቷ እቅፍ የተገኘችው የ15 ቀኗ ጨቅላ ሕጻን

Post by Right » 27 Jun 2022, 15:25

Very sad news. I can’t believe this is happening in Ethiopia.

Please those of you in the Legal community ~ or if you know someone in the legal community please assist the larger Ethiopian community to bring those in the position of power in Ethiopia who can protect the citizens or punish the perpetrators be brought to justice. I believe it is possible to sue in any court in the western world.

These fat [deleted] at PP and the people in charge of the government has a double life in diaspora.

Lawyer fees can be raised and I am pretty sure there are so many Ethiopian lawyers, human right lawyers that can help.





Post Reply