Ethiopian News, Current Affairs and Opinion Forum
sarcasm
Senior Member
Posts: 10186
Joined: 23 Feb 2013, 20:08

ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ቀዳማዊ ፓትርያርክ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ ያስተላለፉት አባታዊ የኀዘን መልእክት

Post by sarcasm » 25 Jun 2022, 07:54

ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ቀዳማዊ ፓትርያርክ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ ሊቀ ጳጳስ ዘአክሱም ወእጨጌ ዘመንበረ ተክለሃይማኖት; በወለጋና በጋምቤላ የአገራችን ክፍል የደረሰውን አሰቃቂ የወገኖቻችን ግድያ አስመልክቶ ያስተላለፉት የኀዘን መልዕክት
+++++++++++++++++++++++++++++++++++++


በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን!
"ወተዘርወ ዕንቊ ቅዱስ ውስተ ኩሉ ፍኖት
“የመቅደሱ ድንጋዮች በጐዳና ሁሉ ራስ ተበተኑ። ሰቆቃ.ኤር. 4፡1

አባታዊ የኀዘን መልእክት

የተወደዳችሁ ኢትዮጵያውያንና ኢትዮጵያውያት በአገር ውስጥ እና በውጭ ያላችሁ የአገርን ክብር ለመጠበቅ በዳር ድንበር ያላችሁ የመንፈስ ቅዱስ ልጆቻችን፤ ዘመናትን ፈጥሮ በሚገዛ፣ ዓለማትን በቃሉ በሚያስተዳድር፣ ለህላዌው መታጣት፣ ለጌትነቱ ዳርቻ በሌለው በሕያው እግዚአብሔር ስም አባታዊ ሰላምታችንን እናስተላልፋለን።

ስሜትን በሚወርር፣ ልብን በሚያሳዝን፣ ጉልበትን በሚሰብር ኀዘን ውስጥ ላሉት ወገኖቻችን፤ ትናንት ባለ ብዙ ቤተሰብ ዛሬ ሌጣ ለሆኑት፣ የክብር ሞትና መቃብር ለተነፈጉት፣ ሰው ሆነው በሰው ለተገፉት፣ ኢትዮጵያዊ ሁነው በኢትዮጵያውያን ለተሠዉት፣ አገር : ሳላቸው እንደ ባዕድ ለተቆጠሩት ለደከሙበት ምድር : በወርቅ ፈንታ ሰይፍ ለተከፈሉት ልጆቻችን እግዚአብሔር ያጽናችሁ በማለት፣ የሞቱትንም ደመ አቤልን ያከበረ አምላክ ደማቸውን እንዲመራመር በመለመን መልእክታችንን እንጀምራለን!

ብዙ መልካም ቃላት በሚነገሩበት፣ የጥበብ ድምፆች በሚያስተጋቡበት፣ መሠረት ፈርሶ ለጉልላት ጌጥ በምንጨነቅበት በዚህ ዘመን፣ “እንዴት ካለው ጊዜ ደረስን ማለት መመጻደቅ ባይሆን ኖሮ የሚባልበት ወቅት ሁኖ አግኝተነዋል። ትናንት ገንዘብን የሚቀሙ “እንዴት የሰውን ልፋት ይወስዳሉም ተብለው በተወገዙበት ምድር ሕይወትን የሚቀሙ፡ የሰው ዘር ቅነሳ የሚያደርጉ ግፈኞች ሲንጎማለሉ ማየት ያሳዝናል። ንጹሐን ወገኖቻችን እግዚአብሔር በሰጣቸው ማንነት ብቻ ሲሞቱ ስናይ የዝቅታችንና የመውደቃችን ልክ ማጣት ጎልቶ ይታያል። በርግጥ የሞቱት ወገኖቻችን ሰማዕታት ናቸውና ቤተ ክርስቲያን ትዘክራቸዋለች። ሰማዕት ስለ እግዚአብሔር ብሎ የሚሞት ነው። እነዚህም ወገኖቻችን እግዚአብሔር በሰጣቸው ማንነት፣ ለምን እንዲህ ተፈጠራችሁ ተብለው የሞቱ ናቸውና ሰማዕታት እንላቸዋለን። ገዳዮችም ቀጥተኛ የእግዚአብሔር ተቃዋሚዎች ናቸው።

በወለጋና በጋምቤላ የአገራችን ክፍል የደረሰውን አሰቃቂ የወገኖቻችን ግድያ ስሰማ እንደ ወትሮው ልቤ በታላቅ ኀዘን ተመትቷል። በመላው የሀገራችን ክፍልም ክረምቱ ዓመት ከዓመት፣ ጠሉም የንጹሐን እንባ ሁኖ፣ “ሽሽታችሁ በክረምት እንዳይሆን ጸልዩ" ያለው የጌታችን ቃል ደርሶ እያየን ነው። ጆሮ ከአቅሙ በላይ በሚሰማበት በዚህ ዘመን ያላችሁ ልጆቻችን አሁንም ልባችሁን እንደ ነቢዩ ዳዊት በእግዚአብሔር አበርቱ። ጠብና ክርክሩ እግዚኣብሔር ከፈጠረው ሰውነት ጋር ነውና እግዚአብሔር ፍርድ እንደሚሰጥ እናምናለን። የሃይማኖት አባቶችም የምናስተምረው ሕዝብ አልቆ ማንን ልናስተምር መሆኑን ደግመን ማሰብ ያስፈልገናል። አገራችን ኢትዮጵያ የሚያስከብሯትን መሪዎች አሁንም እየተጣራች ነውና መንግሥትና ሕዝብ ግፍን በተግባር ማውገዝ ያስፈልጋቸዋል። ነቢዩ ኤርምያስ በኀዘን ልቅሶው - የመቅደሱ ድንጋዮች በጐዳና ሁሉ ራስ ተበተኑ። ብሏል ሰቆቃ ኤር 4፡1። የሰው ልጅ ሕያው የእግዚአብሔር መቅደስ ነውና በየስፍራው ሲገደልና ቀባሪ ሲያጣ ስናይ ከነቢዩ ጋር ለማልቀስ እንገደዳለን።

ጊዜው እየረፈደ፣ ሞትም ዜና እየሆነ፣ ዜጋም ክብሩን እያጣ ስጋትም ገዥ እየሆነ የምንቀጥልበት ጊዜ እንዲያበቃም ታላቅ ጥሪያችንን በሕያው እግዚአብሔር ስም እናስተላልፋለን!

እግዚአብሔር ኢትዮጵያንና ሕዝቦቿን ይባርክ ! ወስብሐት ለእግዚአብሔር አሜን! ሰኔ 16 ቀን 2014 ዓ.ም.
@EOTC

https://www.facebook.com/officialHenokhaile/