Ethiopian News, Current Affairs and Opinion Forum
Assegid S.
Member
Posts: 936
Joined: 11 Aug 2013, 07:11
Contact:

የሳምንቱ ስልኬ XIII

Post by Assegid S. » 17 May 2022, 14:34

https://www.eaglewingss.com/



የሳምንቱ ስልኬ XIII

ሄሎ?

ሃሎ?

ጤና ይስጥልኝ?

አብሮ ይስጥልን

እንዴ? አንተው ነህ እንዴ? ድምፅህ ሲወፈርብኝ ጊዜ እኮ ተጠራጠርኩ

ትንሽ ጉንፋን ነገር ይዞኝ ነው ባክህ። ምነው? ኢመደመበኛው ጓደኛህ መሰልኩህ?

ምን ይታወቃል? ዘንድሮ …

አይዞህ! እኔው ነኝ

ታዲያ … ወደ ቤተመንግስቱ ጎራ ብለህ ፥ ተክለናል ካሉት ዳማከሴ ምናምን ቁረጡልኝ አትላቸውም እንዴ? ነው ወይስ እንደ ፍትህ … የግቢውንም ፍሬ ለመካፈል ከጠቅላይ ሚንስትሩ ጎን መቆምን ይጠይቃል?

እስቲ ይህን ጥያቄህን ለጊዜው አቆይልኝ፥ ከኣማራ ክልል ሲመለሱ ሄጄ እፈትናቸዋለሁ

እኔ ምለው፦ እሳቸውን ግን ምንድነው እንዲህ ኣማራ ክልል የሚያመላልሳቸው?

አሁንስ እኮ ሰውየውን እህል የማይቀምሱ፣ ውሃ የማይጠጡ መልአክ አስመሰላችኋቸው። ሰው በልቶም አይፀዳዳ ነው እንዴ የምትሉት?

ጥያቄ'ኮ ነው፥ አትቆጣ

አልተቆጣሁም። አንተ ግን ምነው ጠፋህ? እኛ እንኳን እዚህ ኑሮ ከብዶብን ደፋ ቀና ስንል ጊዜ አላገኝ ብለን ነው

ጠፋሁ አይደል … ትንሽ አልመች ስላለኝ እንጂ ይህን ያህል መጥፋት እንኳ አልነበረብኝም

መቼ ነው ቀኑ ባክህ … ? ብቻ ልደውልልህ አስቤ … ያው ታውቀው የለ ይሄ እንደ ብረት የከበደ ኑሮ … እሱን ተሸክመን ወዲህ ወዲያ ስንል ስለምንውል ማታ ላይ ይደክመንና በቃ …

ይገባኛል ጎደኛዬ። ኢኮኖሚው እንዲህ ደቆ የተሸከምከው ኑሮ፥ እንኳን ምድር ላይ ላለ ሰው … ጠፈርም ላይ ለከተመ astronaut ያለ ሳተላይት በደንብ ይታያል

ኢኮኖሚውንማ ተወው … መድቀቅ አይደለም ዱቄት ነው የሆነው

ምነው? ተዋጋቻችሁት እንዴ?

እየቀለድክ ነው?

ለምን እቀልዳለሁ? ጠቅላይ ሚንስትሩ ህወሃትን ተዋግተን 'ዱቄት አድርገነዋል' ሲሉ እየቀለዱ ነበር እንዴ?

ሃሃሃሃ … አሁን ያልከው ሳይሆን ለማለት የፈለከው ገባኝ

ጎደኛዬ አይደለህ … ሁሌም ይገባሃል። እኔ ምልህ፦ ታዲያ … ኑሮ እንዲህ ከከበደህ አደባበይ ወጥተህ ሀቅ ሀቁን ለምን አትተነፍስም

በል በል ወደ ሌላ ወስደኽኝ፥ እንዳታስወስደኝ

ቢወስዱህ አይሻልህም? የውሎም ባይሆን የአፈና አበል ከፍለው ይለቁሃል። እንዳውም አፍህን ለጉመህ በማይረባ ደሞዝ ከምትወዛወዝ፥ ታፍነህ ዳጎስ ያለ መሸንገያ "በሻይ" ሂሳብ ያስጨብጡሃል

ይህን የኦህዴድ ጩኸት-አልባ የቶርቸር ቪላ እኮ አትራፊ … ጭስ-አልባ፣ የጎጆ ኢንዱስትሪ አስመሰልከው

ካልፈለክ ተወው። ለኣንተው ብዬ ነው

ምኑን ነው ለእኔ ብለህ?

ስማ … ኣንድ የቆየች ቀልድ ቢጤ ልንገርህ፦ ኣባት ሁሌ መድረክ ላይ የሚቀጠቀጥ ቦክሰኛ ልጃቸው ምርር ይለውና፦ "አባዬ አሁንስ ሁሌ መደብደብ ሰልችቶኛል፥ ስለዚህ ስራዬን ላቆም ነው" ይላቸዋል። ይኼኔ አባት፦ ልጁ የቦክሰኛነቱን ሥራ ቢያቆም የት ውሎ እንደሚያመሽ ስለሚያውቁ … "ስማ ልጄ፦ እኔ ነጋ ጠባ በነፃ ከምደበድብህ መንግስት ደሞዝ እየከፈለህ ቢያስቀጠቅጥህ አይሻልህም?ብለው መከሩት ይባላል

እሺ አባቴ … ምክርህን አስብበታለሁ

lol … እኔ ምለው፦ ሰዎቹ "ማዕከላዊን" ዘግተነዋል ብለው "መካከላችሁ" ከፈቱ እንዴ?

እኔ ምን አውቅልሃለሁ? ጎበዝ ከሆንክ ና ና ጠይቃቸው

ሃሃሃሃ! እሺ መጥቼ እጠይቃቸዋለሁ። ጎበዜ የተባለ ብቻ መሰለህ እንዴ ጎበዝ? አንተ ግን እንዴት ነው … ሳትነግረኝ ቤተሰብ ምናምን መሰረትክ እንዴ?

የምን ቤተሰብ ነው የምመሰርተው?

ምናውቃለሁ? ሰው የሚፈራው ቤተሰቡን፣ ልጁን እያሰበ ነው ሲሉ ስለምሰማ ነው። ተሳሳትኩ እንዴ?

እኔ በፊትም ሆነ አሁን ፈርቼም፣ ቤተሰብ መስርቼም አላውቅም

ያለመፍራቱን እንኳ ድሮም ስለማውቅህ አምንሀለሁ፤ የቤተሰቧን ጉዳይ ግን …

አየህ! ችግርህ እኮ … እምነትህ የሚመረኮዘው ዛሬን ሳይሆን ድሮን ታሳቢ በማድረግ ስለሆነ ነው

እንዴት?

ምን እንዴት ትለኛለህ? ዛሬ ላይ ያሉት ሴቶች ያኔ ድሮ ልጆች እያለን የምናውቃቸውን አይነት ስለሚመስሉህ፤ ፍቅር ያለ … ትዳር መያዝ ደግሞ በየመድረኩ መሐል ድንገት እየተነሱ "ኢትዮዽያ አትፈርስም!” እንደማለት ቀላል ይመስልሀል። ድሮ ልጆች እያለን የምናውቃቸው ሴቶች ትዝ ይልሁል? እነዛ በኣንድ አቡወለድ ብስኩት ኣንድ ዓመት ሙሉ እያገላበጡ የሚስሙን? ወንድሜ … አሁን እነርሱ የሉም! ዛሬ፦ በአቡወለድ ብስኩት አይደለም … በአብ በወልድ ስም ብትማልድ እንኳ፥ ቢሊየነር ካልሆንክ ልቧን ቀርቶ እጁዋን ለሰላምታ የምትዘርጋልህ ሴት የለችም

እግዞ! በል በለኛ

እግዞ'ስ ከምትል ግዞት እንዲወስዱህ ፀልይ … የአፈና አበል አጠራቅመህ ሚሊየነር ብትሆን እንኳ

Ha ha ha … ስዎቹ ግን አሉ?

እነማንን ነው የምትጠይቀኝ?

እነ ምስሉ … እእእእ … ማለቴ እነ ምክትሉ? በቀን … በጠራራ ፀሐይ የሚታፈነው፣ የሚጋዘው የኣማራ ህዝብ ተወካዮች ነን የሚሉት

አሉ። ችግሩ ግን አንተ … ፎቶና እና ምስል ግዴታ የእንጨት ፍሬም (frame) ውስጥ ካልገባ፥ ሺህ ጊዜ በጨርቅ ፍሬም ተለብጦ ቢወዛወዝ አይታይህም

ተው ባክህ "የእንጨት ፍሬም ውስጥ ገብተው" እያልክ የኣማራን ትንሳዔ በመናፈቅ አታጎጎኝ

ታዲያ ምን ልበል? አሁን በቅርቡ እንኳ ባህር ዳር ውስጥ ባማረ ሱፍ ተውበው "ፋኖን ትጥቅ አስፈቱ!” ብለው ትዕዛዝ ሰጥተው ሲወጡ እያየህ … "አሉ ወይ?” ብለህ ትጠይቀኛለህ

ቆይ ግን ሀገር ላይ ሰላም እንዲሰፍን ከሆነ የተፈለገው፦ ከፋኖ ይልቅ መከላከያ ለምን ትጥቅ አይፈታም? ህወሃት ሀገር የሚያሸብረው መከላከያው እየጣለ የሚፈረጥጠውን መሳሪያ እየታጠቀ አይደል እንዴ?

ሰውየው፦ እሱማ "ህዝብን ከማስራብ" የከፋ ህወሃትን የማዳከም ወንጀል ነው። እኔን የገረመኝ ግን፦ ኣሳማው ብአዴን … ከኦህዴድ አልፎ ከኦፌኮ ጋር ተጣምሮ ፋኖ ላይ መዝመቱ ነው። እንደው፦ 'ማረር ከፈለክ ኣማራ ሁን' የሚል ፅሑፍ ያነበብክበት ቦታ ይኖር ይሆን?

የለም! ላለማረር … በለው በአረር ! የሚል ምክር ግን አለኝ

እሱማ የት ይቀራል! “ እንዲህ ጨሶ ጨሶ የነደደ እንደሆን፥ የአመዱ ማፈሻ ስፍራዉ ወዴት ይሆን? ” አይደል የሚለው ጓዴው ባለጎንዴ

ልክ ብለሀል ጓደኛዬ! ኖረንበት ባናየውም፥ ከሰማነው ተነስተን ስንመዝነው … ከኣሳማው ኣዴፓ ይልቅ የኢህአፓ ኡኡታ ኮሚቴ ሺህ ጊዜ ሺህ ይሻላል። ቢያንስ በጩኸት አሮጊቶቹ በርካታ ልጆቻቸውን ታድገዋል

መቶ ፐርሰንት እስማማለሁ!

Wow! መቶ ፐርሰንት ከተስማማህማ … ወደ ሰባ-ሰባት ሳታወርደው በዚሁ እንሰነባበት። አይመስልህም?

ምንድነው ምታወራው? ሁሌም ቢሆን'ኮ ትክክል ስትናገር ሙሉ በሙሉ እንደተስማማሁህ ነው

Nah nah nah nah! እኔና አንተ ተስማምተን የምናውቀው ከስንት ኣንዴ ነው፤ በተለይ ስንለያይ። Unless … አሁን የባህሪ ለውጥ አምጥተህ ካልሆነ በስተቀር

እሺ ይሁንልህ በቃ! የባህሪ ለውጥ አምጥቻለሁ

እንደዛ በለኛ! ከተለወጡ አይቀር ደግሞ እንዲህ እንደ አንተና እንደ ጠቅላይ ሚንስትሩ ልውጥውጥ ማለት ነው እንጂ

ሃሃሃሃ … በል ደና ሰንብት!

አሜን! አንተም ሰላም ሰንብት!

አሜን!