Ethiopian News, Current Affairs and Opinion Forum
Post Reply
Wedi
Member+
Posts: 5615
Joined: 29 Jan 2020, 21:44

በችግሮች የተሞላውን የነስብሃት ነጋ አፈታት በተመለከተ፣ ክፍል 1 + 2 By Andargachew Tsege

Post by Wedi » 28 Jan 2022, 08:46

Andargachew Tsege
January 22 2022

በችግሮች የተሞላውን የነስብሃት ነጋ አፈታት በተመለከተ፣ ክፍል 1

https://www.facebook.com/AndargachewTs/ ... 6758426271

ከሰይጣን ጋር እስክስታ (ዳንስ)

ሰሞኑን የነስብሃት ነጋን መፈታት አስመልክቶ ውሳኔው ተገቢ አለመሆኑን አስተያየቴን በአደባባይ ገልጫለሁ። ተገቢ አይደለም ያልኩበት ምክንያት ግን እንደብዙሃኑ በስሜትና በቁጭት ላይ ብቻ የተመሰረተ አልነበረም። በቁጭትና በስሜት የተቃወሙትም በቂ ምክንያት እንዳላቸው እነስብሃትን ፈቶ የለቀቀው መንግስት ሊያውቅላቸው ይገባል።

ሰለ እነስብሃት እንነጋገር ከተባለ፣ እኩይነት ስጋና አጥንት ተላብሶ በሃገራችን ምድር የተከሰተው በስብሃት ነጋ መሆኑን አውቃለሁ። ከወያኔ ወደ ትግራይ ህዝብ እንዲስፋፋ የተደረገው ጸረ አማራ እና ጸረ ኢትዮጵያ አመለካከት ዋናው አራማጅ ስብሃት ነጋ ነው። በአማራ ህዝብ ላይ ሂሳብ ማወራረድ የሚለውና የአማራን ህዝብ የዘር ማጥፋት ጥቃት ሰለባ ሲያደርገው የኖረው የወያኔ እቅድ የስብሃት ነጋ ነው። የትግራይ ወራሪ ሃይል በአማራ ህዝብ ላይ የፈጸማቸው የግፍና የሰቆቃ አይነቶች በስብሃት የታሰበባቸው ናቸው። በአንድ ወቅት “እንዴት የአማራን ህዝብ እንደህዝብ ትጠላለህ በሁሉም ብሄር ውስጥ መጥፎም ጥሩም ሰዎች ይኖራሉ” ለሚለው የጓደኛው አስተያየት ስብሃት የሰጠው ምላሽ “የአማራ ጥሩ የለውም። ጥሩ አማራ የሞተ አማራ ብቻ ነው የሚል” ነበር። አማራን መግደል፣ መቀጥቀጥ፣ መዝረፍ፣ ሴቶቹን በመድፈር፣ ማዋረድ በጥቃት መሳሪያነት ታስቦባቸው የትግራይ ወራሪ ሃይል ስልጠና የወሰደባቸውና ተግባራዊ ያደረጋቸው ጉዳዮች እንዲሆኑ ያደረገው ስብሃት ለመሆኑ ልንጠራጠር አይገባም። ከትግራይ አልፎ በሌሎች የኢትዮጵያ ክልሎች በአማራው ላይ በጽንፈኛ ብሄረተኞች የሚወሰዱ አሰቃቂ ግድያዎች፣ ዘረፋዎችና መፈናቀሎች መነሻው በወያኔ ውስጥ ተወልዶ ያደገው ወደ ሌሎች ክልሎች እንዲስፋፋ የተደረገው የስብሃት ነጋ የአማራና የኢትዮጵያ ጥላቻ ነው።

ከአማራው አልፈን በአፋር ህዝብ ላይ የቆየው የወያኔ ጥላቻ ምንጩ የስብሃት ነጋና የቡችሎቹ የነመለስ ዜናዊ ጸረ ኢትዮጵያ አቋም ነው። የአፋሮች “እንኳን እኛ ግመሎቻችን የኢትዮጵያን ሰንደቅ አላማ ያውቁታል” የሚለው አባባላቸው እነዚህን ጸረ ኢትዮጵያ ሃይሎች ሁሌም ሲያሳምም የኖረ እንደሆነ አውቃለሁ። ኢትዮጵያን ከቅኝ ገዥዎች ለመከላከል አፋሮች የራሳቸው የታሪክና የጀግንነት አሻራ ያሳረፉ፤ በዚህም የሚኮሩና በኢትዮጵያ ጉዳይ የማይደራደሩ መሆናቸው የወያኔን ጥላቻ እንዲያተርፉ አድርጓቸዋል። በቅርቡም በአሸባሪው የወያኔ ወረራ በከፍተኛ ጭካኔ እንዲጨፈጨፉ፣ እንዲዘረፉና በእምነታቸው ላይ ሳይቀር ነውር እንዲፈጸምባቸው ያደረጋቸው፤ ይህ የኢትዮጵያዊነት ኩራታቸው ነው። ስለዚህ እንዲህ አይነቱ በቀጥታ በአማራና በአፋር ህዝብ ላይ ለተከሰተው ከፍተኛ የሰው እልቂት፣ የንብረት ውድመት፣ የስብእና ውርደት ተጠያቂ የሆነ ሰው ለማናችንም ግልጽ ባልሆነ ምክንያት በነጻ ከእስር ሲለቀቅ ኢትዮጵያውያን ቢናደዱና ቢቆጩ የሚገርም አይሆንም። “ስብሃት ነጋ በተንቤን ዋሻ በመከላከያ በተያዘበት ወቅት በሲቪል ሆነ በወታደራዊ አመራር ስልጣን አልነበረውም። ስለዚህ በህግ ፊት ተጠያቂ ማድረግ አይቻልም” የሚለው አባባል አጥጋቢ አለመሆኑ ብቻ ሳይሆን በኢትዮጵያ ውስጥ ሰዎች በነጻነት የሚታዩበት የፍትህ ስርአት ያለ አድርጎ የሚያቀርብ ስለሆነ አስቂኝም ጭምር ነው። የተጀመረውን የለውጥ ሂደት የምደግፈው ወደ ተስተካከለ የፍትህ ስርአት ሊወስደን ይችል እንደሆነ ተስፋ በማድረግ እንጂ ነጻና ገለልተኛ የፍትህ ስርአት ተገንብቷል ብዬ ስለማምን አይደለም። ማንም ኢትዮጵያዊ አያምንም።

በበኩሌ በነስብሃት መፈታት ተቃውሞየን ያቀረብኩት ከዚህ በላይ ከጠቀስኳቸው ከወገኖቼ ጋር በምጋራው የቁጭትና የንዴት ስሜት አይደለም። በቀል ፈላጊ ስለሆንኩም አይደለም። የኔ አይነት ሰው በመወያየት፣ በሰላምና በእርቅ ችግሮችን መፍታት የተማረው በአካዳሚ ተቋማት ወይም ቂም በሆዳቸው ይዘው ስለይቅርታ ከሚሰብኩ የእምነት ሰዎች አይደለም። መወያየት ባለመቻላችን፣ ለስላምና ለእርቅ ቦታ ባለመስጠታችን በሽዎች የሚቆጠሩ ውድና ብርቅ የሃገሪቱን ልጆች ህይወት ገብረን፤ አያቶቻችንን፣ አባቶቻችንን፣ ወንድሞቻችንና እህቶቻችንን በጅምላ መቃብር እንዲቀበሩና በሚሊዮኖች እንዲሰደዱ አድርገን ኢትዮጵያን ዛሬ ላለችበት የአካልና የመንፈስ ምስቅልቅል በመዳረጋችን ተሸክመነው ከምንኖረው ዘመን የማይሽረው ቁስላችን ነው። በመሆኑም ውሳኔውን የተቃወምኩት ቂም ሳልቋጥር፣ በቀልን ሳልናፍቅ፣ ቁጭትና ስሜቴን ወደ ጎን አስቀምጬ እንደበረዶ በቀዘቀዘ የተረጋጋ መንፈስ ውስጥ ሁኜ ነው። በዚህ ስሜት ውስጥ ሆኜ አንድ መሰረታዊ ጥያቄ ብቻ አንስቼ ነው። ያነሳሁት “የእነዚህ እርኩስ ወንጀለኞች መፈታት ለህዝብና ለሃገር ምን ጠቀሜታ ይኖረዋል” የሚል ጥያቄ ነው። የኢትዮጵያን ህዝብ ዘለቄታዊ ጥቅም የሚያስጠብቅ መስሎ ቢታየኝ የመንግስትን ጥረት በሙሉ ከልቤ ከመደገፍ ወደኋላ አልልም ነበር። ይህ አይነቱ ባህልና ስብእና እንዳለኝ የተቃወምኳቸው ብቻ ሳይሆኑ የወያኔ መሪዎችም ጭምር ያውቁታል። ውሳኔው ትክክል አይደለም ያልኩት ከሃገራዊና ህዝባዊ ጠቀሜታው ይልቅ ጉዳቱ ጎልቶ ስለታየኝ ነው።

እስካሁን ድረስ መንግስት ለምን እነስብሃት ነጋን እንደፈታቸው የሰጣቸው ምክንያቶች እርስበርሳቸው የሚጣረሱ፣ ማንንም ማሳመን ያልቻሉ ናቸው። “ለሰላም ሲባል ነው፤ ፍርድ ቤቱ የጀመረውን ክስ ቢቀጥል ማስረጃ ሊያቀርብባቸው የማይችል ጉዳይ ስለሆነ ነው፤ ሰዎቹ በእድሜ የገፉ በሽተኞች በመሆናቸው እስር ቤት ከሚሞቱና የበለጠ የበቀል አዙሪት ከሚጦዝ ቢለቀቁ ጉዳት አያመጣም ብለን ነው፤ ለብሄራዊ ውይይትና እርቅ መጀመር አስፈላጊ ስለሆነ ነው፡፡” የሚሉ ምክንያቶች በተለያዩ የመንግስት ባለስልጣናት ተሰጥተውናል። የበለጠ ግራ መጋባትን እንጂ ሰዎቹን መንግስት ለምን እንደፈታ የተጨበጠ ነገር አላገኘንም።

ከፍችው ማግስት ጠቅላይ ሚኒስትሩ የፍችው ሃሳብ ለእኛም አስደንጋጭ ነበር ማለቱ የበለጠ ግራ አጋብቶን ነበር። ከዛ በኋላም ጠቅላይ ሚኒስትሩ ለዳያስፖራ በተዘጋጀው የእራት ግብዣ ላይ ያደረገው ንግግር ከተጋባዦቹ ብዙ ጭብጨባ ቢለገሰውም የሃገሪቱን ፖለቲካ ከምር ለምንከታተለው ስዎች ከሁሉም ንግግሮች በባሰ ጉዳዩ አሳሳቢ እንደሆነ ያሳየ ሆኖ አግኝተነዋል። ጠቅላይ ሚኒስትሩ እኛን አስደንግጧል በሚል የሰጠው ማብራሪያ እኔን አስደንግጧል። “ዶ/ር ጌዲዮንና ጓደኞቹ እንደ አስማተኛ የተፈችዎችን የስም ዝርዝር ማንም አስቀድሞ ሳያውቅ በነጻነትና ገለልተኛነት አቀረቡት።”ተብለናል።

ከፍችው ማግስት ዶ/ር ጌዲዮን በጉዳዩ ላይ በሚድያ ማብራሪያ ለመስጠት በመጣበት ወቅት በአንደበቱና በፊቱ ላይ ትልቅ ጭንቀት አይተናል። ያንን የመሰለ በአልጀዚራና በቢቢሲ ሃርድ ቶክ ላይ ኢትዮጵያን በሚያኮራ ደረጃ በእንግሊዝኛ ቋንቋ ከማንም የመንግስት ባለስልጣን በላይ መንግስትን ወክሎ በአንደበተ ርቱእነት የኢትዮጵያን አቋም ማስረዳት የቻለ ሰው፤ በአማርኛ ቋንቋ ስለፍችው ማብራሪያ መስጠት አቅቶት አንደበቱ ተሳስሮ አይተነዋል። ይህን ተመልክተን የአቃቤ ህግ መስሪያ ቤት የተፈችዎችን የስም ዝርዝር በስልጣኑ አቀረበ የተባለውን መግለጫ ለማመን እንዲከብደን አድርጎታል።

ሌሎችም የጠቅላይ ሚኒስትሩ ማብራሪያዎች እጅግ አሳሳቢ ሆኖ አግኝቻቸዋለሁ። ‘የመከላከያ አዛዦች ሹመት እንደጠየቁኝ፣ ተፈናቃዮችና ሌሎችም የራሳቸው ጥያቄ እንደጠየቁኝ ሁሉ ለድል ያበቃኝ ፈጣሪ በይቅርታና በምህረት መንገድ እንድሄድ ጠይቆኛል” ብሎናል። የዚህን አባባል አሳሳቢነት በቦታው እንመለስበታለን። ከጠቅላይ ሚኒስትሩ ውጭ በጉዳዩ ላይ አስተያየት የሰጡ የጠቅላይ ሚኒስትሩ አማካሪዎች፣ አፈቀላጤዎች፣ የመንግስት የኮሚኒኬሽን ባለስልጣናት፣ የፍትህ አካላት የሰጡን አስተያየቶች በቅርጽም በይዘትም አስገራሚ ሆነው አግኝተናቸዋል። አንዳንዶች በቅኔ በተረት መልኩ ሊያስረዱን ሲሞክሩ፣ ሌሎቹ “እመኑን አትቸኩሉ ወደፊት ታዩታላችሁ ብዙ ጥቅም የሚኖረው ውሳኔ ነው” እያሉን ነው። ይህ አባባል የራሱ የጠቅላይ ሚኒስትሩም ነው። እነዚህ ሁሉ ተደምረው ጉዳዩን የበለጠ አወሳሰቡት እንጂ ሌላ የፈየዱት ነገር የለም።

ይህ እንዳለ ሆኖ የፍችው ምክንያት ምን እንደሆነ ባልጠራበት ሁኔታ የተለያዩ ቡድኖችና ግለሰቦች በመሰላቸው መንገድ የውሳኔውን ሚስጥር በመተርጎም አስተያየቶቻቸውን ለመስጠት ሲሞክሩ ታይተዋል። እነዚህ አስተያየቶች ከአራት አቅጣጫዎች የተሰነዘሩ ናቸው። እጅግ አድርባይ የሆኑ ሁሌም ስልጣን ላይ ለወጣ ሃይል ሁሉ በጭፍኑ የማደግደግ ባህል ያላቸው ግለሰቦችና ቡድኖች ከተለመደው የማደግደግ ባህላቸው ተነስተው የመንግስት ውሳኔ ለማንም ግልጽ ባልሆነበት ሁኔታ ውሳኔውን ሲደግፉ ታይተዋል። በደንብ ቢጠየቁ ምኑን እንደደገፉ ራሳቸውም የሚያውቁት አይሆንም። እንደዚህ አይነቶቹ ግለሰቦች ጥቂት ቢሆኑም ድምጻቸውን አጋኖ የሚያስተጋባላቸው አጋር የመንግስት ሚድያ አላቸው። እንዲህ አይነት ሰዎች በሃገር ውስጥም በዳያስፖራውም እንዳሉ ይታያል።

ከመጀመሪያዎቹ ቀጥሎ፤ ከኢህአደጋዊው የጥርናፌ ባህል ያልተላቀቁት የብልጽግና ፓርቲ አመራሮችና አባላት፣ በብልጽግና ፓርቲ ሙሉ ቁጥጥር ስራ የሚገኙ የሚዲያ ተቋማት፣ እንዲሁም ለብልጽግና ፓርቲ ማደሩ ይጠቅማል ያሉ ሌሎች አካላት፣ ለውሳኔው በቂ ምክንያት ሳያቀረቡ የተለመደውን በመንግስት ውግንና የተሞላውን ፕሮፓጋንዳ ሲያካሂዱ እያየናቸው ነው።

ከእነዚህ ውጭ በተለይ በስልጣን ላይ ያለውን መንግስት በበጎ አይን የሚያዩና ተቀራርበው እየሰሩ ያሉ ሃይሎች የውሳኔው ምክንያት ግልጽ ባይሆንላቸውም ኢትዮጵያ ያለችበትን አሳሳቢ ሁኔታ ግምት ውስጥ በማስገባት ሃላፊነት በተሞላው መንፈስ “ይህ ውሳኔ የተጀመረውን በጋራ ሃገር እና ህዝብን የመታደግ አዲስ ባህል በመጉዳት ለሃገሪቱ ጠላቶች ቀዳዳ የሚከፍት እድል ስላለው፣ ቀዳዳ እንዳይከፈት” አበክረው ተማጽነዋል።

በአራተኛ ረድፍ ላይ የቆመው ሁሌም ማናቸውንም የመንግስት ውሳኔ መልካም ይሁን መጥፎ በመቃወም የግልና የቡድን ጥቅም በሃገርና በህዝብ ኪስራ ለማስጠበቅ ቆርጦ የተነሳው ወገን ነው። ለዚህ ሃይል ይህ ግልጽነት የሌለው ውሳኔ የሰርግና ምላሽ ሁኔታ ፈጥሮለታል። በዩትዩብና በማህበራዊ ሚድያ ገንዘብ የመሰብሰብ፣ በመንግስትና በህዝብ መሃከል መቃቃር እንዲፈጠር፣ ሀገር እንዲፈራርስ ያለውን ህልም ማሳኪያ አድርጎ እየሰራበት ይገኛል።

እኔም ይህን ወሳኔ ስቃወም ውሳኔውን ለምን እንደተወሰነ የተለየ መረጃ ኖሮኝ አይደለም። ሆኖም የሃገራችንን የፖለቲካ ሂደት በቅርበት እንደሚከታተል ሰው ለዚህ ውሳኔ ምክንያቶች ይሆናሉ ብዬ የገመትኳቸውን ነጥቦች በሙሉ መዘርዘርና ጥቅምና ጉዳታቸውን ማጤን ከባድ ስራ ነው ብዬ አላምንም። እነስብሃት ነጋን ለመፍታት መንግስት ለምን እንደወሰነ በውል አናውቅም ማለት ምክንያት ሊሆኑ የሚችሉትን ነጥቦች አንድ በአንድ መዘርዘር አንችልም ማለት አይደለም።

የውሳኔውን ምክንያቶች ከመዘርዘሬ በፊት በሁለት ነጥቦችን ላይ ያለኝን እይታ ግልጽ ማድረግ እፈልጋለሁ።

የመጀመሪያው ነጥብ የውሳኔውን አላማ (motive) የተመለከተ ነው። በበኩሌ ይህን ውሳኔ የተቃወምኩት ውሳኔው ቀና ካልሆነ፣ ኢትዮጵያንና ህዝቧን ለመጉዳት በማሰብ የተደረገ ውሳኔ ይሆናል ከሚል ጥርጣሬ በመነሳት አይደለም። ጦርነቱ በፍጥነት አልቆ ኢትዮጵያ ፊቷን ወደ ተረጋጋ የፖለቲካና መንግስታዊ ስርአት ግንባታ እንድታዞር፣ በተለይ ከሁሉም ነገር በላይ የኢትዮጵያና የህዝቧ የዘመናት ማድያት የሆነውን ሃገራዊ ድህነት የመቅረፍ ስራ ጊዜ ሊሰጠው የማይገባ መሆኑን እና ጦርነቱ በዚህ ቀና ህልም ፊት የቆመ ደንቃራ እንደሆነ አድርጎ በተለይ ዶ/ር አቢይ እንደሚያየው አውቃለሁ። ችግሩ ያለው ውሳኔው፣ እውን እንደወሳኞቹ በጎ ምኞት የጦርነቶችን እድሜ በኢትዮጵያ ያሳጥራል ወይ? እውን የተረጋጋ ፖለቲካዊና መንግስታዊ ስርአት ለመገንባት የተሻለ እድል ይፈጥርልናል ወይ? እውን ሁለመናችን ወደ ልማት እና ብልጽግና በማዞር የኢትዮጵያን ህዝብ ለስቃይ የዳረገውን፣ የፖለቲካ፣ የማህበራዊ፣ የሞራልና የስብእና መቃወስ ምንጭ የሆነውን ድህነትን እንድንቀንስ እድል ይሰጠናል ወይ? ነው። በእነዚህ ጥያቄዎች ላይ ጠቅላይ ሚኒስትሩ በእራት ግብዣው ላይ ውሳኔው ያስከብራል ያላቸውን ሶስት ነጥቦች መጨመር እንችላለን። እውን ውሳኔው የኢትዮጵያን ሉአላዊነት፣ ብሄራዊ ጥቅምና ክብር የሚያስጠብቅ ይሆናል ወይ? እንዳውም እነዚህ ሶስት ነጥቦች የተለየ ትኩረት ተሰጥቷቸው ሊፈተሹ የሚገባቸው ናቸው። ሚድያው እንደ ገደል ማሚቱ እየደጋገመ እያስተጋባቸው ስለሆነ።

ሁለተኛው ነጥብ “መንግስት ለምን በውል ውሳኔውን እንደወሰነ ሳታውቁ ትቃወማላችሁ” በሚለው ጉዳይ ነው። ሲጀመር በቂ ማብራሪያ ያልሰጠውና አብዛኛውን ሰው በጉዳዩ ላይ እንዲጠነቁል ያደረገው መንግስት ነው። መጠየቅ ካለበት ለህዝብ በቂ መግለጫ መስጠት የተሳነው መንግስት እንጂ የራሳቸውን መላ በመምታት የሚቃወሙት መሆን የለባቸውም። “በቂ ማብራሪያ መንግስት እስከሚሰጥ ጠብቁ” ለሚሉት ውሳኔው በንድፈ ሃሳብ ደረጃ የሚቀር ቢሆን ኖሮ ምክራቸውን መቀበል ቀላል ይሆን ነበር። ችግሩ መንግስት በቂ ማብራሪያ ሳይሰጥ ውሳኔውን ተግባራዊ እያደረገው ነው። አንዴ ውሳኔው ተግባራዊ መሆን ከጀመረ በተለይ ውሳኔው አንዳንዶቻችን እንደሰጋነው በሃገርና በህዝብ ላይ ጉዳት የሚያስከትል አደገኛ ውሳኔ ሆኖ ከተገኘ መዘዙ የከፋ ሊሆን ይችላል።። ስለዚህ “ወሳኔው ወደ ከፋ ጥፋት ሊወስደን ይችላል” የሚል ጥርጣሬ ያላቸው አካላት የውሳኔው መዘዝ ይሆናል ያሉትን እያቀረቡ መንግስትን ቢቃወሙ፣ ቢሞግቱ፣ መንግስትን ቢያስጠነቅቁ፣ ቢያሳስቡ ወይም ቢማጸኑ “ትክክል ናቸው” ማለት እንችላለን። እኔም ይህን በማመኔ ነው የመንግስትን እርምጃ አጥብቄ የተቃወምኩት። ቀጥሎ የምሸጋገረው ለመንግስት ውሳኔ ምክንያቶች ይሆናሉ ብዬ ያሰብኳቸውን ወሳኝ ነጥቦች ወደ መዘርዘሩ ነው። ነጥቦቹን በወቅቱ ክብደት ሰጥቼ ባስቀመጥኩበት ቅደም ተከተል በተራ ቁጥር አስቀምጣቸዋለሁ። በእራት ግብዣው ላይ ዶ/ር አብይ ያደረገው ንግግር ትንሽም ቢሆን ስራችንን ቀለል አድርጎልናል ብዬ አምናለሁ።

የውሳኔ ምክንያቶች፤

1) ውሳኔው ከውጭ መንግስታት በተለይ ከአሜሪካ መንግስት ጋር የተፈጠረ አዲስ ግንኙነት፣
2) “ጦርነቱ ዞሮ ዞሮ የፖለቲካ መቋጫ ያስፈልገዋል” ከሚል እምነት ለፖለቲካ መቋጫው የእርቅ፣ የድርድርና የውይይት መንገድ ለመክፈት፤
3) በወያኔ ካምፕ ውስጥ ልዩነቶች በመቀስቀስና ክፍፍል በመፍጠር ጦር ሰባቂውን ወገን ለማዳከም፣
4) ከእምነት ጋር የተያያዘ የእርቅና የምህረት ቀኖና ለማስፈጸም የተወሰደ ውሳኔ፣

ውሳኔውን በግራም ሆነ በቀኝ ብናገላብጠው የውሳኔው ምክንያቶች ከዚህ ውጭ ሊወጡ አይችሉም። እስካሁን የተሰጡት ማብራሪያዋች የሚያሳዩትም ይህንኑ ነው።
የገና እለት ከምሽቱ አራት ሰአት በኋላ የኢትዮጵያ ቴሌቪዥን “ሰበር ዜና” በሚል ርእስ መደበኛ ፕሮግራሙን ሲያቋርጥ እኔ የጠበቅኩት መንግስት በትግራይ አሸባሪ ቡድን መሪዎች ላይ የተቀዳጃቸውን የድል ዜና ሊያበስር ይሆናል የሚል ነበር። ሌላው የጠበቅኩት ዜና ትልቅ የእልቂት ወይም ከባድ የሃዘን ዜና ነበር። እነዚህ ሁለት የጠበቅኋቸው ዜናዎች ሳይሆኑ ቀርቶ ከወያኔ ደጋፊዎች ውጭ አድማጭን ያስደነገጠ ዜና ተደጋግሞ ተነበበ።

እነጀዋር እና እነ እስክንድር ለብሄራዊ ውይይቱ ተአማኒነት ሲባል ይፈታሉ የሚል ግምት ቢኖረኝም እነስብሃት ነጋ ግን እንዲፈቱ የሚያደርግ ምድራዊ ምክንያት ይኖራል ብዬ አስቤ አላውቅም ነበር። በተለይ እንዲህ አይነቱ ዜና በበአል ቀን እንዳውም ከመሸ በኋላ እንዲነገር የተፈለገበት ምክንያት ብዙ ጥያቄዎች እንዳነሳ አደረገኝ። የነጀዋርና የእነእስክንድር ከነስብሃት ጋር ተደባልቆ መፈታት ሰበር ዜናው እነስብሃትን ከመፍታት ጋር እንጂ ከነጀዋርና እስክንድር መፈታት ጋር የተገናኘ እንዳልሆነ እንዳስብ አድርጎኛል። እንዲያውም “እነእስክንድርና ጀዋር በዛ ቀን እንዲፈቱ የተደረገው በነስብሃት መፈታት በህዝቡ ውስጥ የሚነሳውን ድንጋጤና ቁጣ ለማደብዘዝ ካልሆነ ሌላ ምክንያት አይኖረውም” የሚል ድምዳሜ ላይ አደረሰኝ። የዜናው ተቻኩሎ የመለቀቅ ጉዳይ፣ በተለይ የእለቱን በአልነት ግምት ውስጥ በማስገባት፣ መንግስት ፍቺውን በተመለከተ ቃል የገባለት አካል ሊኖር እንደሚችልና ቃሉን ለመጠበቅ ሲል የገናን እለት እንኳን ማለፍ የማይችልበት ሁኔታ ውስጥ እንደገባ ነው የገባኝ። “ይህን ማድረግ የሚችሉ አሜሪካኖች ብቻ ናቸው” ብዬ በማሰቤ ነው ለነስብሃት መፈታት ዋናው ምክንያት አሜሪካ ትሆናለች በማለት የደመደምኩት። ሌሎችንም ከላይ ያስቀመጥኳቸውን ምክንያቶች ብዘረዝርም ዋናው ምክንያት ይሆናል ያልኩትን ጉዳይ በጥልቀት መመልከት ጀመረኩ።

1) ውሳኔው ከውጭ መንግስታት በተለይ ከአሜሪካ መንግስት ጋር የተፈጠረ አዲስ ግንኙነት፣

የተለያዩ የአሜሪካ የጥናትና የምርምር ቡድኖች፣ የታወቁ የውጭ ጉዳይ ተንታኝ የህትመት ድርጅቶች፣ የውጭ ጉዳይ ሙያተኞችና ፖለቲከኞች፣ የአሜሪካ መንግስት በምስራቅ አፍሪካ፣ በተለይ በኢትዮጵያ ላይ የምትከተለው የውጭ ጉዳይ ፖሊሲ የአሜሪካንን ብሄራዊና መሰረታዊ ጂኦ ፖለቲካል ጥቅም ክፉኛ የሚጎዳ እንደሆነና መስተካከል እንደሚገባው መወትወት ከጀመሩ ቆይተዋል። ሆኖም የአሜሪካ መንግስት የውጭ ፖሊሲ ላይ ተጽእኖ የሚያሳድሩ እንደነ ሱዛን ራይስ፣ ጌል ስሚዝና ሳማንታ ፓወር የመሳሰሉ የወያኔ ወዳጆችና ቅጥረኞች በአስተዳደሩ ውስጥ ከፍተኛ ስልጣን መያዛቸውና ወያኔ በወታደራዊ ጉልበቱ አሜሪካኖች የጠሉትን የአብይን መንግስት የመጣል እድሉ ገዝፎ በሚታይበት ወቅት አሜሪካ በኢትዮጵያ ላይ የያዘቸውን በሃገራችን ኪሳራ ጥቅሟን የሚያስከብር አቋም ለማስተካከል ፈቃደኛ አልነበረችም። ሆኖም ግን በፖለቲካ 24 ሰአት ረጅም ነው እንደተባለው አሜሪካ አቋሟን የማስተካከል እርምጃ በአጭር ጊዜ ውስጥ እንድትወስድ የሚያስገድዱ ኩነቶች ተበራከቱ።

ዋናው ኩነት የአሜሪካ ፈረስ ሆኖ አዲስ አበባ ይገባል የተባለው ወያኔ በጥቂት ሳምንታት በኢትዮጵያ መከላከያና ሌሎች የጸጥታ አካላት ተቀጥቆጦ ከሞላ ጎደል ከአፋርና ከአማራ ክልል ተጠራርጎ መውጣቱ ነው። በወታደራዊ ጉልበት የአብይ መንግስትን መጣል የማይቻል መሆኑ ግልጽ ሲሆን አሜሪካ ጥቅሟን የምታስከብርበት ሌላ አማራጭ ወደ ማሰብ መሄዷ የግድ ነበር። በዚህ ላይ የቻይና የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር መጀመሪያ ኢትዮጵያን ቀጥሎ ኤርትራን በዚህ የጦርነት ወቅት መጎብኘቱ፣ ለአፍሪካ ቀንድ ልዩ መልእክተኛ እንመድባለን ማለቱ፣ ቻይና ከ300 ቢሊዬን ዶላር በላይ ከአፍሪካ ጋር ላላት የንግድ ትስስር መመደቧ፣ ሌሎችም እንደ ሩሲያ፣ ህንድ፣ ቱርክና ኢራንን የመሳሰሉ ሃገራት ከኢትዮጵያ ጋር ያሳዩት መቀራረብ ኢትዮጵያ ያለአሜሪካ ትብብር ህልውናዋን እና ጥቅሟን አስከብራ የምትሄድ አሜሪካንን የማትፈልግ ሃገር እየሆነች መሄዷ፣ አሜሪካንን እያሳሰባት እንዲመጣ አድርጓታል።

በዚህ ላይ አሜሪካ በወሰደችው አይን ያወጣ ኢትዮጵያን የማጥቃት አቋም የተነሳ በኢትዮጵያ ውስጥ የተጀመረውና፣ በሃገር ውስጥ ወደ ሰፊ ህዝባዊ እንቅስቃሴ እንዲያድግ በመንግስት ያልተፈለገው፣ (ከብልጽግና ፓርቲ ቁጥጥር ውጭ ይወጣል በሚል ስጋት) ሆኖም ግን ወደ ውጭ የተዛመተው “ኢትዮጵያን አትንኩ” (hands off Ethiopia) እንቅስቃሴ እራሱን አጠናክሮ ወደ አለም አቀፉ በቃ (Nomore) ጸረ አዲሱ ቅኝ አገዛዝና ጸረ አሜሪካን ኢምፔሪያሊዝም እንቅስቃሴ ማደጉ ሌላ የአሜሪካን ራስ ምታት እየሆነ መጥቷል። ይህ እንቅስቃሴ በፍጥነት በአፍሪካና በካሬቢያን ሃገሮች ብቻ ሳይሆን በላቲን አሜሪካ፣ በኢራንና በቻይና እየተዛመተ ያለ እንቅስቃሴ መሆኑ ከአሜሪካኖች የተሰወረ አይደለም። አሜሪካኖች የበቃ እንቅስቃሴ ምን ያህል እንዳሳሰባቸው ማስረጃው “በአሜሪካን ሃገር ውስጥ በትውልደ ኢትዮጵያውያን መሃል ተሰሚነት ያላቸው ግለሰቦች እነማን ናቸው?” የሚል ጥናት እንዲያጠና ለአንድ የግል ኩባንያ ገንዘብ ከፍለው ስራ ማስጀመራቸውን ነው። የዚህ ጥናት አላማ መደለል ያለባቸውን ተጽእኖ አሳዳሪዎች መደለል፣ ማስፈራራት የሚገባቸውን ለማስፈራራትና በበቃ ንቅናቄ መሪዎች ላይ ተጽእኖ ለማሳደር ነው።የእነዚህ የተደራረቡ ኩነቶች ድምር አሜሪካ በፍጥነት ከኢትዮጵያ ጋር ያላትን ግንኙነት መርምራ ኢትዮጵያ የያዛቸውን ከአሜሪካ የመራቅና አሜሪካንን የማሳጣት ስራ ማስቆም ቀዳሚ ስራዋ አድርጋ የምትንቀሳቀስበት ሁኔታ ውስጥ እንደምትገባ መተንበይ ከባድ አልነበረም።
አሜሪካ በኢትዮጵያ ላይ ጫና በማድረግ ሁኔታውን ለመቀልበስ የምትሞክርባቸው አማራጮች ሁለት ነበሩ። አንዱ ወያኔ ጥቅም ባይኖረውም፣ ለወያኔ ድጋፍ እየሰጡ ማቆየት፣ የሰብአዊ መብት ጥሰትን፣ የእርዳታ አቅርቦት ችግርን ሰበብ በማድረግ በኢትዮጵያ ላይ በኢኮኖሚ፣ በዲፕሎማሲና ቀጥተኛ ባልሆነ ወታደራዊ መንገድ ተጽእኖ ማድረግ ሲሆን፤ ሌላው አማራጭ አሜሪካ አይኗን በጨው ታጥባ “ድሮም ቢሆን የኢትዮጵያ ወዳጆች ነን፣ ወያኔ ያደረሰውን ጥፋት ተመልክተናል፣ በትግራይ ይሁን በሌላው የሃገሪቱ ክልል የተፈጠረውን ቀውስ መፍትሄ መስጠት የሚችለው የኢትዮጵያ መንግስት ብቻ ነው። የኢትዮጵያ መንግስት እኛን ከሃፍረት ሊያድነን የሚያስችሉ (for face saving purposes) እርምጃዎች ቢወስድ ከኢትዮጵያ መንግስት ጎን በመቆም ወዳጅነታችንን ማጠናከር እንፈልጋለን” የሚል አማራጭ መውሰድ ነው። በገና እለት በተጣደፈ መንገድ የእነስብሃት መፈታታ ሲታወጅ በኔ አእምሮ የመጣው “አሜሪካ ሁለተኛውን አቋም በመውስድ ወያኔን ለጥቅሟ ስትል ለመክዳት ወስናለች” የሚል ነበር። አሜሪካ በማስፈራራት ተጽእኖ እንዳላመጣችብን ገምቼ ነበር።

አሜሪካኖች አንድ ወሳኔ ሲወስኑ በበዙ አቅጣጫ ነገሮችን አጢነው ነው። ከሚያጤኑት ጉዳይ መሃከል ግለሰቦችን ጭምር ነው። አብይን በኢኮኖሚ ማእቀብ፣ በወታደራዊ ፉከራ፣ በዲፕሎማሲ ጦርነት አስፈራርተው ነው እነስብሃትን እንዲፈታ ያደረጉት የሚለውን የአንዳንድ ጓደኞቼን ትንተና ያልተቀበልኩት አሜሪካኖች አብይን በማስፈራራት ቢቀርቡት ጉዳዩን ወደ ኢትዮጵያ ህዝብ ወስዶ የበለጠ ጸረ አሜሪካ የሆነ ስሜት በሃገር ውስጥና በውጭ ሃገራት እንደሚፈጥር፣ በማስፈራሪያ ሊያስጎነብሱት የሚችሉት ሰው እንዳልሆነ ስለሚያውቁ ነው።

ከጠቅላይ ሚኒስትሩ የእራት ግብዣ ንግግር ግልጽ ሆኖ የወጣው ጉዳይ አሜሪካ የማስፈራራት ተጽእኖ እንዳላደረገች ነው። አሜሪካ የኢትዮጵያን አቋም በደንብ ተረድተው መስመራቸውን ለማስተካከል ከተዘጋጁት መሃል አንዷ እንደሆነች ፍንጭ ሰጥቶናል። ዝርዝሩን ማወቅ ስለማንችል አሜሪካ የኢትዮጵያን መንግስት ለመሸንገል እስከምን ርቀት ልትጓዝ እንደወሰነች መናገር አልችልም። ሆኖም ለኢትዮጵያ መንግስት በፍንጭ ደረጃ ቃል የገባቻቸው በርካታ ነገሮች ይኖራሉ የሚል እምነት አለኝ። አንዱ ወደ አግዋ ኢትዮጵያን መመለስ፣ ሌላው የወደሙትን ክልሎች ለመገንባት በሚደረግ ጥረት ሰፊ ድጋፍ ማድረግ፣ ለተጎዱና ለተፈናቀሉ ሰፊ እርዳታ መለገስ፣ የወያኔ መሪዎች ከሰላም ውጭ ሌላ አማራጭ እንደሌላቸው በመንገር ተጽእኖ ማድረግ፣ የአለም የፋይናንስ ተቋማት በራቸውን ለኢትዮጵያ ክፍት እንዲያደርጉ ማድረግ፣ በአሜሪካን ባንኮች ውስጥ እንዳይንቀሳቀስ ያደረጉትን ገንዘብ እንዲንቀሳቀስ መፍቀድና ሌሎችንም ነጥቦች ሊያካትት ይችላል የሚል ግምት አለኝ።

በተለያዩ አጋጣሚዎች፣ ከወያኔ ጋር በጥቅም ከተቆራኙት የጌል ስሚዝ ጋንግ በስተቀር የአሜሪካ መንግስት ባለስልጣናት ለወያኔ መሪዎች የተለየ ፍቅር እንደሌላቸው ገልጫለሁ። አሜሪካ ለወያኔ የምታሳየው ውግንና ወያኔ የአሜሪካን ጥቅምና ፍላጎት በኢትዮጵያ ውስጥ ለማስፈጸም የተመቻቸ መሳሪያ ነው ብላ ከማመን እንደሆነ በተደጋጋሚ አስረድቻለሁ። አሜሪካ ቁርባን የምትገባው ሃገር፣ ድርጅትና ግለሰብ የለም። ወያኔ በመሳሪያነት ጠቀሜታ እንደሌለው በውል የተረዳ የአሜሪካ መንግስት ወያኔን አገልግሎቱ እንዳበቃለት መሳሪያ አውልቆ ቢጥለው የሚገርም አይደለም። አሜሪካ ከወያኔም ጋር ይሁን ከኢትዮጵያ መንግስት ጋር ቋሚ ወዳጅነት ላይ የተመሰረተ ግንኙነት ሊኖራት የማትችል ሃገር ናት። ቋሚ ጥቅሟን የማያስከብሩ እስከሆነ ድረስ ሁለቱን ለመክዳትና ለማጥቃት ወደ ኋላ አትልም።

ግምታዊ በሆነ መንገድ የምንወያይ ቢሆንም አሜሪካ እንዲወገድ ስትፏችር ወደነበረው የአብይ መንግስት ፈገግታ የተሞላ ፊቷን ስታዞር “ምን አገኛለሁ ብላ ነው?” ብሎ መጠየቅ ተገቢ ነው ። በዚህ የተለሳለሰና ዱላ የሚባል ነገር የሌለው በከረሜላ ብቻ በተሞላ አቀራረባቸው አሜሪካኖች ኢትዮጵያን የተጠጉት ምን ማከናወን ፈልገው ነው? የኢትዮጵያ መንግስት ስሟን ባይጠቅስም፣ የአሜሪካንን አዲስ አቀራረብ በድል መልኩ አቅርቦታል። ጠቅላይ ሚኒስትሩ እኛ ሸብረክ አላልንም ያሉት ሌሎች ናቸው ሲለን ስለነማን እየነገረን እንደሆነ ግልጽ ነው። ከዛም አልፎ እነስብሃትን መልቀቅ ጥቅም የሚያስገኝ እንደሆነ በቅኔ እና በተረት እየተነገረን ነው። ስለጥቅም እየነገሩን ያሉት ግለሰቦች “ይህን የአሜሪካ አዲስ አቋም ከነሙሉ ትርጉሙና መዘዙ ተረድተውት ነው ወይ?” የሚል ጥያቄ የሚያስነሳ ሆኖ አግኝቸዋለሁ።

ዶ/ር አብይ ኢትዮጵያ ጠላት ብላ የፈረጀቻቸው አገሮች የሉም ብሎ ነግሮናል። ጠቅላይ ሚኒስትሩ ዲፕሎማት መሆን ስላለበት እነዚህን በመሰሉ ጉዳዮች ላይ በግልጽ መናገር አይችልም። በአደባባይ አገሮችን እየዘረዘረ ወዳጅና ጠላት ሃገራት እያለ እየፈረጀ የኢትዮጵያን የውጭ ፖሊሲ ሰነድ ጽፎ በማሳተም የበተነውን መለስ ዜናዊ አውግዤ፤ ዶ/ር አብይን ጠላትና ወዳጅ እያልክ መንግስታትን በአደባባይ ዘርዝርልን ማለት አልችልም። ይህን ብዬም የጠቅላይ ሚኒስትሩ “ኢትዮጵያ ጠላት ብላ የፈረጀቻቸው ሃገራት የሉም” የሚል አባባሉ ከዲፕሎማሲ ቋንቋ ዘሎ ግን የእውነተኛ እምነት መገለጫ ከሆነ ሃገራችን ትልቅ ችግር ውስጥ ነች።

በተለይ አሜሪካና የምእራብ መንግስታት ለረጅም ዘመናት፣ እሰከ ትናንትና ድረስ ኢትዮጵያን በማጥቃት የፈጸሟቸውን እኩይ ተግባራት ብዙ እንደሆኑ እናውቃለን። ኢትዮጵያ መቼም ቢሆን ራሷን በኢኮኖሚ የቻለች፣ ሰላምና መረጋጋት የሰፈነባት፣ የእኩልነት፣ የፍትህና የነጻነት ምድር ሆና፣ በአፍሪካዊ አርአያነቷ ገና እንድትወጣ አሜሪካና የምእራብ መንግስታት ከቶውኑ አይፈልጉም። አሜሪካና ሸሪኮቿ የምእራብ ሃገራት ሁሌም ማየት የሚፈልጉት በነጮች ቀጭን ክር ታስረው የሚንቀሳቀሱ የአፍሪካ አገሮችን ነው። አፍሪካን በነጮች ምክር፣ ትእዛዝና ድጋፍ ቁጥጥር ስር እንዲወድቁ ማድረግ ከስትራተጂ ጥቅማቸው ጋር በጥብቅ የተሳሰረ ነው። እነዚህ ሃገራት የአፍሪካ ነጻነት፣ ፍትህ፣ ብልጽግና ሰላም እና አንድነት ጸሮች ናቸው።

አሜሪካ ወያኔን በመደገፍ የሸረበችው ሴራ ከዚህ ቀደም ታይቶ በማይታወቅ ደረጃ የኢትዮጵያ ህዝብ ከራሱ ፣ ከቅርብ ጎረቤቶቹና ከአፍሪካ፣ በአሜሪካና በምእራባውያን ተመሳሳይ በደል ከደረሰባቸው ሃገሮችና ህዝቦች በስተቀር፣ አጋር እንደሌለው ለማየት የቻለበት እድል ስጥቶታል። የአሜሪካና የምእራባውያንን የዴሞክራሲና የሰብአዊ መብት ጠበቃነት ጭምብል ወልቆ ለማየት ችሏል። እነዚህ ሃገራት ስለዲሞክራሲና ስብአዊ መብት የሚያወሩት ጥቅማቸው እስከተከበረ እንጂ ጥቅማቸው የማይከበር ሆኖ ካገኙት ሃገር ከማፍረስና ህዝብ ከማጥፋት የማይመለሱ እንደሆነ መረዳት ችሏል። መራባውያን እንደወያኔ አይነቶቹን ሃገር አፍራሽና ህዝብ ጨራሽ ሃይሎች ለመደገፍ ወደኋላ እንደማይሉ ሁላችንም የሃገራችን ደሃ ገበሬ ሳይቀር በአይናችን ያየነው ጉዳይ ነው። ከዚህ ቀደም በርእዮእተ አለም ደረጃ ሲገለጽ የነበረው የምእራባውያን እኩይነት ዛሬ የኢትዮጵያ ህዝብ በቀላሉ ሊረዳው በሚችለው በአሜሪካኖችና በምእራባውያን ድጋፍ ወያኔ በሃገራችን እና በህዝባችን ላይ በፈጸመው አሰቃቂ ሰቆቃና ውድመት ግልጽ ሆኗል። ይህ የህዝብ እውቀት የኢትዮጵያና የአፍሪካ ትንሳኤ መሰረት ነው።

በዚህ የታሪክ መጋጠሚያ የደረሰብን ሰቆቃና ውድመት ይዞት የመጣው አንድ ትልቅ እድል አለ። በቀላሉ የማይገኝ እድል። ራሳችንን እንድንፈትሽ፣ እውነተኛ ወዳጅ ጠላታችንን እንድንለይ አስችሎናል። ወያኔ በዘር ሰነጣጥሮ ሲያባላው የነበረ ህዝብ የአንድነትን ትርጉምና ሃያልነት የተማረበት እድል ሰጥቶታል። የኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን የአፍሪካ ድክመት የአንድነት አለመኖር መሆኑን አሳይቶናል። ከምንም ነገር በላይ በሰላም ለመኖር የውስጥ ችግራችንን ማቃለል፣ ከጎረቤቶቻችንን ጋር በሰላምና በመልካም ጉርብትና መኖር፣ የመላውን የአፍሪካ ህዝብ ወንድማዊና እህታዊ አጋርነት የሚያስፈልገን እንደሆነ አሳይቶናል። የአሜሪካን እርጥባንና በዴሞክራሲና በሰብአዊ መብት ስም የሚፈስ የአዞ እንባ የኢትዮጵያንና የአፍሪካን የባርነት ቀንበር የሚያጠብቅ እንጂ ነጻነት እንደማያመጣ አስረድቶናል። "እኛ የአድዋ እንጂ የአገዋ ልጆች አይደለንም" የሚል ትልቅ ትርጉም ያለው አባባል በምድራችን እንዲሰማ አድርጓል።

አሜሪካኖች በኢትዮጵያውያን እና በኤርትራውያን የተጀመረው በቃ እንቅስቃሴ በሁለቱ ሃገሮች ድንበር ታጥሮ እንደማይቀር አውቀውታል። ጉዳዩ የኢትዮጵያን መንግስት ከአሜሪካ ጫና ማላቀቅ ሳይሆን የአፍሪካን ህዝብ የአህጉሩ ባለቤት የሚያደርግ ስር ነቀል እንቅስቃሴ እንደሆነ ግብቷቸዋል። የኢትዮጵያ ጥንካሬ ከጎረቤቶቿ ከኤርትራና ከሶማሌያ ጋር ያላት ወገናዊ ትስስር እንደሆነ ያውቃሉ። ኢትዮጵያ ከምእራባውያን የሎሌነት ቀንበር ነጻ የምትሆነው፣ ክብሯ፣ ሉአላዊነቷንና ጥቅሟን ማስከበር የምትችለው የአሜሪካኖችን ተጽእኖ ተቋቁማ በምትገነባው ሃገር በቀል ኢኮኖሚ፣ በምርጫዋ ላይ ተመስርታ በምትገባባቸው ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነቶች፣ በራሷ ጥረት በምትገነባው ለሁሉም ዜጎቿ የሚመች ጤነኛ የፖለቲካ ስርአት እንደሆነ ያውቁታል። የብሄራዊ ጥቅሟና ደህንነቷ ምንጭ የህዝቧ አንድነት ጀግንነትና አይበገሬነት እንደሆነ አስቀደመው ያውቁታል።

ዛሬ አሜሪካኖች በፈገግታ የተሞላ ፊታቸውን ወደ ዶ/ር አብይ መንግስት ሲያዞሩ፣ ከዱላ ነጻ የሆኑ ብዙ ከረሜላዎችን ውሰዱ ሲሉ ግባቸው ኢትዮጵያን መልሰው የአሜሪካ ጥገኛ ማድረግ ነው። አድዋን በአግዋ መቀየር፣ ኢትዮጵያ ከቻይና ከሩሲያና ከሌሎች በፈቃዷ ከመሰረተቻቸው ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነቶች ራሷን እንድታርቅ ነው። በተለይ ደግሞ ለአሜሪካ አልገብርም ካለው፣ የኤርትራ መንግስትና ህዝብ ጋር አጥብቃ የያዘችውን ወዳጅነት ኢትዮጵያ እንድታላላ ለማድረግ ነው። በእርዳታ ፣ በዲፕሎማሲ ድጋፍ ፣ በወታደር ስልጠና እና በመሳሪያ አቅራቢነት ፣ የእናንተም ጠላት የኔም ጠላት ነው በሚል ሃፍረት የለሽ እወጃ ስም፣ አሜሪካ ማግኘት የምትፈልገው የአሜሪካ ተላላኪ የሆነች በጎረቤቶቿ በአፍሪካውያን በሌሎችም የአለም መንግስታት አይን በጥርጣሬ የምትታይ ኢትዮጵያን ነው።

የአሜሪካ ፍላጎት ለኢትዮጵያ ክብር ሲል በተጀመረውና የአፍሪካን ክብር ለማስመለስ ወደ ትልቅ እንቅስቃሴ እያደገ ባለው የበቃ እንቅስቃሴ ላይ የኢትዮጵያ መሪዎች ውሃ እንዲቸልሱበት ነው። በእራት ግብዣው ላይ ዶ/ር አብይ በማወቅም ይሁን ባለማወቅ የደያስፖራውን እንቅስቃሴ የእሱን መንግስትና ኢትዮጵያን ከጥቃት ለመከላከል ብቻ እንደተፈጠረ አድርጎ በማቅረብና ንቅናቄው ፊቱን ወደሌሎች ጉዳዮች እንዲያዞር የሰጠው ምክር የአሜሪካኖችን ልብ የሚያሞቅ እንደሆነ መታወቅ አለበት። የበቃ እንቅስቃሴ እንዲበተን ትኩረቱን ወደ ጥቃቅን ነገሮች እንዲያዞር አሜሪካኖች ይፈልጋሉ። የነስብሃት መፈታት ያስነሳው አቧራ የበቃ እንቅስቃሴን ለማናጋት በቅቷል። ኢትዮጵያ የበቃን አለም አቀፍ እንቅስቃሴ በመምራት የፓን አፍሪካን መሪነቱን መረከብ ሲገባት ንቅናቄውን የሚያዳክም ወሳኔዎች በመወሰን ልትጎዳው አይገባም።

በራሱ ህዝብ አቅምና ጥረት ላይ ኢኮኖሚውን፣ ወታደራዊ ጉልበቱን፣ ፖለቲካዊ ጤንነቱን ያልገነባ፤ ከአካባቢው ሃገራት ጋር በመልካም ጉርብትና የማይኖር የአንድ ሃገር መንግስት የአሜሪካ ቁራኛ ሆኖ እንደሚያርፈው አሜሪካኖች ጠንቅቀው ያውቁታል። እንዲህ አይነቱ መንግስት የገዛ ሃገሩንና ህዝቡን ጥቅም ማስከበር አይችልም። አሜሪካኖች እንዲህ አይነቱ መንግስት ከህዝብ የተገነጠለ፣ በህዝብ የተጠላ በመሆኑ ህልውናውን ለማስጠበቅ ከአሜሪካኖች በጎ ፈቃድና ድጋፍ ውጭ መኖር እንደማይችል፤ በብዙ ሃገሮች ላይ ከፈጸሙት ደባ ተነስተው የሚያቁት ሃቅ ነው። እንዲህ አይነት ከህዝቡ ጋር የተኳረፈ መንግስት፣ ህዝብን በአሜሪካ ጠመንጃና የስለላ ቴክኖሎጂ እየቀጠቀጠና እያፈነ ከመኖር ውጭ አማራጭ አይኖረውም።

የነስብሃት መፈታት ከአሜሪካ በኩል ከመጣ የአቋም ለውጥ ከሆነ ዶ/ር አብይ በሰዎቹ መፈታት እናስጠብቃለን ያለውን፣ የኢትዮጵያን ብሄራዊ ጥቅም፣ ሉአላዊነትና ብሄራዊ ደህንነት የሚያስጠብቅ አይሆንም። በዶ/ር አብይና በደጋፊዎቹ ዙሪያ የሚሰጡ መግለጫዎች ይህን ከሰይጣን ጋር የሚደረግ ዳንስና መዘዙን በሚገባ አጢነውታል ወይ የሚል ጥያቄ ጭሮብኛል። አሜሪካ ለኢትዮጵያ መንግስት የፈለገችውን መልካም ነገር ቃል ብትገባም ከአሜሪካ ለሚገኙ ድጋፎች በሚል እነስብሃትን ወደ መፍታት ተኪዶ ከሆነ ውጤቱ ዶ/አብይ የሚወደውን ተረት ልዋስና “በሬ ሆይ ሳሩን አየህና ገደሉን ሳታይ” ይሆናል። ከሰይጣን ጋር እስክስታ መጨረሻው ስቅስቅታ ይሆናል ባይ ነኝ።
2) ጦርነቱ ዞሮ ዞሮ የፖለቲካ መቋጫ ያስፈልገዋል ከሚል እምነት ለፖለቲካ መቋጫው የእርቅ፣ የድርድር፣ የውይይፈት፣
በሚቀጥለው ክፍል በዚህ ርእስ ዙሪያ ያለኝን እይታ ይዤ እቀርባለሁ። ይቀጥላል።


Andargachew Tsege
January 28 2022


https://www.facebook.com/AndargachewTs/ ... 0404732573

በችግሮች የተሞላውን የነስብሃት ነጋ አፈታት በተመለከተ፣ ክፍል 2

የነስብሃት ነጋ መፈታታ ለጦርነቱ የፖለቲካ መቋጫ ለማግኘት ከሆነስ?

ይህን ጉዳይ በሁለት ከፍሎ ማየቱ የተሻለ ነው። ከአሜሪካ መንግስት ፍላጎትና ከኢትዮጵያ መንግስት ፍላጎት አንጻር።

1) በአሜሪካኖች የሚገፋ የፖለቲካ መቋጫ

በተደጋጋሚ የሰማነው ነው። አሜሪካኖች እና ምእራባውያን በወያኔ ጀማሪነት ከኢትዮጵያ መንግስት ጋር የተከሰተው ግጭት ወታደራዊ ሳይሆን ፖለቲካዊ መፍትሄ ያስፈልገዋል ሲሉን ነበር። የምእራባውያን ሚድያዎችም ይህንኑ ሲያስተጋቡ ነበር። ይህን ይበሉ እንጂ ለዚህ አቋማቸው መነሻው “ማናቸውም ግጭቶች መጨረሻቸው ፖለቲካዊ ነው” የሚል መርህ አልነበረም። “የፖለቲካ መፍትሄ ያስፈልጋል” የሚለው ሃሳባቸውን በቋሚነት የሚገፉት አልነበረም።

ወያኔ ጉልበቱ አይሎ አዲስ አበባ የሚገባ መስሎ ሲታያቸው የኢትዮጵያን መንግስት የሚተካ ሌላ መንግስት ሲያዘጋጁ ነበር። በዛን ወቅት “ተደራደሩ” የሚል ሃሳብ ጠፍቶ ነበር። “ወያኔን የሚይስቆመው ሃይል የለም። የወያኔ ወታደሮችና መሪዎች ጀግኞች ናቸው። አትችሏቸውም።” በማለት ሌሎች ኢትዮጵያውያን እጃቸውን ለወያኔ እንዲሰጡ የፕሮፓጋንዳ ስራ ሲሰሩ ነበር። ዶ/ር አብይ እንደነገረንም “ተደራደር ሳይሆን ሃገር ለቀህ ብትወጣ” የሚል ምክር ይለግሱት እንደነበር ነው።

የአሜሪካና የምእራባውያን አቋም ወደ ተደራደሩ የሚያደላው ሁሌም የኢትዮጵያ መንግስት ጉልበት አይሎ ሲያዩት ነበር። ወያኔ የሚሸነፍ ሲመስላቸው መንግስት ከወያኔ ጋር እንዲደራደር ሃሳብ ያቀርባሉ፤ ጫና ይፈጥራሉ። የዚህ ግፊት አላማ በድርድር በሚፈጠረው መንግስት ውስጥ ወያኔን ቦታ እንዲኖረው በማድረግ የተላላኪነት ስራውን እንዲቀጥል ማስቻል ነው።

አሁንም በቅርቡ አሜሪካኖች ለኢትዮጵያ መንግስት እያሳዩት ካለው መለሳለስ ጋር በወያኔ ላይ የያዙትን አቋም በእርግጠኛነት ባናውቅም ወያኔ ላይ ተጽእኖ አድርገው ወደ ድርድር እንዲመጣ የሚፈልጉ ይመስላል። የነስብሃት መፈታት የአሜሪካ መንግስት “ወያኔንና የኢትዮጵያን መንግስት ለማደራደር ምቹ ሁኔታ ይፈጥርልናል” በማለት ባቀረበው ጥያቄ መሰረት የተፈጸመላቸው ሊሆን ይችላል የሚል ግምት መረን የለቀቀ ሊሆን አይችልም።

እዚህ ላይ ማንሳት የሚገባን ጉዳይ ሁኔታዎች ቢመቻቹ እውን የኢትዮጵያ መንግስት ከወያኔ ጋር ለመደራደር ወስኗል ወይ? የሚለው ነው። ለመደራደር ከወሰነ ለመሆኑ የመደራደሪያ ነጥቦቹ ምን ሊሆኑ ነው? ከወያኔ ጋር በመደራደር እውን በኢትዮጵያ ምድር ሰላም ይሰፍናል ወይ? ለእነዚህ ጥያቄዎች አጥጋቢ መልስ ማንም የሚሰጠን አልሆነም። የአሜሪካኖች አቋም ግን ግልጽ ነው። ወያኔን የስልጣን ተጋሪ በማድረግ በጉልበት ማስወገድ ያልቻሉትን የአብይን መንግስት፣ ወያኔን ጉያው ውስጥ ጨመረው ማዳከም ነው። በወታደራዊ ጉልበት የአብይን መንግስት መጣል ካልተቻለ ሌላው ቢቀር የእነሱ ጥቅም አስከባሪ የሆነ ሃይል ከኢትዮጵያ የፖለቲካ መድረክ እንዳይጠፋ ማድረግ ነው።

ብዙዎቻችን ምን እየተካሄደ እንደሆነ አናውቅም። የሚያውቁ የሚመስሉንም የመንግስት ባለስልጣናት አናውቅም እያሉን ነው። ስለዚህ በበኩሌ ይህን ጽሁፍ የምጽፈው በግምት ነው። በክፍል 1 በግምት የጻፍኳቸው ጉዳዮች፣ በተለይ አሜሪካኖች ኢትዮጵያን ለመደለል ብዙ እርቀት ሊሄዱ ይችላሉ ያልኩት ጉዳይ ትክክል ሆኖ ተገኝቷል። በዚያ ግምት ላይ ተመስርቼ ከአሜሪካ ለሚገኝ ማናቸውም እርጥባን ሲባል የሚወሰዱ አቋሞች በደንብ እንዲመረመሩ ለመንግስት ባለስልጣናት ማሳሰቢያ ለመስጠት ተገድጃለሁ። ይህን የማደርገው እንዲህ አይነት ጉዳዮች በጥልቀት የሚፈተሹበት፣ ከፍተኛ ልምድና እውቀት ያላቸው ግለሰቦች የተካተቱበት መንግስትን የሚያማክር የፖለቲካ ካዎንስል በሃገራችን መኖሩን በመጠራጠሬ ነው። ወይም እንደነዚህ አይነት ጉዳዮችን በሚገባ የሚያጤኑና የሚመረምሩ መንግስታዊና መንግስታዊ ያልሆኑ የጥናት እና የምርምር ተቋማት በሃገራችን አለመኖራቸው ነው። ከሁሉም በላይ “መንግስታዊ ስልጣን ላይ ያሉትን አካላት ይጠቅማል” ከሚል እሳቤ ነው።

ከዚህ ተነስቼ አሁንም አሜሪካኖች ለኢትዮጵያ የወገኑ መስለው የኢትዮጵያ መንግስት ከወያኔ ጋር እንዲደራደር የሚሰሩት ስራ ካለ የኢትዮጵያ መንግስት በደንብ ሊያስብበት ይገባል። የኢትዮጵያ ህዝብም ይህን ጉዳይ ነቅቶ መከታተል አለበት። እኔ የመንግስት ባለስልጣን አይደለሁም። ከአሜሪካን መንግስት በህዝብ ስም በሚሰበሰብ እርዳታ መንግስታዊ ያልሆኑ ድርጅት በኢትዮጵያ ውስጥ ከፈቼ መኖሪያዬ አላደረግሁም። ወይም “በአሜሪካ መንግስት ጥቁር መዝገብ ውስጥ መግባት ዋጋ ያስከፍለኛል” የሚል ስጋት የለብኝም። ከዚህ በላይ የጠቅስኳቸው አካላት በየራሳቸው ምክንያቶች ስለአሜሪካን መንግስት ሴራና ደባ በፊት ለፊትና በድፍረት ለህዝብ መናገር አይችሉም። እንደኔ አይነቶቹ ሰዎች ግን የአሜሪካን መንግስት እኩይነት ደግመን ደጋጋመን ለህዝባችን መናገር ይገባናል።

አሜሪካኖች “ጦርነቱ የፖለቲካ መቋጫ ያስፈልገውል” ሲሉ ለኢትዮጵያ ህዝብ አዝነው አይደለም። የአሜሪካ መንግስት በኢትዮጵያ የፖለቲካ ሰውነት ውስጥ መርዝ ለመትከል የሚያደርገው ጥረት መሆኑን መገንዝብ ይገባል። ወያኔ እንደ ድርጅት የሚተርፍበት የኢትዮጵያ ፖለቲካ ምን ሊመስል እንደሚችል መገመት ከባድ አይሆንም።
ወያኔ እስካለ ከሰላሳ አመታት በላይ የዘለቀው የኢትዮጵያን ህዝብ በዘር ከፋፋሎ እርስበርሱ እንዲጠራጠር እንዲተላለቅ ያደረገው መሰሪ አስተሳሰብና ለዚህ አስተሳሰብ ህጋዊ ሽፋን የሰጠው ህገ መንግስት እንዲሁም መንግስታዊና አስተዳደራዊ መዋቅር የሚቀጥልበት ሁኔታ አይቀሬ ነው። ይህን የወያኔ አመለካከት ተሸክመው ጭፍን በሆነ የሃገር፣ የዘር፣ የእምነት ጥላቻ ለሚንቀሳቅሱ ወያኔን ለመሰሉ ሃይሎች ተጨማሪ ጉልበት ነው።

የወያኔ እድሜ መራዘም፣ በሃገራችን በወያኔ የተስፋፋው የሙስና እና የዘረፋ ባህል፤ ከወያኔም በኋላ በሚያስፈራ ደረጃ እየቀጠለ ያለው ይህ ነውረኛ ባህል የበለጠ ስር ሰዶ፣ ድህነት በኢትዮጵያ መድሃኒት ወደሌለው ካንሰር የሚያድግበትን ሁኔታ የሚፈጠር ነው። በሙስና በኑሮ ውድነት፣ በስራ አጥነት እየተጠበሰ አስካሁን በሃገሩ ተስፋ ያልቆረጠውን አዲስ ትውልድ ተስፋ የሚያስቆርጥ ነው። በኢትዮጵያ ህዝብ የነጻነት፣ የፍትህ፣ የእኩልነት፣ የአንድነትና የብልጽግና ተስፋ የሚቀብርና በመቃብሩ ሳጥን ላይ የሚመታ የመጨረሻው ሚስማር ነው።

ከዚህ በላይ ያልኩት እውን የሚሆነው የኢትዮጵያ መንግስት እሺ ብሎ፣ ወያኔም ተስማማቶ ድርድር የሚደረግ ከሆነ ነው። በእኔ እይታ፣ እስካሁን ከሆነውና በመንግስት ባላስልጣናት ከተሰጡ ማብራሪያዎችና ካዘጋጇቸው ሰነዶች ተነስቼ የኢትዮጵያ መንግስት ጦርነቱን በፖለቲካ ውሳኔ ለመቋጨት ሲል ለወያኔ ብዙ ነገሮችን አሳልፎ ሊሰጥ ይችላል የሚል ግምት አለኝ። እንዲህም ሆኖ ትልቁ ጥያቄ የኢትዮጵያ መንግስት ምን ነገሮች ለወያኔ ቢሰጥ ነው ወያኔዎች ማርካት የሚችለው?

ወያኔዎች ባላፉት 27 አመት ብቻ ሳይሆን ባለፉት 4 የለውጥ አመታታ በኢትዮጵያ ህዝብ ላይ የፈጸሙትን ወንጀል እንኳን ይቅር ቢባሉም ከዚህ በላይ ተሻግረው የሚያቀርቧቸውን ጥያቄዎች፣ ከድርድር የሚጠብቋቸው ውጤቶች የኢትዮጵያ መንግስት ፈጽሞ ሊያሟላቸው የሚችላቸው ናቸው ብዬ አላምንም። የወያኔን ጥያቄዎች በሙሉ መንግስት በድርድር ስም አሟላለሁ ብሎ ቢነሳ ለወያኔ እጅን ከመስጠት ልዩነት አይኖረውም። ይህ አካሄድ በሰፊው የኢትዮጵያ ህዝብ ዘነድ የሚቀሰቅሰውን ቁጣና ሁካታ መንግስት የሚያስቆመው አይሆንም። ይህን በማጤን የደርድሩ ጉዳይ ሳይወልድ የሞተ ነገር ይመስላል። ለምን ታዲያ እርቅ፣ ሰላምና ድርድር እንደሚቻል ተደርጎ በመንግስት አካላት ውዥንብር ይነዛል? ግጭቱን ለመቋጨት የሚያስችል ሌላ አማራጭ አላታያቸው ብሎ ይሆን?

2) ግጭቱን የፖለቲካ መቋጫ ለመስጠት በኢትዮጵያ መንግስት የተወስነ ውሳኔ ከሆነስ?

የነስብሃት ነጋን መፈታት አስመልክቶ ሰማይና ምድሩ እንዲዞርብን የሚያደርጉ የተለይያዩ በርካታ ማብራሪያዎች በመንግስት ተሰጥተዋል። ከእነዚህ መሃል አንዱ መንግስት ሰላማዊ የፖለቲካ መቋጫ ለግጭቱ መስጠት እንደሚፈልግ፣ የነስብሃት መፈታታም የዚህ የፖለቲካ ውሳኔ አካል እንደሆነ ነው። ይህ ጉዳይ የገና እለት በድንገት እንደቦንብ ለሁላችንም የፈነዳ ቢመስለንም የብልጽግና አባላት ፓርቲው ባሰናዳው ሰነድ አማካይነት ውይይት እንዳደረጉበት ተነግሮናል። ከዚህ በመነሳት “የነስብሃት ነጋን መፈታት እንደ ዱብ እዳ ማየት የለባችሁም” የሚል ማብራሪያ ተሰጥቶናል። ወደ ቁም ነገሩ ከመግባታችን በፊት በዚህ ነጥብ ላይ አንድ ነገር ማለት ይገባል።

የብልጽግና ፓርቲ አባላት ውይይት እንዲያደርጉበት ፓርቲው ያዘጋጀው ሰነድ ሚስጥራዊ ሰነድ አልነበረም። እንደ እውነቱ ከሆነ ሚስጥር እንደማይሆን እየታወቀ አንዳንድ በሰነዱ ውስጥ መካተት የማይገባቸው ጉዳዮች መካተታቸው ተገቢ አልነበረም። ይህ ሰነድ በወያኔ እጅ የገባ ሰነድ ነው። በሲ አይ ኤ፣ በአሜሪካን ስቴት ዲፓርትመንት እጅ የገባ ሰነድ ነው። የኢትዮጵያ ጠላቶችም ሆኑ ወዳጆች ከአማርኛ ቋንቋ ወደራሳቸው ቋንቋ አስተርጉመው የያዙት ሰነድ ነው። አብዛኛው የሰነዱ ክፍል ለጠላት የሚሰጠው መረጃ ባይኖርም በጣም ጥቂት የሆኑ ነጥቦች ግን የመንግስትን አስተሳሰብና አካሄድ እንዲሁም አቅም ጭምር በማመላከት ለጠላት እቅድ በግብአትነት ሊያገልግሉ የሚችሉ ናቸው። ይህንና ሌሎችንም ጉዳዮች ስናጤን ሰንዱ የበቂ ምክክር ውጤት አለመሆኑን መገንዝብ እንችላለን።

ይህን ሰንድ እንደወያኔ እና እንደ ሲ አይ ኤ፣ ከብልጽግና ፓርቲ አባላት እኩል እኛም አግኝተን አይተነዋል። እንደ መንግስት የሁሉም ስብሰባዎች ሪፖርት ባይደረሰንም በተለያዩ ቦታዎች ላይ የነበሩ የተወሰኑ ውይይት ሪፖርቶች ለእኛም ደርሰውናል። ውይይቱ “ግጭቱን በሰላም መቋጨት” ከሚለው ጥቅል አጀንዳ በታች ወርዶ ከወያኔ ጋር መወያየት” የሚል እንደምታ ይዞ ሲመጣ ተሰብሳቢዎች ተቃውሟቸውን እንደገለጡ ሰምተናል። አንዳንድ ስብሰባዎች ሳይቋጩ መበተናቸውንም መገንዘብ ችለናል። ሰነዱ ዝርርዝ ከሆነ የሰላም አስፈላጊነትና ከጠላት ጋር ተደራድሮ ግጭትን በሰላም መቋጨት በላይ ተሻግሮ ስለ እስረኞች መፈታታ፣ የግለሰቦችን ሰም ማንሳቱ ቀርቶ፣ በጥቅሉም እንኳን ያቀረበው ነገር የለም።
የፓርቲ አባላቱ “ሰዎች እንደሚፈቱ አናውቅም ነበር” የሚሉትን ጉዳይ በሰነዱ ላይ ከሰፈረው የውይይት ነጥብ ተነስቶ እውነት መሆኑን ማረጋገጥ ይቻላል። ይህ ብቻ አይደለም ሰነዱ፣ የትግሉም፣ የመከራውም ተካፋይ፣ የተገኘውም ድል ባለቤት በሃገር ውስጥና በውጭ የሚኖረው መላው የሃገሪቱ ህዝብ እንደሆነ ይናገራል። ይህን ብሎ ግጭቱን ለመቋጨት መደረግ የሚገባውን የሰላምና የድርድር ጥረት ከብልጽግና ፓርቲ አባላትና ደጋፊዎች ጋር ብቻ ወስኖ አስቀርቶታል። ይህ ራሱን የቻለ ትልቅ ጥፋት ነው። ያስከተለውም መዘዝ ቀላል አይደለም።
ሰንዱ በፓዎር ፖይንት የተዘጋጀ ባለ 41 ገጽ ሰንድ ነው። አብዛኛው የስነዱ ክፍል ምንም እንከን የማይወጣለት ለአባላትም ይሁን ለመላው ማህበረሰብ ጭምር በተለያዩ ጉዳዮች ላይ ሰፊ ግንዛቤ የሚሰጥ ሰነድ ነው። በስፋት ተሰራጭቶ ቢሆን። ከዛም አልፎ የሃገራችንን ጠላቶች ምንነት፣ የጦርነት አስከፊነትና የሰላምና መረጋጋት እጦት የብልጽግና ጸር መሆን፣ እርቅና ድርድር እየመረረንም እንኳን ቢሆን ተቀብለን፣ ጦርነትን አቁሞ ፊትን ወደሃገር ግንባታ ማዞር ለምን እንደሚያስፈልግ በሚገባ ያስረዳል። እነዚህ ሁሉ ነጥቦች ችግር የሌለባቸው ናቸው። በሌላ በኩል ግን ሰነዱ ሰላምና ድርድርን የተሳካ ለማድረግ ግጭትን ለማስቀረት በአንድ ወገን ፍላጎት ብቻ የሚሳካ እንዳልሆነ ይዘረዝራል። ሰነዱ ይህን በተመለከተ ቃል በቃል እንዲህ ይላል።

“ሌላኛውም ግማሽ መንገድ እስካልመጣ፣ ይልቁኑም ተቃራኒውን መንገድ ከመረጠ ያኔ ግጭት አይቀሬ ይሆናል። ሰላም በአንድ ወገን ፈቃድ ላይ ብቻ የሚመሰረት አይደለምና። ሰላም የሁለት አካላትን ፍላጎት የሚሻ፣ የሁለት አካላትን ተሳትፎ የሚፈልግ ነው። ሰላም ወዳድ በመሆንና ጦርነትን በመሸሽ ግጭት ከሕይወታችን ውስጥ ይሰረዛል ማለት ዘበትም ሞኝነትም ነው።"

ይህ ነጥብ አጠቃላይ ሃቅን ያስቀመጠ ቢመስልም፣ ወያኔ የሰላም አጋር መሆን እንደማይችል በመጠርጠር የተጻፈ ይመስላል። ይህን ምልከታ ትክክል እንደሆነ የሚያሳየው ነጥብ በሚቀጥሉት መስመሮች ተጽፎ እናገኘዋለን።

ሰነዱ ከግጭቱ በፊት ወደነበሩ ሰላማዊ ወቅቶች በመመለስ ይጀመራል፤

“የለውጡ ኃይል ወደ ስልጣን ሲመጣ አንግቦ የተነሣው ከቀደመው ‹የጉልበት ሰይፍ› የተሻለውን ሰላማዊ የ‹ሰይፍ› መንገድ ነበር።መርሑም ‹በፍቅር እንደመር፣ በይቅርታ እንሻገር› የሚል ነበር በዚህ መርሕም ያለፈውን የፖለቲካ ታሪካችንን በይቅርታ ዘግተን አዲስ የፖለቲካ ምዕራፍን በፍቅር ለመጀመር ተነሣሽነትን ተወስዷል።” ይለናል።

ከዚህ በተጨማሪ ሰነዱ የወያኔን ወቅታዊ የአስተሳስብ ቅላጼ ሲገመግምና መጭውን አስቸጋሪ ወቅት ሲያመላክት እንዲህ ይለናል።

“ሽብርተኛው ህወሓት ባገኘው አጋጣሚ ሁሉ ጸብ አጫሪነቱንና እብሪቱን ማሳየቱ አይቀርም፡፡ ከቻለም ለዳግም ወረራ ራሱን ያዘጋጃል፡፡ስለሆነም ከህወሓት ጋር የሚኖረው ቀጣይ ትግል ዘርፈ ብዙ እና በአጭር ጊዜ የሚቋጭ ላይሆን እንደሚችል መገመት ያስፈልጋል፡፡ስለሆነም የሀገር መከላከያ ሰራዊትን አደረጃጀትና ሁለንተናዊ አቅም የበለጠ ማጠናከር ይገባል፡፡” ይለናል።

እንዲህ አይነት ከነባራዊ ሁኔታ ጋር የተጣጣመ እይታዎች የያዘ ሰነድ ወደ ዋናው የውይይቱ ርእስ ሲገባ ለሰላምና ለድርድር የሚሰጣቸው ምክንያቶች አንዳቸውም ከወያኔ ባህሪ ጋር የሚያያዙ ሆነው ግን አናገኛቸውም ።

በ4.4. ላይ ጦርነቱን በውይይት ማጠናቀቅ በሚለው ርእስ ስር የምናነበው አብዛኛው ነገር፣ ጦርነት ጉዳት ያለው መሆኑን፣ የልማትና የብልጽግና ጸር መሆኑን፣ ጦርነት አቁሞ ጠንካራ ኢኮኖሚ በመገንባት ከወጭ ተጽእኖ መላቀቅን የሚያመላክት ነው። ጦርነቱን ለማቆም ሃገራዊ ምክንያቶች ከደረደረ በኋላ ግን አስገራሚው ነጥብ፣ “ስለሆነም” በሚል ማስተሳስሪያ የሚጀምረው አረፍተ ነገር ነው። “ስለሆነም ለሰላም ያለንን ቁርጠኝነት በተግባር ለአለም ማሳየት አለብን።” ይላል።
ቀጥሎም “ተገደን የገባንበትን ጦርነት ለመቋጨት ወደ ሰላማዊ ውይይት መግባት ይኖርብናል፡፡ ይህንን በማድረጋችን አሰፍስፈው ሊውጡን የተዘጋጁ የውጭ ኃይሎችን ማለዘብም ማሸነፍም እንችላለን፡፡” ይላል።

እነዚህ ሁለት ተያያዥነት ያላቸው አረፍተነገሮች ጦርነቱን አቁመን ወደ ሰላማዊ ድርድር የምንገባው የውጭ ሃይሎችን ፍላጎትና ጫና ለማርካት እንጂ “እውን ከወያኔ ጋር ሰላም የመፍጠር እድላችን ሊሳካ ይችላል” ከሚል ግምገማ እንዳልሆነ የሚያሳዩ ናቸው። ቀደም ብሎ ሰነዱ ወያኔ ከለውጥ መባቻ ጀመሮ የቀረበለትን የሰላም የፍቅር መንገድ የረገጠ መሆኑ ግልጽ አድርጓል።አሁንም ለሰላም ሲባል ከትግራይ ድንበር ላይ የመከላከያ ሰራዊቱ ቢቆምም ወያኔ ውጊያ የማያቆም፣ ውጊያ ስለማቆም ከኢትዮጵያ መንግስት የተወሰነውን ውሳኔ ለጦርነት የሚዘጋጅበት ግዜ አድርጎ እንደሚጠቀምበት ይገልጻል። ሰንዱ የተነበየው እውነት ሆኗል። ወያኔ ከአፋር ክልል ተቀጥቅጦ ከወጣ በኋላ ራሱን አደራጅቶ የአፋር ክልልን ወሯል። የአማራ ክልልን ለመውረር በቂ ዝግጅት እያደረገ ነው።

በዚህ የሰነዱ ክፍል የቀረቡ ነጥቦች፣ በወያኔ ላይ የመረረ ጥላቻ ያላቸውን አባላት ለማሳመን የቀረቡ ይመስላሉ። ከዛም ተሻግሮ ጦርነቱን በሰላም መቋጨት በአለም አቀፍ ማህበረሰቡ ፊት ለሚኖረን የመልካም ገጽታ ግንባታ የሚጠቅም እንደሆነ ይገልጻል። በጣም የሚገርመው ጦርነቱን ከጀረባ ሆነው የሚዘውሩት ረጃጃም የቅርብና የሩቅ እጆች አጀንዳ ምን እንደሆነ ጠንቅቀን ስለምንረዳ በውይይት ማጠናቀቅ ተገቢ ይሆናል። ይህ የሰንዱ ወሳኝ ክፍል ከላይ ስለወያኔ ምንነት ግልጽ በሆነ መንገድ የተቀመጡትን ነጥቦች ወደ ጎን አስቀመጦ ጦርነቱን በሰላም ለመቋጨት ምክንያት ያላቸውን የተግበሰበሱ ነጥቦች በአንድ ላይ አምቆ ይዞ መጥቷል። ምክንያቶቹ አራምባና ቆቦ የሚረግጡ፣ ጥቅል ከሆኑ የግጭት አፈታት አስተያየቶች ተነስቶ ወደሚገርሙ በሃገር ውስጥና ከሀገር ውጭ ካሉ ጉዳዮች ተሳስሮ ተደምድሟል። አንባቢ በውል እንዲረዳው ይህን ክፍል እንዳለ አቀርበዋለሁ።
“ጦርነቱን በውይይት ማጠናቀቅ በየትኛውም አለም ጦርነትን በውይይት መፍታት የተለመደ እንጂ አዲስ ነገር አይደለም፡፡ እንኳንስ የተባበሩት መንግስታትና የአፍሪካ ህብረት መስራች አባላት ሆነን ይቅርና ባንሆንም ጦርነትን በውይይት መፍታት አለምአቀፍ መርሆ ነው፡፡ ይኸ ማለት የሚቆረቁር፣ የሚያም፣የሚጎረብጥ ነገር የለም ማለት አይደለም፡፡
ምንም ይሁን ምን በአለምአቀፍ አደባባይ ሞጋችና አሸናፊ እንጂ ጠላቶቻችን እንደሚከሱን ጦር ነት አፍቃሪ ሆነን መገኘት የለብንም፡፡ ስለሆነም ጥቅሞቻችንን ከማስከበር መለስ ለውይይት መቀመጥ ብልህነት ነው፡፡ የቀጠለ ጦርነቱን በውይይት ማጠናቀቅ በሰሜኑ የሀገራችን ክፍል የተቀሰቀሰው ጦርነት በመንስኤውም ሆነ በፈጠረው የሰው ሕይወት፣ የንብረትና የሀገር ገጽታ ጥፋት ያስከተለውን ሀገራዊ ጉዳት በቃላት ለመግለጽ ያስቸግራል። ጉዳዩን ከሁሉም በላይ መራራ የሚያደርገው ደግሞ ጦርነቱ የጥቂት ግለሰቦችንና የወንጀለኛ ቡድኑን ህልውና ፈቃድ ለማሳካት ተብሎ የተጀመረ መሆኑ ነው። ሆኖም በሂደት የብሔር መልክ እየያዘ መሄዱ ጉዳዩ ከተገመተው በላይ ስፋትና ጥልቀት እንዲኖረው አድርጓል። ከዚህም በተጨማሪ ጦርነቱን ከጀርባ ሆነው የሚዘውሩት ረጃጅም የቅርብና የሩቅ እጆች አጀንዳ ምን እንደሆነ ጠንቅቀን ስለምንረዳ በውይይት ማጠናቀቅ ተገቢ ይሆናል”
ቀጥሎ በሰነዱ ማጠቃለያ የቀርበውን እንመልከት

“ለግጭቱ እልባት መፈለግ ኃላፊነት ከሚሰማው መንግስት የሚጠበቅ ዋነኛ ጉዳይ ነው። በርግጥ የግጭቱ ጠንሳሾች ብዙ የሰላም ዕድሎችን በማምከን የተካኑ ናቸው። ታሪክ አበክሮ የሚነግረን ነገር ቢኖር ብዙዎቹ ግጭቶች ዘላቂ እልባት የሚያገኙት በንግግር፣በድርድርና በስምምነት ነው። ተጠቂውም ምላሹን በኃይል ይመልሳል።ግጭቱም ቢሆን ያወደመውን ንብረት አውድሞ፣የቀጠፈውን ሕይወት ቀጥፎ፣የኋላኋላ መጠናቀቁ አይቀርም። ልዩነቶች በውይይት መጠናቀቅ ሳይችሉ ሲቀሩና ፍላጎትን በሰላማዊ መንገድ ማሳካት ሲያቅት፣ሀገር ከሀገር፤ቡድን ከቡድን ደም አፋሳሽ ግጭት ውስጥ ይገባሉ። ዓለማችን ለብዙዎች እልቂት የዳረጉ ግጭቶችን አስተናግዳለች።

በመንግስት ደረጃ ስለነስብሃት ነጋ መፈታታ እስካሁን ከተሰጡን ምክንያቶች የተሻለ መረጃ የምናገኘው ከዚህ ሰንድ ነው። የቀናትን ቅደም ተከተል ተከትለን የሆነውን ካየነው ይህ ሰንድ ከአሜሪካኖች የአቋም ለውጥ በፊት የተጻፈ ነው። ጸሃፊው የወያኔን ደጋፊዎች እነአሜሪካንን በአንድ አይኑ እያየ እንደሆነ ነው። አሜሪካና ምእራባውያን በኢትዮጵያ ላይ የያዙትን አቋም እንዲያለዝቡ ከማሰብ ጭምር ነው።

በዚህ መንገድ ካየነው አሜሪካኖች ወደ ኢትዮጵያ ከረሜላቸውን ይዘው ይቅረቡ እንጂ ከወያኔ ጋር መደራደር የሚለውን ሃሳብ የውጭ ሃሎችን ለማለዘብ በማሰብ የቀረበው በኢትዮጵያ መንግስት እንደሆነ ነው። “ለውጭ ሃይሎች አልተንበረከክንም የተነበረከኩት እነሱ ናቸው” የሚለውን የመንግስት አባባል እንደገና እንድንፈትሽ የሚያደርግ ነው።
በጦር ሜዳ የወያኔ መሸነፍና የኢትዮጵያ መንግስት እንዲህ አይነት የሰላምና የእርቅ ሃሳብ ይዞ መውጣቱ አሜሪካ ከረሜላዋን ይዛ ወደ ኢትዮጵያ መንግስት ለመጠጋቷ ዋናው ምክንያት ነው። ኽርማን ኮን ሳይቀር “ወያኔ በወታደራዊ ጉልበት የኢትዮጵያን መንግስት መግደርደር አይችልም። መሪዎቹ ያላቸው ምርጫ ህወሃትን አፍርሰው ስደት መሄድ ነው” ብሏል። ይህ አቋሙ ከጥቂት ወራት በፊት ከነበረው አቋሙ 180 ዲግሪ የተቀየረ ነው። ይህ የአቋም ለውጥ የግለሰብ ብቻ አይደለም። የአሜሪካ ፖሊሲ መቀየሩን የሚያሳይ ነው። እንደገመትነውም በ27/1/2022 ከኢትዮጵያ ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የወጣው መግለጫ አሜሪካ ኢትዮጵያን ስትራተጂክ አጋሯ አድርጋ እንደምታይ ከኢትዮጵያ ጋር ያላት ግንኙነት ወደ ቀድሞው ስትራተጂክ ግንኙነት እየተመለሰ እንደሆነ፣ እርዳታ ለማቅረብ፣ ጦርነት ያፈረሳቸውን ከባቢዎች ለመገንባት ነዋይ እንደምታፈስ አዲሱ የአሜሪካ መልእክተኛ እንደተናገሩ ነው። ባለፈው ጽሁፌ እኔም ከዚህ የተለየ ነገር አልጻፍኩም። አሜሪካ ትናንና ኢትዮጵያን ለማፍረስ ቆርጦ ለተነሳ ወገን አግዛ ቆማ እንደነበር ማስታውስ ያስፈልጋል።
እየዋለ እያደረ የታዘብነው “እነስብሃት ነጋን መፍታትና ከወያኔ ጋር ድርድር ማድረግ” የሚለው ውሳኔ የተለያዩ ምክንያቶችና ግፊቶች ውጤት እንደሆነ ነው። በዚህ ጽሁፍ አሁንም መልሰን መላልሰን ማንሳት የሚገባን ጉዳይ እነስበሃት ነጋን መፍታት የሚለው ጉዳይ መጀመሪያ በማን ተቀነቀነ የሚለው እንዳልሆነ ነው። የመፈታቱ ሆነ የመደራደሩ ጉዳይ ከአሜሪካኖች የመጣ ከሆነ ምን ያህል ኢትዮጵያን የሚጎዳ እንደሆነ በዝርዝር ለማሳየት ሞክሬያለሁ። ያለማንም ተጽእኖ በመንግስት በራሱ የተቀነቀነ ሃሳብ ከሆነም ስለጉዳዩ የምናነሳውን መሰረታዊ ጥያቄ አይቀይረውም። ትልቁ ጥያቄ ያለው ከወያኔ ጋር ድርድር ማድረግ ይቻላል ወይ? የሚደረግ ድርድር ሃገርና ህዝብን ይጠቅማል ወይ? የሚል ነው።
ከላይ እንደተመለከትነው የብልጽግና ሰነድ “ወያኔ ሰላም እርቅ ድርድር የሚባል ነገር የማይገባው ነው። ለሰላም እድል ለመስጠት ጦርነት ስናቆም ወያኔ ፋታውን ለጦርነት መዘጋጃ ያደርጋዋል” በማለት በግልጽ ይናገራል። ታዲያ እንዴት ሆኖ ነው እነስብሃት ስለተፈቱ ጦርነት አቁሞ ወያኔ ወደ ድርድር የሚመጣው? ከነስብሃት መፈታታ በኋላ ወያኔ አፋርን ወሯል። ከአማራ ክልል ጠቅልሎ አልወጣም። በአማራ ክልል ላይ ተጨማሪ ወረራ ለማድረግ እየተዘጋጀ ነው። በበኩሌ እነዚህ ጭብጦች የሚያሳዩት በስሜት የምንነዳው የነስብሃትን መፈታት የተቃወመው ስፊ ህዝብ ሳይሆን የወያኔን ምንነት በግልጽ እያስቀመጠ፣ “ለሰላም ለድርድር የሚመች ባህሪ የሌላቸው ናቸው” እያለ ጦርነት እንዲቆም ካለው ቀና ፍላጎት ብቻ በመነሳት ወያኔ ለሰላምና ለድርድር የሚጠራው መንግስት ነው።

የብልጽግና ፓርቲ ስለግጭት አፈታት አለም አቀፍ ተመክሮ በሰነዱ ላይ ያስቀመጠው እንዳለ ሆኖ ግጭትን በሰላማዊ መንገድ መፍታት ስለማይቻልባቸው ሁኔታዎች በአለም አቀፍ ደረጃ የተደረጉ ጥናቶችን ሰነዱ አያካትትም። ለምን ይህ እንዳልተደረገ አላውቅም። ሆኖም ግን በአለም ላይ ብዙ ግጭቶች ሰላማዊ በሆነ ድርድር የተቋጩትን ያህል በጦርነትም የተቋጩ አሉ።37 አመታታ የፈጀው የሲሪላንካ መንግስትና የታሚል ታይገሮች ግጭት የተጠናቀቀው በጦርነት ነው። የአለም አቀፍ ተመክሮ የሚያሳየው በሰላማዊ ድርድር የሚፈቱ ግጭቶች ሁሌም ግጭት ወስጥ ከገቡት ሃይሎች ምንነት ጋር የተሳሰረ ነው። ግጭት የቀሰቀሰው ጉዳይ በምክንያት የተመሰረተ እስከሆነ ድረስ በምክንያት ላይ ተመስርቶ ግጭትን በደርድር መፍታት የሚቻልባቸው እድሎች አሉ።

ነገር ግን ወደ ግጭት የገባው አካል ተጨባጭ ግብ የሌለው፣ ለራሱ ምድራዊ ወይም ሰማያዊ ተልእኮ የሰጠ ከሆነ፣ ከእንዲህ አይነቱ ሃይል ጋር ድርድር አይቻልም። “በሙስናና በግፍ የተጨማለቀውን የኢምፔሪያሊስቶች አለም በሽብር እናጸዳዋለን” የሚል ግብ ከነበራቸው የጣሊያን እና የጀርመን እንዲሁም የሌሎችም አገሮች የቀይ ብርጌድ ድርጅቶች ጋር ድርድር ማድረግ አይቻልም ነበር። ለድርድር የሚቀርብ ነገር ስላልነበራቸው። በተመሳሳይም እምነትን መሰረት ካደረጉ፣ ከእምነት ጋር በተያያዘ ሽብር ውስጥ ከገቡ እንደ አልቃይዳ አይነት ድርጅቶች ጋርም ድርድርና እርቅ ማድረግ አይቻልም። የመደራደሪያ መነሻ የሚሆን ምክንያት ስለማይኖር።
ከዚህ ውጭ ዘረኝነትን ዋንኛ የመደራጃ ርእዮእተ አለም አድርገው ከተነሱ የጀርመኑ ናዚ መሰል መንግስታት ጋር ሰላምና እርቅ የሚባል ነገር አይቻልም። ከእንዲህ አይነቶቹ አካላት ጋር የሚጀመር ግጭት የሚያልቀው በጦርነት፣ በመሸናነፍ ነው። ትልቁ ጥያቄ ያለው ወያኔ በየትኛው ምድብ የሚፈረጅ ድርጅት ነው? የሚለው ነው። ወያኔ ለ27 አመታታ በኢትዮጵያ ህዝብ ላይ የፈጸመውን ግፍና ዘረፋና እንዲሁም ባላፈው አመት ወያኔ በአማራና በአፋር ክልል ያኪያሄደውን የሽብር ስራ ከተመለከትን ዘረኛነትን መሰረት ያደረገ ንበር። ለሌሎች ዘሮች ካለው ጥላቻና ንቀት የሚመነጭ እንደሆነ ነው። የወያኔ የግጭት አላማ በግጭቱ ለሚገኝ የተወሰነ ግብ ሳይሆን በፍጹም ጠቅላይነት ወይም በፍጹም አውዳሚነት የተቃኘ ነው።

መንግስትም “ወያኔ፣ እርቅ ፍቅር መቻቻል፣ ድርድር የማይገባው ድርጅት ነው” እያለን ነው። ሁላችም ያየነው የወያኔ ባህሪይ እና ድርጊት የሚጠቁመው ከወያኔ ጋር የሚደረገው ፍልሚያ ወያኔን በማጥፋት የማይጠናቀቅ ከሆነ ኢትዮጵያ ሉአላዊነቷ ክብሯና ጥቅሟ የማይከበር፣ ሰላም የሚባል ነገር እንደማይኖራት ነው። ይህን ማስፈጸም ሽህ ጊዜ ከባድ መስሎ ቢታይም ከዚህ ያነሰ የኢትዮጵያን ሉአላዊነት ክብርና ጥቅም እንዲሁም ሰላም የሚሰጥ አማራጭ የለም።

የሚታየን እውነተኛ መፍትሄው ከባድ ስለሆነ ብቻ፣ የማይሰራ መሆኑን እያወቅን ቀላል መትሄ መመኘት በልብ ወለድ ድርሰት ወስጥ እንጂ በእውነተኛው የፖለቲካ አለም ቦታ የለውም። ከእውነታ የራቀ የቀላል መፍትሄ መሻት ከባዱን መፍትሄ ተግባራዊ ለማድረግ ከምንከፍለው መስዋእትነት በላይ የከፋ መስዋእትነት ያስከፍለናል።

በእዚህ መንገድ ተጉዘን እስካሁን ብዙ ዋጋ ከፍለናል። ወያኔዎች በይቅርታ በፍቅር እንሻገር ሲባሉ፣ በጥላቻ የሃገር መከላከያ ሰራዊት አርደው ጦርነት ከፈተው ሰቆቃ ፈጽመው ማንነታቸውን አሳዩን። ለጥሞናና ለገበሬዎቻቸው የማረስ እድል ለመስጠት ከትግራይ የመከላከያ ሰራዊት እንዲወጣ ሲደረግ አማራና አፋርን ወረው ግፍ ውርደትና ውድመት ፈጽመው አሳዩን። “ከአፋርና ከአማራ ክልል እናስወጣቸዋለን ነገር ግን ትግራይ አንገባም። ይህ ድርጊታችን ወያኔዎችን ወደ ቀልባቸው ተመልሰው ሌላው ቢቀር በትግራይ ህዝብ ላይ ያደረሱትን መከራ እንዲፈትሹና ስለሰላም እንዲያስቡ ያደርጋቸዋል ተባልን። ይህ ውሳኔያችን ለወያኔዎች ሌላ ዙር ወረራ የመፈጸም አቅም ያደራጁበትን እድል ሰጣቸው እንጂ ወደ ሰላም አላመጣቸውም።

የወያኔ ምንነት፣ በባህርይ ሆነ በተግባር የተገለጸው ምንነቱ፣ ወያኔን የተከፈለውን መስዋእትነት ከፍለን ወያኔን እንደ ድርጅት ከመቅበር ውጭ ሌላ አማራጭ እንደሌለን ነው። አይን ያፈጠጠው ሃቅ ይህ ነው። አዎን ጦርነቱ በመራዘሙ በፍጥነት ፊታችን ወደ ልማት ማዞር አንችልም። ጦርነቱ በመራዘሙ የሚከፈለው ሰብአዊና ቁሳዊ ዋጋ ትልቅ ነው። ሆኖም የሰላሙ አማራጭ የማይሰራ ከሆነ ምን ማድረግ ይቻላል። የሰላሙ አማራጭ የአሜሪካ ተላላኪ የሚያደርገን ከሆነ፣ የሰላሙ አማራጭ ለወያኔ ልንሰጠው የማንችለውንና የማይገባንን ገጸ በረከት እንድንሰጥ በማድረግ ወሳጣዊ አንድነታችንን አናግቶ ቀውስ ውስጥ የሚጨመረን እና ለከፋ ኪሳራ የሚዳርገን ከሆነ ድርድር ቢቀርብን ይሻላል።
በፖለቲካ ህይወት ውስጥ የከባድ ምርጫዎች ሰአት የሚባሉ ወቅቶች አሉ። የኢትዮጵያ መሪዎች በዚህ አይነቱ የከባድ ምርጫዎች ወቅቶች ውስጥ ይገኛሉ። የሚመርጡት ምርጫ የሃገርና የህዝብ ህልወናን አደጋ ላይ የሚጥል ወይም የሚታደግ ሊሆን ይችላል። ባላንበት ወቅት የወያኔን ምንነት እያወቁ፣ የአሜሪካንና የምእራባውያንን ምንነት እየታወቀ ወያኔ ለሰላማዊ የድርድር ሂደት ራሱን ክፍት ሊያደርግ ይችላል በሚል ቀቢጸ ተስፋ መዋተት ትልቅ ስህተት ነው።

ለማጠቃለል፣ በጽሁፌ መጀመሪያ ለነስብሃት መፈታታ ምክንያት ሊሆኑ ይችላሉ ብዬ ካስቀመጥኳቸው አራት ምክንያቶች ውስጥ ሁለቱን ሰፋ አድርጌ ተመልክቻቼዋለሁ። የቀሩት ሁለቱን በአጭሩ በመዳሰስ ጽሁፌን አጠቃልላለሁ። ሁለቱም ምክንያቶች ከተለያዩ የመንግስት ባላስልጣናትና ከራሱ ከዶ/ር አብይ አስተያየቶች ያገኘናቸው እንጂ እኛ የፈጠርናቸው አይደሉም። የመጀመሪያው የነስብሃትን መፈታታ በወያኔ ካምፕ ውስጥ ልዩነቶች በመቀስቀስና ክፍፍል በመፍጠር ጦር ሰባቂውን ወገን ለማዳከም የሚለው ነው። የውሳኔውን ከባድነት ግምት ውስጥ በማስገባት “ይህ ከባድ ወሳኔ በዚህ ተልካሻ ምክንያት የተፈጸመ ነው” ብሎ ማመን ይቸግራል። ስለሆነም ይህ ነጥብ ብዙ ውይይት የሚያስፈለገው አይመስልም።

የመጨረሻው ነጥብ ውሳኔውን ከእምነት የመነጨ የእርቅና የምህረት ውሳኔ የሚያደርገው ነጥብ ነው። ከዶ/ር አብይ አንደበት የነስብሃት መፈታታ ፈጣሪ ካዘዘው ትእዛዝ ጋር የተገናኘ መሆኑ ተነግሮናል። በዚህ ጉዳይ ላይ ብዙ ማለት ቢቻልም በጥቅሉ አንድ መሰረታዊ ነገር ተናግሮ ማለፍ ያስፈልጋል። በኢትዮጵያ ውስጥ ሌላ አደገኛና አስፈሪ የሆነ የሀገራዊ ቀውስ ምክንያት መሆን የሚችል ጉዳይ ቢኖር የፖለቲካ አቋምን ከእምነት የመቀላቀል ጉዳይ ነው። አዎን ኢትዮጵያ የአማኞች አገር ናት። ከብዙ ጊዜ በኋላ ፈሪሃ እግዚአብሄር የሚሰማው መሪ ማግኘቷ በበጎ የሚታይ ነው። ቢሆንም፣ የትኛዎቹም የፖለቲካ መሪዎቿ የፖለቲካ ውሳኔያቸውን ከሚከተሉት እምነት ጋር አያይዘው የሚወስኑት ከሆነ ሁሉም እምነቱን እያጣቀሰ ለሚወስደው የተለያያ አቋም መመዘኛ የሆነ የጋራ መስፈርት የሚያሳጣን ይሆናል። ይህ ሃገርን የሚበትን እንጂ የሚያቆም አይሆንም።

ፈጣሪ የኢትዮጵያን ህዝብ በጥበቡ ይጠብቅ !

Axumezana
Member
Posts: 3990
Joined: 27 Jan 2020, 23:15

Re: በችግሮች የተሞላውን የነስብሃት ነጋ አፈታት በተመለከተ፣ ክፍል 1 + 2 By Andargachew Tsege

Post by Axumezana » 28 Jan 2022, 10:33

አንዳርካቸው፥ ጽጌ ፥ የሚረሳው፥ነግር!

-እርሱና፥ ጋደኛቹ እነዘአምን፥ ዘለቀ፥ የአገራቸው፥ ጥቅም፥ ለግብፅና፥ለኤርትራ፥ ለገንዘብና፤ለፖለቲካ፥ ሸጠው፥ በአገር፥ክህደት ተጠያቂ፥ እያሉ፥ በምህረት፥ መፈታቱን፥ በህዳሴው፥ ግድብ፥ላይ፥ የማን፥አጀንዳ፥ እያራመዱ፥ ይቃወሙ፥እንደነበር ፥የሚታወቅ፥ ነው።

-አሁን፥ኢትዮጵያ፥ለገባችበት፥ አጣብቂኝ፥ዋና፥ተጠያቂ፥መሆኑን በተለይም፥የኤርትራ፥ ጣልቃ፥ገብነትን፥ በማመቻቸትና፥የትግራይ፥የዘር፥ማጥፋት፥ጦርነትን፥ በመስበክና፥በማስተባበርና፥ኢትዮጵያ፥ከምዕራቡ፥አለም፥ እንድትገለል፥ በማድረግ።
-አሁንም፥ ሽንጡን፥ ግትሮ፥የሚከራከረው፥ ኢሳያስን፥ወክሎ፥መሆኑን።

Wedi
Member+
Posts: 5615
Joined: 29 Jan 2020, 21:44

Re: በችግሮች የተሞላውን የነስብሃት ነጋ አፈታት በተመለከተ፣ ክፍል 1 + 2 By Andargachew Tsege

Post by Wedi » 28 Jan 2022, 11:00

Axumezana wrote:
28 Jan 2022, 10:33
-አሁን፥ኢትዮጵያ፥ለገባችበት፥ አጣብቂኝ፥ዋና፥ተጠያቂ፥መሆኑን በተለይም፥የኤርትራ፥ ጣልቃ፥ገብነትን፥ በማመቻቸትና፥የትግራይ፥የዘር፥ማጥፋት፥ጦርነትን፥ በመስበክና፥በማስተባበርና፥ኢትዮጵያ፥ከምዕራቡ፥አለም፥ እንድትገለል፥ በማድረግ።
-አሁንም፥ ሽንጡን፥ ግትሮ፥የሚከራከረው፥ ኢሳያስን፥ወክሎ፥መሆኑን።
Did you forget the missiles that you Tigryans fired to Asmara without any provocation?

Za-Ilmaknun
Member
Posts: 3388
Joined: 15 Jun 2018, 17:40

Re: በችግሮች የተሞላውን የነስብሃት ነጋ አፈታት በተመለከተ፣ ክፍል 1 + 2 By Andargachew Tsege

Post by Za-Ilmaknun » 28 Jan 2022, 12:04

"የወያኔ ምንነት፣ በባህርይ ሆነ በተግባር የተገለጸው ምንነቱ፣ ወያኔን የተከፈለውን መስዋእትነት ከፍለን ወያኔን እንደ ድርጅት ከመቅበር ውጭ ሌላ አማራጭ እንደሌለን ነው። አይን ያፈጠጠው ሃቅ ይህ ነው። አዎን ጦርነቱ በመራዘሙ በፍጥነት ፊታችን ወደ ልማት ማዞር አንችልም። ጦርነቱ በመራዘሙ የሚከፈለው ሰብአዊና ቁሳዊ ዋጋ ትልቅ ነው። ሆኖም የሰላሙ አማራጭ የማይሰራ ከሆነ ምን ማድረግ ይቻላል። የሰላሙ አማራጭ የአሜሪካ ተላላኪ የሚያደርገን ከሆነ፣ የሰላሙ አማራጭ ለወያኔ ልንሰጠው የማንችለውንና የማይገባንን ገጸ በረከት እንድንሰጥ በማድረግ ወሳጣዊ አንድነታችንን አናግቶ ቀውስ ውስጥ የሚጨመረን እና ለከፋ ኪሳራ የሚዳርገን ከሆነ ድርድር ቢቀርብን ይሻላል።
በፖለቲካ ህይወት ውስጥ የከባድ ምርጫዎች ሰአት የሚባሉ ወቅቶች አሉ። የኢትዮጵያ መሪዎች በዚህ አይነቱ የከባድ ምርጫዎች ወቅቶች ውስጥ ይገኛሉ። የሚመርጡት ምርጫ የሃገርና የህዝብ ህልወናን አደጋ ላይ የሚጥል ወይም የሚታደግ ሊሆን ይችላል። ባላንበት ወቅት የወያኔን ምንነት እያወቁ፣ የአሜሪካንና የምእራባውያንን ምንነት እየታወቀ ወያኔ ለሰላማዊ የድርድር ሂደት ራሱን ክፍት ሊያደርግ ይችላል በሚል ቀቢጸ ተስፋ መዋተት ትልቅ ስህተት ነው።

Axumezana
Member
Posts: 3990
Joined: 27 Jan 2020, 23:15

Re: በችግሮች የተሞላውን የነስብሃት ነጋ አፈታት በተመለከተ፣ ክፍል 1 + 2 By Andargachew Tsege

Post by Axumezana » 28 Jan 2022, 15:35

Fact : ሁመራ ለሶስት፥ ቀን በሻብያ፥በከባድ፥ብረት፥የተደበደበው፥ ከሚሳይሉ፥ ጥቃት ከቀናት፥በፊት፥ነበር።

Educator
Member
Posts: 916
Joined: 03 Jun 2021, 00:14

Re: በችግሮች የተሞላውን የነስብሃት ነጋ አፈታት በተመለከተ፣ ክፍል 1 + 2 By Andargachew Tsege

Post by Educator » 28 Jan 2022, 15:50

Andargachew Zige, your bla bla is a little too late. You should never given Mamo Killo the wrong map. You should never invited Shabia in to Ethiopian affairs. You were vengeful and wanted to punish Woyane even at a cost of losing Ethiopia. Guess what, you have lost Ethiopia forever. Oromuma will not preserve Ethiopian unity.

Post Reply