*******************
ከመላ አገሪቱ የተውጣጡ የሀገር ሽማግሌዎች፣ አባ ገዳዎች እና የሰላም እናቶች ዛሬ በወቅታዊ ጉዳይ ዙሪያ ውይይት ካደረጉ በኋላ ባለ ስድስት ነጥብ የአቋም መግለጫ አውጥተዋል።
የሀገር ሽማግሌዎች፣ አባ ገዳዎች እና የሰላም እናቶች በአቋም መግለጫቸው ጦርነት በተካሄደባቸው የሀገሪቱ ክልሎች በደረሰው ሞት፣ ውድመት እና መፈናቀል የተሰማንን ጥልቅ ሃዘን እንገልጻለን ብለዋል።
ሁሉም አካላት በጦርነቱ የተጎዱ ክልሎችን መልሶ ለመገንባት እና ጉዳት ለደረሰባቸው ወገኖች አስፈላጊውን ድጋፍ ለማድረግ በትብብር እንዲሰሩ ጥሪ እናደርጋለን ነው ያሉት።
በተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች መካከል የተፈጠረውን መቃቃር ለመፍታት የአገራዊ ምክክር መድረኩ ትልቅ ሚና እንዲጫወት ጥሪ እናቀርባለን ብለዋል።
መንግስት እስረኞችን በመፍታት በአገሪቱ ሰላም እንዲያሰፍን በተደጋጋሚ ያደረግነውን ጥሪ ተቀብሎ በእስር ላይ የነበሩ የተወሰኑ ሰዎችን ክስ ማቋረጡ ለሰላም ያለውን ቁርጠኝነት ያሳያል፤ በመሆኑም የመንግስትን እርምጃ እያደነቅን አሁንም በጀመረው አኳኋን አጠናክሮ እንዲቀጥል፣ ክልሎችም ይህንኑ መንገድ እንዲከተሉ ጥሪ እናቀርባለን ብለዋል።
በቅርቡ ከእስር የተፈቱት ግለሰቦችም በበኩላቸው የተጀመረው የሰላም መንገድ እውን እንዲሆን የየራሳቸውን በጎ አስተዋጽኦ እንዲያበረክቱ ጥሪ እናቀርባለን ብለዋል።
እኛ የሃገር ሽማግሌዎች፣ አባገዳዎች እና የሰላም እናቶች በአገራችን ዘላቂ ሰላም እንዲሰፍን ሁሉም ታጥቀው ጫካ ያሉ ወገኖች ወደ ሰላማዊ መድረክ ተመልሰው ግጭቶችን በምክክር እንዲፈቱ ጥሪ እናደርጋለንም ብለዋል።
መንግስትም በበኩሉ ይህንኑ ጥሪ ተቀብሎ ሁኔታዎችን እንዲያመቻች እንጠይቃለን ማለታቸውን ኤፍቢሲ ዘግቧል።
ከላይ የተዘረዘሩት የሰላም ውጥኖች እውን እንዲሆኑ እና ዘላቂነት እንዲኖራቸው 11 አባላት ያሉት አገር አቀፍ የሰላም ቡድን ማቋቋማቸውንም የሀገር ሽማግሌዎች፣ አባ ገዳዎችና የሰላም እናቶች ይፋ አድርገዋል።
Please wait, video is loading...