በማለት አድዋ ላይ የትልቁ የየካቲት 23 ቀን ጦርነት ከመፈንዳቱ በፊት ለበላዮቻቸው ሓሳብ አቀረቡ፡ ሀብተ ጊዮርጊስ ዲነግዴ። ለመሆኑ ማን ናቸው? የሀብተ ጊዮርጊስ ዲነግዴ ታሪካቸውን በከፊል ገረፍ ገረፍ እናድርገዋ ከዘውዴ ረታ መጠሐፍ እየቀነጨብን!ሀብተ ጊዮርጊስ ዲነግዴ እንዳሉት wrote:“ . . . ለጠላታችን የፊት ለፊቱን መንገድ ብንለቅለትና የሸሸነው አስምስለን በጀርባው ዞረን ብንከበውና ብንወጋው ድሉን በቶሎ እናገኛለን . . . ”
ሀብተ ጊዮርጊስ ዲነግዴ ማን ናቸው?
የጨቦ ኣና ሰባት ቤት ጉራጌ ተወላጅ። ከአቶ ዲነግዴና ከኣመት አርሴማ በ 1844 ዓ.ም. ተወለዱ።
ባገር አቅኝ ወታደሮች ተማርከው ለቤተ መንግሥት ተሰጡ፡ እዚያዉም አደጉ።
በምርኮ ከተወሰዱ ጀምሮ ለአቅመ አዳም እስኪደርሱ ያደጉት፡ በሣህለ ሥላሴ ንጉሠ ሸዋ ዋና ከተማ በአንኮበር፣ አገረገዥው ኣዛዥ ወልደጻድቅ ዘንድ ነበር።
ወደ አዲስ አበባ እንዲመጡ ተደርጎ፡ አዲስ በተሠራው በምኒልክ ቤተመንግሥት ሥነ ሥርዓት እያጠኑ በአሽከርነት እንዲያገለግሉ ተመደቡ።
ማንበብ ቢችሉም መጻፍ አይችሉም ነበር፡ የተፈጥሮ ብልህነትና ንቃታቸው ግን እጅግ እፁብ ነበር።
በተመደቡበት ሥራ የሚሰጡት አገልግሎትና የሚታይባቸው የኃላፊነት ስሜት አለቆቻቸውን በሙሉ የሚያስደንቅ ነበር።
አጤ ምኒልክ፡ ሀብቴ ዲነግዴን ከጭንጫ አሽከርነት አንሥተው ለልጃቸው ለልጅ አስፋወሰን ምኒልክ የሰጡትን በሸዋ አውራጃ ውስጥ የሚገኘውን የበቾ ግዛት በምስለኔነት እንዲያስተዳድሩ መደቧቸው።
በጥቂት ግዜ ውስጥ ከበቾ ነዋሪ ሕዝብ ጋር በመተባበር መልካም ተግባር መፈጸማቸው ስለታወቀላቸው፡ በአፄ ምኒልክ ፈቃድ የትውልድ አገራቸው የወሊሶና የአመያ አውራጃ ገዥ ሆነው ተሾሙ።
በቤተ መንግሥቱ የጭንጫ አሽከር በነበሩበት ዘመን አብረዋቸው የቆዩት የምድረግቢው ጓደኞቻቸው ሁሉ፣ ሀብቴ ዲነግዴ ከሹመት ወደ ሹመት እያደጉ መሄዳቸው፣ “ጎበዝ ነው ይገባዋል” በማለት ደስታቸውን ከመግለጥ በስተቀር የተመቀኛቸው አልነበረም።
በአድዋው ጦርነት የወሊሶን ጦር ይዘው ዘመቱ። ለአንድ ግንባር ኃላፊነት ለመቀበል ስንዱ መሆናቸውን ባደረጉት አገላለጽ አጤውንና እቴጌይቱን ደስ ስላሰኙ፣ የሚያስፈልጋቸው መሣሪያና ትጥቅ እንዲሰጣቸው ታዘዘላቸው።
በየትኛው ግንባር እንደተዋጉና ጀግንነታቸውን በምን አኳኋን እንዳስመሰከሩ ዝርዝሩን ማወቅ ባይቻልም፣ በደፈናው ትልቅ ተጋድሎ አድርገው አድናቆትን አትርፈዋል እየተባለ ተነገረላቸው።
በአድዋው ጦርነት ዋዜማ “ጠላትን የፊት ለፊቱን መንገድ ብንለቅለትና የሸሸነው አስመስለን በጀርባው ዞረን ብንከበውና ብንወጋው ድሉን በቶሎ እናገኛለን . . .” የምትለው ሓሳባቸው አጤ ሚኒልክ ጀሮ ደርሳ፣ ይህ ልጅ የተባረከና አርቆ የማየት ማለፊያ ሐሳብ አለው በማለት፣ ከዚህ ጊዜ ጀምሮ ሀብተ ጊዮርጊስ አጠገቤ ይሁን ብለው ለጦር አበጋዛቸው ለፊተውራሪ ገበየሁ ትዕዛዝ ሰጡ።
እሁድ የካቲት 23 ቀን 1888 ዓ.ም. አድዋ ላይ ጠላት ድል በሆነበት ዕለት የጦር አበጋዙ ፊታውራሪ ገበየሁ አባ-ጎራው፣ በውጊያው ላይ እንዳሉ በጥይት ተመትተው ሞቱ። አባ-ዳኘው ምኒልክም “አገሬን ነፃ አወጣሁ፣ ገበየሁን አጣሁ።” እያሉ በጀግኖቻቸው መካከል በብርቱ አለቀሱ።
ሀብተ ጊዮርጊስ ዲነግዴ ከአድዋ ጦርነት በኋላ ምኒልክ ወደ መናገሻ ከተማቸው ሲመለሱ፡ ተከትለው መጥተው አዲስ አበባ እንዲቆዩ ተደረገ። እንደ ደጀ ጠኚ ለዘጠኝ ወራት ከቆዩ በኋላም . . .
ጥር ወር 1889 ዓ.ም. በታላቁ የምኒልክ ቤተ መንግሥት አንድ ትልቅ የሹመት ቦንብ ፈነዳ። “ . . . ዳግማዊ አፄ ምኒልክ ንጉሠ ነገሥት ዘኢትዮጵያ መልካም ፈቃዳቸው ሆኖ፣ በሟቹ በጀግናው በፊተውራሪ ገበየሁ ምትክ፣ አቶ ሀብተ ጊዮርጊስ ዲነግዴን ከፊተውራሪነት ማዕረግ ጋር የጦር ጠቅላይ አበጋዝ ሽንዲሆኑ ሾመዋቸዋል . . ።” ሲል ጸሐፊ ትዕዛዝይ ስማ! ነጋሪት፣ ክተት ሠራዊት! ብሎ ለሕዝብ አስታወቀ።
በሟቹ ገበየሁ ቦታ ንጉሠ ነገሥቱና እቴጌይቱ እጩ የሚያደርጓቸው፣ ከታወቁት ጀግኖች መካከል እንደ ሊቀ መኳስ ኣባተ ቧያለውና ኣንደ ደጃዝማች ባልቻ ኣባ-ነፍሶ የመሳሰሉትን እንጂ፣ እኚህን ያልታወቁትን ሀብቴ ዲነግዴን ብድግ አድርገው ይህንን እጅግ ከፍተኛ ሥልጣን ያሸክሟቸዋል ብሎ ያሰበ ወይም የገመተ አንድም ሰው አልነበረም።
ገበየሁ ባይሞቱ ኖሮ ሀብተ ጊዮርጊስ ዲነግዴ የምኒልክ ቤተመንግሥት የዘበኞች አዛዥ ሊሆኑ ታስበው ነበርም ይባላል።
በዘመኑ በነበረው ሥርዓት ጠቅላይ የጦር አበጋዝ (ማለት የጦር ሚኒስትር) ሆኖ የሚሾመው ሰው መጠሪያው “ፊታውራሪ” ይሁን እንጂ ማዕረጉ የ”ራስ” ደረጃ ነው። ፊታውራሪ ሀብተ ጊዮርጊስ በተሾሙበት ዕለት “የራስ ወርቅ አስረው” ከቤተመንግሥቱ ወደ-ማረፊያ ቤታቸው ሲሄዱ፣ አፄ ምኒልክ ለምንም ያላደረጉትን ቡሊት የተባለችዋን በቅሏቸውን ሰጥተው በደመቀ አጀብ እንዲጓዙ ፈቀዱላቸው።
በተጨማሪም ንጉሠ ነገሥቱ ራሳቸው ፊታውራሪ ሀብተ ጊዮርጊስ ማረፊያ ቤት ድረስ ሄደው ለሹመቱ የደስ-ደስ በተዘጋጀው የምሳ ግብዣ ላይ በመገኘት የማይጠብቁትን ከፍተኛ ክብርና ደስታ አጎናጸፏቸው።
ሀብቴ ዲነግዴ፣ ከ1889ዓ.ም. እስከ 1919 ዓ.ም. ድረስ፣ ለሠላሳ ዓመታት የኢትዮጵያ የጦር አበጋዝና ሚኒስትር ሆነው በትልቅ ሥልጣን ሲኖሩ፡ ዐዋቂና ዘዴኛ በመሆናቸው “አባ መላ”፣ በትዕግሥታቸውና በጥንካሪያቸው “አባ-መቻል” እየተባሉ ተጠርተዋል።
አጤ ምኒልክ ከሞቱ በኋላም፡ ከነበሩት መኳንንቶች ሁሉ በሥራ ልምድ የበለጸጉና በሥልጣናቸውም እጅግ የተፈሩ በመሆናቸው፣ በሕዝቡ ዘንድ "ጌታ ፊታውራሪ" የሚል የተከበረ የመጠሪያ ስም ተጨምሮላቸዋል።
ዘውዴ ረታ ከጣፉት የሀብተ ጊዮርጊስ ታሪክ የተቀነጨበ።